Print this page
Saturday, 10 April 2021 12:26

ጠ/ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ማዕከል ትሆናለች አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

የቴሌኮም ዘርፍን ወደ ግል በማዘዋወር ጉዳይ ቴሌኮም ሪቪው አፍሪካ ከተሠኘ መፅሔት ጋር ከትናንት በስቲያ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ገበያ ማዕከል ለማድረግ መታቀዱን ገልፀዋል።
ከመፅሔቱ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በዋናነት በቴሌኮም ዘርፉ ወደ ግል የማዘዋወር ሂደት ላይ አተኩሮ ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ጠ/ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፉን የእድገትና የብልጽግናዋ አንቀሳቃሽ ማድረግ የሚያስችላትን እቅድ ነድፋ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን አብራርተዋል፡፡
መንግስት ቴሌኮምን ወደ ግል  ለማዘዋወር የወሰነው የሃገሪቱን በቴክኖሎጂ ከፍ ያለ ደረጃ የመድረስ ምኞት ከግብ ለማድረስ በማሰብ መሆኗን ያስረዱት ጠ/ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ብልጽግናና እድገት እውን የሚሆንበት አንዱ ዘርፍ የቴክኖሎጂና ቴሌኮም ዘርፉ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግናና የልማት ጉዞ የጀርባ አጥንት መሆን ትፈልጋለች ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ይህም እቅድ በቅርቡ ይፋ በተደረገው የ10 ዓመት ብሔራዊ የእድገት እቅድ ውስጥ ተካቷል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፉ በአንድ መንግስት ድርጅት እጅ በቂና ጥራት ያለው አገልግሎት ማቅረብ አላስቻለም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ በሃገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት የሚወስኑ የግል ኩባንያዎች ካለው የገበያ ፍላጎት በእጅጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ የሃገሪቱንም የእድገትና ልማት እቅድ ያግዛሉ የሚል እምነት  አለኝ ብለዋል፡፡
የሃገሪቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እድገት በማረጋገጥ ግዙፍ የአይሲቲ ፓርክ እየገነባ መሆኑን ይህም የሃገሪቱን የአገልግሎት ዘርፍ ዲጂታል ለማድረግና ለማዘመን በእጅጉ አጋዥ መሆኑን ጠ/ሚኒስተሩ አስረድተዋል፡፡
መንግስት እ.አ.አ በ2025 ዲጂታላይዝድ የሆነች ኢትዮጵያን እውን የማድረግ እቅድ እንዳለው የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እድገቱም የግብርናውን፣ የጤናውን፣ የአገልግሎት፣ የትምህርት የቱሪዝምና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በመሰረታዊነት ይለውጠዋል ብለዋል፡፡

Read 1073 times