Tuesday, 06 April 2021 00:00

“የምትፈልጉትን የሚሰጥ”፣ ወይስ “የሚያስፈልጋችሁን የሚያውቅ”፣ ወይስ “ነፃነታችሁን የሚጠብቅ” መንግስት?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)

    “መንግስት ያውቅላችኋል”!
“ምናልባት፣ የምትፈልጉትን ነገር ታውቁ ይሆናል። የሚያስፈልጋችሁን ግን፣ መንግስት ያውቅላችኋል”... ይሄ፣ የልማታዊ መንግስት አባባል ነው። እንደ ተንከባካቢ ወላጅ ሆኖ ይጀምራል። ከዚያ “ቁጡ አሳዳጊ ሞግዚት” እየመሰለ ይሄዳል።
አለቦታው ቢዝነስ ውስጥ እየገባ፣ በብዙ ፕሮጀክቶች አማካኝነት፣ ብዙ ሃብት ሲያባክንና የብድር እዳ ውስጥ ሲገባ ይቆያል። ወጪውና እዳው ሲበዛ፣ አለቅጥ ገንዘብ እያተመ፣ በዋጋ ንረት አገርን ያማርራል። ትንሽ ቆይቶ፣ ሞግዚትነቱ እየደበዘዘ፣ ቁጣው እየደነደነ ይመጣል። ዜጎችን እንደ “ጥፋተኛ ታራሚ” የሚቆጥር የእስር ቤት አለቃ ይሆናል።
ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሌላ የመንግስት ቅኝት አለ። ከፕሮጀክቶች ይልቅ፣ ወደ ድጎማ ያዘነብላል።
“ሕዝብ ያውቃል”!
“ምን ትፈልጋላችሁ? ያሻችሁን ጠይቁ። መንግስት በነፃ ያቀርብላችኋል”... ይሄ ደግሞ፣ የህዝባዊ መንግስት አባባል ነው - populist እንዲሉ። አለቦታው አለአቅሙ፣ ልጆችን “ለማሞላቀቅ” የሚያምረው ልወደድ ባይ ዘመድ፣ ወይም አላዋቂ አያት ይመስላል።
ዛሬም ስጦታ፣ ነገም በነፃ ስጦታ! ብዙም ሳይቆይ፣ ስጦታው ያልቅና፣ እንደ ቀጣፊ ደላላ፣ እየሸነገለ ለመወደድ ይሯሯጣል። አንዱን ከሌላው እያናከሰ፣ የአንዱ ጎራ ተቆርቋሪ ለመሆንም ይሞክራል። የሕዝባዊ መንግስት አጀማመርና አወዳደቅ፣ ከዚህ አይለይም። ልማታዊ መንግስትም የኋላ ኋላ፣ አጨራረሱ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። የአገራችን ፓርቲዎች በሙሉ፣ ከእነዚህ ወደ አንዱ ያዘነበሉ ናቸው።  
የፓርቲዎችን የምርጫ ዘመቻ ትታዘባላችሁ። ሁሉም የአገራችን ፓርቲዎች፣ በዚህ በዚህ ይመሳሰላሉ ማለት ይቻላል። ቢያንስ ቢያንስ ግን፣ ሁሉም ባይሆኑም እንኳ፤ አብዛኞቹ ፓርቲዎች፣ “ሁሉንም ነገር በነፃ እንሰጣለን፣ ድጎማ በላይ በላዩ እንጨምራለን” እንደሚሉ አትጠራጠሩ። “ገንዘቡን ከየት ያመጡታል?” የሚል ነው ጥያቄው።
ያው፣ እንደልማታዊ መንግስት፣ ሕዝባዊ መንግስትም፣ ወጪው እጅግ እየበዛ ሲሄድ፣ በዜጎች ላይ ተጨማሪ ታክስ መጫን ይጀምራሉ። ከዚህ ጎን ለጎንም፣ ካመት አመት እየተበደሩ፤ እዳ ያከማቻል። ዞሮ ዞሮ የማይቀር ነገርም አለ። በገፍ ገንዘብ እያተሙ፣ አገሬውን በዋጋ ንረት ያናጋሉ።
3. “የጥበቃ ሰራተኛ”!
የመንግስት ስራ፣ “ከጥበቃ ስራ” ማለፍ የለበትም የሚል ሌላ አማራጭ አባባልም አለ። መንግስት፣ የዜጎች ሞግዚት ወይም አለቃ መሆን የለበትም። “ሃላፊነቱ የተወሰነ፤ ስልጣኑም የተገደበ” መሆን ይገባዋል። በቃ፤ የጥበቃ ሰራተኛ ነው - night watchman እንዲሉ።
ትክክለኛ መንግስት፣ ሰላምን ይጠብቃል። ከዚያ ውጭስ? ከዚያ ውጭ፣ ሰዎችን በሰላምታ መቀበልና ተጨባብጦ መሸኘት? ይሄ፣ ከ”ከንቲባ አንደበት” የወጣ፣ ቁምነገር ያዘለ የቀልድ አባባል ነው። “ከንቲባው” ስራው ምን እንደሆነ ሲጠየቅ፣ “shake hands, and... shake hand and shake hands again”... የሚል መልስ ሰጥቷል። እና፣ በአጭሩ፣ የመንግስት፣ የሁል ጊዜ ስራ፣ ሰላምታ ማቅረብ ነው?
“ከተማው ገጠሩ አማን ነው? አገር ምድሩ ሰላም ነው?”... እያለ ይጠይቃል - ተመራጭ ፖለቲከኛ፣ ከንቲባውም፣ ፕሬዚዳንቱም። በእርግጥ፣ መንግስት ማለት ተመራጭ ፖለቲከኛ ማለት ብቻ አይደለም። ትክክለኛ የመንግስት ስራን ለማከናወን የሚቀጠሩ ትክክለኛ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ - ፖሊስ፣ ወታደር፣ ዳኛ። ሕግና ስርዓትን ያስከብራሉ። የተመራጭ ፖለቲከኞች ስራስ ምንድነው? ወደተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ጎራ እያሉ፤ “እንዴት ነው? ሁሉም ነገር በስርዓት እየሄደ ነው? አማን ነው? ሰላም ነው?” ብለው ይጠይቃሉ - ተመራጭ ፖለቲከኞች።
ይሄማ፣ የ3 ዓመት ህፃንም አያቅተውም ትሉ ይሆናል። “little big shots” የተሰኘውን አዝናኝና ተወዳጅ ፕሮግራም የምታስታውሱ ከሆነ፣ “ከንቲባ” ተብሎ የቀረበውን ህፃን ልትረሱት አትችሉም። የአንዲት ደቃቃ ከተማ ከንቲባ እንዲሆን የተመረጠ ህፃን ነው። ለመሆኑ፣ ስራህ ምንድነው? ሰዎችን በሰላምታ መጨበጥ በማለት መልስ ሰጥቷል - የ3 ዓመቱ ከንቲባ። ይሄው ነው። ሌላ ስራ የለውም።
ታላቅ ወንድሙም፣ በሦስት ዓመት እድሜው፣ የትንሿ ከተማ ከንቲባ ሆኖ “ሰርቷል”። ስራው ደግሞ፣ ሰዎችን በሰላምታ መጨበጥ። ሌላስ? በሰላምታ መጨበጥ። ነገሩ፣ እንደ ቀልድ ነው። ግን ደግሞ፣ ቁምነገር ይዟል።  “የተመራጭ ፖለቲከኛ ስራ፣ የዚህን ያህል ቀላል መሆን አለበት” እንዲህ ቀላል መሆን አለበት የሚል መልዕክት ያስተላልፋል። ግን አትርሱ።ከላ መንግስት ማለት፣ “ተመራጭ ፖለቲከኛ” ማለት ብቻ አይደለም።
መቼም፣ ከተመራጭ ፖለቲከኛና ከምርጫ በፊት፤ ህግና ስርዓት ይኖራል። ድንበርን የሚጠብቅ ወታደር፤ በየመንገዱና በአደባባዩ ፖሊስ መኖር አለበት - ከምርጫ በፊት። ዳኝነትን የሚሰጥ ፍ/ቤትም ይኖራል።
እነዚህ መሠረታዊ የመንግስት ስራዎች ከተሟሉ፣ ሌላው ሌላው ሁሉ፣ የመንግስት ስራ ሳይሆን፣ የእያንዳንዱ ሰው ድርሻ ነው። በግል፣ በቤተሰብም ሆነ በማህበር፣ ሰዎች በሰላም፣ ኑሯቸውን ያቃናሉ፤ ህይወታቸውን ይመራሉ። ይማማራሉ፤ ይገበያያሉ። እንደየዝንባሌያቸው፣ በመደጋገፍና በመዋደድ፣ ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ በመከባበርና በሰላም ይኖራሉ።
እንቅልፍ ወዳድ ፕሬዚዳንት - አገርን ላለማወክ!
ሰዎች ከመንግስት መጠበቅ የሚገባቸው ትክክለኛ ነገር፤ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲያስከብር ነው - በፖሊሶች፣ በወታደሮች፣ በዳኞች። እና ታዲያ፣ የተመራጭ ፖለቲከኛ፣ የፕሬዚዳንት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ስራ ምን ሊሆን ነው? ሰዎችን በሰላምታ መጨበጥ?... የአገሬው ፕሬዚዳንት፣ ከሰላምታ ጋር ዘወትር የሰላም ጥያቄዎችን ያቀርባል። “እንዴት ነው አገሩ?”፣ “ከተማው ገጠሩ ሁሉ ሰላም ነው?” ብሎ እያለ ይቆጣጠራል።
“መንገደኞችን የሚተናኮል ሽፍታና ዘራፊ አለ? ሸፍጠኛ ቀማኛ ሁሉ የእጁን እያገኘ ነው? ከውስጥ በኩል ሰላምን የሚረብሽ፣ ከውጭ በኩል ድንበርን ለመድፈር፣ አገርን ለመውረር የሚቃጣ ወንጀለኛ እንዳይኖር፣ ከመጣም የሚቀጣ... ህግና ስርዓታችን፣ ተደላድሎ እየቀጠለ ነው? እንደዚያ ከሆነ መልካም ነው፤ መልካም ነው። በርቱ። ደግሞም ስራችሁ ነው” እያለ ሰላምታውን ሲያቀርብ ያረፍዳል - ፕሬዚዳንቱ።
የምሳ ሰዓት ይደርሳል። ከዚያ የሸለብታ እረፍት ይኖረዋል። ከሸለብታ በኋላ ብቅ ሲል፣ ተጨማሪ ስራ አይኖርበትም። እለቱን በሰላምታ መሸኘት ብቻ ነው የሚቀረው - “ሰላም እደሩ። ሰላምን ጠብቁ። ስራችሁ ነው።” ብሎ ለአገሪቱ ፖሊሶች አደራውን ከነማሳሰቢያው ሰጥቶ የእለት ስራውን ያጠናቅቃል። የከንቲባ፣ የፕሬዚዳንት፣ የጠ/ሚኒስትር ስራ፣ የዚህን ያህል እጀግ ቀላል መሆን ነበረበት። ለህፃንም የማይከብድ።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ፤ በስልጣን ዘመናቸው ገለጹትን አንድ ሃሳብ ላስታውሳችሁ። እንግዲህ 43ኛው ፕሬዚዳንት አይደሉ ጆርጅ ቡሽ? ከበፊቶቹ ፕሬዚዳንቶች መካከል፣ የትኛውን ያደንቃሉ? ተብለው ተጠየቁ። ጆርጅ ቡሽ፣ የትኛውን ዝነኛ፣ የትኛውን ድንቅ ፖለቲከኛ፣ በአርነት ቢጠቅሱ ጥሩ ነው? ካቪን ኮሊጅ... የሚል ነው የቡሽ ምላሽ። ማን? ማን ነው ኮሊጅ? ሰውዬው ዝነኛ አይደለም - ካልቪን ኮሊጅ ይባላል።
የዛሬ 100 ዓመት ገደማ፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ነበረው ካልቪን ኮሊጅ፣ ዝነኛ ባይሆንም አስገራሚ ታሪክ አለው። እንቅልፍ ይወዳል። በጊዜ ይተኛል። 11 ሰዓት ሙሉ እንቅልፉን ይለጥጣል። ወደ ስራ ከመግባቱ፣ ብዙም ሳይቆይ የምሳ እረፍት ይደርሳል። ከምሳ በኋላ፣ ሁለት ሶስት ሰዓት ያሸልባል። አንዳንዴም ለ4 ሰዓታት ይተኛል። ከተኛበት ሲነሳ፣ የእለቱ የስራ ሰዓት ሊገባደድ ተቃርቧል። ፈገግ ሊያሰኝ ይችላል። መልዕክቱ ግን ሌላ ነው።
የተመራጭ ፕሬዚዳንት ስራ፤ እንዲህ ቀላልና ትንሽ መሆን አለበት የሚል ሃሳብ ያዘለ መሆኑ ነው - ቁም ነገሩ። መንግስት፣ አለስራው እዚህና እዚያ እየገባ ነገር ሲያቦካና ሲያመሳቅል፣... “ባለብዙ ስራ” ልሁን ሲል፤ የአገር ሸክም የዜጎች ውጋት ይሆናል። ካልቪን ኮሊጅ፣ የአገር ሸክምና የዜጎች ውጋት ከመሆን ተቆጥበዋል። ታክስን ሸክም አቅልለዋል። የመንግስትን ወጪ ቀንሰዋል። ኢኮኖሚ እንዲያድግ እድል ከፍተዋል። በዚህም ይመሰገናሉ።
በግዴታ እረፍት እንዲወጡ በሕግ ማስገደድ! በየአመቱ የ6 ወር እረፍት!
አብዛኛው ከንቲባና  ፕሬዚዳንት፣ አብዛኛው ተመራጭና ፖለቲከኛ፣ ልኩን አውቆ፣ አደብ ገዝቶ፣ ስራው ላይ ብቻ ማተኮር አይፈልግም። “ምንም ነገር አይቅርብኝ” ባይ ይሆናል። ጠብ እርግፍ ይላል። እንዲህ አይነት አዋኪ ፖለቲከኞችን ለመግራት፣ ወከባቸውንም ለመቀነስ ምን መፍትሄ አለ?
የህገመንግስት ዋነኛ አገልግሎት ምን ሆነና? ለእያንዳንዱ ባለስልጣን፣ የስራውን ምንነትና የስልጣኑን ልክ፣ ገድቦና ቆጥሮ የሚያሳውቅ ልጓም ነው - ህገመንግስት። ግን፣ ብዙዎቹ ተመራጮችና ፖለቲከኞች፣ ለልጓም አስቸጋሪ ናቸው።
የቴክሳስ ግዛት ህገመንግስት የተለያዩ ተጨማሪ ዘዴዎችን ለመጠቀም ሞክሯል። ለምሳሌ፣ የክልሉ መስተዳድር፣ በነዋሪዎች ላይ የገቢ ግብር መጫን አይችልም ይባል - የክልሉ ህገመንግስት። ይህም ብቻ አይደለም።
የክልሉ ምክር ቤት፣ በየአመቱ ለ6 ወር፣ በግዴታ እረፍት ይወጣል። በቃ፣ ምክር ቤቱ፣ ለግማሽ ዓመት ዝግ ነው። ፖለቲከኞች፣ ዜጎችን ከማወክ የማይቆጠቡ፣ በራሳቸው ፈቃድ የማይተኙ ከሆነ፣ ምን ማድረግ ይቻላል? የስብሰባ አዳራሻቸውን እና ቢሮዎቻቸውን ለግማሽ ዓመት መዝጋት!
ችግር ነዋ። መንግስት፣ “ባለ ብዙ ስራ” ለመሆን ሲንከወከው፤ ወጪው እየጨመረ፤ ሃብት ማባከን ይለምዳል። ፖለቲከኞች እለት በእለት ሲሰበሰቡ፣ የሚያደርጉት ቢያጡ፣ ቁምነገር ቢያልቅባቸው፣ የሚዘባርቁትና የሚሸርቡት ነገር አያጡም።
“የፈለጋችሁትን ነገር በነጻ እንሰጣለን” ይላሉ ብዙዎቹ።
ሌሎች ደግሞ እንደ ቁጡ አባት መሆን ያምራችኋል። “ማህበር መስርቱ፤ አንድ ለአምስት ተደራጁ፤ የባንክ ሂሳብ ክፈቱ፤ መብራት ቆጥቡ፤ ቤት ኪራይ አትጨምሩ፤ ለጤንነት ስፖርት ስሩ፤ የጓሮ አትክልት አልሙ፤ ያገለገለ መኪና አትግዙ፤ አዲስ መኪናም ቅንጦት ነው፤ ከገዛችሁበት ዋጋ ሁለት እጥፍ ታክስና ቀረጥ ትከፍታላላችሁ። ህንፃ መስራት ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፤ ልብስ ፋብሪካ ግን ልማታዊ ነው፤ ማስቲካ ፋብሪካ ግን ያሳፍራል”.... ምን የማይሉት ነገር አለ?
እንደተንከባካቢ ወላጅ ሆኖ፤ እለት በእለት መዓት ምክር በማዝነብ ይጀምርና፤ በማግስቱ ወደ ቁጣና ወደ ትዕዛዝ ይገባል። የአገሬውን ሰዎች በሙሉ፣ እንደ ህፃናት ነው የሚያያቸው - የሚፈልጉትን እንጂ የሚያስፈልጋቸውን አያውቁም” ይላል። ግን ችግር የለም፤ “የሕዝቡን እውነታኛ ፍላጎት መንግስት ያውቅላችኋል፤ እኔ አውቅላችኋለሁ” ይላል - እንደ ወላጅ። ችግሩ ምንድ ነው? ሁል ጊዜ ሕጻን ሆኖ የሚኖር ጤናማ ሰው የለም። “ራሱን የሚችል አዋቂ ሰው” ይሆናል።
ለነገሩ፣ መንግስትና ሕዝብ፤ በተፈጥሯቸው፣ “ወላጅና ህፃን” አይደሉም። ፖለቲከኞች ግን ያስመስላሉ። “የግል መኪና ቅንጦት ነው። የግል ታክሲ ይወደድባችኋል። በአነስተኛና በቅናሽ ዋጋ፤ የልብ የሚያደርስ የአውቶቡስ አገልግሎት አቀርብላችኋለሁ” ይላሉ - እንደ ወላጅ።
መንግስት፣ እንዲህ ቃል እየገባ ስንት አመት አለፈ? አንድ ሁለት ዓመት? ኧረ፣ ከዚያ በፊትም፣ መንግስት፣ ሲምል ሲፎክር ነበር። ለአምስት ለአስር ዓመት? ኧረ ከዚያ በፊትም ነው። ሃያ እና ሰላሳ ዓመት? የኢህአዴግን ዘመን ተሻግረን፣ የድሮ ታሪኮችን ማንበብ ብንጀምር፣ በደርግ ጊዜም፣ ባስ ያለ ታሪክ እናገኛለን። አውቶቡስ ተርፎ እንደሚትረፈረፍ ቃል ከመግባት አልፎ፣ ፉከራም ዛቻም ተጨምሮበት ነበር።
ግን እንደምታዩት፣ ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላም፣ የመንግስት ቃል ፖለቲከኞች ዲስኩር አልሰመረም። የትራንስፖርት ችግርና ወረፋ እየተባባሰ ሲትረፈረፍ ነው የምናየው።
ከዚህ ጎን ለጎን ነው፣ የመንግስት ምስል የሚቀየረው። ከተቆርቋሪ ወላጅ፣ ወደ ቁጡ ወላጅ፣ ከዚያም እንደ እስር ቤት አለቃ ለመሆን ይቃጣዋል። ሰዎችን እንደ ጥፋተኛ ታራሚዎች ማየት ይጀምራል። ሚኒባስ ታክሲዎችን፣ “እዚህ ሂዱ፤ እዚያ አትሂዱ” ብሎ የሚቆጣጠራቸውና የሚቀጣቸው ለምን ሆነና! እንዲያውም፣ አዲስ አበባን ከሚኒባስ ታክሲዎች አላቅቃታለሁ ብሎ የሚዝተውም በዚሁ መንፈስ ነው። ዝቶ አልቀረም። ባለ ሰማያዊ ቀለም ሚኒባስ ታክሲዎች ምን ያህል ቁጥራቸው እንደተመናመነ ተመልከቱ። የታክሲ ወረፋው ደግሞ በዚያው መጠን ረዝሟል።
ግን አይገርምም። መንግስት፣ “ባለ ብዙ ስራ” ለመሆን ሲሞክር፤ ውሎ አያደረ ችግሮችን የሚያባብስና አዳዲስ ጣጣዎችን የሚሸርብ ሆኖ ያርፈዋል።
የሰዎችን ነጻነትና መብት፣ በህግና በስዓት የማስከበር “ትክክለኛ ስራው” ላይ ብቻ ቢያተኩርኮ፤ ለዜጎችም ለመንግስትም ትልቅ እረፍት በሆነ ነበር - ለሰላማዊ እንቅልፍም ጊዜ ያገኝ ነበር።

Read 6415 times