Saturday, 03 April 2021 00:00

የ7ኛው “ጉማ ፊልም ሽልማት” አንኳር እውነታዎች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 “ቁራኛዬ “ በ12 ዘርፍ ታጭቶ በሰባት ዘርፍ አሸናፊ ሆኗል
                             
             ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 18 ምሽት ስካይ ላይት ሆቴል ከወትሮ በተለየ አገሪቱ አለኝ የምትላቸውን ታዋቂ ዝነኞች አስተናግዷል። በምሽቱ የተካሄደው ዓመታዊው 7ኛው ጉማ  የፊልም ሽልማት ስነ-ስርዓት ሲሆን መርሃ ግብሩ ላይ፤ በ18 ዘርፎች የታጩ ፊልሞችና የፊልም ባለሙዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዕለቱም የሚያስደንቁ፣ የሚያሳዝኑ የሚያስተዛዝቡና የሚያስደስቱ ሁነቶች ተከስተዋል።
አምና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የሽልማት ስነ-ስርዓቱ ያልተካሄደ በመሆኑ በ2011 እና በ2012 የተሰሩና መስፈርቱን ያሟሉ 45 ፊልሞች የተወዳደሩ ሲሆን በእያንዳንዱ ዘርፍ አምስት አምስት እጩዎች ለመጨረሻው ዙር አልፈው ነው አሸናፊዎች ለሽልማት የበቁት።
በዚሁ መሰረት “ቁራኛዬ” የተሰኘው ፊልም በ12 ዘርፎች ታጭቶ፣ በ7ቱ ሽልማቶችን ጠራርጎ የወሰደ ሲሆን “እንሳሮ” በ13 ዘርፍ ታጭቶ አራት ሽልማቶችን በመውሰድ ይከተለዋል።
መድረኩ በታዋቂውና አንደበተ ርዕቱው  አርቲስት ሽመልስ በቀለ የተመራ ሲሆን፣ የመክፈቻ ንግግሩን ያደረገው የሽልማት አዘጋጁ አርቲስት ዮናስ ብርሃነ መዋ ነው። ዮናስ በንግግሩ ለዚህ ሽልማት መሳካት የደከሙትን ተባባሪዎች  በተለይም የምንጊዜም የጉማ ሽልማት ብራንድ ስፖንሰር የሆነውን በደሌ ስፔሻልን አመስግኗል። “የዘንደሮውን ሽልማት ለየት የሚያደርገው” አባቴ ብርሃነ መዋ፣ በዚህ አዳራሽ መገኘቱ ነው” ያለው ዮናስ፤ አከለናም ባለፉት ስርዓቶች አባቴ ሲታሰርና ሲሰቃይ ቆይቷል፤ ያላሰረው ብልፅግና ብቻ ነው፤ አሁን ከብልፅግና ጋር እላተማለሁ ቢል እኔ ነኝ የማስረው” በማለት ታዳሚውን አስፈግጓል። አቶ ብርሀኑ መዋም በሀገር ባህል ልብስ ሽክ ብለው ወደ መድረኩ ሲወጡ ታዳሚው ከመቀመጫው በመነሳት በጭብጨባና በፉጨት አድናቆቱንና አክሮቱን ገልጾላቸዋል። “ስለሰጣችሁኝ ክብር በእጅጉ አመሰግናለሁ፤ ዛሬ እዚህ መድረክ ላይ በመገኘቴ በእጅጉ ደስ ፤ ብሎኛል” ካሉ በኋላም ዛሬ ከእኔ ይልቅ በዚህ መድረክ ላይ ለመገኘት እንደጓጓች የቀረችው ባለቤቴ፣ የዮናስ እናት ብትኖር ምኞቴ ነበር፤ እነሆ በአፀደ ስጋ ከተለየችኝ 500 ቀናት ተቆጠሩ…” ሲሉ ተናገሩ በዚህም የታዳሚው ስሜት ተነክቶ ነበር። (በነገራችን ላይ አቶ ብርሃነ መዋ ከዚህ ቀደም የባለቤታቸውን ሞት ተከትሎ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ ስለ ባለቤታቸው  የጻፉት ማስታወሻ የብዙዎችን ስሜት የነካ አይንን በእንባ የሚሞላ ነበር) በዕለቱም ከዚያው ፅሁፍ ተመሳሳይ የሆነ የሀዘን መግለጫ ነበር የተናገሩት።
አቶ ብርሃነ መዋ በትግል ህይወታቸው፣  እንዴት በስደት ከሀገር እንደወጡ፣ያሳለፉትን የስደት ህይወት ለታዳሚው ያወጉ ሲሆን ልጃቸው ዮናስ ብርሃነ መዋ ለሀገሩ ስላለው ጥልቅ ፍቅር፣ እንዴት ፈተናዎችን እንዳለፈ፣ ሀገሩን ለማገልገል ስላሳየው ቁርጠኝነት፣ በመግለጽ በአደባባይ አመስግነውታል። “እኔ በአካል ከአገር ብወጣም ስሜ ጨርሶ እንዳይወጣና በህዝብ እንዳልረሳ ስሙን “ዮናስ ብርሃነ መዋ” እያለ እየጠራና እየተጠራ፣ እኔን በህዝብ ውስጥ ስላቆየኝ አመሰግነዋለሁ” ካሉ በኋላ አክለውም ዮናስ ሀገሩን እንዲወድ አድርጋ ስላሳደገችው እናቱ በትምህርቱ  ስላገዙት ወዳጆች ስለጠንካራዋ የዮናስ ሚስትና በርካታ ወዳጆቻቸው በማንሳት አመስግነዋል።
ሌላው ጉዳይ እንደተለመደው ጉማ ሽልማት ሰዓት ያለማክበር አባዜው ዘንድሮም አለቀቀውም። አርፋጅነት እንደተፀናወተው ነው። 11፡00 ይጀምራል የተባለው ስነ-ስርአት፤ ምሽት 1፡00 መጀመሩንም እንጃ።
አለባበስን በተመለከተ ጉማ ሁሌም ታዳሚዎች ደረጃውን የጠበቀ ልብስ በመልበስ የሽልማቱን፣ የፊልሙንና ሙያተኞችን ክብር እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ ይሰጣል። ይህንን ማሳሰቢያ አክብረው እጅግ ማራኪ፣ የሀገራቸውንና የኢንዱስትሪውን ክብር በጠበቀ መልኩ ለብሰው የመጡ የመኖራቸውን ያህል ለራሳቸውም ለታዳሚም ሆነ አሊያም ለሙያቸው ክብር የማይመጥን አሸማቃቂ አለባበስ የለበሱ ከእርቃን ያልተሻለ አለባበስ የለበሱም አልጠፋም። ይሄም ብዙ ጉርምርምታና ቅሬታ የፈጠረ ሲሆን በሌላ በኩል ራሳቸውንና የሀገራቸውን ክብር ጠብቀው ለለበሱት ደግሞ ልብን የሚያሞቅ አድናቆት ተችሯቸዋል።
አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮንና ባለቤቱ፣ አርቲስት መሰረት መብራቴ፣ አርቲስት መስከረም አበራ፣ አርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆና ሌሎች በማራኪና ውብ አለባበስ የሽልማት ስነ-ስርዓቱ  ሞገስ ሆነው አምሽተዋል።
በአለባበስ ዙሪያ ያነገጋገርናቸው ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየታት፣ “የጉማ ሽልማት አዘጋጆች የአለባበስ ስነ-ስርዓትን በተመለከተ መልዕክት በሚያስተላልፉበት ጊዜ ዝግጅቱን የሚመጥንና ደረጃውን የጠበቀ አለባበስ ልበሱ ከማለት ባለፈ የኢትዮጵያን ህዝብ ባህል ፣   ስነ-ልቦናና ክብር የማይመጥን፣ ቅጥ ያጣ አለባበስ መልበስ እንደማይፈቀድም ማሳሰብ ይገባቸዋል” ብለዋል።
ወደ ሽልማቱ ስንመጣ 45 ያህል ፊልሞች መስፈርቱን አሟልተው ከእያንዳንዱ ዘርፍ አምስት አምስት ፊልሞች የተመረጡ ሲሆን፡- በተማሪ አጭር ፊልም ዘርፍ “ግራግዛት” ፊልም አሸንፏል። በምርጥ አጭር ፊልም ዘርፍ “ቀብድ” የተሰኘው ፊልም ሲያሸንፍ የፊልሙ ባለቤት ኢሳያስ ታደሰ ከረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ እጅ ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ በትግርኛ ንግግር ያደረገ ሲሆን ንግግሩ ሲተረጎም “በአሁኑ ወቅት በትግራይ ሰብአዊ መብት እየተጣሰ፣ እህቴ እየተደፈረች፣ እናቴ እያለቀሰችና ንፁሃን እየሞቱ በዚህ ሽልማት ልደሰት እቸገራለሁ፤ ጊዜው ሲፈቅድ አከብረዋለሁ” የሚል መንፈስ ያለው ነው ተብሏል።
 በምርጥ ድምጽ ዘርፍ “ወጣት በ97” ፊልም ሲያሸንፍ፣ በምርጥ ፊልም ሙዚቃ “ህዳር” የተሰኘው ፊልም አሸናፊ ሆኗል። በምርጥ ስኮርና በምርጥ የገፅ ቅብ (ሜካፕ) በሁለቱም “ቁራኛዬ” ፊልም ሲያሸንፍ፣  በምርጥ የፊልም ፅሁፍም “ቁራኛዬ” ተሸልሟል።
በምርጥ ቅንብር (ኤዲቲንግ) ዘርፍ “እንሳሮ” አሸናፊ  ሲሆን፣ በምርጥ ምስል ቀረፃ (ሲኒማቶግራፊ) ዘርፍም “እንሳሮ” ተሸልሟል።  ምርጥ ተስፋ የተጣለባት ሴት ተዋናይት ዘርፍ “ሱማሌው ቫንዳም” ፊልም ላይ በአስገራሚ ብቃት የተወነችው ህፃን ዮሃና ሙሉጌታ አሸንፋለች። በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ወንድ ተዋናይ “ቁራኛዬ” ያሸነፈ ሲሆን፣ በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ ዘርፍም “ቁራኛ” ፊልም አሸንፏል። በምርጥ ረዳት ሴት ተዋናይት በ”እንሳሮ”  ፊልም ላይ የተወነችው  መስከረም አበራ ተሸላሚ ሆናለች። በምርጥ ዋና ተዋናይት ዘርፍ በ”ወጣት በ97” ፊልም መሪ ተዋናይቷ ዘሪቱ ከበደ ተሸላሚ ስትሆን እሷ በቦታው ባትገኝም ሽልማቷን በተወካይ ወስዳለች። በምርጥ ወንድ መሪ ተዋናይ ዘርፍ “ሱማሌው ቫንዳም” ሲያሸንፍ መሪ ተዋናይ የሆነው ሄኖክ ወንድሙ ሽልማቱን ወስወዷል። በምርጥ የበደሌ ስፔሻል የህዝብ ምርጫ ፊልም ዘርፍ “እንሳሮ” ያሸነፈ ሲሆን፣ በምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ አሁንም “ቁራኛዬ” ፊልም አሸናፊ ሆኗል። የህይወት ዘመን አገልግሎት በሚለው ዘርፍ የክብር ዶ/ር አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ተሸልመዋል።
ላለፉት ሰባት ዓመታት (አምና በኮቪድ ከመስተጓጎሉ በቀር) የኢትዮጵያን ፊልሞች በተለያዩ ዘርፎች እየገመገመ ሲሸልም የቆየው “ጉማ ፊልም አዋርድ” ዘንድሮ መካሄዱ በወረርሽኙ ሳቢያ ተቀዛቅዞ የከረመውን የፊልም ኢንዱስትሪውን እንደሚያነቃቃው የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የከርሞ ሰው ይበለን፡፡


Read 332 times