Print this page
Saturday, 10 April 2021 13:26

ድብርት የሚሉት ነገር...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

  "እናማ...“አንድ የጀርመን ፈላስፋ...” “ስሙን የማላስታውሰው የእንግሊዝ ደራሲ...” ምናምን አይነት ጆከሮች ከምትመዙ ..ለምን በምንም ይሁን በምንም ስማቸውን የሰማናቸውን እነ ሌኒንን፣ እነ ቼ ጉቬራን ምናምን አትጠቅሱልንም! መረጃና ማስረጃ አቅርቡ አትባሉ!"
          
           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የምር ግን ዘንድሮ... አለ አይደል... ‘ተደብራችሁ ውላችሁ፣ ተደብራችሁ እደሩ’ ያለን ነው የሚመስለው፡፡ ነገ በጠዋቱ ቤት ውስጥ ይጀምራችኋል፡፡ እንዴት መሰላችሁ... ተዘገጃጅታችሁ (ለወንድ ‘ተኳኩላችሁ’ ማለት ይቻላል እንዴ! አይ...ዘንድሮ የአንዳንዶቻችንን ነገር ስናይ ወንዶች ‘ተኳኩላችሁ’ የሚለውን  ቃል የመጠቀም መብታችን እንዲከበር የኢንስታግራም የምናምን ዘመቻ ሳንከፍት አንቀርም!)
እናላችሁ... ከመታጠቢያ ቤት ‘ግሩሚንግ’ በኋላ ቁርስ ጠረዼዛ ላይ ትሰየማላችሁ፡፡ (እኔ የምለው...አንዳንዴ ምኑም፣ ምናምኑም ወገባችንን ሊቀነጥሰው ሲደርስ “ግዴለም ለሁለት ለሦስት ሳምንት ቁርስን ዘልዬ ምሳና እራት ብቀማምስ ይበቃኛል፣” ብለን ቀበቷችንን ለማጥበቅ ስንሞክር የሆነ የጤና ባለሙያ በሆነ መንገድ ይመጣና “ቁርስ የቀኑ ዋነኛ ምግብ በመሆኑ ማንም በምንም አይነት ቁርስ ሳይበላ መውጣት የለበትም፣” ይላችኋል፡፡ እንግዲህ አንዴ ‘ቀበቶ ካሰርን’ በኋላ ምን እናድርገው!)
እናላችሁ ገና ‘ቀበቶ ማሰር’ ሳትጀምሩ ቁርስ ጠረዼዛ ስትቀመጡ “ዛሬ አሪፍ ቁርስ በልቼ የተወለወለ ቅል መስዬ ነው ቢሮ የምገባው፣” ብላችሁ ብትጠብቁ፣ ብትጠብቁ ብቅ የሚል የለም፡፡ ትንሽ ቆይቶ እማወራዋ ብቅ ትልና “አሁንም ተቀምጠሀል እንዴ! እኔ እኮ የሄድክ መስሎኛል፣” ትላለች፡፡ “አሁንም ተቀምጠሀል እንዴ!” ብሎ አማርኛ ምንድነው! “እንዳይረፍድብህ ቢሮህ አካባቢ ዘቢብ ኬክ በሻይ ቅመስና ግባ፡፡” ምን... ለሻይና ለዘቢብ ኬክ በጠዋቱ ‘ፎርቲ’ ብር! የምን የሚያስጠላ ‘አፕሪ ዘ ፉል’ ‘ግንቦት ዘ ፉል’ ምናምን ነገር ነው! “ቁርስ የለም ማለትሽ ነው እንዴ!” የምትለው ዓረፍተ ነገር እንዴት ብላ ትውጣ! እማወራዋ ትቀጥላለች።
“ምን መሰለህ፣ ፍርፍር እንዳልሠራልህ መሶቡ ባዶ ነው፡፡ ጤፉም እንደሆነ ሀያ አምስት ኪሎ በሦስት ወር እንዴት ብሎ ይብቃቃ!” ትልና ቦክሰኞች ‘አፐርከት’ እንደሚሉት አይነት ከስር ወደላይ ‘ይቀመሰልህ’ ትላችኋለች፡፡ “ድንገት እኮ ከሰማይ ዱብ ያለ ነው የሚመስለው!” እንደሚባለው አይነት ነገር ማለት ነው። እማወራዋ ማለሳለሻ ትጨምራለች… “አምስት ቀን የሆናት ዳቦ አለች፡፡ እስዋን በሻይ ልስጥህ እንዴ!” ጎሽ...ገንፎ በቅቤ ስታስቡ ዳቦ በሻይ! ያውም አምስት ቀን የከረመች ፉርኖ! የማንም የምንም ሳትሉ ተነስታችሁ ውልቅ ነው፡፡ የመጀመሪያው ድብርት፡፡
ወደ መከረኛ ታክሲ ሰልፍና ግፊያ። ሰዉ  በመስመር የቆመ ይምሰል አንጂ አንዳንዱ ሰልፍ አሁን፣ አሁን ግፊያ በሉት። (እኔ የምለው...በጾም ሰሞን አንዳንዱ ዳሌ እንዴት ነው ይህን የሚያካክለው!… አንድ ሰሞን ‘የጾም እንቁላል’ ይሉ እንደነበረው ‘‘የጾም ስጋ’ የሚባል ነገር ተጀመረ  ወይስ እኛ የማናውቀው ‘ካልኩሌሽን’ የሰጣችሁ አለ!) እናላችሁ... ደግነቱ ገና ሰዉ መተራመስ ስላልጀመረ ሰተት ብላችሁ በሩ ወለል ወዳለው ወደ አንደኛው ታክሲ ትሄዳላችሁ። ልክ ልትገቡ ስትሉ ረዳቱ “ወዴት ነው?” ይላችኋል፡፡ (እነሱን ልጆች ግን ሲያበሽቋችሁ ‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ በማይመስለው ‘ተለዋጭ’ ስማቸው ጮክ ብሎ መጣራት አያሰኛችሁም! እሱ ቃል ሌላም ትርጉም አለው ብዬ ነው፡፡ ረዳቶች... ረጋ በሉልና! )
“አራት ኪሎ፡፡”
“አራት ኪሎ አይሄድም፡፡ ካዛንቺስና ሀያ ሁለት ብቻ፡፡”
“በዛው በኩል አይደለም እንዴ የምታልፉት!” “ታፔላው ላይ አራት ኪሎ ተብሎ ተጽፎበት የለም እንዴ!” ምናምን በሚል ብትጨቃጨቁ ውጤቱን ስለምታውቁት “ይቅርብኝ፣” ትሉና ወደ ኋላ ማፈግፈግ ትጀምራላችሁ፡፡ እናማ... ከረዳቶች ጋር ከመጨቃጨቅ ይሰውራችሁ። ልክ ነዋ... የመብት ማስከበር ጉዳይ ሳይሆን ልክ የሆነ ችሎት...አለ አይደል... “ለሦስት ወር ከሁለት ሳምንት ከታክሲ ረዳቶች ጋር ያጨቃጭቅህ!” የሚል የፍርድ ውሳኔ የተላለፈብን ነው የሚመስለው፡፡  
እንደውም እኮ...አለ አይደል...ምንም ባታደርጉ እንኳን “ምን ይንጠራራል!” “ታከሲውን የገዛ መሰለው!” አይነት ነገር ሲወርድባችሁ ጠጥታችሁ ጭጭ ነው፡፡ ባስ ሲል ደግሞ “ምነው ሀይገር መሰለህ እንዴ!” (የታክሲና የአውቶብስ ነገር የ‘ክላስ’ መለያ ምናምን መደረጉ ነው እንዴ!) እናላችሁ... “ሁሉንም ጊዜ ይፈታዋል፣” አይነት ‘ታይም’ ያልጠበቀ ፍልስፍና እያሰባችሁ ስታፈገፍጉ የሆነ እጅ ወደ ታክሲው በር ገፋ እያደረጋችሁ “አራት ኪሎ አይደለህ...ግባ፣” ይላችኋል። ስሙኝማ...የምር ግን “ለጣይም ፈንጋይ ያዝለታል፣” የሚለውን ተረት ትክከለኛነት የምታረጋግጡት ረዳቱ የከለከላችሁን ተራ አስከባሪው ከግፍተራ ጋር ሲፈቅድላችሁ ነው፡፡
የምር ግን... ደግሞም በዛኛው ዘመን ‘ተጨቋኝ መደብ’ ይባል በነበረው ውስጥ መሆናችሁን የምታወቁት እንዳትገቡ ስትከለከሉም መንገድ ተዘግቶባችሁ። እንድትገቡ ሲፈቀድላችሁም ተገፍትራችሁ! (እኔ የምለው... ምርጫው እንደዚህ እየቀረበም ሲመጣ አንድም “ሌኒን እንዳለው…” ብሎ የሚጠቅስ  ፖለቲከኛ ይጥፋ! ሰውየው አሉ የተባለውን ሰምታችሁ የለ…የሆነ ስብሰባ ላይ ብደግ ብለው “ሌኒን እንዳለው የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች…” ይላሉ፡፡ እናላችሁ... አንደኛው ተሰብሳቢ… “አንቱ…መቼ ነው ደግሞ ሌኒን እንዲህ ያለው?” ሲላቸው ምን ብለው ቢመልሱ ጥሩ ነው…“እሱ ምን ያላለው ነገር አለ!” ልክ ነዋ… እውነት እንነጋገር ከተባለ በዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች ሴራ ዝምታ ነው እንጂ ‘ቦተሊከኞቻችን’ ምን ያላላችሁት ነገር አለ!  እኛ ጭጭ ያልነው ጭቅጭቅ ምን ያደርጋል ብለን ነው፡፡
“አንድ የጀርመን ፈላስፋ በአንድ ወቅት እንደተናገረው...”
“ስሙን የማላስታውሰው የእንግሊዝ ደራሲ እንዳለው...”
እናማ...“አንድ የጀርመን ፈላስፋ...” “ስሙን የማላስታውሰው የእንግሊዝ ደራሲ...” ምናምን አይነት ጆከሮች ከምትመዙ ..ለምን በምንም ይሁን በምንም ስማቸውን የሰማናቸውን እነ ሌኒንን፣ እነ ቼ ጉቬራን ምናምን አትጠቅሱልንም! መረጃና ማስረጃ አቅርቡ አትባሉ!
 እናላችሁ...የታክሲው ረዳት የከለከላችሁን ታክሲ ተራ አስከባሪው የቬቶ መብቱን ተጠቅሞ ውሳኔውን በመገልበጥ እንድትገቡ ይፈቅድላችኋል፡፡ ስሙኝማ... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... ምን ይመስለኛል መሰላችሁ... እንደ ተራ አስከባሪዎች ‘ሰልፍ ዲተርሚኔሽን’ በራሳቸው መንገድ  የተረጎመ የለም፡፡ ብዙ ቦታ እኮ... ‘ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ’ አይነት ስልጣን ነው ያላቸው፡፡ እኛን እንደፈለጉ የሚያደርጉን ረዳቶች እኮ በተራቸው የተራ አስከባሪዎችን ስደብ ቁጣና...ብሎም ጥፊና እርግጫ ሁሉ ይቀምሳሉ፡፡ እነ እንትና...ይሰማል! ለጣይም ፈንጋይ አለው ለማለት ያህል ነው፡፡
እናማ... እንድትገቡ የፈቀደላችሁ ተራ አስከባሪው፣ ረዳቱ አራት ኪሎ እስክትደርሱ  በግልምጫና አልፎ፣ አልፎም በማጉረመረም መከራችሁን የሚያበላችሁ እናንተን! ፌይር አይደለም፡፡ የምር ግን....የአንዳንድ ቀኑ ድብርት በቃ ነክሶ ንቅንቅ የለም፡፡ ታዲያላችሁ...ደግሞ የታክሲው ሬድዮ ተከፍቶ ምን የሚል ዜና ብትሰሙ ጥሩ ነው... “የእንትን የገቢዎች ቢሮ ግብራቸውን በጊዜ በማይከፍሉ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ፤” ኸረ እባካችሁ...ሳንደበር ቢሯችን ወይም የምንሄድበት ስፍራ እንድረስበት፡፡ አሀ፣ ልክ ነዋ...በ‘እርምጃ ተወሰደ’ ስንት ጉድ የተካሄደበት አገር እኮ ነው፡፡ ለምንድነው ‘እርምጃ’ ከማለት “በህግ ይጠየቃሉ...” አይነት ‘ጨዋ’ አነጋገሮች የማይጠቀሙት!
እናማ...“ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል” የሚል መልእክት ሳትለጥፍ ጊዜ እየቀደማት ያለች ካፌ ውስጥ ለቀጠነች ሻይና ለደከመች ተቆራጭ ዓርባ ብር ስትጠይቁ ካልተደበራችሁ በምን ልትደበሩ ነው!
እናማ...ዘንድሮ፣
እንዲሁ ነጋ ጠባ እየወዘወዘን ያለው የኑሮ ነገር ደብሮናል፡፡
መያዣ መጨበጫ ያጣ የሚመስለው የሀገራችን ፖለቲካ ደብሮናል፡፡
ከማይክራፎን ጋጋታና ከቴሌቪዥን ድርድር ባለፈ ጠብ የሚል ነገር የሌለበት የመግለጫ ጋጋታ ደብሮናል፡፡
ሌላውን ወገን ማለትም ከእኛ ወገን ያልሆነውን ሁሉ ከማውገዝና ከመገዝገዝ የተሻለ ነገር የማንሰማባቸው ቃለ መጠይቆች ደብረውናል፡፡
ከትናንት ወዲያም፣ ትናንትም፣ ዛሬም ተመሳሳይ የሚመስል ነገር የሚናገሩ አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ደብረውናል።
ከድብርት ነጻ የሆነውን ዘመን ያምጣልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1283 times