Saturday, 17 April 2021 11:19

በትግራይ 150 ሰዎች በረሃብ ሞተዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   “መንግስት ያልተቋረጠ መሰረታዊ ድጋፍ እያደረገ ነው”
                        
          በትግራይ ከሚካሄደው ጦርነት ጋር በተገናኘ ለዜጎች በቂ የምግብና መድሃኒት እርዳታ አለመቅረቡን ተከትሎ 150 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ ከትናንት በስቲያ በትግራይ ጉዳይ ላይ ለመከረው የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታ ም/ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ያመለከቱ ሲሆን በትግራይ ያለው ቀውስ አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል ብሏል።
በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ያስከተለውን ጉዳትና ወቅታዊ ሁኔታ ለመገምገም ስብሰባ የተቀመጠው የጸጥታው ም/ቤት፤ ስለ ሁኔታው እንዲያስረዱት የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ሃላፊ ማርክ ሎው ኩክን የጋበዘ ሲሆን ሃላፊውም ስለ ጦርነቱና ጉዳቶቹ በሰፊው ዘርዝረው ሪፖርታቸውን አቅርበዋል።
ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን፣ የኤርትራ ወታደሮችም ከክልሉ ለቀው ስለመውጣታቸው ማረጋገጫ አለመገኘቱን ያወሱት ሃላፊው፤ የፀጥታው ሁኔታ እንደተገመተው እየተሻሻለ አይደለም፤ ሰዎች በየቀኑ ለስቃይ እየተዳረጉ ነው ብለዋል።
የምግብ እርዳታ በሚፈለገው መጠን እየቀረበ አለመሆኑን ተከትሎ 150 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን፤ ሴቶችን አስገድዶ የመድፈር ድርጊት ልክ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቃት እየተቆጠረ መሆኑን ሃላፊው በሪፖርታቸው አመልክተዋል።
በዚህ የአስገድዶ መድፈር ድርጊትም ከ8 ዓመት ህጻናት ጀምሮ እየተደፈሩ መሆኑንና አብዛኞቹ ደርጊቶችም በቡድን የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ተብለው የሚገለጹ መሆናቸውን ነው ሃላፊው የገለፁት።
አብዛኞቹ ጾታዊ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ያሉትም ወታደራዊ ዩኒፎርም በለበሱ ወንዶች መሆኑም በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን የሚበዙት የጥቃቱ ሰለባዎችም ተገቢውን ህክምና እያገኙም ሃላፊው።
በዚህ የተባበሩት መንግስታት መግለጫ ጉዳይ ሮይተርስ ያነጋገራቸው በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ  አምባሳደር ታዬ አፅቀ ስላሴ በበኩላቸው፤ “መንግስት ሁሉንም የተባሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየመረመረ ይገኛል፤ ሪፖርቱ ስሜታዊነት የተንጸባረቀበትና አንዳች አላማን ለማሳካት ያለመ እንጂ ሙሉ ለሙሉ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ በማስረጃ የሚያስረዳ አይደለም” ብለዋል።
ሰብአዊ ድጋፍና እርዳታም በተገቢው ያለማቋረጥ እየቀረበ መሆኑን አምባሳደሩ አስረድተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ ማርክ ሎውኩክ፤ በትግራይ ክልል እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት መንግስት ቸል እንዳይል ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለጸጥታው ም/ቤት በቀረበው የተዛባ ገለጻ ማዘኑንና በተሳሳተ መረጃ  አቋም እንዳይዝ ስጋት እንዳለው የገለፀው አምባሳደር ታዬ አፅቀ ስላሴ፤ የሃላፊው ገለጻ የመንግስትንና የአጋሮቹን ጥረት ሁሉ ዋጋ የሚያሳጣ ሲሉ ኮንነዋል።



Read 1088 times