Saturday, 03 April 2021 18:16

ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ዛሬ ድርድር ይጀምራሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብፅ አዲስ ድርድር ዛሬ ይጀምራሉ።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚካሄደው ይኸው የሶስትዮሽ ድርድር፤ ኢትዮጵያ እየገነባች ባለው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የውሃ አሞላል ቀጣይ ሂደት ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በትዊተር ገፃቸው ከላይ ያሰፈሩት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ዛሬ የሚጀመረውና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገውን የሶስትዮሽ ድርድር በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት የሊቀ መንበርነት ቦታን ከደቡብ አፍሪካ የተረከበችው የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ትመራዋለች። ለሶስቱ ተደራዳሪ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮችና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሮች ግብዣ መደረጉንም ዶ/ር ስለሺ ገልፀዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች፣ የሶስቱ ተደራዳሪ አገራት ባለሙያዎችና ታዛቢዎች በድርድሩ ላይ እንደሚገኙም ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቱን ጉልህ ጉዳት ሳያስከትል፣ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመጠቀምና ምክንያታዊ በሆነው የተፋሰሱ አጠቃቀም ላይ ያላት አቋም ቁርጠኛ ነው ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ ፅፈዋል፡፡


Read 10248 times