Saturday, 10 April 2021 14:09

ኢትዮጵያዊ የሆኑት ስዊድናዊ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • በኢትዮጵያ ከ38 ዓመታት በላይ ተመላልሰው ኖረዋል ፡፡
       • በ3 ተከታታይ ኦሎምፒያዶች የማራቶን ድሎችን በማስመዝገብ 3 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል፡፡
       • ስፖርት በስርዓተ ትምህርቱ እንዲካተት ያደረጉና የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሆነው ያገለገሉ የመጀመርያው የስፖርት መምህር ናቸው፡፡
       • በዓለም አቀፍ ውድድሮች የኢትዮጵያ አትሌቶች ማናጀር እና አሰልጣኝ በመሆን ሲሆን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሥራቾች አንዱና ምክትል           ፕሬዝዳንት ሆነው ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አባል የነበሩ ሲሆን በሞተር ስፖርት ፤በጅምናስቲክ፤ በሰርከስና           ሌሎች የስፖርት እንቅስቃሴዎች ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል፡፡
       • በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቦርድ አባልነት በተለይም ዋና ጸሐፊነት ለ36 ዓመታት የሰሩ ሲሆን ለ12 ዓመታት የአለርት ሆስፒታል ማናጀር               ነበሩ፡፡


          እንደመግቢያ
ሻምበል ኦኒ ሄርማን ኒስካነን በፊንላንድ ዋና ከተማ ሄልሲንኪ  (ኦገስት 30/ 1910 እኤአ) የተወለዱ ቢሆንም ከ3 ዓመታቸው በኋላ ወደ ወላጆቻቸው  አገር ስዊድን ተመልሰው ሶላኖ በተባለች ከተማ እስከ ወጣትነት ዘመናቸው መጨረሻ ኖረዋል።  በስካውት አገልግሎት፤ በውትድርናና የስፖርት ሙያዎች  ማሳለፋቸው ልዩ ስብዕና አጎናፅፏቸዋል።  ስካውት በመሆናቸው በበጎ አድራጎት እና በጎ ፈቃድ የሚያገለግሉበትን ባህርይ ሰጥቷቸዋል። በውትድርናው ስነምግባርን፤ ጀግንነትና አገር ወዳድነትን ተምረዋል፡፡ ስፖርት ደግሞ ዋንኛ ዝንባሌያቸው ነበር፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት ፅናትን፤ ብቃትን አዳብረዋል፡፡ ስዊድን ውስጥ ለመታወቅ የበቁ ምርጥ ሯጭ ሲሆኑ አሰልጣኝ እና  የውድድር አዘጋጅ በመሆንም ሰርተዋል፡፡ ሩጫን መወዳደር ያቆሙት  30ኛ ዓመታቸው ላይ ነበር፡፡ ለፊንላንድ በወዶ ዘማችነት ጦርነት ተሰልፈው በመድፍ ፍንጥርጣሪዎች በእግራቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው ነው፡፡
ከ38 ዓመታት በላይ ተመላልሰው በኖሩባት  አገር ኢትዮጵያ  በስፖርት ፤በቀይ መስቀል አገልግሎት፤ በሰብዓዊ አድራጎት፤ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ባከናወኗቸው ተግባራት ከፍተኛ ዝናና ከበሬታን አትርፈዋል፡፡  በክቡር ዘበኛ  የስፖርት መኮንን ሆነው ከተሾሙ በኋላ ካዴቶችን ከስር መሰረቱ በስፖርት አሰልጥነዋል፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ታላቁ የስፖርት መድረክ ኦሎምፒክ እንድትገባ ያነቃቁ ሲሆን፤ የመጀመርያዎቹን የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ካፈሩ ባለሙያዎችም አንዱ ናቸው።  ኢትዮጵያ በ3 ተከታታይ ኦሎምፒያዶች የማራቶን ድሎችን  በማስመዝገብ 3 የወርቅ ሜዳልያዎች የተጎናፀፈች ብቸኛ አገር የሆነችበትን ልዩ ክብረወሰን አስይዘዋታል፡፡ የረጅም ርቀት ሩጫን ኢትዮጵያውያን ባህላቸው  እንዲያደርጉ ፈር ቀደዋል፡፡ በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ስፖርትን ያካተቱ የመጀመርያው የስፖርት መምህርም ናቸው፡፡ በቀይመስቀል እና በህፃናት አድን ስራዎች ኢትዮጵያን በማገልገል ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲን አሳድገዋል፡፡
ሻምበል ኦኒ ከ28 ዓመታት በፊት (ማርች 30 /1984) እኤአ ላይ ሶላኖ በሚገኝ መኖርያ ቤታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ፒያ በርግማን የተባለ የቅርብ ወዳጃቸው የመጨረሻውን ቃለምልልስ አድርጎላቸው በሴቭ ዘ ችልድረን መፅሄት ላይ በፃፈው የታሪክ ማስታወሻ ‹‹ ኢትዮጵያዊ የሆኑት ስዊድናዊ››  የሚለውን ርእስ ተጠቅሟል፡፡ እስከ 73 ዓመታቸው ድረስ ኢትዮጵያን ያገለገሉ  ታላቅ ሰው እንደነበሩ  ሲጠቁም ‹‹የሰው አገር ሰው  ነበር። በሁሉም ሁኔታዎች ላይ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ተሰለፈ፤ ማንም ከእንግዳ አይቆጥረውም ፡፡ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ሆኗል፡፡ ሁሉም ማንነቱን ያውቃል፤ በስራውም ይኮራል፡፡›› ሲል ገልጿል፡፡ ይህ የስፖርት አድማስ ማስታወሻ ለኢትዮጵያ ብዙ ውለታ የሰሩትን ሻምበል ኦኒ ሄርማን ኒስካነን የሚያስታውስ ነው፡፡
ስዊድናውያን ወደ ኢትዮጵያ መጡ
ስዊድናውያን ለኢትዮጵያ  ልዩ ክብርና ስፍራ  ይሰጣሉ፤ ዋናው ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያውያን በነፃነት ለመቆየት ያደረጉትን ተጋድሎ  ያደንቁታል። አቢስኒያ ተብላ በምትጠራበት ዘመን ሁሉ ነበሩ። ከ1866 እኤአ ጀምሮ  የስዊድን ሚስዮኖች ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን  በስዊድን ኢቫንጀሊካል ሚሽን የመጀመርያው ትምህርት ቤት በ1896 እኤአ ላይ መሰራቱም በታሪክ መዝገብ ሰፍሯል፡፡  ከጣሊያን ወረራ በፊት በ1924 እኤአ ላይ አፄ ሐይለስላሴ  ስዊድንን ለአምስት ቀናት መጎብኘታቸው የሁለቱ  አገራት ጥንታዊ ግንኙነት ማጠናከሩን “Sweden and the Italo-Ethiopian Crisis 1935” በተባለ የጥናት ወረቀታቸው የፃፉት ስዊድናዊው ፕሮፌሰር ሰቨን ናቸው፡፡ ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት ስዊዲናውያን በቀይመስቀል እርዳታ ውስጥ መሳተፋቸውን ለቀይመስቀል መኪናዎች የድጋፍ ገንዘብ በማሰባሰብ ከአርበኞች ጎን ቆመው ነበር፡፡  ጣሊያን ከኢትዮጵያ ከተባረረች በኋላ አፄ ኃይለስላሴ አገራቸውን በስልጣኔ ለመምራት የነበራቸውን ፍላጎት ለማሳካት ከአሜሪካ እና ከእንግሊዝ ይልቅ የድጋፍ ጥሪያቸውን ያቀረቡት ለስዊድን ነበር። ስዊድናዊው ፕሮፌሰር በታሪክ ጥናታቸው እንዳሰፈሩት የንጉሱን ጥሪ ተከትሎ ከ600 እስከ 700 ስዊድናውያንና ቤተሰቦቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ፤ በውትድርና፤ በህክምና፤ በቀይ መስቀል፤ በስፖርት፤ በትምህርነት፤ በቴሌኮም፤ በፖሊስ፤ በአየር ኃይልና ሌሎች መስኮች  መሰማራታቸውንና  በወቅቱ የስዊድን መንግስትም ለዜጎቹ ክፍያ የሚሆን እስከ 6 ሚሊዮን የስዊድሽ ክሮነር ለኢትዮጵያ መለገሱንም አስታውሰዋል፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከፍተኛ ማዕረግ ያላቸው የውትድርና ባለሙያዎች፤ ሚስዮናውያን፤ መምህራን፤ ዲፕሎማቶች፤ የብሮድካስት ባለሙያዎች፤ ዶክተሮችና የህክምና ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ከስዊድን ውጭ ሲወጡና ወደ ሌላ አገር ለስራ ሲጓዙ የመጀመርያቸው ነበር፡፡
ከስዊድን የውትድርና ባለሙያዎች  መካከል ጄነራል ቫይኪንግ የተባሉት በክቡር ዘበኛ እየሰሩ ነበር፡፡ በስዊድን ስቶክሆልም ሴቪያ ሊቭጋርዴ በሚባል ተቋም ውስጥ የስፖርት አሰልጣኝ  ከነበሩት ሻምበል ኦኒ  ጋር ሲገናኙ  ጥያቄ አቀረቡላቸው፡፡ በክቡር ዘበኛ የስፖርት መኮንን ሆነው እንዲቀጠሩና ካዴቶችን በሁለት ዓመት ኮንትራት እንዲያሰልጥኑ ነበር ያግባቧቸው፡፡ ሩጫን ካቆሙ በኋላ በስፖርት አሰልጣኝነትና በውድድር አዘጋጅነት ጥሩ ልምድ የነበራቸው ሻምበል ኦኒ፤ የቀረበላቸው የስራ እድል እንደብዙዎቹ ስዊድናውያን በፀጋ ተቀብለዋል። ከባለቤታቸው ጋር ሰፊ ምክክር አድርገው  ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የወሰኑትም በ1946 እኤአ ላይ ነበር፡፡ ከስቶክሆልም ወደ አዲስ አበባ ጓዛቸውን ጠቅልለው  የመምጣቱ ጉዳይ ግን ቀላል አልነበረም። እስከ 11 ኪውቢክ ሜትር የሚመዝነውን ሙሉ የቤት እቃቸው፤ አስቤዛና ጓዛቸውን ከስቶክሆልም ጅቡቲ የሚጓዝ መርከብ ወደ ኢትዮጵያ ማድረስ ነበረባቸው፡፡ ከሌሎች ስዊድናውያን ጋር ወደ አዲስ አበባ የመጡት ደግሞ በአሜሪካ የጦር መጓጓዣ አውሮፕላን ቦይንግ ቢ 17 ቻርተር በረራ ተሳፍረው ሲሆን ስዊድናዊው ካርል ጉስታቭ  ቮን ሮሰን አብራሪው ነበር፡፡ የሻምበል ኦኒ የቅርብ ወዳጅ የነበረው የአቪዬሽን ባለሙያ ቮን ሮሰን በኢትዮጵያ አየር ሃይል መስራችነቱ የሚታወቅና እንደኢትዮጵያዊ የሚታይ ስዊድናዊ ነበር፡፡
ሻምበል ኦኒ በክቡር ዘበኛ ውስጥ የስፖርት መኮንን ሆነው መስራት ሲጀምሩ ሌሎች ስዊድናዊ የውትድርና ባለሙያዎች  መኖራቸው ከአገሬው ህዝብ ጋር በቶሎ ለመላመድ አግዟቸዋል፡፡ ለስፖርት ስልጠናው የተመደቡት የክቡር ዘበኛው    መቶ ሃያ አምስት ካዴቶች በልዩ ተሰጥኦ እና ተፈጥሯቸው ንጉሰነገስቱ እንደመለመሏቸው በማስታወሻቸው ያሰፈሩት ሻምበል ኦኒ ካዴቶቹ ለማንኛውም ስፖርት አሰልጣኝ ምቹ ቁመና እና የአካል ብቃት ቢኖራቸውም ስለ ስፖርት  ህግና ስልጠናን ጠለቅ ያለ እውቅት እንዳልነበራቸው፤ ባዶ እግራቸውን ኳስ ሲጫወቱ ጥፍራቸው እስኪነቀል ይጠልዙ እንደነበር  በግርምት አስተውሰው ፅፈዋል፡፡ የስፖርት ስልጠናው ለክቡር ዘበኛው ካዴቶቹ መሰጠት ከጀመረ በኋላ  ስፖርተኞቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ አሳይተው አዲስ አበባ ላይ በየጊዜው የሚካሄዱ ውድድሮች ሁሌም የሚያሸንፉ ሆኑ፡፡ ካዴቶቹ እነ አበበ ቢቂላ፤ ባሻዬ ተክሉ፤ አበበ ዋቅጅራ፤ ዋሚ ቢራቱ፤ ማሞ ወልዴ…. ሌሎችም ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያን በኦሎምፒክ ማማ
ሻምበል ኦኒ በክቡር ዘበኛ የስፖርት መኮንን ሆነው ባገለገሉባቸው ሁለት ዓመታት ለታላቁ የስፖርት መድረክ የሚበቁ የኢትዮጵያን አዳዲስ ኦሎምፒያኖች መፍጠር ችለዋል፡፡ በ1948 እኤአ ላይ የኢትዮጵያን ኦሎምፒክ ኮሚቴ በአባልነት ከተቀላቀሉ በኋላ በለንደን ኦሎምፒያድ ላይ በተመልካችነት ተሳትፈዋል፡፡ ከ4 ዓመታት በኋላ በ1952 እኤአ ላይ ደግሞ በፊንላንድ ሄልሲንኪ ኦሎምፒኩ ሲካሄድ የኢትዮጵያ ልዑክ ከመሆናቸውም በላይ ለኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጠኛ ወክለው ተሳትፈዋል፡፡ በለንደንና ሄልሲንኪ ኦሎምፒያዶች የነበራቸውን ልምድ በመንተራስ ወደ ኦሎምፒክ መድረክ ኢትዮጵያን  ለማስገባት ተንቀሳቀሱ፡፡ አዳዲስ የኢትዮጵያን ኦሎምፒያኖችን ለኦሎምፒክ ለማብቃት በጣሉት መሰረት ላይ ተማምነዋል፡፡ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ከሆነች በኋላ ቀጣዩ ምዕራፍ  ወደ ተሳትፎ እንድትሸጋገር ማድረግ ነበር፡፡
በ1956 እኤአ በሜልቦርን አውስትራሊያ በተካሄደው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ በቃች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች አሰልጣኝ ለዚሁ ኦሎምፒክ እየሰሩ ቢቆዩም በስዊድን ጦር ሰራዊት በነበራቸው የማይቀር የውትድርና አገልግሎት ሳቢያ  ከኦሎምፒክ ቡድኑ ጋር ለመጓዝ አልቻሉም፡፡ ከሜልቦርን ኦሎምፒክ በኋላ በኢትዮጵያ ሯጮች አሰልጣኝነታቸው የቀጠሉ ሲሆን በ1960 እኤአ በሮም ኦሎምፒክ የአበበና የሌሎች የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች አሰልጣኝ ሆነው ተሳትፈዋል፡፡ ለአበበ እግር የሚበቃ ጫማ ተፈልጎ ጠፋ፡፡ ሊያደርገው የሞከር ጫማ እግሩን ስላቆሰለው አብረው መከሩ በባዶ እግሩ እንዲሮጥ ተወሰነ። በማራቶን የመጀመርያውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ አስገኘ፡፡
በ1964 እ.ኤ.አ. በቶኪዮ ኦሎምፒያድ ላይ ደግሞ ሻምበል ኦኒ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቴክኒክ አማካሪ  ነበሩ፡፡ አበበ ቢቂላ በማራቶን ሁለተኛውን የኦሎምፒክ ድሉን አሸነፈ፡፡ እ.ኤ.አ. 1968 በሜክሲኮ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ላይ በተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቴክኒክ አማካሪ ሆነው ስራቸውን የቀጠሉ ሲሆን ለረጅም ጊዜ ያሰለጠኑት ማሞ ወልዴ በኦሎምፒክ ማራቶን ከማሸነፏም በላይ ሌሎች ጥሩ ውጤቶችም ተገኝተዋል ፡፡ ኢትዮጵያም በሶስት ኦሎምፒያዶች በተከታታይ የኦሎምፒክ ማራቶንን በማሸነፍ ሶስት የወርቅ ሜዳልያዎችን የሰበሰበች ብቸኛዋ አገር ሆና እስካሁን ያልተደፈረ ልዩ ክብረወሰን አስመዘገበች፡፡
በካናዳ ሞንትሪያል እ.ኤ.አ. 1976 ላይ ኦሎምፒክ ሲዘጋጅ ሻምበል ኦኒ  የኢትዮጵያ ማራቶን ሯጮች አሰልጣኝ ሆነው እየተዘጋጁ ነበር፡፡  የአፍሪካ ቡድኖች በፖለቲካ ምክንያት ኦሎምፒኩን ለመቃወም በመወሰናቸው ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡
በስፖርት ስልጠና፤ ትምህርትና አስተዳደር
ሻምበል ኦኒ በክቡር ዘበኛ የስፖርት መኮንነት እየሰሩ በነበረ ጊዜ በሳምንት ሁለት ጊዜ በደብረዘይት በሚገኘው አየር ሃይልም የስፖርት መምህር ሆነው  አገልግለዋል፡፡ የስፖርት መኮንን ሆነው በቆዩበት ክቡር ዘበኛ የሁለት ዓመት ኮንትራታቸውን እንደጨረሱ የትምህርቱን መስክ እንዲያገለግሉ ተጠርተዋል፡፡ በሃላፊነታቸውም የመጀመርያውን ብሄራዊ የስፖርት ፕሮግራም ከማውጣታቸውም በላይ ስፖርት በስርዓተ ትምህርቱ እንዲካተት  አድርገዋል፡፡ የስፖርት ትምህርት አዲስ ነገር ስለነበር በመላው ኢትዮጵያ በመዘዋወር ማስተዋወቅ ነበረባቸው፡፡ በጅምናስቲክ አሰልጣኝነት የሰሩበትን እድል ተጠቅመው ኢትዮጵያውያን የጂምናስቲክ አሰልጣኞች በየግዛቱ ተዘዋውረው በማስተማር ለስፖርት መምህርነት አብቅተዋል። ይህም በትምህርት ቤቶች ለስፖርት ያለው ፍላጎት እንዲጨምር አስችሏል፡፡ የስፖርት መምህርነቱንም ፈርቀዳጅ የሆኑበት በአዲስ አበባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለ2 ዓመት በመስራት በተግባር አሳይተው ነበር፡፡  ከዚህ በኋላ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ በስነ ጥበባት የአካል ብቃት ትምህርት ክፍል ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙ ሲሆን የትምህርት ሚኒስትሩም አማካሪም ሆነው የሚያገለግሉ  ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ የስፖርት አስተዳደር ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው የህይወት ታሪካቸው ያመለክታል። የትምህርት ቤቶች የአትሌቲክስ ማህበርን መስርተው  በሊቀመንበርነት ሲያገልገሉ በርካታ ውድድሮች በመላው ኢትዮጵያ አዘጋጅዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሥራቾች አንዱ ሲሆኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ለብዙ ዓመታት ከመስራታቸውም በላይ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በበርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማናጀር እና አሰልጣኝ  በመሆንም ሰርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አባል የነበሩ ሲሆን በሞተር ስፖርት፤ በጅምናስቲክ፤ በሰርከስና ሌሎች የስፖርት እንቅስቃሴዎች ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ሻምበል ኦኒ ኒስካነን በኢትዮጵያ ስፖርት ያከናወኗቸው ፈርቀዳጅ ተግባራት ከምሰሶዎቹ አንዱ ያደርጋቸዋል፡፡ በስዊድኗ ከተማ ሶላኖ በሚገኝ መኖርያ ቤታቸው የተሰባሰቡ የፎቶ፤ የቪድዮ፤ የህትመትና የቁስ አይነቶች መካከል ከ400 በላይ ሜዳልያዎች እና ከ100 በላይ ዋንጫዎች መገኘታቸው የነበራቸውን ልዩ አስተዋፅኦ ይመሰክርላቸዋል፡፡
የቀይመስቀልና የህፃናት አድን  
ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ
ሻምበል ኦኒ ኒስካነን ከአፄ ሐይለስላሴ የቀረበ ወዳጅነት ስለነበራቸው ንጉሱ ለስፖርትና ሌሎች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ስራዎች ትኩረት እንዲኖራቸው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮችን  ሲያዘጋጁ በመክፈቻውና በመዝጊያ ስነስርዓቶች  ላይ በክብር እንግድነት ንጉሱ እንዲገኙ አስለምደዋል፡፡
ለናሙና ያህል በድሮው የጃንሆይ ሜዳ የቀይመስቀል ኢንተርናሽናል ፌስቲቫል ማዘጋጀታቸውን ማንሳት ይቻላል፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ የኢትዮጵያና የስዊድን ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያድግ ነው ያደረጉት፡፡ የፌስቲቫሉን መጀመር ያደነቁት ንጉሱ  የመጋልቢያ ሜዳ አሰርተው የግልቢያ ፈረሶችም ሰጥተዋል፡፡ በስዊድንና በኢትዮጵያ የወታደሮች ቡድኖች ባደረጉት ኳስ ግጥሚያም የተጀመረው ፌስቲቫሉ የስዊድን ዳንሰኞች አስደናቂ ትርኢት፤ የዳርት ጨዋታ፤ ኢላማ ተኩስ እና ቶምቦላ የተካሄደበትም ነበር፡፡ ንጉሱ ለቶምቦላው ነጭና አዲስ ቮልስዋገን መኪና በስጦታ አበርክተው የመጀመርያውን እጣ ራሳቸው ማሸነፋቸውን ሻምበል ኦኒ በታሪክ ማስታወሻቸው ገልፀውታል። ፌስቲቫሉን ከማዘጋጀታቸውም በላይ  የስዊድን የባህል ዳንስ ቡድን መሪና አስተማሪ ሆነው ያደረጉት ተሳትፎ የሚያስደንቅ ነበር፡፡ በፌስቲቫሉ ጅማሮ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ተጠቃሚነት ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሸጋገር ሰርተዋል፡፡  7ሺ ኢትዮጵያን ዶላር ገቢ በማግኘት ለኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማቋቋሚያ እንዲሆን ለግሰዋል። ፌስቲቫሉን   በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሲዘጋጅ ደግሞ ከ17000 ኢትዮጵያን ዶላር በላይ እንዳስገኘ መዝግበዋል፡፡
ሻምበል ኦኒ ኒስካነን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ ሆነው በትርፍ ጊዜያቸው በ1948 እኤአ  መስራት ጀምረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አባል እና የቦርድ አባልነት እንዲሁም በተለይም ዋና ጸሐፊነት  ለ36 ዓመታት ሰረተዋል፡፡ በከበሩ የሰብዓዊ አገልግሎቶች ውስጥ የተሳተፉ ሲሆን፤ በተፈጥሮ አደጋዎች ተጎጂዎችን ለማዳን በኢትዮጵያ በተለያዩ ሥፍራዎች ተዘዋረው በታላቅ ፍቅር አገልግለዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ባጋጠሟት ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በመሰማራት  እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ሰብአዊ ተግባራትን ፈፅመዋል፡፡ የኢትዮጵያ የቦይ ስካውት ማህበር ብሔራዊ ምክር ቤት መስርተውም በኮሚሽነርነት ሰርተዋል፡፡ ለ12 አመታት የአለርት ሆስፒታል ማናጀር ሆነው በማገልገል ከበሽታው ጋር በተያያዘ የነበረውን ጎጂ አስተሳሰብ ያጠፉ ሲሆን፤ የመላው አፍሪካ የሥጋ ደዌ እና መልሶ ማቋቋም ማሰልጠኛ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነውም ያገለገሉ ነበሩ፡፡
ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸውን በመጠቀምም ለበርካታ ዓመታት የስዊድን የሕፃናት አድን ፌዴሬሽን ከፍተኛ አማካሪም ሆነው ሰርተዋል። በኢትዮጵያ ፤ በአፍሪካና በአውሮፓ ለሴቭ ዘ ችልድርን ሲያገለገሉ ገቢ በማሰባሰብ ከፍተኛ ሚና ከመጫወታቸውም በላይ እስከ 73 ዓመታቸውም የህፃና አድን ድርጅቱን በአማካሪነት አገልግለዋል። ከስዊድን ለጋሾች ጋር በመተሳሰር የመፀዳጃ ቤት ግንባታ፣ የትምህርት ቤት አቅርቦቶች፣ ድልድይ ግንባታ፣ የመንደሩ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ቁሳቁሶች፣ አግዳሚ ወንበሮች እና ወንበሮች ወዘተ በተሰሩባቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶችና የልማት እቅዶች ላይ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡
ሻምበል ኦኒ ሄርማን ኒስካነን  ለ38 ዓመታት በኢትዮጵያና በመዲናዋ አዲስ አበባ ተመላልሰው ባሰለፉት ህይወት በኦሎምፒክ ካስመዘገቧቸው ወርቃማ ታሪኮቻቸው ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስመሰግን አገልግሎት የነበራቸው ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ በልማት መስክ የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ ማኅበራትን በማገልገል በተወጡአቸው ተልዕኮዎች፤ ለሰብአዊ እንቅስቃሴዎች እድገት በግል ባበረከቱት አስተዋፅኦ፤ ለቆሰሉት፣ ለታመሙና በጦርነት ለተጎዱ ሰዎች በሰጡት እንክብካቤ፤ በበርካታ ማህበራዊ እና የበጎ አድራጎት ሥራዎቻቸው በመደነቅ ልዩና ከፍተኛ የክብር ሽልማቶችን ሰብስበዋል፡፡
ሚያዚያ 27 ቀን 1958 ዓ.ም ላይ የኢትዮጵያ የክብር ሜዳይ የተሸለሙ ሲሆን በስዊድንም የሮያል ቫሳ  (የመጀመሪያ ደረጃ) ኒሻንም ተቀዳጅተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል እና የስዊድን ቀይ መስቀል የወርቅ ሜዳሊያዎችን ከመጎናፀፋቸውም በላይ በኖርዌይና በስዊድን ሌሎች የክብር ሽልማቶችን የሰበሰቡ ናቸው፡፡  
ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ
ይህን መፅሃፍ ያዘጋጀው ሰለሞን ሃለፎም የተባለ ፀሃፊ ነው፡፡ መፅሃፉ የኦኒኒ ኒስካነን የሕይወት ታሪክ ነው ፡፡ በዚህ መፅሃፍ ላይ ስለሮም ኦሎምፒክ እንዲህ ነው የተፃፈው…
‹‹አበበ በዚያ ምሽት ሀውልቱን ቀና ብሎ ሲመለከት ደሙ ፈላ:: ሀውልቱ በጨለማው መሃል እንደጆቢራ ተገትሯል:: ቆፍጣናው ወታደር በግፍ የተጨፈጨፉት ወገኞቹ ታሰቡት:: በባዶ እግራቸው እስከ መጨረሻው እስትንፋስ ድረስ ለተዋጉት የኢትዮጵያ አርበኞች ደም መላሽ ሆኖ ፋሽስቱን የጣሊያን መንግሥት ሊበቀለው ቆረጠ:: ትንፋሹን አሰባስቦ ፍጥነቱን ጨመረ:: እስካሁን ድረስ ከጎኑ እየተከታተለ አላፈናፍን ያለውን ሞገደኛውን የሞሮኮውን ራህዲ ትቶት ወደፊት ሸመጠጠ:: መዳረሻው ላይ ጣሊያን ሰራሹ ድንጋያማው ኦሎምፒያድ ስታዲዮም ባልደፈርም ባይነት እየራደ ነው:: አበበና የኮንስታንቲን ቅያስ ፊት ለፊት ተፋጠጡ:: የኢትዮጵያን ሕዝብ አደራ ያነገበው ጥቁሩ አፍሪካዊ ከፊት ለፊቱ ተገትሮ የሚርደውን ግምብ ድጋሚ በዓለም ፊት ለማዋረድ ፍጥነቱን ጨምሮ በቁርጠኝነት ወደፊት ተፈተለከ። የመጨረሻውን ክር ሲበጥስ የድካም ስሜት ፈጽሞ አልታየበትም። ሁለት ሰአት ከአስራ አምስት ደቂቃ ከአስራ ስድስት ሴኮንድ:: አኩሪ ሰዓት:: እየተቅበጠበጠ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረው አሰልጣኙ ኦኒ ኒስካነን በሰዎች መሃል እየተሽሎከሎከ መጥቶ አበበ አንገት ላይ ተጠመጠመ። ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ ለአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ በአንገቱ ላይ አጠለቀ:: ያገሩ ልጅ አበበ ዋቅጅራም በጣም ብዙ ታዋቂ አትሌቶችን ቀድሞ በሁለት ሰአት ከሃያ አንድ ደቂቃ ሰባተኛ ሆነ:: ጉሮ ወሸባዬ! ድል ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ሆነ።ነጭ አምላኪው አለም ተገረመ፤ አፈረም:: ኢትዮጵያና አፍሪካ ግን አንገታቸውን ቀና አድርገው በልጃቸው ኮሩ:: አንዳንድ የጣሊያን ጋዜጦችም “ኢትዮጵያን ለመውረር ድፍን የጣሊያን ሠራዊት ዘመተ:: ጣሊያን ግን በአንድ ቁርጠኛ የኢትዮጵያ ወታደር ተወረረች” በማለት በበነገታው በፊት ገጾቻቸው ላይ ጻፉ::››

Bikila: Ethiopia’s Barefoot Olympian
በ2009 ለህትመት የበቃ መፅሃፍ ሲሆን ደራሲው ቲም ጁዳህ  ይባላል፡፡ ደራሲው ስለመፅሃፉ ይዘት ሲገልፅ አበበ ቢቂላ በሮማ ኦሎምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሲሮጥ ዓለምን አስደነቀ ፡፡ በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፈ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካዊ ሲሆን ይህ ድሉም የስፖርት ጀግና ፣ የአፍሪካ ጀግና አድርጎታል፡፡ ብዙዎች ለመጀመርያ ጊዜ ያወቁት የመጀመሪያ ጥቁር አፍሪካዊ ነበር ፡፡ ቢቂላ ለዘመኑ የተፈጠረ ታላቅ ሰው ነበር - በአዲሲቷ አፍሪካ የተስፋ ምልክት።›› ብሏል፡፡ ቲም ጁዳህ በመፅሃፉ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ አበበ ቢቂላ እውነተኛ ታሪክ ከአሰልጣኙ ስዊድናዊው ኦኒ ኒስካነን ጋር መተረኩንና  ሁለቱም የስፖርቱን ዓለምን በታላቅ ታሪክ ስለማናወጣቸው ተወስቷል፡፡

Read 1127 times Last modified on Saturday, 10 April 2021 14:37