Tuesday, 06 April 2021 00:00

የመቀሌዋ የግቢያችን የጦርነቱ ቃል አቀባይ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (brooha3212@gmail.com)
Rate this item
(6 votes)

 ክፍል 9፡ ከጦርነት ፍርሃት ወደ ኢኮኖሚያዊ ችግር
                      
              ጦርነቱ እየገፋ ሲመጣ በክልሉ መንግስት ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች አንድ በአንድ እየተቋረጡ ሄዱ፡፡ ከህዳር 17 ቀን 2013 ጀምሮ የቧንቧ ውሃ እንደተቋረጠ ነው፤ ለሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታትም ያለ ቧንቧ ውሃ ከጉድጓድ እየተጠቀምን አሳለፍን፡፡ ከህዳር 21 ቀን 2013 ጀምሮ ደግሞ መቀሌ ላይ መብራት እንደጠፋ ነው፤ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታትም ያለ መብራት በጨለማ ውስጥ አሳለፍን፡፡ በዚህም ምክንያት፣ ሰሞኑን በቅርብ ርቀት ስንሰማው የነበረው ጦርነት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለማወቅ አልቻልንም፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረበት ቀን ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ጀምሮ በመላው ትግራይ የኢንተርኔትና የባንክ አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው፡፡ ስልክም የሚሰራው ትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ጦርነቱ እየገፋ ሲሄድ ግን ስልክ የሚሰራባቸው የትግራይ አካባቢዎችም እየጠበቡ ሄደው በስተመጨረሻ መቀሌ ላይ ብቻ ተወሰነ፡፡
በዚህም የተነሳ ለአንድ ወር ያህል አዲስ አበባ ከሚገኙት ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን ተነጥለን ቆየን፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ቤተሰቦቻችን ‹‹ከሞት ተርፈው ይሆን?!›› እያሉ በየቀኑ ይጨነቃሉ፡፡ በዙሪያችን ምን እየተደረገ እንደሆነ አናውቅም፤ ከሁሉም ጋር ተነጥለን ደሴት ሆነናል፡፡ በዚህ ወቅት መቀሌ በመብራትና በስልክ ብቻ ሳይሆን በትራንስፖርትም ከአዋሳኝ የገጠር ቀበሌዎች ተነጥላለች፡፡ በዚህም የተነሳ ከየአቅጣጫው ወደ መቀሌ ሲገቡ የነበሩ ምርቶች ሙሉ በሙሉ ቆመዋል፡፡
ባንክ ዝግ በመሆኑ በህዳር መጀመሪያ፣ መቀሌ ላይ ያሉ የክልልና የፌዴራል መ/ቤቶች፣ ከደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም ገንዘብ በመበደር፣ ለሰራተኞቻቸው ደምወዝ ከፈሉ፡፡ ሆኖም ግን፣ በምርት የአቅርቦት እጦት የተነሳ የሸቀጦች ዋጋ እስከ 400% ድረስ አሻቀበ፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ4500 ብር ወደ 8000 ብር፣ አንድ ሻማ ከ4 ብር ወደ 10 ብር፣ አንድ ኪሎ ቲማቲም ከ20 ብር ወደ 95 ብር ተተኮሰ፡፡ እናም ኑሮ በእጅጉ ከበደ፤ ሰው በየቤቱ የነበረው አስቤዛ ማለቅ ጀመረ፤ ያለው ለሌለው እያካፈለ መኖር ጀመረ። እኛም የጤፍ ዱቄት ጨርሰን አከራያችን እማማ ፃድቃን ከራሳቸው ቀንሰው ሰጡን፤ ደግነታቸውን አመስግነን ተቀበልን፡፡  ከቤት የሚተርፍና የሚጣል እህል ጠፋ፤ ውሾችና ድመቶች ተራቡ፡፡ መብራት ላይ የተገነባው የሰው ልጅ ስልጣኔ፣ አይናችን እያየ መቀሌ ላይ መንኮታኮት ጀመረ፡፡ ኑሯችን ሁሉ ወደ ጥንታዊ ዘመን ሰው እየሆነ ሄደ፤
ማብሰያችን ከኤሌክትሪክ ምድጃ ወደ ከሰል፤ ከከሰል ወደ ዲንጋይ ምድጃ ተቀየረ፤
የመጠጥ ውሃችን ከሃይላንድ ወደ ቧንቧ፣ ከቧንቧ ወደ ጉድጓድ ውሃ ተቀየረ፤ የጉድጓዱን ውሃ ሳያፈሉ የጠጡትም በጠና ታመሙ፤
ሰዓት መቁጠር አቆምን፣ ጊዜውም ተደበላለቀብን፤
ሰው ሁሉ እጁ ላይ ያለው ገንዘብ ማለቅ ሲጀምር፣ ሸቀጦች ከተሰቀሉበት ዋጋ በአስደንጋጭ ፍጥነት ወረዱ፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ኪሎ ቲማቲም ከ95 ብር ወደ ሦስት ብር ወረደ፡፡ አንድ እንቁላል ከሰባት ብር ወደ አራት ብር ዝቅ አለ፤ ዶሮ ከ500 ብር ወደ 150 ብር ወረደ፡፡ በርካታ አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚገዛቸው አጥተው ተበላሽተው ተጣሉ፡፡
ህዳር 25 ቀን 2013 የልጄ እናት በጠዋት ተነስታ ‹‹ሌሊት የሆነ ህልም አየሁ›› አለችኝ፤
እኔም፤ ‹‹ምን ዓይነት ህልም?›› አልኳት፤
እሷም፤ ‹‹ዶ/ር ደብረፅዮንና ደጋፊዎቹ ነጭ ፈረስ እየጋለቡ ሲመጡ አየሁ፤ ፈረሰኞቹን ከፊት ሆነው የሚመሩት ደግሞ የቃል አቀባያችን ባልና ጓደኛው ናቸው፡፡ የበፊቷ ቤት አከራዬ እማማ ዓመተ ደግሞ ከኋላ ሆነው መኪና እየነዱ፣ ፈረሰኞቹን ሲከተሏቸው መንገድ ላይ አገኙኝና ‹‹ነይ ግቢ›› ሲሉኝ፣ እኔ ግን ‹‹አይ አልገባም›› አልኳቸውና እሳቸው እየሾፈሩ ሄዱ›› አለችኝ፡፡
እኔም፤ ‹‹በህልም መኪና መንዳትና ነጭ ፈረስ መጋለብ ምንድን ነው ትርጉሙ?›› አልኳት፡፡
እሷም፤ ‹‹ሞት ነው!!›› አለችኝ፡፡
እኔም ደነገጥኩና፤ ‹‹እና ደብረፅዮንና የቃል አቀባያችን ባል ይሞታሉ ማለት ነው!!? በይ ይሄንን ነገር ለማንም እንዳትናገሪ!! በተለይ ቃል አቀባያችን እንዳትሰማ›› በማለት አስጠነቀቅኋት፡፡ ከሳምንታት በኋላ የቃል አቀባያችን ባል ምንም ሳይሆን በሰላም ተመልሶ መጣ፤ የዶ/ር ደብረፅዮንም ነገር ይፋዊ በሆነ መግለጫ እስከ አሁን አልታወቀም፤ እናም ‹‹የነጭ ፈረሱ ህልም›› ሳይሰራ ቀረ፡፡
ህዳር 26 ቀን 2013 መከላከያ ኃይል ተመልሶ ወደ መቀሌ ገባ። ከተማውም ከሚሊሺያዎች የጥይት እሩምታ ተገላገለች። ከአይደር ሆስፒታልም ምንም የተሰረቀ ዕቃ እንደሌለ ታወቀ።
ህዳር 27 ቀን 2013 መቀሌ አይደር ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው ወፍጮ ቤት ውስጥ ለህወሓት ወታደሮች ሊላክ የተዘጋጀው የተፈጨ በርካታ ኩንታል የጤፍ ዱቄት ለህዝቡ በነፃ ተከፋፈለ። እኛም 20 ኪሎ ዱቄት ደረሰንና በእሷ ማገገም ጀመርን፡፡
ባለፈው ህዳር 21 ቀን 2013 መቀሌ ላይ መብራት ከጠፋ ወዲህ ስለ ጦርነቱ ምንም መረጃ ማግኘት የማይቻል ሆነ። ሆኖም ግን፣ ከሁለት ክስተቶች ህወሓት ሙሉ በሙሉ ስለመሸነፉ ፍንጭ አገኘን። የመጀመሪያው፣ ህዳር 26 ቀን 2013 ከመቀሌ ወጥቶ የነበረው የመከላከያ ኃይል ተመልሶ መምጣቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ መቀሌ አይደር ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው ወፍጮ ቤት ለህወሓት ሰራዊት ሊላክ የተዘጋጀው የተፈጨ የጤፍ ዱቄት ለህዝቡ በነፃ መከፋፈሉ ነው።
ሆኖም ግን፣ አብዛኛው የመቀሌ ህዝብ እነዚህን ነገሮች እያየም እንኳ ‹‹ህወሓት ተመልሶ ይመጣል›› የሚል ተስፋ አለው። ነገሩ የ1983ቱን ክስተት ያስታውሰኛል፡፡ በወቅቱ ፕሬዚደንት መንግስቱ ኃ/ማርያም ወደ ዚምባብዌ የሸሹበትና ኢህአዴግ አዲስ አበባን የተቆጣጠረበት ወቅት ነበር፡፡ ታዲያ አዲስ አበባ ላይ በየቀኑ ‹‹መንጌ ብዙ ሺህ ወታደር አስልፎ በኬንያ በኩል እየመጣ ነው!!›› እየተባለ በስፋት ይወራ ነበር፡፡ ትጥቁን በየሜዳው ጥሎ የተበተነ ሰራዊት፣ ባለመሞቱ ፈጣሪውን ያመሰግናል እንጂ እንደገና ተሰባስቦ፣ ሞራሉን ገንብቶ፣ መሳሪያ አንግቦ (እሱም ከተገኘ)፣ መልሶ ይዋጋል ማለት አመክንዮ ላይ ሳይሆን ምኞት ላይ የተንጠለጠለ ተስፋ ነው፡፡
ቃል አቀባያችን ከግቢያችን ከጠፋች ከአንድ ሳምንት በኋላ ተመልሳ መጣች። ግቢ ውስጥ ያገኟት ሴቶችም ከፍ ባለ ድምፅ ‹‹የጠፋ ሰው!! በመከራ ቀን ትተሽን ሄድሽ አይደል!! ለመሆኑ፣ ምን አዲስ ነገር አለ?›› ብለው ጠየቋት፡፡ እሷም ‹‹መከላከያ የአክሱምንና የሽሬን ወጣቶች ቤት ለቤት እየገባ እየገደላቸው ነው፤ ሴቶችንም እየደፈረ ነው፡፡ ኢሳያስ ደግሞ ፈንጥዟል፤ መከላከያ መቀሌ በመግባቱ ኢሳያስ ተደስቶ አሰብንና ቀይ ባህርን ለአማራ ሰጥቷል። ሌላው ያልነገርኳችሁ ነገር ደግሞ፣ በማይካድራ የተጨፈጨፉት ትግራዋዮች ናቸው፤ ጭፍጨፋውን የፈፀመው ደግሞ መከላከያ መሆኑ ተረጋግጧል፤ ለዚህም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማይካድራውን ጭፍጨፋ ገብተን እናጣራ ብሎ ሲጠይቅ መንግስት የከለከለው፡፡ በነገራችን ላይ፣ ሰሞኑን መቀሌን ቀውጢ የሚያደርግ የድል ዜና ትሰማላችሁ፤ ህወሓት በርካታ ከተሞችን በማስለቀቅ ወደ መቀሌ እየገሰገሰ ነው፤ ህዳር 30 መቀሌ ይገባል፡፡ ከዚያ በፊት ግን ዶ/ር ደብረፅዮን አዲሳባን በሚሳየል ሊያጠፋት ስለሆነ የውጭ ሀገር ዜጎች ከአዲሳባ እንዲወጡ የ72 ሰዓታት ጊዜ ሰጥቷቸዋል›› በማለት በድል አድራጊነት ስሜት እየተኮፈሰች ወደ ቤት ገባች፡፡ እኔም ከዚያን ዕለት ጀምሮ ቀንና ሰዓት መቁጠር ጀመርኩ፤ 72 ሰዓቱ አለቀ፣ ህዳር 30ም አለፈ፤ ሚሳየሉም የለም፤ ህወሓትም አልመጣም!!
ታህሳስ 3 ቀን 2013 በመቀሌ የባህታ ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የተገኙት ባህታውያን «ከዚህ በኋላ ሰላም ነው፤ አትጨነቁ» እያሉ ህዝቡን አፅናኑት። እነዚህ ባህታውያን ህዳር 16 ቀን 2013 የኪዳነ ምህረት ቀን ላይ ራሳቸውን በሰንሰለት እየገረፉ ስለ መጪው የመከራ ቀናት ዋይታ ሲያሰሙ ነበር፡፡
ታህሳስ 4 ቀን 2013 ከሰዓት 11:30 ላይ ላለፉት 14 ቀናት በመቀሌ ጠፍቶ የነበረው መብራት ተመልሶ መጣ። ህዝቡም በየግቢው ዕልል አለ። ስልክም ተከፍቷል፡፡ ከጥቅምት 25 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 4 ድረስ ለ39 ቀናት ደብዛቸው የጠፉ ቤተሰቦች በስልክ መፈላለግ ጀመሩ፡፡ ይሙቱ ይትረፉ የማይታወቁ፣ ተነጣጥለው የነበሩ ወላጅና ልጆች መፈላለግ ያዙ፡፡ በጦርነት አሊያም በረሃብ ያለቅን የመሰላቸው ቤተሰቦች በርካታ ናቸው፤ በርግጥም ከረሃብና ከጦርነት ተርፈናል፡፡
ከሁሉም የሚያሳዝኑት ግን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ጥቅምት 24 ለትምህርት ወደ መቀሌ ሄደው ሌሊቱኑ ጦርነት የተጀመረባቸው ተመራቂ ተማሪዎች በርካታ ናቸው፤ የእነዚህ ተማሪዎችን ቤተሰቦች የ39 ቀናት ፀፀት ሳስበው፣ ውስጤ ያለቅሳል፤ ሳያውቁት ልጅን ወደ ጦርነት የመላክ ፀፀት!!! ከ39 ቀናት ጭንቀትና ፀፀት በኋላ እነዚህ እናቶች፣ የልጆቻቸውን ድምፅ በስልክ ሲሰሙ አለቀሱ!! ‹‹ልጄ! እማዬ!›› እየተባባሉ ተላቀሱ!! እናቶችም ‹‹ልጄ፤ እኔ ነኝ ገዳይህ!›› እያሉ ስልክ ላይ አነቡ!! በሁለቱም ጫፍ የማያቋርጥ ለቅሶ ሆነ!!
(ይቀጥላል….)

Read 7118 times