Saturday, 03 April 2021 18:32

“አድዋ” ሽልማት ሀሙስ ተካሄደ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በጃንተከል መልቲ ሚዲያና ኤቨንት አዘጋጅነት በየአመቱ ሊካሄድ የታቀደው አድዋ ሽልማት ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ለአድዋ ድል ታሪክ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱትን በመሸለም ተከናውኗል። የዘንድሮው ሽልማት እንደ መጀመሪያ ዙር አዋርድ፣ ሜዳሊያና የምስክር ወረቀት በመስጠት እስከ ዛሬ አድዋ እንዲዘከር፣ ከፍ እንዲልና እንዲጎላ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉትን በማመስገን ተጠናቅቋል።
ሀሙስ ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል በተካሄደው የምስጋና ስነ-ስርዓት ላይ ከተመሰገኑትና ሽልማት ከተበረከተላቸው ውስጥ ሎሬት  ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ፕ/ር ሀይሌ ገሪማ፣ መራሄ ተውኔት አባተ መኩሪያ፣ አርቲስት ዓለም ፀሐይ ወዳጆ፣ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ አርቲስት እጅጋየው፣ ሽባባው (ጂጂ) ወጣት ሜላት ዳዊትና ሌሎችም ይገኙበታል።
እንደ ጃንተከል መልቲ ሚዲያ ኤቨንት መስራችና የአድዋ ሽልማት ሀሳብ አፍላቂ አቶ ሰለሞን ገለታ ገለጻ፣ “አድዋ” ሽልማት በአረንጓዴ ምንጣፍ (በቄጤማ ጉዝጓዝ) እንዲደረግ የታሰበው የአያቶቻችንን ታሪክ ለመዘከር ነው ያለ ሲሆን አዳራሹ ከበር ጀምሮ በሚያምር ቄጤማ አሸብርቆ ነበር።
አድዋ ሽልማት በቀጣዩ ዓመት ስለ አድዋ ፊልም የሰሩ፣ በሙዚቃና በተለያየ ሂደት ከፍ ያደረጉ የሚሸለሙበት ሲሆን በቋሚነት የካቲት 25(26) ቀን በየዓመቱ እንደሚደረግ ተገልጿል። ድሉ የአፍሪካዊያን ጭምር በመሆኑ የቱሪዝም ሀብት በማድረግና ከአፍሪካ እንግዶችን በመጋበዝ ጭምር ይከበራል ብሏል ሰለሞን ገለታ።
ሽልማቱ (አዋርዱ) ክብ ጋሻ መሃል ላይ የአፍሪካ ካርታ ከዚያ የፈረጠመ ክንድ፣ መደቡ አናት ላይ ዘውድ ከዚም ዋናው መደቡ ጥቁር ተደርጎ የተሰራ ሲሆን ይህም የአድዋን ሽልማት ከትክክለኛ ታሪኩ ጋር ለማገናኘት የተሞከረበት ነው ሲሉ ስለ ሽልማቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ ለመታደም የአለባበስ ህግ የሚኖር ሲሆን ማንኛውም መደቡ ነጭ የሆነ ባህላዊ ልብስ ብቻ እንደሚለበስ ገልጸው ይሄም የአድዋ ዘማቾችን ትክክለኛ አለባበስ በማንጸባረቅ ተተኪው ትውልድ እንዲማር ይደረጋል ተብሏል።

Read 1059 times