Saturday, 03 April 2021 18:44

“እንደ ልቤ እንድናገር...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

     (ምስኪኑ ሀበሻ እንደ ልማዱ ድምጹን አጥፍቶ፣ አንድዬ ዘንድ ጎራ ብሏል፡፡ ውለታ ለመጠየቅ፡፡ ምን ይሆን የፈለገው?)
       
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! አንድዬ!
አንድዬ፡— ማነህ? ጮክ ብለህ ተናገር፡፡ ድምጽህ እየተሰማኝ አይደለም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እኔ ነኝ፣ አንድዬ! ምስኪኑ ሀበሻ ነኝ፡፡
አንድዬ፡— አንተው ነህ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ! ረሳሁህ እንዳትለኝና.... በቃ ለመጨረሻ ጊዜ አንደኛዬን ተስፋ ቆርጬ ቁጭ እንዳልል፡፡
አንድዬ፡— እኔን ሰበብ ማድረጉን ተወውና... ነገረ ሥራችሁን ሁሉ ሳየው ሁላችሁም ተስፋ የቆረጣችሁ ነው የምትመስሉት፡፡ ምን እንደምትፈልጉ እንኳን እኔ እናንተ እራሳችሁ የምታውቁት አይመስለኝም፡፡ እንደገና ጠፍጥፌ አልሠራችሁ ሆኖብኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደገና ጠፍጥፈህ ብትሠራንም ሳይብስብን ይቀራል ብለህ ነው!
አንድዬ፡— እሱን እናንተ እወቁ፡፡ የሆነስ ሆነና ምነው ድምጽህ እንዲህ ሰለለብኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኑን አንስቼ ምኑን ልተውልህ፣ ድምጻችን ብቻ ሳይሆን ጠባያችንም ስልል ብሏል፡፡ ልባችንም ስልል ብሏል፡፡
አንድዬ፡— በል ደግሞ ነገሩን ሁሉ በእኔ አሳብና እንደለመዳችሁት ምን አደረግንህ? ምን በደልንህ? በለኝ አሉ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አልልም አንድዬ፣ የራሳችንን ጉድ እያወቅሁማ በጭራሽ እንደሱ አልልም፡፡
አንድዬ፡— ጎሽ ለአንድ ቀንም እኔን ሳታማርሩ ከዋላችሁ ጥሩ ነው፡፡ እሺ፣ ዛሬ ምን እግር ጣለህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ውለታ እንድትውልልለኝ ልጠይቅህ ነው የመጣሁት፡፡
አንድዬ፡— ይቺ ናት ጨዋታ የምትሏት ተረት አሁን ገና ትርጉሟ ገባኝ፡፡ ሌላው ቀረና ጥያቄህ ጭራሽ ውለታ ሆነና አረፈው!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን መሰለህ... የሆነ ነገር ውስጥ ክተተኝና ውለታ ዋልልኝ፡፡
አንድዬ፡— ጉድ እኮ ነው! ደግሞ ምን ውስጥ ነው የምከትህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፤ የሆነ ቡድን፣ ወይ ድርጅት፣ ወይ ማህበር ምናምን አስገባኝና  ወይ ሊቀ መንበር፣ ወይ ሰብሳቢ..ብቻ የሆነ ስልጣን ላይ አስቀምጠኝ፡፡
አንድዬ፡— ምነው እስከ ዛሬ እንዲህ አይነት ጥያቄ ጠይቀኸኝ አታውቅ! ዛሬ ምን አዲሰ ነገር ቢገኝ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ብቻዬን ቀረሁ አንድዬ...ብቻዬ ቀረሁ፡፡ እንዴት መሰለህ... ሰዉ ሁሉ ተዋናይ ሆኖ መድረክ ላይ ወጣና በሰፊው አደራሽ ውስጥ እኔ ብቻ ተመልካች ሆኜ ቀረሁ!
አንድዬ፡— ታዲያ አንተም እንደ እነሱ መድረኩ ላይ ወጥተህ መተወን ነዋ!
ምስኪን ሀበሻ፡— በየት ብዬ፣ አንድዬ! በየት ብዬ! እንኳን እዛ አካባቢ ሊያስጠጉኝ ቀርቶ፣ አሁንማ በበሩ ለማለፍም ሳይከለክሉኝ አይቀሩም፡፡
አንድዬ፡— ቆይ አትጣደፋ!  ረጋ ብለህ አስረዳኝ፡፡ እነማን ናቸው እነሱ የምትላቸው?
ምስኪን ሀበሻ፡— እነማን ልበልህ አንድዬ? እነ እከሌ እንዳልልህ አኔም እኮ እነማን እንደሆኑ ግራ ግብት ነው ያለኝ፡፡
አንድዬ፡— ዛሬስ፣ እንደው ዘለፍከኝ አትበለኝና የሰለለው ድምጽህ ብቻ ሳይሆን አእምሮህም ነው፡፡ እነማን መሆናቸውን ሳታውቅ ነው እንዲህ አደረጉኝ፣ እንደዛ በደሉኝ፣ በበር አላሳልፍ አሉኝ የምትለኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን መሰለህ አንድ  ጊዜ አንድ ነገር ይሆናሉ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሆነ ነገር ይገለባበጡና ተቃራኒውን ይሆናሉ፡፡
አንድዬ፡— ምስኪን ሀበሻ፤ እኔ ላይ ቅኔህን መለማመዱን ተወውና ልትል የፈለግኸውን ነገር በሚገባኝ ቋንቋ አስረዳኝ።
ምስኪን ሀበሻ፡— ምን መሰለህ አንድዬ፣ ዛሬ ላይ በየመድረኩና በየቴሌዥኑ በሚናገሩት ነገር፣ በሚያሰሟቸው መልካም ቃላት እናመስግናቸዋለን፡፡ አንድ ሳምንት ሳይሞላቸው በዛው መድረክና በዛው ቴሌቪዥን ጣቢያ ይመጡና ይህኛውን ወገን መዛለፍ፣ ያኛውን ወገን ማንቋሸሽ፣ ከስንት ዘመን በፊት በሰላም አርፈው ለዘለዓለም ህይወት አንተ ዘመድ የመጡትን እናቶችና አባቶች ክብር ማሳጣት ዋና ሥራቸው ይሆናል፡፡ ትንሽ ቆይቶ እንደገና ይለወጡና ጠዋት እንደ ሃይማኖት አባት ያደርጋቸውና፣ ከሰዓት በኋላ ደግሞ ራሳቸው የፈጣሪን ቦታ ይዘው ቁጭ ይላሉ፡፡ አንድዬ፣ አንዴት ግራ እንዳጋቡን ልነግርህ አልችልም፡፡
አንድዬ፡— እና ይህን ሁሉ ከሚያደርጉት ጋር ቀላቅለኝ ነው የምትለኝ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አይደለም አንድዬ፣ አይደለም፡፡ ሩቅ ሆኜ እጄን አጣጥፌ ቁጭ ብዬ ምኑንም ምናምኑንም እየወረወሩብኝ መከራ ከሚያበሉኝ፣ አጠገባቸው ብሆን የሚሠሩትን ስለማይ ይተዉኛል፡፡
አንድዬ፡— መጀመሪያ ነገር ለምን ብለው ነው ምኑንም ምናምኑንም የሚወረውሩብህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኑን አውቄው፣ አንድዬ፡፡ ዘንድሮ እኮ በእኛይቱ ሀገር ማንም ሆንክ ማንም ከየት አቅጣጫ እንደሆነ ሳታውቀው ወይ ስድቡን፣ ወይ እርግማኑን፣ ወይ ማስፈራሪያውን ይወረውሩብሀል። እርስታቸውን አልገፋህ፣ ሚስታቸውን አላባበልክ፣ ወይ የቆየ የቤተሰብ ቁርሾ የለህ...የእነሱ ቡድን አባል ስላልሆንክ ብቻ ኳስ ያደርጉሀል፡፡
አንድዬ፡— ጥሩ፣ አሁን ያልገባኝ ነገር አንተ ስልጣኑን የምትፈልገው እንደ እነሱ ሌላው ላይ ቂምህን ልትወጣ ነው ወይስ አነሱን ራሳቸውን ልትበቀል?
ምስኪን ሀበሻ፡— በጭራሽ አንድዬ፣ ሁለቱንም አይደለም፡፡
አንድዬ፡— እንደሱ ካልሆነ አንደኛውን ከእነኚህ አይነቶቹ መራቁ አይሻልም?
ምስኪን ሀበሻ፡— ማን እሺ ቢል አንድዬ! በቃ ተገላገልኳቸው፣ ከአጠገባቸው ጠፋሁላቸው፣ አገሩ  ይስፋቸው ስትል፣ በየት በኩል እንደመጡ ሳታውቀው ሲገዘግዙህ ታገኛቸዋለህ፡፡
አንድዬ፡— አንተ የእኔ ጀግና ደግሞ ስልጣን ከያዝክ በኋላ ልክ ልታገባቸው ነዋ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደሱ ሳይሆን፣ አጠገባቸው ሆኜ ሁሉንም አንቅስቃሴያቸውን ስለማይ እንዳሻቸው ሊጫወቱብኝ አይችሉም፡፡
አንድዬ፡—  ስልጣን ከያዝክ በኋላ፣ አንተም እንደ እነሱ ብትሆንስ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እንደ እሱማ በምንም አይነት አይሞከርም፡፡ እኔ በምንም አይነት  እንደ እነሱማ አልሆነም፡፡
አንድዬ፡— ለካስ ስትታዘብን ኖረሀል አትበለኝና ብዙዎቻችሁ አኮ ከበላዮቻችሁ ያሉትን ስትረግሙ ትቆዩና ስልጣኑን ስታገኙ እንደውም ይብስባችኋል፡፡ ምንድን ነበረች፣ አንድ የምትደጋግሟት አባባል አለች... ዙሩን ታከሩታላችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— በእርግጥ አንዳንዶች አሉ...
አንድዬ፡— አንዳንዶች ሳትሆኑ፣ ብዙዎቻችሁ፡፡ አሁን አንተ የምትፈልገው የትኛው ቦታ ለመግባት ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— እዚህ ትልቀኛው ቦታ...አንድዬ፣ እንደምንም ብለህ አንድ ጊዜ እግሬ እንዲገባ አድርግልኝ፡፡  
አንድዬ፡— ስንት ቦታ አለልህ አይደል እንዴ! እሱ ላይ ምነው ዓይንህን ጣልክ?
ምስኪን ሀበሻ፡— እንደ ልቤ መናገር ስለምፈልግ፡፡ ህዝብ በቴሌቪዥን እያየኝ ሳልሳቀቅ፣ የሚቆጣኝ አለ ሳልል እንደ ልቤ ለመናገር፡፡
አንድዬ፡— መታየቱን ነው የፈለግኸው መናገሩን?
ምስኪን ሀበሻ፡— ሁለቱንም አንድዬ...ሁለቱንም እፈልጋለሁ፡፡ ዘለዓለም የበይ ተመልካች መሆን ሰለቸኝ፡፡
አንድዬ፡— ታዲያ እኔን ከማነካካት ራስህን ችለህ አትገባም?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ...ራስህን ችለህ ግባ አልከኝ! ስንት ነገር  አለ መሰለህ... ሁሉም ራሱን ቢችልማ ጥሩ ነበር፡፡
አንድዬ፡— ስማኝ፣ ምስኪኑ ሀበሻ... ለአሁኑ እንደ ምንም ብለህ በራስሀ መንገድ ግባና የመጣልህን እንደ ልብህ ተናገር፡፡ ሌላ ጊዜ ግን የመጣልህን እንደ ልብህ መናገር ሳይሆን አስበህና መዝነህ መናገር ስትጀምር፣ ያኔ አግዝህ አንደሆነ እናያለን፡፡ በል ደህና ሁን፡፡ ሰላም ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 933 times