Saturday, 10 April 2021 12:43

በዚህ ሳምንት በኮቪድ-19 ስርጭት መጠን አ.አ ቀዳሚነቱን ይዟል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

                       
           በዚህ ሳምንት በኮሮና የስርጭት መጠን ከመላው የአገሪቱ አካባቢዎች አዲስ አበባ ቀዳሚነቱን የያዘ ሲሆን 7 ቀናት ውስጥ 5 ሺ 870 ሰዎች  በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። በኦሮሚያ 1146 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን አማራ ክልል ደግሞ በሳምንቱ ውስጥ 354 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
በሳምንቱ ውስጥ በመላው አገሪቱ 14 ሺ 955 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፤ 193 ሰዎች በበሽታው  ህይወታቸውን አጥተዋል።
ኮሮና በከፍተኛ መጠን መሰራጨቱን ተከትሎ፣ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር  ያወጣው መመሪያ ፤ ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ በበርካታ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እየተጣሰ ነው ተብሏል።
በቅርብ የኮቪድ የስርጭት መጠን በአስደንጋጭ ሁኔታ እያሻቀበ መምጣቱን ተከትሎ፣ ከጤና ሚኒስቴር ከሰላም ሚኒስቴርና ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እንዲሁም ፌደራል ፖሊስና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጣ ግብረሃይል ተቋቁሞ መመሪያን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል። በዚሁ መሰረትም ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ47ሺ በላይ ሰዎችና 115 ተቋማት መመሪያውን ጥሰው ተገኝተዋል። በእነዚህ መመሪያውን በሚጥሱ አካላት ሰዎችና ተቋማት ላይ አስተማሪ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ተብሏል። 20 ግለሰቦችን 10 ተቋማት ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑንም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጤና ሚኒስቴር ባወጣው መመሪያ እንደተገለጸው በየደረጃው ያሉ አመራሮች  ያለ ማስክ ከመንቀሳቀስና ስብሰባዎችን ከማድረግ እንዲቆተቡ ሆቴሎች ከተፈቀደው የሰው ቁጥር በላይ ማንኛውም አይነት ስብሰባዎችና ማህበራዊ ዝግጅቶችን እንዳያከናውኑና የሃይማኖት ተቋማትም ማስክ ማድረግን አስገዳጅ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
በተያያዘ ዜና፤ በአገሪቱ ከፍተኛ እጥረት ያጋጠመውን የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያዎችን ችግር በጥቂቱ ለማቃለል ያስችላል የተባለ 180 ቬንትሌተሮች ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 በሽታ ስርጭት ከአፍሪካ በ4ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ስትሆን ደቡብ አፍሪካ በ1ሚሊዮን 550 ሰዎች መያዝና በ52846 ሰዎች ሞት ቀዳሚነቱን ይዛለች። ሞሮኮ በ496ሺ ሰዎች ሁለተኛ ስትሆን ቱኒዝያ በ254 ሺ ሰዎች ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ በ206ሺ 589 ሰዎች መያዝ በአራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።


Read 10733 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 11:08