Saturday, 03 April 2021 00:00

“ፍቅር ማለት ነፃነት ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  …አንዳንድ ሰዎች ግንኙነታቸውን ጥሩ ወይም መጥፎ የሚያደርገው ሌላው ሰው ይመስላቸዋል። ህይወት ግን እንደዚያ እይደለችም። ለፍቅር ሃይል፤ “ፍቅር የምሰጠው ሌላው ሰው ፍቅር ሲሰጠኝ ብቻ ነው” ማለት አይቻልም፡፡ አንተ ቀድመህ ካልሰጠህ በቀር ምንም ነገር አታገኝም፡፡
ሁሌም  የሰጠኸውን ትቀበላለህ እናም ነገሩ ፈጽሞ  ከሌላው ሰው ጋር አይገናኝም፣ አንተን ብቻ የሚመለከት ነው! ነገሩ አንተ ከምትሰጠውና ከሚሰማህ ስሜት ጋር ብቻ የተገናኘ ነው።
ከማንኛውም ሰው ጋር ያለህን ግንኙነት ለማሻሻል የምትሻ ከሆነ፣ የዚያ ሰው በጎ ነገሮች ላይ አተኩር። የዚያ ሰው የምትወድለት የምታደንቅለትና ምስጋና ሊቸረው ይገባዋል የምትላቸውን ነገሮች ፈልግ። አሉታዊ ነገሮቹ ላይ ከማተኮር ይልቅ ሆን ብለህ የምትወድለትን ነገር ለመፈለግ ብትጥር የማይታመን ተዓምር ይፈጠራል። ምናልባት ላንተ በሌላው ሰው ላይ አንድ የማይታመን ነገር- የፍቅር ኃይል ነው። ምክንያቱም የፍቅር ኃይል አሉታዊነትን ያከሽፋል፤ በግንኙነት ውስጥ ያለውን አሉታዊነት ጨምሮ። አንተ ማድረግ ያለብህ፤ የዚህን ሰው የምትወድለትን ነገሮች በማሰስ፣ የፍቅርን ኃይል ለዓላማህ ማዋል ነው። ያኔ ግንኙነታችሁን በተመለከተ ሁሉም ነገር ይለወጣል።
በፍቅር ኃይል የታደሱ በመቶዎች የሚሰሉ ግንኙነቶች አውቃለሁ። ከሁሉም ግን ሊፈርስ የተቃረበ ትዳሯን በፍቅር ኃይል ማቃናት የቻለች የአንዲት ሴት ታሪክ ጎላ ያለ ስፍራ ይሰጠዋል። ምክንያቱም ይህቺ ሴት ፍቅር መስጠት ያለውን ሃይል ስትረዳ፣ ምንም እንኳ ትዳሯ በችግሮች የታጠረ ቢሆንም ወዲያውኑ የደስታ ስሜት በውስጧ ለመፍጠር ወሰነች። ያኔ ቤታቸው ውስጥ ያረበበው የደመና ድባብ ተገፈፈ። እናትየዋ ከልጆቿ ጋ የነበራት ግንኙነት ተሻሻለ። ከዚያም የጋብቻ ፎቷቸውን አውጥታ ፊት ለፊት አኖረችው- በየቀኑ ለመመልከት፡፡ ይሄን በማድረጓ አንድ አስገራሚ ነገር ተከሰተ። ለባሏ የነበራትን የቀድሞ ፍቅር አስታወሰች። ፍቅር ተመልሶ ሲመጣ ተሰማት። የፍቅር ስሜት በአስደናቂ ሁኔታ በውስጧ እየበረታ መጣ። ባሏን እንደ አዲስ አፈቀረችው። ከፍቅሯ ታላቅነት የተነሳ የባሏ ድብርትና ቁጣ ጥሎት ጠፋ። ጤንነቱ መመለስ ጀመረ። ከቤቷ ብር ብላ ለመጥፋት ትመኝ የነበረችው ወይዘሮ፤ ወደ ትዳሯ ተመልሳ የሚቀናበት ፍቅር ፈጠሩ፡፡
በግንኙነት ውስጥ ፍቅርን መስጠትን በተመለከተ ሰዎችን ስለሚያሳስት አንድ ነገር እናውራ። ይኼ ነገር ብዙዎች ማግኘት የሚገባቸውን ህይወት እንዳያገኙ ከልክሏቸዋል። ነገሩ አሳሳች የሆነው ሰዎች ፍቅር መስጠት የሚለውን ጉዳይ በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱት ነው። ለሌሎች ፍቅር መስጠት የሚለው ጉዳይ በጣም ግልጽ እንዲሆንልህ፣ ለሌሎች ፍቅርን አለመስጠት ምን ማለት እንደሆነ መረዳት አለብህ።
ሌላውን ሰው ለመለወጥ መሞከር ፍቅር መስጠት አይደለም! ለሌላው ሰው የሚበጀውን  እኔ አውቅለታለሁ ብሎ ማሰብ ፍቅር መስጠት አይደለም! ራስን ትክክለኛ ፣ ሌላውን ጥፋተኛ  ማድረግ ፍቅር መስጠት አይደለም! ነቀፌታ፣ ወቀሳ፣ ማማረር፣ መነዛነዝና አቃቂር ማውጣት ፍቅር መስጠት አይደለም!
በግንኙነታችን ውስጥ መውሰድ የሚገባንን ጥንቃቄ የሚሳይ አንድ ታሪክ ላካፍልህ። አንዲት የተማረረች ሚስት፣ ልጆቿን ሰብስባ ባሏን ጥላው ከቤት  ትወጣለች። ባል ሆዬ፤ በዚህ ክፉኛ ስሜቱ ተጎዳ፣ ሁሉንም ነገር በሚስቱ ላይ አላከከ። ውሳኔዋንም አልቀበልም ብሎ አሻፈረኝ አለ።
ሃሳቧን ለማስለወጥ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። እሱ ይሄን ሁሉ ያደረገው ለሚስቱና ለቤተሰቡ ካለው ፍቅር እንደሆነ ሊያስብ ይችላል። ድርጊቱ ግን የፍቅር አልነበረም። ለትዳራቸው መፍረስ ተጠያቂ ያደረገው ሚስቱን ነው። እሱ ትክክለኛ፣ ሚስቱ ግን ጥፋተኛ እንደሆነች ነበር የሚያምነው። ሚስቱ የራሷን ምርጫ ለማድረግ የወሰደችውን ውሳኔ አልተቀበለም። በመጨረሻ ሚስቱ አካባቢ እንዳይደርስ በፖሊስ ቢነገረውም አሻፈረኝ በማለቱ፣ በቁጥጥር ስር ውሎ ወህኒ ወረደ።
ሰውየው የማታ ማታ ፍቅር እየሰጠ እንዳልሆነ ተገነዘበ። ሚስቱ የምትፈልገውን የመምረጥ ነጻነቷን ሲነፍጋት ፍቅር እየሰጠ አልነበረም። በዚህም የተነሳ እሱም ነጻነቱን አጣ። የመሳሳብ ህግ የፍቅር ህግ ነው። እናም ህጉን መተላለፍ አይቻልም። ህጉን ከጣስክ እራስህን ትጥሳለህ። የፍቅር ህግን የምትከተል ከሆነ ሌላው  ያሻውን እንዳይመርጥ መብቱን አትነፍግም፣ ምክንያቱም ይሄ ፍቅር መስጠት አይባልም።  ልብህ ሲሰበር በጉሮሮ ስለት የመላክ ያህል ስቃይ አለው። እንዲያ ሆኖ ግን የማንንም ሰው ያሻውን  የመምረጥ መብት ማክበር አለብህ። ለሌላው የሰጠኸውን አንተም ታገኘዋለህ። የሌላውን ሰው የመምረጥ ነጻነት ስትነፍግ ፣ የራስህን ነጻነት የሚነፍጉ አሉታዊ ነገሮችን ትጠራለህ። የገንዘብ ፍሰትህ ሊቀንስ ይችላል ወይም ጤናህ ይታወካል አሊያም ስራህ ይበላሻል። እነዚህ ሁሉ ደግሞ ነጻነትህን ይጎዱታል። ለስበት ህግ ሌላ ሰው የሚባል ነገር የለም። ለሌሎች የምትሰጠውን ለራስህ እየሰጠህ ነው።
ለሌሎች ሰዎች ፍቅር መስጠት ማለት፣ በላይህ ላይ እንዲረማመዱ ወይ እንዲጫወቱብህ መፍቀድ ማለት አይደለም፤ ይሄም ፍቅር መስጠት አይባልም። ሌላው ሰው እንዲጠቀምብህ ማድረግ ያን ሰው አይጠቅመውም፣ አንተንም በእርግጠኝነት አይጠቅምህም። ፍቅር አስቸጋሪ (ከባድ) ነው፤ እና በህጉ አማካኝነት እንማራለን፣ እናድጋለን፣ ውጤቱንም እናያለን። ስለዚህ ሌላ ሰው እንዲጠቀምብህ ወይ እንዲጫወትብህም መፍቀድ ፍቅር አይደለም።
(“ተዓምራዊው ኃይል” ከሚለው መፅሐፍ የተቀነጨበ፤ 2003 ዓ.ም)Read 553 times