Saturday, 03 April 2021 18:21

ከምርጫው በኋላ የአዲስ አበባ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(13 votes)

  • አዲስ አበባ ላይ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ቢያሸንፉ ስልጣን በቀላሉ ያስረክባሉ የሚል እምነት የለኝም - የፖለቲካ ምሁር
     • ህዝብ መርጦን ስልጣን መረከብ ካልቻልን፣ የሚሆነው ጊዜው ሲደርስ እናያለለን - ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ
    • ኢዜማ አዲስ አበባን የተመለከተ የምርጫ ማኒፌስቶውን ማክሰኞ ይፋ ያደርጋል
      • ምርጫውን ለሚያሸንፍ ፓርቲ ስልጣኑን በሰላም በማስረከብ ታሪክ እንሰራለን - ብልፅግና
                   
            አገሪቱ በተለያዩ የደህንነትና የፀጥታ ስጋቶች ውስጥ ሆና በምታካሂደው የዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ላይ አሸናፊ ሆኖ ለሚመጣ ፓርቲ ብልጽግና ስልጣኑን በቀላሉ ያስረክባል የሚል  እምነት እንደሌላቸውና በተለይም በአዲስ አባባ ከተማ ውስጥ የሚደረገው ምርጫ ውጤት  እንደሚያሳስባቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ምሁራን ተናገሩ፡፡
የምርጫው ውጤት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ ቦታዎች መካከልም አዲስ አበባ ከተማ ቀዳሚዋ እንደሆነች የሚናገሩት የፖለቲካ ምሁሩ፤ ገዢው ፓርቲ በአዲስ አበባ  ልዩ ዞን እያለ በሚጠራቸው የከተማዋ አካባቢዎች እያከናወነ ያለው ተግባር የምርጫውን ውጤት በፀጋ  ለመቀበል የማያስ ችለው እንደሆነ አመልካች ነው ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ ከተማን ወክለው ለሚወዳደሩት ፓርቲዎች ህዝቡ ድምፅ ቢሰጣቸውና በምርጫው ቢያሸንፉ ከተማዋን በሰላማዊ መንገድ ከገዢው ፓርቲ የመረከብ እድሉን ያገኛሉ የሚል እምነት እንደሌላቸውም ነው የፖለቲካ ምሑሩ የገለጹት፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ድምፅ  አግኝተው ምርጫውን የሚያሸንፉ ቢሆንም ከተማዋን ከከበቧት ውስብስብ ችግሮች በማላቀቅ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት ለመኖር የሚችልባት ከተማ ለማድረግ ከሚጠብቃቸው ፈተና የበለጠ የሚፈተኑት ስልጣኑን ከገዢው ፓርቲ ላይ ለመረከብ በሚያደርጉት ትግል ነው ይላሉ - የፖለቲካ ሊቁ።
መድረሻውን አዲስ አበባ ከተማን ብቻ በማድረግ በ6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ የሚወዳደረው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፤ የህዝብ ድምጽ አግኝቶ በምርጫው ቢያሸንፍ ገዥው ፓርቲ ስልጣኑን በቀላሉ አሳልፎ ይሠጣል የሚል እምነት እንደሌላቸውና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣናችንን በሰላም እናስረክባለን በሚለው ቃልም እንደማይዘናጉ የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት አባልና ጋዜጠኛ ወግ ደረስ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው በተረኝነት የሚፈጸመውን በደል፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትና በዜጎች ላይ የሚፈፀመው በደሎችን በመቃወም የተደራጀና ወደ ፓርቲነት የተቀየረ ፓርቲ ነው ያሉት አቶ ወግደረስ ህዝቡ፣ ይዛችሁት የመጣችሁት የፖለቲካ ማኒፌስቶ ያግዘናል፣ ከተማችንን በእኩልነትና በፍትሀዊነት ልታስተዳድሩልን ትችላላችሁ ብሎ ከመረጠንና መንግስት ስልጣኑን ለማስረከብ ፍቃደኛ ካልሆነ  ጊዜው ሲደርስ የምናየው ይሆናል ብለዋል፡፡
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ የከተማዋን ነዋሪ ህዝብ ከመጣበት ተረኛ መንግስት እጅ ፈልቅቆ በማውጣት ሁሉም ዜጋ በእኩልነትና በፍትህ የሚኖርባትና ተጠቃሚ የሚሆንባትን ከተማ ለመመሰረት ይታገላል ያሉት አቶ ወግደረስ አንድ ብሔር ብቻ የከተማዋ ልዩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት አጥብቀን የምንታገል በመሆኑ ህዝቡ በምርጫው እንዲሳተፍና ድምፁን እንዲሰጠን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ኢዜማ በበኩሉ፤ የአዲስ አበባ ከተማን የሚመለከተውን የምርጫ ማኒፌስቶ በመጪው ማክሰኞ ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የህዝብና አለማቀፍ  ግንኙነት ሃላፊው ዶ/ር  ቢቂላ ኡሪሳ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆኑ ህዝቡ በምርጫው ላይ እምነት ሊያሳድር  እንደሚገባው ጠቁመው በምርጫው ብናሸንፍ ስልጣን ልንረከብ አንችልም ከሚል ስጋት ሊላቀቁ ይገባል ብለዋል፡፡
መጪው ምርጫ በአገሪቱ ታሪክ በጣም ትልቅ የዲሞክራሲ ስርዓት መሰረት የሚጣልበት በመሆኑ ማንም ዜጋ አሳንሶ ሊመለከተው አይገባም ያሉት ዶ/ር ቢቂላ፤ ከፓርቲ በላይ የሆኑ አገር፣ህዝብ፣ሰላምና ዲሞክራሲ የተባሉ ነገሮች መኖራቸውን ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መንግስት ምርጫው ነፃ፣ገለልተኛ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የገለጹት ኃላፊው በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ ያሸነፈ ፓርቲ ከተገኘ ለኢትዮጵያ ትንሳኤዋ ነው  ብለዋል፡፡
ያ ሁሉ ዋጋ የተከፈለው አንድን ፓርቲ ወይም ግለሰብ ወደ ስልጣን ለማምጣት አይደለም ያሉት ዶ/ር ቢቂላ መጪው ምርጫ በአገሪቱ  ያልታየ አዲስ  ታሪክ የምንሰራበት እንዲሆን  ነው ብለዋል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገና ምርጫው ሳይካሄድና ማሸነፋቸውን ሳያውቁ ብናሸንፍ ስልጣን አይሰጠንም የሚል ስጋት ማሳደራቸውና ስጋታቸውንም ወደ ህዝቡ ማጋበታቸው ተገቢነት የሌለው ተግባር ነው ያሉት ዶ/ር ቢቂላ፤ ምርጫውን አሸንፈው ይምጡና ቀጣይ ሂደቱን ይመለክቱ ብለዋል። ብልጽግና ፓርቲ እንደማንኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ እኩል የሚወዳደር ሆኖ ሳለ የተለየ ዕድልና ጥቅም እንደሚያገኝ አድርጎ ማሰቡና መናገሩ ተገቢ አይደለም ሲሉም። ተችተዋል ብልጽግና በምርጫው ቢሸነፍ ካሁን አሁን በአገሪቱ ባልተለመደ ሁኔታ በልዩ ስነ ስርዓት ስልጣኑን ላሸነፈው ፓርቲ እንደሚያስረክብ ላረጋግጥ እፈልጋለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ህዝቡም ከስጋት ነፃ ሆኖ በምርጫው ለመሳተፍና የምርጫ ካርድ ወስዶ የሚፈልገውን ፓርቲ ለመምረጥ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል ሲሉም አክለዋል- ዶ/ር ቢቂላ፡፡

Read 11134 times