Sunday, 11 April 2021 00:00

መምህር ታዬ ቦጋለ - በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

         • የሃይማኖት አባቶች ሥራቸውን ቢሰሩማ ምስቅልቅሉ ባልተፈጠረ ነበር
         • የልሂቃኑ የተዛቡ ትርክቶች እያገዳደሉን ነው
        • ሃዘን የማንሰማበት፣ ደም የማይፈስበት ጊዜ እየናፈቀን ነው
        • በውጭ ጠላት የምንደፈረው ንከፋፈልና ስንለያይ ነው

          መምህር ታዬ ቦጋለ የታሪክ ባለሙያና የማህበረሰብ አንቂ ናቸው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያና በተለያዩ የኪነ-ጥበብ መድረኮች ላይ እየተጋበዙ በጥልቀት በአንዳንድ ልሂቃን ሆን ተብሎ የተፈጠሩ የተዛቡ ትርክቶችን በማስመልከት ማህበረሰቡን ያነቃሉ። የታሪክ ትምህርትን ትክክለኛ ዓላማ ያስረዳሉ፡፡ ፍቅርና አንድነትን ይሰብካሉ፡፡
የታሪክ መምህሩ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነትታቸውም ይታወቃሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-

             አሁን አገራችን ላለችበት ምስቅልቅል ሁኔታ የዳረገን ምንድን ነው ይላሉ?
የመጀመሪያውና አሁን ላለንበት ችግር መሰረት የሆነው ስርዓቱ ነው።  ባለፉት  27 ዓመታት የነበረውንና አሁንም የቀጠለውን መንግስታዊ ሥርዓቱን እንደ ትልቅ መንስኤ  መውሰድ እንችላለን። ራሱ ስርዓተ መንግስቱ የተመሰረተው ከሌሎች አገሮች በተለየ በብሔረሰብ ፖለቲካ ላይ ነው። የብሄረሰብ ፖለቲካ በመሆኑም ህዝቡን ያደራጁት በብሄረሰብ እንጂ በአስተሳሰብ ላይ ተመስርተው እይደለም። ይህም ብቻ አይደለም። የብሔረሰብ ትርክቱ ራሱ ፊት ለፊት አይናገሩት እንጂ በተግባር በግልጽ በሚታይ ሁኔታ አንዱን ብሔረሰብ ጨቋኝ፣ ሌሎቹን ተጨቋኝ አድርጎ የማሳየት ሁኔታ ነው ሲንፀባረቅ የኖረው። ሁለተኛው፤ ስርዓተ ትምህርቱ የተቀረጸበት መንገድ “ስነ-ምግባር” ለተባለው ክፍል ሰፊ ቦታና ትኩረት አይሰጥም። “ስነ-ዜጋ” በሚል በህገ-መንግስትና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ላይ የሚሰጠው ትምህርት የባህሪ ለውጥ የሚያመጣና የታነጸ ትውልድ የሚፈጥር አይደለም።
ሶስተኛው ነገር፤ የትምህርት ስርዓቱ ከፖለቲካ ነጻ አለመሆኑ ነው፡፡  በአንድ ፓርቲ ተፅዕኖ  ሥር የወደቀ ነበር፡፡ የወጣቶች አደረጃጀት፣ የሴቶች አደረጃጀትና ሌሎች አደረጃጀቶችን  በመፍጠር የሀሳብ ፍጭት እንዳይኖር ሲሰራ ነው የከረመው። ጋዜጠኞች በየሰበቡ ይታሰራሉ፡፡  ፖለቲከኞች ዘብጥያ ወርደው ይረሳሉ፡፡ በፓርቲው ውስጥ ደግሞ ከአንድ አካባቢ የተሰባሰበ ቡድን… ልብ በይ፣ ከአንድ ክልል አይደለም፤ ከአንድ አካባቢ የተሰባሰበ ቡድን፣ በሌሎች ላይ ተፅዕኖና ጫና ሲያሳርፍ ነው የኖረው በሁሉም የህይወት ዘርፎች፡፡ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ነው አሁን በሀገራችን እየታየ ላለው ምስቅልቅል የዳረገን።
ግን እኮ ለውጡ ከመጣም በኋላ ግጭቱ፣ ደም መፋሰሱ፣ መፈናቀሉ… ተባብሶ ነው የቀጠለው…
ለውጡ ከመጣ ወዲህ ምንድነው የተከሰተው ስንል… ገዢው ፓርቲ  በአንድ ላይ ጸንቶ በራሱ የቆመ አይደለም። ምንም እንኳን በመደመር ፍልስፍና ውስጥ የተቀረፀ ሁኔታ መፈጠሩን ቢገልፁም። ለምሳሌ የትግራይ ብልፅግና እና የአማራ ብልፅግና፤ ሆድ ለሆድ ተገናኝተው የሚነጋገሩ አይደሉም።
የትግራይ  ብልፅግና የሚባልኮ ከእነ አካቴው አልነበረም...
ትክክል ነው አልነበረም፤ አልተቀበሉትም፤ ባለመቀበላቸውም ከመንግስት በተፃራሪ ሆነው ቆመው ነበር። ለተወሰነ ጊዜ ኢህአዴግ በሚል ስሪት ውስጥ አብረው ከተጓዙ በኋላ ነው ብልፅግና ሲመሰረት በይፋ ራሳቸውን ያገለሉት። ግን ደግሞ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ተመስርቷል። የትግራይ ብልጽግና እና የአማራ ብልጽግና ግን በተፃራሪ ነው የቆሙት። የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ  ከአማራው ብልጽግና ይልቅ  ከተለያዩ የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተሻለ ይቀራረባል። የአማራ ብልጽግና ከኦሮሞ ብልጽግና ይልቅ አማራ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የበለጠ ይቀራረባል። የአፋር ብልጽግና እና የሶማሌ ብልጽግና ሰሞኑን እንዳየነው፤ ከሁሉም በኩል የሚወጣው መግለጫ በጣም የሚያሳዝንና ክልላዊ ስሜትን የያዘ፣ አንዱ ሌላውን የሚወነጅል ነው። ብልጽግና ሁሉንም በአንድ ጠርንፎ እንደ አገራዊ ፓርቲ አቀራርቦ አለመያዙ፣ አሁን ላለው ችግር አንዱ መንስኤ ነው። ሁለተኛው ተቃዋሚ የሚባሉት ፓርቲዎች፣ በጥሩ ርዕዮተ አለማዊ ፍልስፍና ተቋቁመው፣ የራሳቸው የሆነ ፕሮግራምና ፖሊሲ አውጥተው፣ ምርጫው እስኪደርስ በደጋፊነት በመቆም፣ በባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት ሲገባቸው ሁልጊዜ መቃወምን ብቻ ግብ አድርገው መንቀሳቀሳቸው አገሪቱን አልጠቀማትም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ፓርቲዎች የመንግስትን ጥሩ ጎን የመደገፍና የማጉላት ጅምር አሳይተዋል፡፡
አገር እንዲህ ምስቅልቅል ውስጥ ስትገባ የምሁራን፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች የት ናቸው? ሚናቸው ምን መሆን ነበረበት?
አብዛኛውን ምሁር ስንመለከት “silent majority” በሚባለው ውስጥ ተካትቷል አይሞቀውም አይበርደውም።
እንዴት? ለምን?
ምክንያቱም ያለፉ የፖለቲካ ስርዓቶች የሚቃወሙ ሰዎችን  ሲያጠፏቸው ነው የታየው። ደርግም ተቃዋሚ የሚባሉትን እነ ኢህአፓን፣ መኢሶንን፣ ኢዲዩንና ሌሎችን ጨፍልቆ ነው ህልውናውን ያረጋገጠው። የተናገሩ የተቃወሙ ሰዎች ሲበሉ፣ ሲገደሉ ነው ያዩት። ከማህበረሰቡም ምንም አይነት ቦታ ሳይሰጣቸው እንደቀሩ ተመልክተዋል። በሌላ በኩል፤ አንድ ለአምስት በሚል አፋኝ ጥርነፋ እያንዳንዱ ምሁር የተያዘበት ሁኔታ ነበር። በለውጡ ሰሞን ምሁራን በሰፊው ወደ ፖለቲካው የመግባት ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም፣ ትንሽ ቆይቶ ሁኔታዎች ከሚጠብቁት በተቃራኒ  በመሄዳቸው እጃቸውን ሰበሰቡ፡፡ “ለምንድን ነው እንዲህ አይነት ነገር ውስጥ ገብቼ የምንቦጫረቀው” እያሉ መቀመጥን መረጡ። የሀገርን ችግር ማስተካከል፣ ቆሻሻን ማንሳትና ማጽዳት እንደ መንቦጫረቅ ነው የሚቆጠረው። በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች፣ ምሁራን ዘንድ ችግር አለ። ወደ ሃይማኖት አባቶች ስትመጪ፤ ባለፉት ዓመታት፣ የሃይማኖቶት አባቶችና የማህበረሰቡ ልሂቃን ተሰሚነት እንዳይኖራቸው በሃይል ተሰርቷል። ይሄ ምን አመጣ? ሽማግሌን የሚሰማ ወጣት እንዳይኖር አደረገ፡፡ (ልክ የጋሞ ወጣቶች ሽማግሌዎችን እንዲሰሙ አድርገው እንደቀረጿቸው ሌላው ያንን ማድረግ የለበትም ወጣቱ በተለያየ ሱስ እንዲያዝ፣ ለትምህርት ግዴለሽ እንዲሆን ፣ በአቋራጭ መክበርና ሙስና እንደ ህጋዊ ስርዓት እንዲቆጠር አመለካከት ላይ ተሰራ። በዚህና መሰል ችግሮች ላይ ስራ አጥነትና የመኖሪያ ቤት ችግር ሲጨመር፣ በሚነደው እሳት ላይ ቤንዚን የሚጨምሩ ጉዳዮች ናቸው።
የሀይማኖት አባቶች የሚጠበቅባቸውን ሰርተዋል ማለት ይቻላል?
ሥራቸውን ቢሰሩ ይሄ ሁሉ ነገር አይከሰትም ነበር። በሀገር ላይ ይህ ሁሉ ችግር ሲከሰት፣ ንፁሃን ደማቸው እንደ ውሃ ሲፈስ እንኳን የሃይማኖት አባቶች ወጥተው ሲያወግዙ በብዛት አናይም። በዚህ ሁኔታ ማን ከማን  ይማር? ብለሽ እንድትጠይቂ ያደርግሻል። በኬንያ 2ሺ የቲንክ ታንክ ቡድን አለ። መንግስትን አቅጣጫ የሚያሳይ፣ የተለያዩ ፖሊሲዎችን የሚቀርጽና የሚያወጣ፣ የተሳሳቱ አሰራሮችን የሚያርምና ከነመፍትሄው የሚያመጣ ነው - ይሄ 2 ሺህ ቲንክ ታንክ ቡድን። ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ 300 የቲንክ ታንክ ቡድኖች አሉ። እኛ አገር ግን አንድም ቲንክ ታንክ ቡድን የለም፤ አንድም! በዘመነ ወያኔ አንድ ለማቋቋም ተሞክሮ ተቋቁሞ ነበር፤ ብዙ ርቀት ከተኬደ በኋላ ግን ፈረሰ። እኔም ነበርኩበት። ብዙ ለፍተንበት ለአገር ይበጃል ያልነውን  ሰርተን አቀረብን፤ ሆኖም ተቀባይነት አላገኘንም። ምናለ የኢትዮጵያ ምሁራን ተሰብስበው አቅም አጎልብተው፣ ለሀገር የሚበጅ ነገር ቢሰሩ የሚለው ሃሳብ  በአእምሮዬ ይመላለሳል። ችግሩን ለመፍታት እርሶ በግልዎ ምን እያደረጉ ነው?
እንግዲህ በኢትዮጵያ ላይ የተዛቡ ትርክቶች አሉ። የተዛቡ ትርክቶች ብቻ ሳይሆኑ የታሪክ ትምህርት ዓላማ ምንድን ነው ከሚለው ነው የምነሳው። በአጭሩ አላማው ያለፈውን በማጥናት፣ ዛሬን በጥሩ መሰረት ላይ ማነጽና ነገን ብሩህ ማድረግ ነው-የታሪክ ትምህርት ዓላማ፡፡ ይህንን መሰረት ያላደረገ ነገር፣ ከታሪክ ትምህርት ጋር ይጣላል። አሁን ላይ ትርክቶቻችን እያጣሉን እያገዳደሉን ነው። አሁን ያለው ትውልድ በትርክት ውስጥ ተጠያቂ አይደለም። ከሳሽ የለም፣ ተከሳሽ የለም፣ ዳኛ የለም፣ ፈራጅ የለም፣ ካሳ ከፋይም የለም። ልሂቃን ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሚያ ማድረጋቸው ነው ችግር የፈጠረው። የኔ የመጀመሪያው መነሻ፣ እያጣላን ያለው ታሪክ ከሆነ፣ ታሪኩን ሚዛናዊ አድርገን ማየት አለብን።
የፖለቲካ ልሂቃኑ፤ ጨፍጫፊም ሆነ ጨቋኝ ወይም በዝባዥ ማህበረሰብ የሚባል የሚባል እንደሌለ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው። እንደ ማህበረሰብ ወይም ብሄረሰብ ሌላው ላይ በደል ያደረሰ የለም። ችግሩ ግን ሚዲያ ላይ በተለያየ መንገድ ያራግቡታል።  ምሁራኑ በአንድ ላይ  ሲሰበሰቡ ገዢ መደብ ካልሆነ በስቀተር ኢትዮጵያ ውስጥ ጨቋኝ ብሔረሰብ አልነበረም ይላሉ። ይሄንን ግን ደፍረው ፊት ለፊት አውጥተውና አድምቀው አያንፀባረቁም። ይሄ ነው ችግር የፈጠረውና እውነቱ እንዳይወጣ ያደረገው። በእኔ በኩል፤ ስለዚህ  ይሄንን በደንብ በማሳየት በማህበረሰብ ደረጃ የበደለ፣ በኢትዮጵያን ታሪክ ውስጥ እንደ ሌለ እናገራለሁ። ሌላ ገዢ መደብ ነው ከተባለ ደግሞ ገዢ መደቡ ከተለያየ ማህበረሰብ የተውጣጣ እንደሆነ በማስረጃ አስረግጦ ህዝቡ እንዲገነዘብ ለማድረግ እየሰራሁ ነው።  በደልና ጭቆና የሚፈጽሙት ጦረኞችና ገዢዎች እንጂ ማህበረሰብ አይደለም።
በአሁኑ ወቅት  በየቦታው ጥቃቶች ግድያዎች፣ማፈናቀሎች፣...ብዙ ግፎችና በደሎች እየተፈፀሙ ነው፡፡ ከዚህ በፍጥነት መላቀቅ እንዴት ነው የምንችለው? እርስዎ ምን ይታይዎታል?
እንደ አገር የተጀመረ ነገር አለ፤ ያዝ ለቀቅ ሆነ እንጂ፡፡ የሀገሪቱን ችግር ለመቅረፍ ብሄራዊ ንግግር ተጀምሯል። እዚህ ላይ እኔም ተሳታፊ ነበርኩኝ። እንዳልሽው  አሁን በየቀኑ ሀዘን ነው የምንሰማው፡፡ ሀዘን የማንሰማበት ደም የማይፈስበት ወቅት እየናፈቀን ነው። ስለዚህ በአስቸኳይ ከሰባቱ የሃይማኖት ተቋማት የተወከሉ 14 ሰዎች አሉ። አባ ገዳዎች፣ ኡጋዞች፣ ኡስታዞች አሉ፡፡ የተለያዩ የማህበረሰብ  ልሂቃን፤ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የመንግስት አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ። እዚህ አገር ላይ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት እነዚህ አካላት አገራዊ ስራ ካልሰሩ በምርጫው ሂደትና ከምርጫው በኋላ የከፋ አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል ግምቱ አለኝ። የሚታዩ ምልክቶችም አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ አካላት ተሰብስበው (ልክ ባለፈው ኮሮና በተከሰተ ጊዜ የሃይማኖት ተቋማት በቴሌቪዥን  ትምህርት እየሰጡ ፀሎት ይደረግ እንደነበረው ለህዝብ ትምህርትና ምክር በመስጠት የመረጋጋት ሁኔታ መምጣት አለበት፡፡ ወጣቱን ሊያቀራርብ የሚችል ስራ የሰላምና የመረጋጋት ሁኔታ መፈጠር አለበት። የሃይማኖት አባቶች፤ በየቦታው እየተገደሉ ስላሉ ንፁሃን በአደባባይ ማውገዝ አለባቸው። ይሄ ግዴታቸውም ነው። ምክንያቱም 98 በመቶ ኢትዮጵያዊያን አማኝ መሆናቸውን አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ። የእምነት ተቋማት፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስራቸው ለሚገኙ አባላት በሙሉ ማስተማር፣ ማንቃት፣ ለሀገር ህልውና የሚበጅን ነገር በህብረተሰቡ ውስጥ ማስረፅ አለባቸው። መንግስትም በአካባቢ ደረጃ ሊፈታ የሚችለውን በአካባቢ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚፈታውን በዚያው ደረጃ በመፍታት ከምርጫው በፊት መስራት አለበት። ሚዲያውም በአንድነት፣ በፍቅር፣ የሀገርን ክብርን ማስቀደም ላይ አተኩሮ መትጋት ይኖርበታል። ህብረተሰቡም በየቦታው የሚከሰተውን የንፁሃን እልቂት በነቂስ ሰልፍ ወጥቶ ማውገዝ አለበት።  ፍቅራችን መመለስ፣ አንድነታችን መምጣት አለበት። ይህ ካልሆነ በውጪ ጠላትም ተከበናል እኮ። የምንደፈረው እኛ ስንበታተንና ስንለያይ ነው። ለውጭ ጠላት መጠቀሚያ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይገባናል። ለዚህ ደግሞ አገሪቱ ላይ ያሉ ተዋንያን በሙሉ ሚናቸውን መጫወት አለባቸው።
በተለያዩ አካባቢዎች ለሚደርሰው የንጹሃን ግድያና ዘር ተኮር ጥቃት፣ መንግስት “ኦነግ ሸኔ”ን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ አንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ “ኦነግ ሸኔ” የሚባል ሀይል የለም ይላሉ፡፡ እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ኦነግ ሸኔ የኦነግ ወታደራዊ ክንፍ ሆኖ የተቋቋመ ሀይል ነው።
ለዚህ ማስረጃዎ ምንድን ነው?
ይሄንን ከመጀመሪያውም  ራሳቸው ሲናገሩት ነበር።   በመጨረሻ ላይ የኦነግ መስራች ዳውድ ኢብሳ አንድ መግለጫ አወጡ። “እኛ ሸኔ ከቁጥጥራችን ውጪ ነው፤ ከዚህ በኋላ ከእኛ ጋር አይደለም” ማለታቸው ይታወሳል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን ኦነግ ሸኔ፤ “አባ ቶርቤ” የተሰኘ ገዳይ ቡድን አስቀምጦ ይንቀሳቀስ ነበር። ይሄ ሸኔ የሚባለው ቡድን፣ ድጋፍ የሚደረግለት ከማን ነው የሚለውን ማየት ይቻላል። አንደኛ አሁን ያለው ኦሮሚያ ብልፅግና ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደሚደግፉት ግልጽ የሆነ ማሳያ ላቅርብልሽ። በቅርብ ጊዜ የኦሮሚያ ፖሊስና የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባወጡት መረጃ፤ 1 ሺህ 100 የኦሮሚያ ልዩ ሃይል አባላት ከኦነግ ሸኔ ጋር ሲሰሩ ተገኝተው በቁጥጥር ስር ውለዋል። እኛ አካባቢ ያሉ በሰላም የሚታገሉ 13 ፖሊሶችን ገድለዋል። ከ40 በላይ የኦሮሞ አመራሮችን ገድለዋል። ስለዚህ ገዳዮች አሉ፤ አስገዳዮችም አሉ። መረጃ ሰጪዎችም ከውስጥ አሉ። እሱ ብቻ አይደለም፤ እያደራጁ በደንብ ያሳልፏቸዋል። ማህበረሰቡ የሚከላከልባቸውና የሚቃወምባቸው ቦታዎች ላይ ኦነግ ሸኔ መንቀሳቀስ አልቻለም። ሴሉን በሚገባ የመሰረተበትና ጥሩ ድጋፍ የሚያገኝባቸው ቦታዎች ላይ ደግሞ በደንብ መንቀሳቀስ ችሏል።
ለምሳሌ የት?
ለምሳሌ ቦረናና ጉጂ ውስጥ ነበር፤ ኦነግ ሸኔ። ነገር ግን ሰፊ ጥቃት ሳያደርስ (አንዴ ጌዲኦዎች ላይ የደረሰ ጥቃት አለ) ህዝቡ ስለተቃወመው፣ ቦረናና ጉጂ አካባቢ በቁጥጥር ስር ነው። አርሲ አካባቢ ባለፈው ከተፈጠረው ጥቃት ጀርባ ተባባሪ የሆኑ የፖሊስ፣ የልዩ ሃይልና የአስተዳደር ሰዎች ነበሩ። ይሄንን መንግስትም ያመነው ጉዳይ ነው። ስለዚህ መዋቅሩን ኦሮሚያ ብልፅግና ድረስ የተከለ፣ ነገር ግን “ኦነግ ሸኔ” የሚል ስም የያዘና የሚንቀሳቀስ ሃይል ስለመኖሩ ራሳቸው የገዳይ ቡድኖቹ ይመሰክራሉ። በአጠቃላይ ኦነግ ሸኔ፤ በኦሮሚያ ብልፅግና ሰፊ ድጋፍ ያለው፣ በአንዳንድ ልሂቃንም የሚደገፍ፣ ማህበረሰቡ ግን የማይፈልገው ሀይል ነው። ለምን አይፈልገውም? ከተባለ፤ ወደ 700 የሚደርሱ ኦሮሞዎችን ገድሏል፣ 1 ሺህ 400 የሚሆኑትን አቁስሏል፣ የኦሮሞ ተወላጆችን እንጨት አስለቅሞ በለቀሙት እንጨት አቃጥሏል፣ ደፍሯል፡፡  የኦሮሞ ህዝብ የሚጠቀምበትን 17 ባንክ ዘርፏል። ጤና ጣቢያ ላይ ሰፍሯል። ተመልከቺ ጤና ጣቢያ ላይ!! ይህንን ስትመለከቺ ማህበረሰቡ አይፈልገውም፤ አይደግፈውም። በመንግስት እንደሚደገፍ ራሱ መንግስትም ይገልፃል። “ውስጣችን አሉ፤ እናጠራለን” ብሏል፡፡ ነገር ግን ይህንን ሃይል ማጥፋት አይቻልም ወይ? ከተባለ፣ይቻላል። ቁርጠኝነት ካለ ማጥፋት ይቻላል። ማጥፋት ስላልተፈለገ ነው እንጂ። ደርግ እኮ ቀጥ አድርጎ ይዟቸው ነበር። በዘመነ ወያኔ መዋቅር ፈጥሮ በአንድ ለአምስት አደራጅቶና ማህበረሰቡን አንቀሳቅሶ ይዟቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ሰው አልገደሉም ማለት አይደለም፤ ብዙ ሰው ገድለዋል።
አሁን የሚፈፀመው ግድያና ጥቃት “ዘር ተኮር ጅምላ ጭፍጨፋ” ነው እየተባለ ነው። እርስዎም ያምኑበታል?
ዘር ተኮርና ጅምላ ጭፍጨፋ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ዶ/ር ራፋኤል ሌምኬን ባወጣው አጠቃላይ ትንተና፤ ጅምላ ጭፍጨፋ (ጄኖሳይድ) ማለት፤ አንድ ማህበረሰብ “ባጠፋው ጥፋት ሳይሆን፣ የሆነ ቡድን፣ የሆነ ሃይማኖት ወይ የሆነ ፓርቲ አባል በመሆኑ ከተገደለ ጅምላ ጭፍጨፋ ነው” ይላል።  አሁን እየተፈጸመ ያለው “ዘር ተኮር ጭፍጨፋ” መሆኑን ማንም ሊክድ አይችልም። ይህንን ቃል እንዳንጠቀም ለማለባበስ የሚሞክሩ አንዳንድ ሰዎች አሉ። አንድም ለፖለቲካ ትርፍ አሊያም በሌላ በኩል የአገር ገፅታ እንዳይበላሽ በሚል። በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 8 ላይ ከሁሉም በላይ ከህገ-መንግስትም በላይ፣ ለህዝብ ሉአላዊነት ቅድሚያና ክብር ይሰጣል። ከአንቀጽ 8 አኳያ ነገሩን ካየነው፣ የጅምላ ጭፍጨፋ ነው፤ ብሔር ተኮር ጥቃት ነው።
ጋሞዎች የተገደሉት በጋሞነታቸው ነው። ኮንሶዎች፣ ጌዲኦዎች አማራዎች የተጨፈጨፉት ...በማንነታቸው ነው። ኦሮሞዎችም የተገደሉት በፖለቲካ አመለካከታቸው “ኦነግን አንቀበልም፤ አናስተናግድም” በማለታቸው ነው። ይሄ ሁሉ በጅምላ ጭፍጨፋ ስር የሚፈረጅ ነው። በዚህ ጭፍጨፋ በአንድ ጊዜ 100 ሰው 150፣ ሰው ይገደላል። ህፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ ወጣቶች፣ የእምነት አባቶች ይጨፈጨፋሉ። በነገራችን ላይ ክርስቲያኖች ወይም ሙስሊሞች ናቸው ተብለው ከተጨፈጨፉ፣ ይሄም ጄኖሳይድ ነው።
በየክልላቸው ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ያልቻሉ በየጊዜው ዜጎች የሚገደልባቸው፣ የህዝባቸውን ደህንነት ማስጠበቅ ያልቻሉ... የክልል አመራሮች ለምን በህግ  አይጠየቁም? የሚል ምሬትና  ቅሬታ ይቀርባል  እርስዎ ይህን እንዴት ያዩታል?
በዚህ ጉዳይ ላይ ዶ/ር ዐቢይ አንድ ጊዜ በተናገሩት ንግግር ብጀምርልሽ ደስ ይለኛል። ሲዳማዎችና ወላይታዎች ውስጥ ኤጀቶ የሚባል አንድ ቡድን ተቋቁሞ ሲዳማ አካባቢ ወላይታዎችን አጠቁ በተባለ ጊዜ አንድ ነገር ተናግረው ነበር፡፡ “እነዚህ ሰዎች ሲገደሉ ዝም የሚል የደቡብ ክልል አመራር ስልጣን ላይ ምን ያደርጋል? ለምን አይለቅም?!” ብለው ነበር። ይሄንን አንድ በይ። ሁለተኛው አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው እንደተሾሙ “ከአሁን በኋላ በእኔ  አመራር ስር አንድ ቀበሌ ወይም አንድ ወረዳ አሊያም ዞን ላይ ችግሮች ቢፈጠሩ አመራሮችን እናንጠለጥላቸዋለን” ነበር ያሉት፡፡ በተጨባጭ  ስንመለከት ግን “አንድ ሰው ቢገደል” ሲሉ የነበሩት ሰው፤ አሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተገደሉ ምንም ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ይሄ አንድ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ ያልተፈለገ የጠነከረ ከላይ እስከ ታች የተሳሰረ ድጋፍ የሚደረግለት ሀይል አለ፡፡ አንዳንዴም “የኦሮሚያ  ብልጽግና እኮ ኦነግ ነው” ብለው የኦነግ ደጋፊዎችን ጭምር ወደ ራሳቸው ለማምጣት የሚያስችል፣ ለፖለቲካ ትርፍ የሚሰራ ስራ ነው፤ በሌሎች ደም ላይ ማለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ዶ/ር ዐቢይ ለደቡብ የተናገሩት ኦሮሚያም ላይ ይሰራል ማለት ነው፡፡ ቤኒሻንጉል ላይም ይሰራል ማለት ነው፡፡ እኔ እንደ ማህበራዊ አንቂ፤ የመተከል የንፁሃን ጭፍጨፋ የመንግስት እጅ አለበት ብዬ በይፋ ፅፌያለሁ፡፡ ይሄን ያልኩት የመንግስት እጅ ባይኖርበት ማስቆም ስለሚቻል ነው። ጠንካራ የሆኑትኮ ችግሩን አስቁመዋል። ቁርጠኝነት ያላቸው መሪዎች ክልላቸውን የተረጋጋና ሰላማዊ አድርገዋል፡፡ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ መሃመድ ለዚህ ዋናው ምሳሌ ናቸው፡፡ ያንን ሰላም የጠማው፣ እድሜ ልኩን በፀጥታ ችግር ሲታመስ የነበረ ክልል፣ ከሌላው ክልል የተሻለ ሰላማዊ አድርገዋል። አማራ ክልልም ይበጠበጥ ነበር፤ የተወሰኑ ቡድኖች ተደራጅተው ሰው ይገድሉ ነበር ይዘርፉም ነበር፡፡ ተመስገን ጥሩነህ ተመድበው ሲሄዱ ፀጥ አደረጉት፤ በዚያው ቀጥሏል። የተወሰኑ ብልጭ ድርግም ከሚሉ ችግሮች በስተቀር በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው ክልሉ። አፋርም ሰሞኑን ከሶማሌ ክልል ጋር በቦታ ምክንያት ከመጋጨታቸው በስተቀር አፋርም መረጋጋት ችሏል፡፡ አሁን ከምርጫው ጣቢያ ጋር ተያይዞ አምስት የምርጫ ጣቢያዎች ወደ አፋር ተካላሉ በሚል በተነሳው አለመግባባት አስከፊ ነገር ተከስቷል፡፡ የሁለቱንም መግለጫ ሳይ፤ አፋር “የሶማሌ ልዩ ሀይል የአፋር አርብቶ አደሮችን እየመታ ነው” ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ ሶማሌ ክልል የአፋር ልዩ ሀይል የሶማሌ አርብቶ አደሮችን እየመታ ነው በማለት እየተወነጃጀሉ ነው፡፡ ቀደም ሲል ክልሎቻቸው ተረጋግተዋል ቁርጠኝነት ካለ ግጭትና ግድያን ማጥፋት ማስቆም ይቻላል።
ከክልል ልዩ ሀይሎች ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሃሳቦች ይነሳሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
እንደውም ቀደም ብዬ ካነሳኋቸው የመፍትሄ ሀሳቦች ጋር እንዲካተትልኝ የምፈልገውን ጥያቄ ነው ያነሳሽልኝ፡፡ አንዱና በፍጥነት መሰራት ያለበት ጉዳይ ልዩ ሀይል ትግራይ ላይ ችግር ፈጥሯል፣ልዩ ሀይል ህገ-መንግስታዊ አይደለም፣ ፖሊስ ግን  ህገ መንግስታዊ ነው ልዩ ሀይል ቀኑን በትክክል ባላስታውሰውም፣ በቅርብ ነው የተቋቋመው፡፡ ይሄ ልዩ ሀይል የያዘው መሳሪያ የማይፈቀድ ነው፡፡ በጣም ግርማ ሞገስ ያለው፣ ማንም ሊነፃፀረውና ሊገዳደረው የማይችል ጦር መያዝ ያለበት የፌደራል መንግስት ነው፡፡ ነገር ግን ካልተሳሳትኩ፣ ኦሮሚያ 35ኛ ዙር ልዩ ሀይል አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡ ይሄ የክልሎች ጡንቻ መፈርጠም ነው ማዕከላዊ መንግስቱን የሚያዳክመው፤ ስለዚህ ልክ አይደለም፡፡ ለምን ተፈልጎ ነው ይሄን ሁሉ ልዩ ሀይል ክልሎች የሚያሰለጥኑት? ይህንን እያዩ ነው  ኦነግ ሸኔዎች “እኛ ንፁሀንን አንገድልም፤ በስማችን እየነገዱ ንጹሀንን የሚገድሉት የመንግስት ልዩ ሀይሎች ናቸው” እያሉ መግለጫ የሚያወጡት፡፡ ይሄን ሀይል በቶሎ ወደ ፌደራል ፖሊስ፣ወደ መከላከያና ወደ ሌሎች ህገ-መንግስታዊ የሰራዊት ተቋማት መበተንና ህብረ ብሔራዊ እንዲሆኑ መጣር አለበት፡፡ ሰላም ማስከበር ነው ስራቸው ወደ ተለያየ ቦታ ቢቀላቀሉ ህግ ማስከበርኮ ቋንቋ አይጠይቅም፡፡ መከላከያው የተዋቀረውም በቋንቋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ወደተለያዩ ህገ-መንግስታዊ ተቋማት መበተናቸው የክልሎችን ፉክክር ስለሚያስቆምና የማዕከላዊ መንግስትን አቅም ከመፈታተን ስለሚታደግ፣ መንግስት በዚህ ላይ አፋጣኝ ስራ መስራት አለበት ባይ ነኝ፡፡
በመጨረሻ የሚሉት አለ?
ለዚህ አገር የሚበጀው ቅድም ያነሳሁት ነው። በመጀመሪያ ቅንነት ያስፈልጋል፡፡ አሁንኮ የበላንን ትተን ያልበላንን ነው የምናከው፡፡ የዚህ አገር ችግር ከፍተኛ ሥራ አጥነት፣ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ያውም በየቀኑ የሚያሻቅብ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመኖሪያ ቤት ችግር አለ፡፡ የሴተኛ አዳሪ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ የለማኙ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው፣ የጎዳና ተዳዳሪው ብዛት ለጉድ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ዝርፊያውና ቅሚያው ተባብሷል ሰዎች መኪና አቁመው፣አምሽተው መግባት የማይችሉበት ከፍተኛ የሆነ ምስቅልቅና የሽፍታ መግነን አለ፡፡ የበሉን ችግሮች እነዚህ ስለሆኑ በነዚህ ላይ ብናተኩርና ችግራችንን ብንፈታ ለዚህ ደግሞ  ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው አካላት የቤት ስራቸውን ቢሰሩ የማናልፈው ችግር የለም ነው የምለው፡፡

Read 2819 times