Print this page
Monday, 12 April 2021 00:00

“ለሕዝቤ ምን ይዤለት ልመለስ?”

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

“የመንግስታቱ ማህበር ዋና ዓላማና ግብሩ፣ ኃይለኛው መንግስት አቅሙን ተማምኖ ደካማውን እንዳያጠቃ ትክክለኛውን ፍርድ ለመስጠትና የትልቁንም ሆነ የትንሹን መብት በእኩል ለማስከበር ስለሆነ አንድ አባል  መንግሥት የፈፀመውን ግፍ ዘርዝሬ በማቅረብ ፍርዳችሁን እጠይቃለሁ። ዛሬ ባለንበት ሰዓት ከሁሉም ይበልጥ የዓለምን ህዝብ እጅግ ሊያስጨንቀውና ሊያሳስበው የሚችለው የዓለም መንግስታት ተስማምተው ለሰላም የሚያወጧቸውን ሕጎች በጉልበትና በማን አለብኝ መንፈስ እየተነሱ የሚደመስሱ መሪዎች መፈጠራቸው ነው። የፋሽስት መንግስት ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽመውን የግፍ ስራ በሌሎች ሀገሮች ላይ ለማድረግ ምን ያግደዋል?... ከህግና ከሰባዊ መንፈስ ውጭ ሁሉ አሰቃቂ የሆነ እልቂት ቢደርስባትም ሰላማዊና ሃይማኖተኛ የሆነው የአገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለነጻነት የሚያደርገውን ተጋድሎ እስከ እለተ ሞቱ የጠነከረ ስለሆነ፣ በየጫካው በዱር በገደሉና በየበርሃው እየተዘዋወረ በመዋጋት ጠላቱን ከማስጨነቅ አላቋረጠም።… ወደ ዠኔቭ የመጣሁት እውነትን ብቻ ተመርኩዤ፣ አቤቱታዬን ለእናንተ ለማመልከትና የመንግስታት ማህበርን እርዳታ አግኝቼ የነፃነት ትግሌን  ወደምቀጥልበት ቦታ ለመሄድ መሆኑን እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። ስለዚህም በንግግሬ መደምደሚያ ላይ የምጠይቃችሁ፤ ለህዝቤ ምን ያዤለት እንደምመለስ መልሳችሁን እንድትሰጡኝ ነው።”
ንጉሠ ነገሥቱ ሕዳር 18 ቀን 1928 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ደሴ ተጓዙ። ለሁለት ወር ጊዜ ደሴ ላይ ቆይተው ወደ ኮረም ተጓዙ። መጋቢት 10 ቀን 1928 ዓ.ም ኮረም ላይ ከራስ ካሣ ኃይሉና ከራስ ስዩም መንገሻ ጋር ተገናኙ። ከሁለት ቀን በኋላም ሐዩ ደረቅ አምባ በተባለ ቦታ ሰፍረው ራስ ካሣ ፣ ራስ ስዩም፣ ራስ ሙሉጌታና የንጉሡ አማካሪዎች ደጃዝማች ወንድራድ፣ ደጃዝማች ወልደ አማኑኤል፣ ደጃዝማች አደፍርሰው፣ ሊጋባ ጣሰው፣ ፊታውራሪ አሸናፊ እንዲሁም ሻለቃዎችና ባለ ሌላ ማዕረጎች በተገኙበት ስብሰባ ተካሄደ። የሚይጨው ጦርነት አቅዶ ወጣ። ጦሩ አራት ቦታ ተመደበ። አንደኛው ምድብ በንጉሡ የሚመራ ሆነ። ከእሳቸው ሥር ቀኛዝማች መኩሪያ ባንትይርጉ ዋና ሆኑ። በግራ የተሰለፈውን ራስ ጌታቸው አባተ፣ በቀኝ የተሰለፈውን ራስ ስዩም መንገሻ፣ በመሀል ሆኖ በግራና በቀኝ እየተደገፈና እየደገፈ የሚዋጋውን ጦር ራስ ካሣ ኃይሉ እንዲመሩት ተወሰነ። ጦርነቱ መጋቢት 21 እንዲደረግ ቢታሰብም አልሆነም። ጠላት ያስታጠቃቸውን መሳሪያ ይዘው ከንጉሡ ጎን እንደተሳተፉት የጨርጨር ባላባቶች ሁሉ የአዘቦ ኦሮሞዎች ለመሰለፍ ቀን ይሰጠን ስላሉና፣ ራስ ጌታቸው ጦሩ አልተሰበሰበልኝም ስላሉ የውጊያው ቀን መጋቢት 22 ቀን ሆነ።
የማይጨው ጦርነት ከ85 ዓመት በፊት መጋቢት 22 ቀን ንጋት አስራ አንድ ሰዓት ላይ ተጀመረ። የኢትዮጵያ ጦር አካባቢውን ቀድሞ ይዞ ምሽግ ሰርቶ ከጠበቀው ከጣሊያን ጦር ጋር ከላይ በቦምብና በመትረየስ፣ ከታች በመድፍና በመትረየስ እየተደበደበ፣ እሬሳ በሬሳ ላይ እየተነባበረ እየወደቀ፣ በወንድሙ ሬሳ ላይ እየተረማመደ፣ እንደ ቅጠል እየረገፈ ተዋጋ።
ምን ህል ባንዳ ኢትዮጵያዊ፣ ከጣሊያን ጋር ምሽግ ገብቶ እንደ ተዋጋ የጻፈልን የለም። በነፍሱ እየተወራረደ ከምሽግ ምሽግ  እየተወረወረ፣ አምስት የሚሆኑ ምሽጎችን ባስለቀቀውና ጣሊያኖች ይመኩበት የነበረውን ቫልስቴሪ የተባለውን የጦር ክፍል እያርበደበደ በነበረው የኢትዮጵያ ጦር ላይ ለጣሊያን ያደሩ የራያና የአዘቦ ሰዎች ጦር ሰርተው፣ ከጀርባ ገብተው ጨፈጨፉት። በእጁ ሊያስገባ የተቃረበውን ድል አስነጠቁት። ንጉሠ ነገሥቱ፣ አንዳንድ ተራ ወታደር ጦር ሜዳ ገብተው  የተዋጉበት የማይጨው ጦርነት በተሸናፊነት ተደመደመ። ከሞት የተረፈው ጦር በየአቅጣጫው ወደ ኋላ መመለስ ያዘ።
ሠራዊቱ ተበታትኖ እየተመለሰ በነበረበት ጊዜ የገጠመውን የከፋ አሳዛኝ ሁኔታ የሚነግሩን  ጳውሎስ ኞኞና ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ናቸው። ጳውሎስ “የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት” በተባለ መፅሐፉ፤ ሰራዊቱ ቀን ቀን በየጫካው ተደብቆ እየዋለ፣ ለሊት ለሊት ይጓዝ እንደነበር፣ በተለይም አሸንጌ ሐይቅ አካባቢ የሚገኘውን ኮረብታማና ገላጣ አካባቢ በሌሊት ለማለፍ አስቦ እንደነበር አመልክቶ፣ ጣሊያኖች “እኛ ምንፈልገው ንጉሡን ነው እንጂ እናንተን ወታደሮቹን አይደለም። ለሊት ለሊት እያረፋችሁ ቀን በብርሃን መጓዝ ትችላላችሁ” የሚል ወረቀት በመበተናቸው፣ ቃላቸውን አምኖ፣ ወታደሩ ቀን መጓዝ እንደ ጀመረ፣ 150 አይሮፕላኖች አሰማርተው በቦምብ፣ በመርዝ ጋዝና በመትረየስ እንደጨፈጨፉት፤ እሱም 28 አይሮፕላን እንደጣለባቸው ያስረዳል።
“በሽሉን ተሻግሮ ወደ መቅደላ ጉዞውን ሲያቀና ቀድሞ ተጉዞ የነበረው ጦር በወረሂመኖች እየተገደለ የሚገኘው ሬሳ ቁጥሩ ከመጠን ያለፈ ነበር። እንደዚሁም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር በሚመጣው ጦር ላይ አደጋ ለመጣል ወርሂመኖች አልቆረጡም ነበር። ወታደሩን በጥይት፣ በካራ፣ በጦር እየገደሉ መሳሪያና ልብሱን ከመግፈፍ፤ በመርዝ አድክሞ መግፈፍ የተሻለ ነው ብለው መክረው ኖሮ፣ በብዙ ርሃብና ችግር የተንገላታውንና በቦምብ መርዝ የተጠቃውን ወታደር በሸሎ በተባለው ወንዝ ዳርቻ ከወዲህና ከወዲያ ማዶ የሚበላ ቂጣ ሸጡለት።
ወታደሩ ቂጣ ማግኘቱን እንጂ ከምን የተጋገረ መሆኑን ሳያስብ ከኪሱ ባገኘው ገንዘብና በወገቡ ጥይት እየገዛ መብላት ጀመረ። የአንክርዳድ ቂጣ በልቶና ውኃ ጠጥቶ መራመድ አልቻለም። በየዛፉ ስር እየተኛ ቀረ።” በማለት ደጃዝማች ከበደ ተሰማ “የታሪክ ማስታወሻ” በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የገጠመውን መከራ መዝግበዋል። ወደ አርበኝነት የገባው ለአምስት አመትም መረራ ተጋድሎ አድርጎ፣ የሀገርን ነፃነትና  ክብር ወደ በነበረበት የመለሰው፣ ይህን ዓይነቱን ግፍ ለማለፍ የቻለው ወገን መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል።
መሐን ላይ የተመከረው እያፈገፈጉ የመዋጋት እቅድ ቀርቶ፣ ንጉሠ ነገስቱና ተከታዮቻቸው፣ በዋድላ ድላንታ በወረሂኖ አድርገው ወደ አዲስ አበባ ጉዟቸውን ቀጠሉ። ማለፊያ ይሆናሉ ተብሎ የታሰቡ አካባቢዎች አንዳንዶቹን ጠላት ቀድሞ ስለያዛቸው አቅጣጫ በመለወጥ በሚዳና በመራቤቴ  አቋርጠው ፍቼ ደረሱ። ለሊቱን ተጉዘው አዲስ አበባ ገቡ። ከንጉሡ ጋር ከጦር ሜዳ ተመለሱና አዲስ አበባ ሆነው አገር ሲጠባበቁ ቆዩ፤ ከፍተኛ የመንግስቱ ባለስልጣናት በታላቁ ቤተ-መንግሥት ውስጥ ስብሰባ አደረጉ። በዚህ ስብሰባ የተነሱ ሁለት ሃሳቦች ማለትም የመንግስቱን መቀመጫ ወደ ጎሬ ማዛወርና ወደ ደፈጣ ውጊያ ገብቶ አገርን መከላከል ቀርቶ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ዓለም ማህበር ሄደው አቤት እንዲሉና ጦሩ በየሀገሩ ገብቶ በሽፍትነት ነፃነቱን እየተከላከለ እንዲቀጥል ተወሰነ። ንጉሠ ነገስቱ፣ ቤተሰቦቻቸው፣ እነ ራስ ካሳ ኃይሉ፣ ራስ ጌታቸው አባተ፣ እነ ደጃዝማች መኮንን ሚያዚያ 24 ቀን 1928 ዓ.ም ወደ ጅቡቲ ተጓዙ። ራስ ጌታቸው ከኢየሩሳሌም ተመልሰው ለጣሊያ ገብተው፣ በወር 7000 ሊሬ የሚከፈላቸው  ሰው መሆናቸው መጠቀስ ይኖርበታል።
የንጉሡ ወደ አውሮፓ ያደረጉት ጉዞ ከመፍራትና ከመሸሽ ሲቆጠር መቆየቱ ይታወቃል። የንጉሠ ነገስቱ ጀኔቫ መሄድ የሀገራቸውን እጣ የመወሰን እድል እንዳለው ከተረዱት ሰዎች አንዱ  አቶ መኮንን ሀብተወልድ ነበሩ።  “የንጉሠ ነገሥቱ ጀኔቫ ላይ የሚያደርጉት ንግግር የተመሰረተበትን ዓላማ ስቶ ለኮለኒያስቶችና ለጥጋበኞች መሳሪያ የሆነውን የመንግስታቱን ምንነት ማህበር ለዓለም ያጋልጣል። ምን አልባትም የህይወቱ ፍፃሜ ይሆናል። ኢትዮጵያም ትድናለች” ብለው የገለጡትን ማውሳት ተገቢ ይሆናል።
“ለሕዝቡ ምን ይዠለት ልመለስ” የሚለው የንጉሡ አቤቱታ፤ ከማኅበሩ ያስገኘው ነገር ባይኖርም፣ የጣሊያን ከጀርመን ጎን መሰለፍና  ለእንግሊዝ ስጋት መሆን ለተገፋችው ኢትዮጵያ፤ የድል መንገዷን የሚቀድ ምዕራፍ እንዲከፈትላት አደረገ። በአምስት ዓመቱ የአርበኞች ትግል፤ በእንግሊዝ የጦር ድጋፍ ኢትዮጵያ ነጸነቷን መልሳ ለማስከበር ችላለች።
ከዚያም በፊት ሆነ ከአፄ ቴዎድሮስ በኋላ ነገሥታቱ ከሰራዊታቸው መሐል ሆነው አዋግተው፣ ድል ያረጋሉ ወይም እንደ አፄ ዮሐንስ በጦር ሜዳ ይሞታሉ። እነሱ ሲማረኩና ሲሞቱ ጦርነቱ ያበቃል። ሰራዊቱም ይፈታል። የአፄ ኃይለ ሥላሴን ወደ አውሮፓ ጉዞ ሽሽት አድርገው የሚያዩ ሰዎች መመዘኛቸው ይህ ነው። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ሃሳባቸውን እንዲነግሩኝ የጠየቅኋቸው የጦር መኮንኑና ደራሲው ገስጥ ተጫኔ፤ “ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመውረር እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት ንጉሠ ነገሥቱ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸውን ያሳለፉት ለጦርነት በመዘጋጀት ሳይሆን ስልጣናቸውን በማደላደል ነበር።
የመሳሪያ እቀባም በሀገራችን ተጥሎ እንደነበር መዘንጋት ደግሞ የለብንም። ጦርነቱ በአቅም በማይመጣጠኑ መካከል የተደረገ በመሆኑ የኢትዮጵያ መሸነፍ የሚጠበቅ ነው ብንልም፣ ሰራዊቱና ገበሬው በሚያስደንቅ ሁኔታ መዋጋቱን ልንክድ አንችልም። ጣሊያን ከታንክ፣ ከመድፍ ከመትረየስ በተጨማሪ በአውሮፕላን ቦምብ መጣል፣ የመርዝ ጋዝ መርጨትና ከአየር በመትረየስ ለመደብደብ የተገደደው ጦርነቱ ስላየለበት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። የንጉሱን መሰደድ እንደ ሽሽት የሚያዩት ወገኖች፤ የልማድ ጉዳይ እንጂ በወቅቱ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑ የታመነ ነው። ንጉሱ ከአገር ባይወጡ ኖሮ ጦርነት ላይ ሊገደሉ ወይም ሊማረኩ ይችሉ ነበር። ከተማረኩ ደግሞ የጣሊያንን መንግስት አውቀው እንዲቀበሉ እንዲፈርሙ ሊገደዱ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ለጣሊያን ገዥነቷን ያረጋግጥላታል። ዘለዓለም እንደ ተገዛን እንኖራለን ባንልም፣ የነጻነት ትግሉን ያከብደው ነበር። በጣልያን መካከል የጦር ጓደኝነት መፍጠር አልፎም የሁለተኛው የአለም ጦርነት መጀመር እንግሊዝ፣ የምስራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛቷን ላለማጣት፣ የኢትዮጵያን ድጋፍ መፈለግ፣ ንጉሠ ነገሥቱ ከእንግሊዝ የጦር መሳሪያ ልዩ ልዩ ድጋፍ ለማግኘት፣ አገራቸውንም ነፃ ለማውጣት አስችሏቸዋል። የእርሳቸው በውጭ አገር መኖር በአርበኞቻችን ዘንድ "ንጉሰ ነገስታችን ይመጣል፤ ባንዲራችን ተመልሶ ይቆማል" የሚል ተስፋ እንዲያድርባቸውና ትግላቸውን እንዲገፉበት በማድረግ፣ የነበረውን ዋጋም ልንዘነጋ አይገባም።” በማለት አስረድተውኛል።

Read 8583 times