Saturday, 17 April 2021 11:17

“ትግራይ ለሴቶች የመከራ ምድር ሆናለች”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  በትግራይ በተካሄደውና አሁንም ባልተቋጨው ግጭትና ጦርነት ምክንያት ሴቶችና ህፃናት ዘረፈ ብዙ ሰቆቃዎችን እየተጋፈጡ መሆኑን ያመለከተው በሰብአዊ ድጋፍ የሚሰራው “ኬር” የተሰኘው አለማቀፍ ተቋም፤ አስገድዶ መደፈርን ጨምሮ ሴቶች ለስነ ልቦና ቀውስና ለአዕምሮ መታወክ በስፋት እየተዳረጉ ነው ብሏል፡፡
ከጥቅምት ወር ጀምሮ በተካሄደው ጦርነት ከ4መቶ ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንና ከእነዚህ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውን  ያመለከተው የተቋሙ ጥናት፤ አንዳንድ መንደሮች ሙሉ በሙሉ ሰው አልባ ሆነው ወደ ባድማነት መቀየራቸውንም ጠቁሟል፡፡
ከትናንት በስቲያ ሀሙስ ይፋ የሆነው የተቋሙ ጥናት፤ የአካባቢ ምልከታ ጨምሮ በተለያዩ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ የሚገኙ 95 ያህል ሰዎችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ የተሰራ መሆኑም ታውቋል፡፡
በጥናቱም በትግራይ በተለይ ሴቶች እየተጋፈጧቸው ያሉ ችግሮችና የደረሱባቸው ዋና ዋና ጉዳቶች የተለዩ ሲሆን ከእነዚህም በተፈናቀሉበት ቦታ መጠለያ ማጣት፣ደህንነቱ ባልተጠበቀ መጠለያ ውስጥ ሳሉ በአልፎ ሂያጁ ሁሉ እየተደፈሩ መሆኑና ከማያውቋቸው ወንዶች ጋር መጠለያ ለመጋራት መገደዳቸው ተጠቅሷል።
ሴቶችና ልጃገረዶች መጠነ ሰፊ የመደፈር አደጋ እያጋጠማቸው እንደሆነ በጥናቱ መረጋገጡን የጠቆመው ተቋሙ፤ በተለይ ግጭት ሲቀሰቀስ፣ከግጭት ለማምለጥ በሚደረግ ሩጫ  መሀል መንገድ ላይ እየታፈኑ እንደሚደፈሩ፣ ከካምፕ ውጪ ለማገዶ ለቀማና ውሃ መቅዳት ርቀው ሲሄዱ ያለ ማንም ከልካይ ሴቶች እየተደፈሩ መሆኑን  ያመለክታል፡፡
ሌላው ሴቶች እየተጋፈጡ ያለው ችግር የምግብና አልሚ ምግብ እጥረት ነው፡፡ በተለይ እናቶች ልጆቻቸው ከተመገቡ በኋላ የሚመገቡ በመሆኑ ምግብ ከሚበሉበት የማይበሉበት ጊዜ በእጅጉ እንደሚበዛ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ በተጨማሪም በካምፕ ውስጥ ሴቶች ያለምንም ክፍያ ለተለያዩ የጉልበት ስራዎች እየተዳረጉ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ በቀን ለ11 ሰዓታት ያህል ያለ  ማቋረጥ በተለያዩ ስራዎች ላይ ተጠምደው ይውላሉ ብሏል፡፡
የህክምናና ጤና አገልግሎቶችን በተመለከተ በአጠቃላይ በትግራይ ከነበሩ 260 ያህል የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 31 ብቻ ሲሆን እነሱም የተሟላ አገልግሎትየላቸውም ተከሏል፡፡  በዚህም በተለይ ነፍሰ ጡር፣ አራስና  የጤና እክል ያለባቸው ሴቶች ከህክምና ክትትል ከተገለሉ ቆይቷል ብሏል ሪፖርቱ፡፡
ሌላው ሴቶችና ህጻናት በዋናነት እየተጋፈጡ ያለው ችግር የስነ ልቦና ቀውስ መሆኑን ያወሳው ጥናቱ፤ አብዛኛዎቹ በቀጥታ ከጦርነት መሃል የወጡ በመሆኑ እንቅልፍ አልባና ድንጉጥ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ለስነ ልቦና መረበሽ የተዳረጉ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የውሀና የንጽህና አገልግሎት በተመለከተ በመጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ለቤተሰባቸው ውሃ ለማግኘት በቀን ከ50 እስከ 60 ደቂቃ በእግራቸው እየተጓዙ ከምንጭ  እንደሚቀዱ በዚህ መሃልም የመደፈር አደጋ እንደሚገጥማቸው ጥናቱ አመልክቷል፡፡
በብዙ መከራ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ሴቶችን ከሰቆቃ ለመታደግ መንግስትና የረድኤት ድርጅቶች ርብርብ እንዲያደርጉና በተለዩት ችግሮች መሰረት ድጋፎችና የኑሮ ማሻሻሎች እንዲደረጉ “ኬር” የተሰኘው አለማቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ተቋም ጠይቋል፡፡Read 560 times