Print this page
Saturday, 03 April 2021 18:18

“ጠ/ሚኒስትሩ ቢሸነፉ እንደ ቃላችው ስልጣን ያስረክባሉ ብዬ አላምንም

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

  መጪው ምርጫ ካለፉት የተሻለ ባይሆንም የባሰ ግን አይሆንም  አቶ ክቡር ገና
                       
            ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመጪው አገራዊ ምርጫ ቢሸነፉ እንደ ቃላቸው ስልጣናቸውን በሰላማዊ መንገድ ያስረክባሉ የሚል እምነት  እንደሌላቸው አቶ ክቡር ገና ተናገሩ፡፡ መንግስት መጪው ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ ኃላፊነቱን በአግባቡ   ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል፡፡
በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ኢዜማን ወክለው የሚወዳደሩት ታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያና የፓን አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ክቡር ገና ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት የአገሪቱን መፃኢ ዕድል ለመወሰንና ሁኔታዎችን ለመለወጥ ከዳር ሆኖ መመልከቱ ትርጉም የሚሠጥ ሆኖ ባለማግኘታቸውና  ከውስጥ ገብተው ሁኔታዎችን ሊለውጡ የሚችሉበትን ነገር ለማድረግ በማሰብ ወደ ምርጫው መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
“ምርጫ ችግር ፈቺ ነው ብዬ አላምንም” የሚሉት አቶ ክቡር ገና፤ ችግሮቹ ከምርጫው ማግስት ጀምሮ የሚቀጥሉ በዓመት በሁለት ዓመት የማይፈቱና እንደውም አብዛኛዎቹ እየባሰባቸው የሚሄዱ ናቸው” ብለዋል፡፡ መጪው አገራዊ ምርጫ ከቀደሙት ይለያል ማለቱ አስቸጋሪ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ክቡር፤  ምርጫው ከቀደሙት የተሻለ ይሆናል ለማለት ባያስደፍርም የባሰ ይሆናል የሚል እምነት እንዳሌላቸው ግን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ያለው ዕድል ይሄው በመሆኑና በዚህ ውስጥ ተወዳድሮ ማለፍ የግድ ስለሚል ወደ ምርጫው መምጣታቸውንም ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተደጋጋሚ የሚናገሩትና ምርጫውን ብንሸነፍ በደስታ ስልጣናችንን ለአሸናፊው ወገን አናስረክባለን የሚለው ቃላቸውን እንደማያምኑበትና ይህ ሁኔታም ይፈፀማል ብለው እንደማይጠብቁ አቶ ክቡር ገና ተናግረዋል፡፡ “እንዲህ አይነቱ ቃል ከፖለቲካ ትርፍና ህዝቡን ለመሸንገል ካልሆነ ተቀባይነት ያለው ነው ብዬ አላምንም” ያሉት አቶ ክቡር፤ “ጠ/ሚኒስትሩ የፖለቲካ መሪ ሆነው፣ ለዳግማዊ ስልጣን እየተወዳደሩ ብንሸነፍ ስልጣን እናስረክባን” ማለታቸው አሳማኝ ነው ብዬ አላምንም ብለዋል፡፡

Read 11140 times