Print this page
Saturday, 10 April 2021 13:48

ከአለማችን የኮሮና ክትባቶች ለአፍሪካ የደረሳት 2 በመቶ አይሞላም ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

      በመላው አለም ለተለያዩ አገራት ዜጎች ከተሰጡት 690 ሚሊዮን ያህል የኮሮና ክትባቶች ውስጥ ለአፍሪካ አገራት የደረሳቸው ከ2 በመቶ በታች ያህሉ ብቻ እንደሆነ የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።
45 የአፍሪካ አገራት የኮሮና ክትባቶችን ማግኘታቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 43ቱ ክትባቶችን መስጠት መጀመራቸውን ያስታወሰው ድርጅቱ፣ ለአፍሪካ አገራት ከደረሱት 31.6 ሚሊዮን የኮሮና ክትባቶች ውስጥ እስካሁን ድረስ ለዜጎች የተሰጡት 13 ሚሊዮን ያህሉ ብቻ መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የኮሮና ክትባቶችን ያገኙት ከአምስት ሳምንታት በፊት ነበር ያለው ድርጅቱ፣ ብዙዎቹ አገራት ያገኙት ክትባትም ከህዝብ ቁጥራቸው አንጻር እጅግ አነስተኛ መሆኑን አመልክቷል።
በአፍሪካ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 4.3 ሚሊዮን መድረሱን የጠቆመው ድርጅቱ፣ በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥርም ከ114 ሺህ በላይ መድረሱን አክሎ ገልጧል፡፡
በሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዜናዎች ደግሞ፣ በህንድ ባለፈው ረቡዕ ብቻ ከ126 ሺህ በላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው በምርመራ መረጋገጡን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን የዘገበው ሮይተርስ፣ በአገሪቱ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 12.9 ሚሊዮን መድረሱንና የሟቾች ቁጥር ደግሞ 166 ሺህ 862 መድረሱን አመልክቷል፡፡
አልጀዚራ በበኩሉ፤ ሳዑዲ አረቢያ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ያልወሰዱ ምዕመናን ከረመዳን ጾም ጀምሮ ወደ ታላቁ የእስልምና እምነት ቅዱስ ስፍራ መካ እንዳይገቡ መከልከሏን የዘገበ ሲሆን፣ ውሳኔው ከሃጅና ዑምራ ተጓዦች በተጨማሪ ፀሎት (ሶላት) የሚያደርጉትንም እንደሚመለከት ገልጧል።
የአገሪቱን የሃጅና ዑምራ ሚኒስትር ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ሁለተኛ ዙር ክትባት የወሰዱ ምዕመናን ወደ ስፍራው በቀጥታ መግባት የሚችሉ ሲሆን፣ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት የወሰዱት ደግሞ ከ14 ቀናት በፊት የተከተቡ መሆን እንዳለባቸው ውሳኔው ያመለክታል፡፡


Read 1733 times
Administrator

Latest from Administrator