Saturday, 10 April 2021 12:29

መንግስት “ኦነግ ሸኔ”ን በሁለት ሳምንት ውስጥ ለመደምሰስ አቅዷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ በምዕራብ ወለጋ በተደጋጋሚ በንጹሀን ዜጎች ላይ ለደረሱ ጥቃቶችና አሰቃቂ ግድያዎች ተጠያቂ የሚያደርገውን የ“ኦነግ ሸኔ” ቡድን በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ አቅዶ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
ከሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ ያጋጠመውን የሠላማዊ ዜጎች ጭፍጨፋ ተከትሎ “ኦነግ ሸኔ” ሙሉ በሙሉ መደምሰስ የሚያስችል እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ያስታወቀው ክልላዊ መንግስቱ በዚህም በርካታ የድርጅቱ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውን ጠቁሟል።
የቡድኑ አባላት  በመደምሰስ ዘመቻ ወቅት ለቡድኑ አባላት  ሽፋን የሰጡም ሆነ ከቡድኑ ጋር ተባባሪ ሆነው በተገኙና ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ የመንግስት አካላት ላይ እርምጃ ይወስዳል ብሏል-የክልሉ መንግስት፡፡
በአሁኑ ወቅት ከዚህ በፊት ጥቃት በተፈጸመባቸውና ጥቃት ሊፈጸምባቸው ይችላሉ ተብለው በተሰጉ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ተደራጅቶ የተጠናከረ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ያስታወቀው ክልላዊ መንግስቱ፤ ህብረተሰቡን በሚሰበስበው መረጃ መሰረትም የፀጥታ ሃይሎች እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ጠቁሟል።
በምዕራብ ወለጋ በተለይ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት ዘላቂ መፍትሔ በሚያገኝበት እንዲሁም የኦሮሞና አማራ ህዝብ ግንኙት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት አግባብ ላይ የሁለቱ ክልል አመራሮች ከሰሞኑን ምክክር አድርገው መጠነ ሰፊ መግባባት ላይ መድረሳቸውን የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል።

Read 11430 times