Saturday, 10 April 2021 12:54

6ኛው አገራዊ ምርጫ 2013 ኢዜማ ለአዲስ አበባ ያዘጋጀው የ5 ዓመት እቅድ ምን ይዟል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 • የቀበሌ ቤቶች በሽያጭ ወደ ነዋሪዎች ይተላለፋሉ
          • 5 መቶ ሺ የሥራ ዕድሎች ለፍጠር ታቅዷል

        ለ138ቱ የአዲስ አበባ ም/ቤት ወንበሮች እጩዎችን አዘጋጅቶ ወደ ምርጫ የገባው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ( ኢዜማ)፤አሸናፊ ሆኖ ከተማዋን የሚመራ ከሆነ ሊተገብራቸው ያቀዳቸውን ዋና ዋና ግቦች ለመገናኛ ብዙኃን 23 ገፅ ባለው ሰነድ ይፋ አድርጓል፡፡
“ብሩህ ተስፋ ለአዲስ አበባ፡-138 ቁልፍ ግቦች” በሚል ኢዜማ ያዘጋጀውን የቃል ኪዳን ሰነድ (አዲሰ አበባን ብቻ የተመለከተ ማኒፌስቶ) ይፋ ባደረገበት ስነ-ስርዓት ላይ የፓርቲው መሪ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ የኢዜማ የአዲስ አበባ የቂርቆስ ክ/ከተማ እጩ አቶ ክቡር ነጋ  እንዲሁም የኢዜማ የአዲስ አበባ ም/ቤት የካ ክ/ከተማ ተወዳዳሪ አቶ አሮን ሰይፉ ሰነዱንና ፓርቲው አዲስ አበባ ላይ ሊያሳካው የሚሻውን ግብ አብራርተዋል። አዲስ አድማስን ጨምሮ ከሌሎች መገናኛ ብዙኃሃን ለቀረባቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኢዜማ ለአዲስ አበባ የወጠነው ምንድን ነው? ምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ይሰጣል? የሚሉትን የሰነዱን አንኳር ነጥቦችና መሪዎቹ የሠጡትን ማብራሪያ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኘው ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡


           ኢዜማ በአዲስ አበባ የሰራው ጥናት…
ፓርቲያቸው የአዲስ አበባን ችግር ለማወቅና መፍትሄ የሚላቸው ሃሳቦችን ለማመንጨት ጥናት ማካሄዱን  ያወሱት  ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ፤ በጥናቱ የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ችግር መጠነ ሰፊና እጅግ ስር የሰደደ፤ ከተገመተው በላይ የሆነ መሆኑን ተረድተናል ብለዋል፡፡ በጥናቱ ወቅት የቤት ለቤት መጠይቆች እየተደረጉ ጥናቱ መሰራቱን፤በየወረዳው ቢያንስ አስር ዋና ዋና ችግሮች ተለይተው መውጣታቸውን አስገንዝበዋል፡፡
“በሶስቱ ሳምንት የጥናት ወቅት አዲስ አበባን በሚመለከት ያየነው ችግር እጅግ በጣም  ከሚነገረው በላይ ነው፤ የአዲስ አበባ ህዝብ ምን ያህል አስቸጋሪ ህይወት እንደሚኖር ነው ያየነው” ያሉት ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ፤ በምቾት ቀርቶ መሰረታዊ ኑሮ እንኳ ለመኖር የሚቸገሩ ዜጎች ቁጥር ከሚገመተው በላይ ሆኖ አግኝተነዋል ይላሉ፡፡
ፓርቲው የቃል ኪዳን ሰነዱንም ያዘጋጀው እነዚህን በጥናቱ የተለዩ ችግሮች መነሻ በማድረግ መሆኑን፣ነገር ግን ሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች ችግርን ያካተተ አለመሆኑን፣ ለማካተትም የማይቻል መሆኑን ነው ያወሱት፤ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ ሰነዱን ባስተዋወቁበት ንግግራቸው፡፡
ኢዜማ ከ30 በላይ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ጥናትን መነሻ አድርጌ ነው ያዘጋጀሁት ባለው የአዲስ አበባ ከተማ የቃል ኪዳን ሰነዱ፣  አስራ አምስት ዋና ዋና የትኩረት መስኮችንና ግቦችን አስቀምጧል። እነዚህም የመልካም አስተዳደር ጉዳይ፣ የከተማዋ  ሰላምና ደህንነት ጉዳይ፣ ዘመናዊ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጉዳይ፣የመሰረተ ልማቶችን መዘርጋትና ማዘመን፣ ምቹ የንግድና መዋዕለ ነዋይ ከባቢ የመፍጠር፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነት ማሻሻል፣ የመኖሪያ ቤቶች እጥረት መቅረፍ፣ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት የመዘርጋት፣ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር የመቅረፍ፣ጥራትን የማሳደግ፣የማህበራዊ ከለላ ስራዎች፣ የከተማዋን የጥበብ ማዕከል የማድረግ ውጥን፣የፅዳትና ውበት ጉዳዮች ናቸው፡፡ በእነዚህ 15 የትኩረት ጉዳዮች ላይም ኢዜማ በሰነዱ ዝርዝር እቅዶችን ነድፏል፡፡
በከተማዋ የመልካም
አስተዳደርን  ለማስፈን ….  (አቶ ክቡር ገና )
የሰነዱ ዋና የመነሻ ቁልፍ ሃሳብ፤ አዲስ አበባ የሁላችንም የጋራ ከተማ ነች የሚል ነው፡፡ ድሮ አዲስ አበባ ትንሹም ትልቁም ሃብታሙም ድሃውም ተለያይቶ የማይኖርባት ከተማ ነበረች አሁን ይሄን ከተማ፣ ይሄን መሰሉን ሰፈር ነው ያጣናው። ዛሬ አዲስ አበባ ዶርሜተሪ ይመስለኛል፡፡ ስራ ሌላ ቦታ አዳር ሌላ ቦታ ነው፡፡ በመሃሉ ያለው የኑሮ ግንኙነት ጠፍቷል፡፡ መተሳሰብ ጠፍቷል፡፡ ችግር ሲመጣ እንኳ መሰባሰብ የሚቻልበት መንገድ የለም። ይሄ ከተማ ነው ወይ? ከተማን እኮ ከተማ የሚያደርገው ህዝቡ ነው፡፡ ታዲያ ህዝቡ ዛሬ የት ነው ያለው? ህዝብ የሚያቀራርብ ነገር ለምን ጠፋ? አሁንም ያለው የብልጽግና አካሄድ ህዝብን የሚያርቅ እንጂ የሚያቀራርብ አይደለም፡፡ ይሄን መለወጥ የሚቻለው በቀጣይ 25 እና 30 ዓመታት ያለ ማቋረጥ በሚሰሩ ስራዎች ነው፡፡
በመልካም አስተዳደር ጉዳይ ያስቀመጥናቸው 15 ዋና ዋና ነጥቦች አሉ፡፡ መልካም አስተዳደር የሁሉም ነገር መጀመሪያ ነው፡፡ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአዲስ አበባ አስተዳደርን ስንመለከት በከፊል የከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ስራዎች አሉ፤ በከፊል ደግሞ የፌደራል መንግስት ሆነው ይታያል፡፡ እነዚህን እንዴት ነው ወደ ከተማ አስተዳደሩ አጠቃለን ማስተዳደርና ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ራሷን በራሷ  ማስተዳደር የምትችለው የሚለውን በሚመልስ መልኩ ነው ይሄን ጉዳይ የቃኘ ነው፡፡
ስለዚህ አዲስ አበባ ራሷን በራሷ ልታስተዳድር እንድትችል ከዚህ  በፊት ሲተገበሩ የነበሩ ህጎችን፣ ደንቦችን መመሪያዎች ይከለሳሉ፣ በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ የህግ አውጪ ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚ አካላት የየራሳቸውን ድርሻና ሃላፊነት በህግ እንዲወጡ ይደረጋል፡፡ በተለይም ከተማዋ ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብቷ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ተግተን እንሰራለን፡፡
ሌላው አነጋጋሪ ሆኖ የሚታየው የአዲስ አበባ ወሰን ጉዳይ ነው፡፡ እኛ በተቻለ መጠን ወሰኗን ማካለል ያስፈልጋል ብለን ነው የምናምነው። ስናካልል ከጎረቤት ጋር በመነታረክ ወይም ለመነታረክ መሆን የለበትም፡ ዋናው ዘመናዊ ከተማ ለመገንባትና የታክስ ጉዳይን ለማስተዳደር ነው፡፡
 በሌላ በኩል ይሄን ሰነድ ስናዘጋጅ ከጥናቱ ያገኘነው ውጤት እንደሚያመለክተው በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ መስሪያ ቤቶች የተንሰራፋ በብሔር ማንነት፣ በዘመድ አዝማድና በዘር ላይ የተመሰረተ የስልጣን ሹመትና የስራ ሃላፊነት አለ። ይሄ መስተካከል አለበት፡፡ ይሄ የሚስተካከልበትንና ዜጎች በብቃታቸው ብቻ ተወዳድረው የሚሾሙበትና በእኩልነት የሚዳኙበትን ሥርዓት እንፈጥራለን፡፡ ሌሎች የመልካም አስተዳደርን ለማምጣት የምናከናውናቸውን በሰነዱ በዝርዝር አስቀምጠናል፡፡ ሌላው የሠላምና ደህንነትን የተመለከተው እቅዳችን ነው፡፡ አሁን በምናየው ሁኔታ ብዙ ችግር እንዳለ ተረድተናል፡፡ በተለይ የፖሊስ አስተዳደሩ ወደ ከተማዋ እንዲመለስ እናደርጋለን፡፡ በከተማዋ ማህበረሰብ መካከል አለመግባባት መቃቃርን ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮች ቀድሞ በመለየት መቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት እንዘረጋለን፡፡ ዘመናዊ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ለመስጠትም በዋናነት ቴክኖሎጂ እንጠቀማለን፡፡ አገልግሎቶች በሙሉ ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
የመሰረተ ልማት አውታሮችን የመዘርጋትና የማዘመን ጉዳይ ጥራትን ቅድሚያ ያደረገ እንዲሆን እናደርጋለን። የመጠጥ ውሃ ችግርን ለመቅረፍ የከርሰ ምድር ውሃ አቅርቦት የማስፋፋት ስራዎች በልዩነት ይመራሉ፡፡
መሰረተ ልማትን ከማዘመን አንጻር ፓርቲያችን ከያዛቸው እቅዶች አንዱ በከተማዋ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች የስራ መግቢያና መውጫ ሰዓቶች ላይ ለውጥ ማድረግ ነው። ነዋሪው የተሻለ የትራንስፖርትና የመንግስት አገልግሎቶችን እንዲያገኝ፣ እንደ መስሪያ ቤቶቹ የስራ ባህሪ የስራ ሰዓት ለውጦች ይደረጋል፡፡ ቅዳሜም ጭምር የሚሰራበት ሁኔታ ይኖራል፡፡
የሥራ እድል ፈጠራ፣የኑሮ ውድነት ቅነሳ ….
የስራ እድል ፈጠራ ላይ በተለይ ለወጣቱ ሰፊ ትኩረት ይሠጠዋል፡፡ እንዴት አድርገን ነው የስራ እድሉን የምናስፋፋው የሚለው ላይ በአንድ በኩል የቴክኖሎጂ ስራዎች ለማስፋፋት እንሞክራለን፡፡ በተለይ ደግሞ የንግድ ተቋማት ስራቸውን ሊገድብ የሚችሉ ህጎችን በመቀነስ ወጣቶች ወደ ንግድ እንዲገቡ የሚያግዙ ተግባራት ይከናወናሉ። በከተማዋ 23 በመቶ ወጣቶች ስራ አጥ እንደመሆናቸው ወጣቶች ስራ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ስልጠናዎች እንሰጣለን፤ በምርጫ ዘመኑ አመታዊ የስራ ቀጣሪና ተቀጣሪ መድረክ  በማዘጋጀት 5 መቶ ሺ የስራ እድል እንዲያገኝ እንሰራለን፤ በተቻለ መጠን ወጣቶች የስራ እድል እንዲያገኙ ሰፊ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፡፡
የኑሮ ውድነት  እንግዲህ በሁለት መንገድ ሊፈታ ይችላል፡፡ አንደኛው ለሰራተኛው ደሞዝ መጨመር ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ የሠራተኛውን ወጪ መቀነስ ነው። በእነዚህ ሁለት አካሄዶች ለውጦች እንዲኖሩ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ በተለይ ብዙ መዋዕለ ንዋይ የማይጠይቁ ነገር ግን ከፍተኛ ገቢ ሊያመጡ የሚችሉ ከባህል ጋር የተያያዙ ኢንዱስትሪዎች እንደ ሙዚቃ ቲያትር፣አርክቴክቸር የጌሚንግ ፕሮግራሞች እንዲስፋፉ በፖሊሲ ደረጃ እናዘጋጃለን፡፡
የከተማዋን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል….
 ኢዜማ ከዚህ አንጻር ሰፊ ጥናት አድርጎ በቃል ኪዳን ሰነዱ የዘረዘርናቸውን ለመተግበር አቅዷል፡፡ ለምሳሌ በከተማዋ አስተዳደር ስር ያሉ የቀበሌ ቤቶች ለሚኖሩበት ቅድሚያ በመስጠት፣ የቤቶቹን ባለቤትነት በሁለት አመታት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከመንግስት ወደ ነዋሪዎቹ በሽያጭ ለማዘዋወር የሚያስችል አሰራር ቀይሰን ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ በሌላ በኩል፤ በመጪዎቹ 5 ዓመታት በአስሩም ክፍለ ከተሞች ከ2 መቶ ሺህ ያላነሱ የመኖሪያ ቤቶች በመገንባት አነስተኛ ገቢ ላላቻው ነዋሪዎች በሽያጭ ወይም በኪራይ እንዲቀርቡ ምቹ ሁኔታ እንፈጥራለን፡፡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣የህፃናት መዋያ፣መፃሀፍት ቤቶችና የልጆችና የአረጋዊያን ስፖርት ማዘውተሪያዎች ያካተቱ እንዲሆኑ እናደርጋለን፡፡
ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋትና የትራንስፖርት አገልግሎት ማሻሻል  … በአዲስ አበባ የየካ ክ/ከተማ እጩ  አቶ አሮን ሰይፉ)
የአዲስ አበባ የመሬት ይዞታ አስተዳደር እጅግ ኋላ ቀር በሙስና የተጨማለቀ፣ነዋሪውን በከፍተኛ ሁኔታ እያማረረ ያለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሄን አሰራር ለከተማዋ ነዋሪ በሚሆን መልኩ እናዘምነዋለን፡፡ የመሬት ወረራን እናስቆማለን፣በህገ ወጥ ሰፈራ የተያዙ ቦታዎችና ቤቶች ወደ ህግ ስርዓት እንዲገቡ እናደርጋለን። የከተማውን ትራንስፖርት ችግር ለመፍታት በርከት ያሉ አማራጮች አሉን፡፡ አንዳንድ ሰዎች ብስክሌቶችን እንዲጠቀሙ የማበረታታት እቅድ አለን። በቅናሽ ብስክሌቶች እንዲቀርቡና የብስክሌት መንገዶች እንዲሰሩ ይደረጋል። አሁን ያሉት መንገዶች እንዲሰፉ እንዲዘምኑ ይደርጋል፤ የእግረኛ መንገዶች በጥራት ይሰራሉ።
ትምህርት ከማስፋፋት አኳያ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ሁሉም የመንግስት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ እናደርጋለን፤ ለሁሉም ተማሪዎች ታብሌቶች እንዲሰጡ ይደረጋል፡፡ ፓርቲው በከተማዋ በተለያዩ ደረጃ ህብረተሰቡን የማህበራዊ ከለላ ተጠቃሚ የሚደርጉ እቅዶችም አሉ፡፡ ለከተማዋ የጥበብ ዕድገት ልዩ ትኩረት ይሠጣል፡፡ ከተማዋ የአፍሪካ የጥበብ ማዕከል እንድትሆን በሠፊው ይሰራል፣ ልዩ ትኩረትም እናደርጋለን፡፡ የአፍሪካውያን የጋራ የጥበብ በአል ግንቦት 17 ቀን በአዲስ አበባ እንዲከበር እናደርጋለን። በዚህ ቀን ከመላ አፍሪካ ታላላቅ የጥበብ ሰዎች የሚሰባሰቡበትና ታላለቅ ትዕይንተ ጥበብ የሚካሄድበት ይሆናል፡፡ ሌላው ከተማዋን ውብና አረንጓዴ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይም  በፒያሳ፣አራት ኪሎ፣ሜክሲኮ፣ሽሮሜዳ አስኮና አየር ጤና አካባቢዎች የሚገኙ ዋና ዋና የህዝብ  መሰብሰቢያ ስፍራዎችና አደባባዮችን እንቅስቃሴ ፍሰትን በሚያሳልጥ፣የእግረኞችን እንቅስቃሴ ምቹና የተሳለጠ የሚያደርግ መንገድ እንዲያከናውኑ ይደረጋል፡፡
 በከተማዋ የሚፈፀመው የመሬት  ወረራ ህጋዊነት እያገኘ መምጣቱ  (ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ)
 ይሄ ምርጫ በሚደርስ ጊዜ አማልላለሁ እየተባለ መሬት የማደል ሁኔታ ለእኔ የሞኝ ጉዞ ነው፡፡ መሬት እሰጣችኋለሁ የመሳሰሉት ማማለያዎች እርባነ ቢስ ናቸው። ይሄ ህዝብ ሞኝ አይደለም፤ ሁሉንም ያውቀዋል። በምርጫ ጊዜ የሚደረገውን ሁሉ ያውቃል፡፡  ይሄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሬት እንሰጣችኋለን እየተባለ የሚደረገው ነገር በተለይ ሃብታሞችን ዒላማ ያደረገና ብልጽግና ከእነሱ እርዳታ ለማግኘት ያለመ ነው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለው ሞኝነት የትም አያደርስም፡፡ ብልጽግና ከበፊቱ ኢህአዴግ ተምሯል ብዬ አስብ የነበረው አንዱ ይሄን ጉዳይ ነበር ነገር ግን አልተማረም፤ በውሸት ፕሮፓጋንዳና ማማለል ውጤት እንደማያመጣ በምርጫ 97 ታይቷል። አርከበ የሚል ሰው አሁን የት እንዳለ አላውቅም አዲስ አበባን ሌላ አደርጋታለሁ ያለ ሰው እንኳ ራሱ በተወዳደረበት ካዛንቺስ  መመረጥ አልቻለም፡፡ ብልጽግናዎች አሁንም ከዚህ መማር አለባቸው። መሬት በማደልም ሆነ በሌላ ማማለያ የሚገኝ ስልጣን የለም፡፡ ይሄ ህዝብ ሁሉንም ያውቃል። በዚያ መልክ የሚገኝ ስልጣንም ጊዜያዊ ነው፡፡ እውነት ላይ የቆመ ግንኙነት ነው ከህብረተሰቡ ጋር መፍጠር የሚገባው። ከተለመደው የኢህአዴግ  መንገድ ውጡ ነው የምንላቸው፡፡ ከተመረጣችሁ  በኋላ ከፈለጋችሁ አድርጉት፡፡ አሁን ግን ይሄን ጨዋታ ተውት፡፡
አዲስ አበባ ራሷን በራሷ በማስተዳደር ጉዳይ የኢዜማ አቋም….
 በሃገራችን ህግ አንድ ሰው 6 ወር ይሁን አንድ ዓመት በዚያ ቦታ ከኖረ በቦታው ላይ መመረጥ መምረጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ የሰው የዚያ አካባቢ ነዋሪ ነው፡፡ ከተሞች ደግሞ በምንም ተአምር  በደምና በዘረመል ተቆጥረው የዚህ ተወላጅ የዚያ ተወላጅ የሚባሉ ቦታዎች አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛ ከተሞችን ማን ያስተዳደራቸው በሚለው ጉዳይ፣ ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ሃገራዊ ፖሊሲ ነው ያለን። ያም ከተማ የራሱ የሆኑ የተለዩ ፍላጎቶች አሉት፡፡ በዚያ ምክንያት ሁሉም ከተሞች መተዳደር ያለባቸው የከተማውን ህዝብ ፍላጎት በሚያውቁ የከተማው ነዋሪ በሆኑ ነው፡፡ ይሄ ዘር ቆጥሮ የሚደረግ ነገር አይደለም። አጠቃላይ በሃገር ደረጃም መኖር ያለበት እሳቤ ይሄ ነው፡፡ ይሄ ለአዲስ አበባ ብቻ አይደለም። ለሁሉም ከተሞች ነው፡፡ ከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች በከተሞች መስፋፋት ይጠቀማሉ እንጂ ተጎጂ አይሆኑም፡፡ ዋናው በእኩልነት መጠቀሙ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል ያሉ ሰዎች ከአዲስ አበባ መስፋፋት የበለጠ ይጠቀማሉ እንጂ የሚጎዱበት ምክንያት የለም። ይሄን ዝም ብለን የዘር ጉዳይ አናድርገው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ  ዝም ብለው ገጠር እየኖሩ አይዘልቁም፡፡ ከዓመታት በኋላ ገጠሬው ከተሜ ይሆናል። ከተሞች የወደፊት የሁሉም ሰው የህይወት ማዕከል ነው የሚሆኑት፡፡ ዋናው ገጠር ያለው ከከተሞች እንዴት ይጠቀማል የሚል ነው እንጂ ከተማ መስፋፋቱ ተፈጥሮአዊ ነው። ይህ አሁን የተወጠረው  የዘር እሳቤ እንዲሁ እንደተወጠረ ይቆያል፤ ከሚል እሳቤ መውጣት አለብን፡፡ የወደፊቱን አርቀን ማየት አለብን። ስልጣኔ ማሰብ አለብን፡፡ ስልጣኔ ሲመጣ አብዛኛው ወደ ከተማ ተስቦ ከተሜ ይሆናል፡፡ አሜሪካን ሃገር ሲጀመር የከተማ ነዋሪው 10 በመቶ ምናምን ነበር፤ አሁን 97 በመቶ ሆኗል፡፡ 3 በመቶ ነው የገጠር ነዋሪ። ሁሉም ሃገር እንዲህ ነው የጀመረው። ስለዚህ ከተሞችን የመጋጫ ከማድረግ ወጥተን ገጠር ያሉ ሰዎች ህይወት በከተሞች መስፋፋት የሚሻሻልበትን ነገር ማሰብ ነው ያለብን፡፡ ከዚህ ከመናቆር ፖለቲካ ስንወጣ እነዚህ ሁሉ እየታዩን ይሄዳሉ፡፡ ከተሞችን ዛሬ ባለው ሁኔታ ብቻ እያሰብን የመጋጫ ማዕከል አናድርጋቸው 97 ላይ ኢህአዴግ የአዲስ አበባን ህዝብ ከኦሮሚያ ህዝብ የማይረባ ሂሳብ  ሰርቶ ለማጣላት ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡ ስለዚህ ከዚህ አይነቱ ከንቱ ሙከራ እንውጣ፡፡ ከተሞች ፈጽሞ የመጋጫ ማዕከላት ሊሆኑ አይገባም፡፡


Read 1705 times