Monday, 12 April 2021 00:00

"የሁለቱ መደመሮች" መጽሐፍት ዳሰሳ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ውድ አንባቢያን፡- ይህ ጽሁፍ፤ ቅዳሜ መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ሆሄ የስነ ጽሁፍ ሽልማት ድርጅት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የዶ/ር ዐቢይ አህመድን “የመደመር መንገድ” (2013) የተሰኘውን መጽሐፍ ለመዳሰስ በከፊል የተዘጋጀ ነው። ጽሁፉ ረጅም በመሆኑ በዝግጅቱ ላይ ያቀረብኩት በጣም አነስተኛውንና ወሳኙን ክፍል ብቻ ነው። ረዘም ያለ ጽሁፍ የማንበብ ልምድ እየጠፋ መሆኑን አውቃለሁ። ትልልቅ ሃገራዊ ጉዳዮችን በአንድ መስመር የትዊተር ወይም የፌስቡክ መስመሮች ማቅረብ ግን አይቻልም። ይህን ተረድታችሁ በትዕግስት እንድታነቡ በአክብሮት እጋብዛችኋለሁ፡፡
                አንዳርጋቸው ጽጌ


          መንደርደሪያ
“መደመር” የሚል ርእስ የተሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መጽሐፍ በ2012 ሲወጣ በሃገር ውስጥ አልነበርኩም። ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ የመጽሐፉ መታተምና መሰራጨት የቀሰቀሰው መቁነጥነጥ ረግቦ ነበር። የመጽሐፉ ግምገማና ዳሰሳም አልቆ ነበር። እኔም ይህን መጽሐፍ በወጉ ለመዳሰስ ፍላጎቱ ቢኖረኝም የዳሰሳው ወቅት ያለፈ ስለመሰለኝ ፍላጎቴን መግታት ነበረብኝ።
ሆኖም ግን በወቅቱ በመጽሐፉ ዙሪያ የተሰጡ አስተያየቶችን፣ ዳሰሳዎችንና ግምገማዎችን ከማዳመጥና ከማንበብ አልቦዘንኩም። በርካታ ዳሰሳዎች ወይም አስተያየቶች በአድርባይነት የተሞሉ፣ የማይተናነሱት በጋጠ ወጥነት፣ ከዛ የተረፈው በገምጋሚዎች የእውቀት ልኬት የተወሰኑ እንደሆነ ለመታዘብ ችያለሁ።
በኢትዮጵያ መጽሐፍትን በአድርባይነትና በግብዝነት መገምገም፣ ከዛም አልፎ ፈጽሞ አንድም መስመር ሳያነቡ ወይም ከአንድ ትልቅ መጽሐፍ ሁለት መስመሮችን ወስደው ዳሰሳና ትችት ለማቅረብ በየትኛውም መድረክ ላይ በድፍረት መቅረብ የማያሳፍራቸው ሰዎችን እያየሁ ነው። የመደመር መጽሐፍ ዳሰሳም ከዚህ የተለየ እጣ አላጋጠመውም። ይህ የግል ግንዛቤዬ ነው።
“መደመር” ሰፊ አንባቢ የማግኘት እድል ያለው መጽሐፍ ነው። ተጽእኖ አሳዳሪነቱ ግዙፍ እንደሚሆን አያጠያይቅም። መጽሐፉ በወጉ ሳይዳሰስ ቀረ የሚል ቁጭት እንዲያድርብኝ ያደረገውም ይህ ነጥብ ነበር። ሰሞኑን ግን ከዚህ ቁጭት የሚገላግለኝ አጋጣሚ ተፈጠረ። ይህ አጋጣሚ የሁለተኛውና ከመደመር ጋር ግንኙነት ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ “የመደመር መንገድ” የሚለው መጽሐፍ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለንባብ መብቃቱ  ነው። ሁለቱ መጽሐፎች ተያያዥነትና ተደጋጋፊነት ስላላቸው እግረ መንገዴን የመጀመሪያውን ጭምር ብዳስሰው አግባብነት ያለው መሰለኝ። በመሆኑም ይህን “የሁለቱ መደመሮች” የተሰኘውን ዳሰሳ አቀረብኩ።
የመጽሐፎቹ ተመሣሣይነትና ልዩነት
መጽሐፎቹ በጣም ተደጋጋፊ ሃሳቦችን የሚያነሱ ናቸው። ይህን ስል ልዩነት የላቸውም ማለት አይደለም። አላቸው። ልዩነታቸው ግን ከኔ ዋነኛ የዳሰሳ ቅኝት አኳያ አይደለም። የመጀመሪያው “መደመር” ትኩረት፣ መደመር ለሚለው ቃል ትርጉም በመስጠትና በዚህ ትርጉም አማካይነት የሃገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህላዊና የሌሎችንም ስብራቶቿን መፈተሽና የመጠገኛውን መንገድ ማመላከት ነው። ሁለተኛው “የመደመር መንገድ” መደመር የሚለውን ቃል በተለያዩ ትረካዎች አማካይነት የበለጠ ማብራራትና ማጎልበት እንዲሁም ተጨማሪ ትርጉም መስጠት ነው። ሁለተኛው መጽሐፍ “መደመርን” በተመለከተ በመጀመሪያው መጽሐፍ ላይ ያልተካተቱ ነገሮችን አካቷል። የመጽሐፉ ዋና ትኩረት ግን እዚህ ላይ አይደለም።
“የመደመር መንገድ” አብዛኛዎቹ ገጾች የጠፉት በማሰላሰል ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በሚተረኩ ጉዳዮች ላይ ነው። ትረካው የመደመር ሃሳብ በዐቢይ አእምሮ ውስጥ እንዴት እያደገ እንደመጣ ከልጅነቱ እስከ ጎልማሳነቱ ካለፈባቸው የህይወትና የስራ ተሞክሮዎች ጋር እያዛመደ የሚያቀርብበት ነው። እነዚህ ጉዳዮች በመጀመሪያው መደመር ነካ የተደረጉ ቢሆንም፣በሁለተኛው መደመር ሰፋ ተደርገው ቀርበዋል።
“የመደመር መንገድ” ውስጥ ሌሎች የተለያዩ በርካታ ትረካዎች አሉ። ኢህአዴግ ውስጥ ህይወት ምን ይመስል እንደነበር፣ ኢህአዴግን ለመቀየር ስለተደረገው ትግል፣ ከሶስት አመት በፊት ስለመጣው ለውጥ፣ ፈተና እና ድሎቹ፤ ከለወጡ በኋላም ስለተደረጉ ትግሎችና ድሎች ይተርካል። ስለተከናወኑ ስራዎች፣ ሌሎች የመደመርን ሃሳብ ስላበለጸጉት የዶ/ር ዐቢይ ግላዊ ገጠመኞች፣ ስለ ወደፊት ህልሞችና ስለ ሌሎችም ጉዳዮች ተተርኳል። በነዚህ ትረካዎች መሃልም የመደመር ሃሳብ በተደጋጋሚ ይነሳል።  
ሆኖም ግን እነዚህ ትረካዎች በመደመር ላይ ከሚሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም መግለጫ  ይልቅ በሚሰጡን አዳዲስ መረጃዎች የላቀ ፋይዳ አላቸው። እነዚህ ትረካዎች ጸሃፊው ምን አይነት ሰው? ምን አይነት እውቀትና ክህሎት አለው? ምን ያልማል? ህልሙን ለማሳካት ምን ያህል እልህና ቁርጠኛነት አለው? የሚሉ ጥያቄዎች ለሚያነሱ በቂ መልስ የሚሰጡ ናቸው።
ሃገራችን ውስጥ መጽሐፍ በገለልተኛነት የሚያነቡ ብዙ ዜጎች መኖራቸውን ብጠራጠርም ከተገኙ ግን በዐቢይ ነገሮችን እርስ በርሳቸው አጎናጉኖ ለአንባቢ በሚጥም ለዛና ውበት ደረቅ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮችን ማቅረብ በመቻሉ መገረማቸው አይቀርም የሚል እምነት አለኝ።  
እነዚህ ትረካዎች “የመደመር መንገድ” ሲመረቅ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፣ በማህበረሰባችን ውስጥ አንዳንዶች እያነሱት ነው በማለት ላነሳው ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ። ዳኛቸው ጥያቄውን “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራ የላቸውም ወይ በዚህ አይነት አስቸጋሪ ወቅት መጽሐፍ የሚጽፉት? እያሉ ነው” በማለት ነበር ያቀረበው፡፡ እነዚህን ትረካዎች የሚያነብ ሰው የሚያነሳው ጥያቄ፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ይጽፋሉ” የሚል ሳይሆን “ባይጽፉ ምን ይሆኑ ነበር” የሚል ይሆናል። ጉዳዩን በደንብ የተረዳው “ባይጽፉ ሊያብዱም ይችሉ ነበር” ሊል ይችላል። ቀልዴን አይደለም።
 ዶ/ር ዐቢይ በሁለቱ መጽሐፎች ውስጥ ያሰፈሯቸውን ከጭንቀት፣ ከቁጭት፣ ከእልህ፣ ከቁጣ፣ ከምኞት፣ ከፍላጎት፣ ከህልም፣ ከትልምና ከሌሎች ነገሮችና ስሜቶች ጋር የተያያዙ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ሃሳቦች በጭንቅላታቸው ይዘው በምንም አይነት ጤነኛ ሆነው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስራ ሊሰሩ እንደማይችል እነዚህ ትረካዎች ማስረጃ ናቸው። ሃሳባቸውን በማጋራታቸው ከሚያገኙት ጥቅም ባሻገር ጽሁፎቹ ጠ/ሚኒስትሩ ለራሳቸው የሰጡት የስነ አይምሮ ቴራፒ ተደርገው መወሰድ የሚችሉ ናቸው። ይህ ቴራፒ የዐቢይን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስራ ያቀለለው እንጂ ያከበደው እንደማይሆን እምነቴ ነው።
የዳሰሳው ዳራ
የዐቢይ መጽሐፎች ከበርካታ የዳሰሳ አቅጣጫዎች ሊታዩ የሚችሉ እጅግ በርካታ ጉዳዮች አጭቀው የያዙ ናቸው። አጭቀው ስል በቀላሉ መወሰድ የለበትም። የኔ የዳሰሳ ትኩረት በሁለቱም መጽሐፎች ርእስና በውስጥ ገጻቸው ዐቢይ ትልቅ ትርጉም በሰጠው “መደመር” በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ይህን የማደርገው በሁለቱ መጽሐፎች ውስጥ ዐቢይ በሚያነሳቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ ዳሰሳ ማድረግ፣ ከዳሰሳ ክልል አውጥቶ ሌላ መጽሐፍ የሚያጽፍ ሆኖ ስላገኘሁት ነው።
ክዚህ በመነሳት የዳሰሳዬን ዳራ እንደሚቀጥለው በሁለት ርዕስ ከፍዬ አቀርበዋለሁ። የመጀመሪያው ከይዘት ባሻገር የሁለቱን  መጽሐፎች ጥንካሬና ድክመት የምዳስስበት ይሆናል። ሁለተኛው  የሁለቱንም መጽሐፎች የይዘት ዳሰሳ የማቀርብበት ክፍል ነው። አስፈላጊ ሆኖ ሳገኘው በሁለቱም የዳሰሳ ክፍሎች ሁለቱንም በአንድ ላይ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሳይገኝ በተናጠል የምዳስስበት አግባብ እንደምከተል አስቀድሜ መግለጽ እሻለሁ።
“መደመር” 2012 እና “የመደመር መንገድ” 2013፤ ከይዘት ባሻገር “የመደመሮቹ” ጥንካሬና ድክመቶች
ወደ ይዘቱ ሳልገባ ሁለቱም መጽሐፎች በበርካታ ጥንካሬዎች የታደሉ ሆነው ያገኘኋቸው ሲሆን  እነዚህን አጠር አጠር አድርጌ አቀርባቸዋለሁ፡፡  
ጉዳዩ የገንዘብ አቅም እንደሆነ ቢገባኝም፣ ለህትመት ጥራት የተሰጠው ትኩረት በከፍተኛ የጥራት ልቀት የተዘጋጁ መጽሐፎች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ከመጽሐፎቹ  አጠራረዝ ጀምሮ፣ የሽፋኖቹን የምስል ጥራት አካቶ፣ እያንዳንዱ ገጽ የታተመበት የህትመት ጥራት፣ ለእይታ ማራኪነትና ለመነበብ ያለው ሳቢነት የመጽሐፎቹ መልካም ጎን ነው።
መጽሐፎቹ አግባብነት ባላቸው ክፍሎች፣ ምእራፎችና ንኡስ ምእራፎች የተከፋፈሉ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ሁለቱም መጽሐፎች ከአጠቃላይ ቅርጻቸውና ይዘታቸው ጋር የማይሄዱ ክፍሎችና ምዕራፎች መያዛቸው እንደ ድክመት ሊታይባቸው ይችላል። በኔ እይታ።
በመጀመሪያው መጽሐፍ የወጭ ጉዳይን በተመለከተ የገባው ክፍል እንዳለ መቅረት ይችል ነበር። ምክንያቱን በሚቀጥሉት ገጾች አቀርባለሁ። “የመደመር መንገድ”ም የተወሰኑ ምእራፎች ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ናቸው። በመጽሐፉ የምረቃ ወቅት የተጠቀሰው “የብልጽግና ተረክ” የተሰኘው ምእራፍ፣ በውስጡ ብዙ ቁም ነገሮችን የያዘ ቢሆንም፣ የፕሮፓጋንዳ ጎኑ ያየለ ስለሚመስል ቢቀር ጥሩ ነበር። የመጽሐፉን የአጻጻፍ ወጥነት ያደናቀፈው ይመስላል፡፡ ሌሎችም ይህን ንኡስ ምእራፍ ተከትለው የመጡ ሌሎች ንኡስ ምእራፎችም የስራ ዘገባ የሚመስል ነገር አላቸው። በውስጣቸው ብዙ ቁም ነገር ቢኖራቸውም፣ ከትረካ የራቁ ስለሚመስሉ እነሱም ባይገቡ መጽሐፉን በውበትም ሆነ በይዘት የሚያደኸዩት አይሆንም ነበር።
በሁለቱም መጽሐፎች፣ አረፍተነገሮች በቀላሉ አንባቢ ሊረዳቸው የሚችሉ፣ አጫጭር፣ የሚደጋገሙ አታካች ስንኞችና ቃላት ያልበዙባቸው ናቸው። የፊደል ግድፈት ወይም ስህተት የማይታይበት ምልኡ የአርትኦት ስራ ተካሂዶባቸዋል። ሁለተኛው መጽሐፍ ትንሽ የአርትኦት ችግር ቢኖርበትም።
የመጀመሪያው መጽሐፍ “መደመር” በተለይ፣ በተበጣጠሰ መልኩ እዚህም እዚያም ሲወረወሩ የምናያቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ እሳቤዎችን አመለካከቶችን፣ ጽንሰ-ሃሳቦችን በአንድ መጽሐፍ ውስጥ በጥቂት ገጾች በቀላሉና በተደራጀ መንገድ ማቅረብ ችሏል።
በሁለቱም መጽሐፎቹ ዐቢይ በግብዝነት ላይ ለተመሰረተ አዋቂ ሊያስመስለው ስለሚችል ጉዳይ አልተጨነቀም። ራሱም ሆነ ማንም ግለሰብ ሊያቀርባቸው የሚችሉ አመለካከቶችን፣ አባባሎችን፣ አስተያየቶችን፣ የአዋቂዎች ድጋፍ ያላቸው ለማስመሰል ጽሁፉን አላስፈላጊ በሆኑ ጥቅሶች አልሞላውም። ይህ አጻጻፍ ለትረካው ያልተደነቃቀፈ አፈሳሰስ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ብዙ ጊዜ በባእድ ቋንቋ ውይይት የሚደረግባቸውን፣ የሃገራችን ምሁራን “በአማርኛ ለማቅረብ አስቸጋሪ ናቸው” በማለት በባእድ ቋንቋ ሲያስተናግዷቸው የኖሩ የሃገራችንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች፣ እይታዎች፣ እሳቤዎችና መፍትሄዎችንም፣ ደራሲው በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በኦሮምኛ ጭምር ማቅረብ መቻሉ ትልቅ ክንዋኔ ነው።
በመጽሐፎቹ ውስጥ በተለይ በመጀመሪያው መጽሐፍ የቀረቡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ነክ፣ የተለያዩና የረቀቁ አተያዮች፣ ንድፈ ሃሳባዊ መሟገቻዎች በቀላሉ ምሁር ያልሆነ አንባቢ ሳይቀር ሊረዳው በሚችል ሃገራዊ ቋንቋ በመጻፍ፤ በርከት ያለ አንባቢ ሌላ ጊዜ የማይደፍራቸውን የሃሳብ ዘርፎች ደፍሮ ማንበብ እንዲችል፤ አንብቦም የራሱን አቋም እንዲወስድ፣ ከሌሎች ጋር ሃሳብ እንዲቀያየርና እንዲከራከር የሚያስችል አቅም የሚሰጠው ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
 የመጽሐፎቹ  ጸሃፊ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆኑ፣ ከዚህ ቀደም መሰረታዊ በሆነ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ መጽሐፍትን ለማንበብ ፍላጎት የማይኖረውን የህብረተሰብ ክፍል፣ እነዚህን መጽሐፎች እንዲያነብ ያደርገዋል። ይህ  ብቻ ሳይሆን ከዚህም ንባብ ተነስቶ በሃገሩ ጉዳይ ዙሪያ የተጻፉ ሌሎች መጽሐፎችን የማንበብ ፍላጎት እንዲኖረው የሚያበረታታ፣ የአንባቢን ቁጥር በማሳደግ በጎ ተጽእኖ ማሳደር የሚያስችል እንደሆነ  አምናለሁ፡፡
መጽሐፎቹ በተለይ “መደመር” በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን የሃገራችንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮችንና  (ዶ/ር ዐቢይ እንደሚለው “ስብራቶች”) መፍትሄዎቻቸውን  በዝርዝር ያቀረበ በመሆኑ ምንም አይነት የረባ የድርጅት ፕሮግራምና ፖሊሲዎች ለሌላቸው የሃገራችን በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌላው ቢቀር ፍላጎቱ ካላቸው፣ ለፕሮግራም መጻፊያ ወይም ለፖሊሲ ጥናት መነሻ የሚሆኑ መንደርደሪያ ሃሳቦችን የሚያስታጥቃቸው እንደሚሆን አስባለሁ፡፡ ከየትም ተቆርጦ በሚለጠፍ ስልት ከሚዘጋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራም፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ፕሮግራም መጻፍ እንዲችሉ ያግዛቸዋል። የፖለቲካ ድርጅቶች ከጥቅል ፕሮግራም ወደ ዝርዝር የሴክተር ፖሊሲዎች ጥናት የመሻገር ግዴታ እንዳለባቸው ይጠቁማቸዋል። ፖለቲካ ከስሜት ወጥቶ በምክንያት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በጎ ጫና ያሳርፋል።
ትልቁ የመጽሐፎቹ ጥንካሬ በስልጣን ላይ የሚገኝ አንድ መሪ “የሃገራችን ዋና ዋና ችግሮችና መፍትሄዎቻቸውም እነዚህ ይመስሉኛል” በማለት ሃገሪቱን ወዴት ሊወስዳት እንደሚሻ ሁሉም ዜጋ በአደባባይ እንዲያየው ጽፎ ማሳተሙ ነው። እንኳን ሃገር የሚመሩ ፖለቲከኞች ቀርተው ህይወታቸውና ሙያቸው ሃሳብን በሃሳብ መሞገት የሆነው የአካዳሚ ሰዎችም፣ መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ለመሰንዘር ድፍረት ባጡበት ሃገርና ዘመን፣ የሃገሪቱ መሪ የሆነ ሰው ሃሳቡን፣ ጨዋውም ባለጌውም፣ አዋቂውም አላዋቂውም እንዲያነበውና የፈለገውን አስተያየት እንዲሰጥበት በማድረግ ለህዝብ ማቅረብ መቻሉ ትልቅ ፋይዳ አለው።
መጽሐፎቹ የደራሲውን ደጋፊዎች በጽናት ከጎኑ እንዲቆሙ፣ ተቃዋሚዎቹ ለምን እንደሚቃወሙት ምላሻቸውን በአግባቡ፣ በጽሁፍ እንዲሰጡ ያበረታታሉ። በጨበጣ የሚደረግን የተቃውሞ ባህል ያዳክማሉ። ከዛም አልፎ ሀገርና ህዝብን ሊያሻግሩ የሚችሉ ሃሳቦችን በአአምሮዋቸው ወይም በቢሮ መሳቢያቸው አስቀምጠው፣ የአላዋቂን ትችትና የባለጌን ስድብ ፈርተው ምንም ላለማለት በፍርሃት ተሸብበው የሚኖሩ የሃገሪቱ ልሂቃን፣ ከፍራቻ ቆፈናቸው ወጥተው በሃሳብ ማህበረሰብን የመምራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያበረታታሉ።
“የመደመር” ጥንካሬ ተደርጎ መታየት ቢችልም፣ በሌላ በኩል የድክመት ጎን የታየበት ጉዳይ፣ ከዐቢይ እምነቶች ጋር የማይስማሙ አመለካከቶች በንጽጽር በሚቀርቡበት ወቅት ደራሲው በተቻለ መጠን ሃሳቦችን በገለልተኛነት የማቅረቡ ጉዳይ ነው። በሃገራችን የተለመደው የራስን አመለካከት ትክክለኛነት ለማስረገጥ የሌላውን የማጣጣል፣ የማንቋሸሽ፣ በአሽሙር፣ በስድብና በፍረጃ የሚያቀርብ አለመሆኑ ከመጽሐፉ ጠንካራ ጎኖች ጋር የሚመደብ ሃቅ ነው። ይህም ለሰለጠነ የተዋስኦ ባህል የራሱን ድርሻ ተጫውቷል።
ይህን ስል ግን፣ “ዐቢይ ከራሱ እምነት ጋር ተቃራኒ የሆኑ የፖለቲካ ይሁን የኢኮኖሚ ነክ አመለካከቶችን ወይም እሳቤዎችን በሚገባ ያላቀረበባቸው ቦታዎች የሉም” ማለት አይደለም። ከይዘት ውጭ ባሉ ጉዳዮች ላይ በድክመት ማቅረብ የምችለው አንድ ነጥብ ቢኖር ይህ ብቻ ነው። ይህ ድክመት አንድ ይሁን እንጂ ትልቅ ድክመት ይመስለኛል።  ይህ ድክመት ተቃራኒ  አመለካከቶችን በደንብ ካለማወቅ ወይም ካለመረዳት ወይንስ “በተሟላ መንገድ ማቅረቡ የራስን አቋም ያዳክማል” ከሚል ይሁነኝ ተብሎ የተደረገ መሆኑን  ማወቅ አይቻልም። ለምሳሌ “ኢህአዴግ በረጅም የስልጣን ዘመኑ ምንም አልሰራም” የሚሉ ወገኖች ከጭፍን ጥላቻ ወይም ሌሎች የሰሩትን በበጎ ከማያይ ባህላችን የሚመነጭ አመለካከት ብቻ አድርጎ በሚያየው አተያይ ላይ ዐቢይ ያተኩራል። ይህ የዐቢይ እምነት እውነትነት የለውም ማለት አይደለም።
በሌላ በኩል ግን “ኢህአዴግ ከቆየበት የስልጣን ዘመን ርዝማኔ፣ ካገኘው መልካም አጋጣሚ አኳያ ሲታይ፣ ሃገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ማስመዝገብ ትችል ከነበረው እድገት መጠነኛ ሊባል የሚችል እድገት ማስመዝገብ ባለመቻሉ፣ የሃገሪቱን እድገት ወደ ኋላ የጎተተ እንጂ ወደፊት ያመጣ ተደርጎ ትንሽም እውቅና ሊሰጠው አይገባም” የሚለውን ምክንያታዊ ክርክር በሚገባ አይፈትሸውም።
በኢህአዴግ ላይ የሚቀርበው ነቀፋ “ድርጅቱ ካለማው ያጠፋው በዝቷል። ሃገሪቱ ያስመዘገበችው አሉታዊ እድገት ነው” የሚለው ክርክር በዚህ አይነቱ አመክንዮ ላይ የተመሰረተ ጭምር መሆኑን የሚያሳየው ክርክር በመጽሐፉ ውስጥ ቦታ አላገኘም፡፡ (መደመር ገጽ 25፣ ገጽ 33 ገጽ 155-156 በሌሎችም ገጾች ከሁኔታዎች ማእቀፍ ውጭ ኢህአዴግ ያስመዘገባቸውን ድሎች በአንጻራዊነት የሚያቀርቡ ትረካዎች የቀረቡባቸው ገጾች ናቸው። “በመደመር መንገድ” ገጽ 25 #ቤተኛ ባይተዋር; በሚለው ርእስ ስር ተመሳሳይ እይታ ይንጸባረቃል።)
ዛሬ በፖለቲካ ሆነ በኢኮኖሚ መስኩ ሃገሪቱ የምትገኝበት እጅግ አስፈሪ የሆነ ረግርግ (ሌላው አካባቢ ቀርቶ 30 አመት ሙሉ ወያኔ የተሻለ አመራር ሲሰጠው ነበር በሚባልበት በትግራይ ውስጥ ያለውን እጅግ አሰቃቂ የድህነት ረግርግ እያየን ነው። ይህን እያየን በ30 አመት ስላደገ የሃገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢና ስለተከናወኑ የልማት ስራዎች ማውራት እንችላለን ወይ∙?) በኢህአዴግ ዘመን መሰራት ሲገባቸውና መሰራት  እየተቻሉ ካልተሰሩ ወይም ሆን ተብሎ ለግል ጥቅም ሲባል በሃገር ኪሳራ ከተሰሩ እኩይ ተግባራት ጋር በቀጥታ ስለሚያያዙ፣ ኢህአዴግ መለካት ያለበት የኢህአዴግ የስታቲስቲክስ ጽህፈት ቤት በሚያቀርበው ወገንተኛ የእድገት አሃዝ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ አቅሙ፣ ሃብቱ፣ እውቀቱና በነበረው የተመቻቸ ሃገራዊ ሁኔታ በኢህአዴግ ዘመን ሊያከናውን ይችል ከነበረው ተአማኒነት ካለው ግምታዊ የእድገት አሃዝ አኳያ ብቻ ነው። በመጽሐፉ የተለያዩ ገጾች ዐቢይ ሃገሪቱ በከንቱ ስላባከነቻቸው እድሎች በቁጭት የጻፈ ቢሆንም ይህ ቁጭት የኢህአዴግን ተጨባጭ ክንዋኔዎች መለኪያ አድርጎ አያቀርብም፡፡  
ሌላ አንድ ምሳሌ ልጨምር።
በግለሰቦችና በቡድን መብቶች ቀዳሚነት በሚደረገው ሙግት ዙሪያ “የግለሰብ መብት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል” የሚሉ ወገኖችን ሃሳብ በተሟላ መንገድ በመጽሐፉ የቀረበበት ሁኔታ አይታይም። በተለይ የግለሰብ መብት ተሟጋቾች “ለቡድን መብት ለመቆም መሰባሰብ የሚቻለው ለቡድን መብት የሚቆረቆሩ ግለሰቦች በቅድሚያ መብታቸው ተከብሮ ለቡድን መብት የሚቆም ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሲጀምሩና ድርጅት ሲፈጥሩ መሆኑን፣ ከዛም አልፎ በቡድን መብት በቆመው ድርጅት ውስጥም የግለሰቦች መብት ካልተከበረ “የቡድን መብት አስከባሪ ነን” የሚሉ መሪዎች፣ በእውን የቡድኑን መብት እያስከበሩ እንደሆነ መጠየቅ፣ በቡድኑ ውስጥ የሚነሱ ሌሎች የቡድን መብቶች ጥያቄ ማቅረብ የማይቻልበት፣ አባላቱ የቡድኑን እንቅስቃሴ በነጻነት መፈተሽ የማይችሉበት አፋኝ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል” በማለት ለሚያቀርቡት ክርክር ዶ/ር ዐቢይ ቦታ አልሰጠውም።  
“የቡድን መብቶች መከበር የግለሰቦችን መብት እንደማያስከብር፣ እንደውም በቡድን መብት ማስከበር ስም የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ትልቁ አደጋቸው የግለሰቦችን መብት፣ የሌሎችን ቡድኖች መብት የመጨፍለቅ አደጋ መሆኑ ስፋት ካለው የሰው ልጆች ተመክሮ የሚያቀርቡትን መከራከሪያ ጸሃፊው አይመለከተውም። የሃገራችንም ተመክሮ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ሃቅ መሆኑ በደራሲው እውቅና አልተቸረውም።
በተቃራኒው የግለሰቦች መብት መከበር ግን በተደራጀ መንገድ የቡድን መብት ለማስከበር ለሚንቀሳቀሱ በሩን እንደሚከፍት፣ ከዛም አልፎ የቡድን መብት በሚገባ ለመከበሩ ከቡድኑ ውስጥም ይሁን ከቡድኑ ውጭ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት የግለሰብ መብት መከበር ወሳኝ መሆኑን በምክንያት ላይ ተመስርቶ ለሚቀርበው ክርክር መጽሐፉ ቦታ አይሰጠውም። እንደውም ዶ/ር ዐቢይ “የግለሰብ መብት አቀንቃኞች የቡድን ማንነትን በማጥፋት … ጭቆናውን የሚያድበሰብስና የጭቆና ቅሪትን የሚተው…” በሚል የግለሰብ መብት መቅደም አለበት የሚሉትን ከሚዛናዊነት በራቀ አቀራረብ ይተቻቸዋል። (መደመር ገጽ 90)
እራሱ ዐቢይ እንደጻፈው፣ ኢህአዴግ ከልጅነቱ ጀምሮ መላው ህይወቱን ያሳላፈበት፣ ልምድም፣ እውቀትም የገበየበት፣ ራሱም የወጣትነት ጉልበቱንና እውቀቱን ኢንቨስት ያደረገበት ድርጅት ከመሆን ጋር የተያያዘ ከስሜት ተላቆ ያላለቀ አመለካከት ውጤት ይመስላል። (“የመደመር መንገድ”፣ “ሰሚ ፍለጋ” በሚለው ርእስ ስር ገጽ 5 የዐቢይና የኢህአዴግ ቁርኝት ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነ ከፖለቲካ ሀሁ ቆጠራ፣ ከምንዝር እስከ አለቃነት ያደረሰውን የስራ ተመክሮዎች በዚህ ድርጅት ውስጥ ማግኘቱን በበጎ ትውስታ -with fondness - መልኩ ጽፎታል)፡፡
ዐቢይ የኢህአዴግ ህገ መንግስት፣ የዘር ፌደራላዊ አስተዳደር፣ ዝግ የዘር የፖለቲካ ኢኮኖሚና ማህበራዊ አደረጃጀት “እውን በዚህ ሃገር ውስጥ ብዝሃነትን ያስጠበቀ፣ ለቡድኖች መብት መከበር ጥያቄ መፍትሄ የሰጠ ወይንስ ሁሉም ተያይዞ ወደሚጠፋፋበት የዘሮች ፍጥጫ የሚወስድ የጥፋት መንገድ?” የሚል ጥያቄ አያነሳም። “መደመር” ከገጽ 116-117 ላይ የቀረበው ሰፋ ያለ ሃተታ፤ ህገ መንግስቱ የብሄረሰቦችን መሰረታዊ መብቶች ያስጠበቀ፣ የሚጎድሉት ነገሮች የአፈጻጸም እንጂ የፖሊሲ ችግር እንደሌለበት የሚገልጽ ነው።  
በዚሁ መጽሐፍ  ገጽ 117 ላይ ዐቢይ፣ የአፈጻጸም የሚላቸውን ችግሮች ለመፍታት ከለውጡ በኋላ “የተወሰዱት “የዴሞክራሲያዊ ማሻሻያ እርምጃዎች” ያበረከቱትን አስተዋጽኦ “ሃገራዊ መግባባትን በማጠናከር ሰላማችንን ያመጡ ናቸው” ይለናል። አዎን መደመር በተጻፈበት ወቅት የነበረው ሃገራዊ ሁኔታ ይህን ቢመስልም፣ መደመር የተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ፣ በሃገሪቱ የተከሰቱ ሁኔታዎች ግን ይህን አባባል ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው።
ዐቢይ ኢህአዴግን ለመመዘን ከውጭ ተመልካች ይልቅ “ቤተኛ ባይተዋር” መሆኑ የተሻለ አቅም እንደሚሰጠው ቢያቀርብም (የመደመር መንገድ ገጽ 25) ከዚህ በላይ ባቀረብኳቸው ምሳሌዎች እይታ፤ ከባይተዋርነቱ ይልቅ ቤተኛነቱ በማየሉ የኢህአዴግን መሰረታዊ ጉድለቶች ማየት እንዳይችል አድርጎታል ለማለት ተገድጃለሁ። ምክንያቱ ይህ ሊሆን አይችልም ብለው ለሚጠረጥሩ ሌላው ምክንያት መሆን የሚችለው የሚቀጥለው ብቻ ነው።
ችግሩ የወቅቱ የዐቢይ የፖለቲካ ስልጣን የቆመበት መሰረትና በወያኔ ዘመን በተሟላ የመንግስት ድጋፍ፣  ስር እንዲሰድ የተደረገው ዘርን ተኮር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በቀላሉ መጋፋት የሚችሉት እንዳልሆነ ከመረዳት ከመጣ የፖለቲካ ስሌት ጋር የተገናኘ ይመስለኛል። ዐቢይ በመጽሐፉ ብዙ ነገሮችን ያየበትን ስፋትና ጥልቀት ለተመለከተ አንባቢ፣ ከላይ ባቀረብኳቸው ምሳሌዎች ዙሪያ ጸሃፊው የወሰዳቸው አቋሞች “ከእውቀትና ተመክሮ ማነስ የመነጩ ናቸው” ብሎ ለመቀበል ይከብደዋል። እነዚህ ምሳሌዎች ቁልፍ የሆነውን የሃገሪቱን አንኳር የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉዳዮች የሚመለከቱ መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።
ይህንንም ብዬ ግን መጽሐፉ የሌሎችን ግለሰቦችና ቡድኖች ሃሳቦችና አመለካከቶች በተቻለው መጠን ሃቅን ተመርኩዞ በገለልተኛነት ለማቅረብ የሄደበት ከፍታ በጎ ለሆነ በሚዛናዊነት ላይ ለተመሰረተ የተዋስኦ ባህል ማበረታቻ ሆኖ እንዲታይ ያደርገዋል።
“የመደመር መንገድ”ን የሥነ ጽሁፍ ውበት አለማድነቅ አይቻልም። የዶ/ር ዐቢይ የጸሃፊነት ክህሎት የታየበት መጽሐፍ ነው። ከዛም አልፎ ጸሃፊው በሃገራችን የተንሰራፋውን የማንበብ ባህል ችግር በመረዳት አንባቢን ለመሳብ በርካታ ቁምነገሮችን እያዋዛ በመጻፉ፣ መጽሐፉ ተነባቢ እንዲሆን  ያደረገው ጥረት ተሳክቶለታል የሚል እምነት አለኝ። ለሌሎች በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ለመጻፍ ለሚፈልጉ ጸሃፍት በጎ ምሳሌ ሊሆን ይችላል።
ከይዘት ውጭ ያልኩትን ዳሰሳ ሳሳርግ፣ አንድ መጽሐፍ ሲዳሰስ መጽሐፉ የተገለጸባቸው እጅግ በርካታ ጥንካሬዎች እያሉት ጥቂት ድክመቶች ላይ አተኩሮ መጽሐፉን በድክመት የተሞላ አድርጎ የማቅረብ ሌላው ከአድርባይነት የመጽሐፍ ዳሰሳ ባህላችን በተቃራኒው የቆመው አፍራሽ የዳሰሳ ባህላችን ነው። ይህ ባህል ሊታረም የሚገባው ነው። ከዚህ እይታ በመነሳት የዶ/ር ዐቢይ  መጽሐፎች ከይዘት ውጭ ባሉት መመዘኛዎች እጅግ የተዋጣላቸው ናቸው ማለት ይቻላል። ቀጥሎ የማልፈው ወደ ይዘት ዳሰሳ ነው።        

Read 1784 times