Saturday, 17 April 2021 11:30

ግማሽ ያህሉ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን መመዝገብ አልቻሉም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   በግንቦት መጨረሻ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ከተዘጋጁ 50 ሺህ ያህል የምርጫ ጣቢያዎች መካከል ግማሽ ያህሉ የመራጮች ምዝገባን ማከናወን አለመቻላቸውን ቦርዱ ያስታወቀ ሲሆን እስከ ትናንት በስቲያ ሐሙስ በ25 ሺህ 151 ጣቢያዎች ብቻ ነው መራጮች የተመዘገቡት ብሏል። ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ በበኩላቸው ዜጎች የመራጭነት ካርድ በመውሰድ በምርጫው በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ቦርዱ ከትግራይ ክልል በስተቀር በቀሪዎቹ 11 የሃገሪቱ ክልሎች የከተማ አስተዳደሮች በድምሩ 50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ዘርግቶ የመራጮች ምዝገባ ለማካሄድ ጥረት ቢያደርግም እንደታሰበው መራጮችን መመዝገብ አለመቻሉንም አመልክቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ በአጠቃላይ በ10 ክፍለ ከተሞች 1ሺህ 848 የምርጫ ጣቢያዎች ተደራጅተው የነበረ ሲሆን የመራጮች ምዝገባ የጀመሩት 1 ሺህ 662 መሆናቸውንና ቀሪዎቹ  186 ጣቢያዎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ምዝገባ እንዳልጀመሩ ተጠቁሟል።
ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት ያህል ብቻ በቀረው የመራጮች ምዝገባም መግለጫው እስከተሠጠበት እለት ድረስ በአዲስ አበባ 2 መቶ ሺህ ያህል ሠዎች ብቻ በመራጭነት መመዝገባቸው የተገለፀ ሲሆን ይህም ዜጎች ለምርጫው ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ያመለክታል ተብሏል።
በአፋር ክልል በአጠቃላይ 1 ሺህ 432 የምርጫ ጣቢያዎች ቢዘጋጁም አንድም የመራጮች ምዝገባ የጀመረ ጣቢያ እንደሌለ ታውቋል። ለዚህም ምክንያቱ ቁሳቁስ ለማሰራጨት የፀጥታና የትብብር ጉድለት መስተዋሉ ነው ተብሏል፡፡
በአማራ ክልል በአጠቃላይ 12 ሺህ 199 አጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች የተዘጋጁ ቢሆንም እስካሁን ከግማሽ በታች በሚሆኑት ማለትም በ6ሺህ 558 ያህሉ ጣቢያዎች ብቻ የመራጮች ምዝገባ መጀመሩ ነው የተመለከተው።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 699 አጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች የተደራጁ ቢሆንም በአሁን ወቅት መራጮችን እየመዘገቡ ያሉት 286 ያህሉ ብቻ ናቸው መሆናቸው ተጠቁሟል።
የተሻለ አፈጻጸም በተስተዋለበት የጋምቤላ ክልል 431 የምርጫ ጣቢያዎች ሲኖሩ፣ በ383 ያህሉ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ ነው።
17 ሺህ 623 አጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች (ትልቁ ቁጥር ነው) የተደራጀበት  የኦሮሚያ ክልል፤ አራቱን የወለጋ ዞኖች ጨምሮ በበርካታ ቦታዎች የመራጮች ምዝገባን ማከናወን ያልተቻለ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን እስካሁን ምዝገባ ማከናወን የቻሉት 8 ሺህ 545 ያህል ብቻ ናቸው ተብሏል።
ከክልሉ ውጪ ያሉ የሃረሪተወላጆች በሃረሪ ክልል ስር ሆነው በያሉበት የሚመርጡበት እድል እንዲመቻችለት ምርጫ ቦርድን ጠይቆ ይሁንታ በተነፈገው የሃረር ክልል በአጠቃላይ 285  የምርጫ ጣቢያዎች ቢዘጋጁም፣ መራጮችን እየመዘገቡ ያሉት 120 ያህል ብቻ ናቸው።
431 አጠቃላይ ምርጫ ጣቢያዎች ባሉት የድሬድዋ አስተዳደር ደግሞ 209 ጣቢያዎች ብቻ መራጮችን እየመዘገቡ ነው ተብሏል።
በደቡብ ክልል 8 ሺህ 281 አጠቃላይ የምርጫ ጣቢዎች ቢኖሩም፣ ምዝገባ እያከናወኑ ያሉት 5 ሺህ 271 ያህሉ ሲሆን አዲስ በተደራጀው የሲዳማ ክልል ደግሞ 2 ሺህ 247 የምርጫ ጣቢያዎች ተደራጅተው፣ 2 ሺህ 117 ያህሉ መራጮችን እየመዘገቡ መሆኑ ተጠቁሟል።
እንደ አፋር ክልል ሁሉ የሶማሌ ክልልም እስካሁን ምንም የመራጮች ምዝገባ አልተጀመረም። የሶማሌ ክልል አጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች 4 ሺህ 57 ናቸው።
ለምርጫ ጣቢያዎች አለመከፈትና የመራጮች ምዝገባ በታሰበው መንገድ አለመከናወን የመጓጓዣ እጥረት፣ በየክልሉ ያሉ የፀጥታ ችግሮችና የየክልል ሃላፊዎች ተባባሪ አለመሆን በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ቦርዱ በተፈናቃዮችና በመከላከያ ሰራዊት ካምፖች የመራጮች ምዝገባ ጣቢያዎችን የመክፈት ውጥን የነበረው ቢሆንም እንዳልተሳካለት አመልክቷል። ይህም የሆነው ከመንግስት አካላት ትብብር በማጣት ነው ብሏል-።
በተለይ በሶማሌ ፣ አፋር፣ በአራቱ የወለጋ ዞኖች ቁሳቁስ የማሰራጨት፣ የምርጫ ጣቢያዎች የመክፈት ችግሮች መከሠቱ ከሁሉም አሳሳቢ መሆኑን ቦርዱ በጉዳዩ ላይ በሃያት ሪጀንሲ በሰጠው መግለጫው አመልክቷል።
ቦርዱ እስከ ማክሰኞ ሚያዚያ 12 ቀን 2013  ያለውን የመራጮች ምዝገባ ውጤትና የመሻሻል ሁኔታ ተከታትሎ ሪፖርት በማድረግ በጋራ ከፓርቲዎች ጋር መክሮ መፍትሄ እንደሚያበጅ አስታውቋል።
ተ.ቁ    ክልሎች    የምርጫ ጣቢያ ብዛት    የተከፈቱ ጣቢያዎች
1    አፋር    1,432    0
2    አማራ    12,199    6,558
3    ኦሮሚያ    17,623    8,545
4    ደቡብ    8,281    5,271
5    ሲዳማ    2,247    2,117
6    ጋምቤላ    431    383
7    ሶማሌ    4057    0
8    ሐረር    285    120
9    ቤንሻንጉል ጉሙዝ    699    286
10    ድሬደዋ    431    209
11
    አዲስ አበባ    1,848    1,661

Read 10950 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 11:35