Print this page
Saturday, 27 March 2021 14:09

ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ዝሆኖቹን ይፋለማሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  የኢትዮጵያ  ብሄራዊ ቡድን ከስድስት ወራት  በኋላ  ካሜሮን  የምታስተናግደውን 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ አንድ ጨዋታ ቀርቶታል፡፡ ዋልያዎቹ ከትናንት በስቲያ  በ5ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታቸው ማዳጋስካርን 4ለ0 ካሸነፉ በኋላ የማለፍ እድላቸውን አስፍተዋል፡፡ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ላይ ለኢትዮጵያ  አራቱን ግቦች ያስቆጠሩት በመጀመሪያው የጨዋታ ጊዜ አማኑዔል ገብረሚካዔል፣ ጌታነህ ከበደና አቡበከር ናስር እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ  ላይ ሽመልስ በቀለ ናቸው፡፡ ከውጤቱ በኋላ በምድብ አስራ አንድ ከአይቬሪኮስት፤ ከማዳጋስካርና፤ ከኒጀር ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአምስት ጨዋታዎች 9 ነጥብንና 5 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ መሪነቱን ይዟል፡፡   ሰባት ነጥብ ይዛ ምድቡን እየመራች የቆየችው አይቬሪኮስት ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ በ5ኛው ዙር የምድብ ማጣርያ ኒጀርን በቶጎዋ ከተማ ሎሜ ላይ  ትናንት ገጥማለች፡፡ ከምድቡ ወደ የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፈውን ለመወሰን 6ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች ወሳኝ ይሆናሉ።  በመጨረሻው የምድብ ማጣርያ ጨዋታ አይቬሪኮስት ከኢትዮጵያ እንዲሁም ኒጀር ከማዳጋስካር ጋር የሚገናኙ ይሆናል፡፡
ዋልያዎቹ ከ5ኛ ዙር የምድብ ማጣርያ  ጨዋታቸው  በፊት  በኢንስትራክተር አብረሃም መብራቱ  እየተመሩ በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ በማዳጋስካር ከሜዳቸው ውጪ 1ለ0 ሲሸነፉ በሁለተኛው የምድብ ማጣርያ ደግሞ ባህርዳር ላይ አይቬሪኮስትን 2ለ1 አሸንፈዋል፡፡ በ3ኛው የምድብ ማጣርያ ጨዋታ በአዲሱ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በመመራት ከሜዳቸው ውጪ በኒጀር 1ለ0 የተረቱ ሲሆን በ4ኛው የምድቡ ማጣርያ ኒጀርን 3ለ0 አሸንፈዋል፡፡ ዋልያዎቹ በምድባቸው ካደረጓቸው ጨዋታዎች 3ቱን በሜዳቸው ላይ ማሸነፋቸው ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ የሚችሉበትን ተስፋ አጠናክሮታል፡፡
በምድቡ የመጨረሻ ዙር ማጣርያ ጨዋታዎች ዝሆኖቹ  በአቢጃን ከተማ በሚገኘው ስታዴ ኦሎምፒኩዌ አላሳኔ ካውቶራ ላይ ዋልያዎቹን ሲያስተናግዱ ማዳጋስካር ደግሞ በቶማሲና በሚገኘው የባርኪዲሚ ስታድዬም ኒጀርን ይገጥማሉ፡፡ዝሆኖቹ ከዋልያዎቹ  የሚያደርጉት ጨዋታ ከምድቡ የሚያልፈውን የሚወስን ሲሆን ኢትዮጵያ  አቻ ውጤት ካስመዘገበችም በሁለተኛ ደረጃ ለማለፍ ከኒጀርና ከማዳጋስካር የተሻለ እድል ይኖራታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በታሪክ ለ11ኛ ጊዜ አፍሪካ ዋንጫን ለመሳተፍ ሲያነጣጥር  አይቬሪኮስት ደግሞ 24ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ለማሳካት ነው፡፡ ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ለመጨረሻ ጊዜ ያለፉት ከስምንት ዓመታት በፊት ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እንደሆነ ይታወሳል፡፡
የአይቬሪኮስት ብሄራዊ ቡድን በ2020 እኤአ ላይ ያደረጋቸውን 4 ጨዋታዎች ያሸነፈ ቢሆንም 2021 ከገባ በኋላ ድል ሊቀናው አልቻለም፡፡ በምድቡ 4ኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታ በሜዳቸው ከማዳጋስካር 1ለ1  የተለያዩ ሲሆን በሜዳቸው ተሸንፈው አያውቁም፡፡ ዝሆኖቹ አቢጃን ላይ ባደረጓቸው ያለፉት 12 ጨዋታዎች ሽንፈት የገጠማቸው አንዴ ነው፡፡  ፈረንሳዊው የአይቬሪኮስት አሰልጣኝ ፓትሪስ ቢዩሜሌ ትናንት ከኒጀር ጋር እንዲሁም በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር ለሚያደርጓቸው የመጨረሻ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች   የ18 ዓመቱን አማድ ዲያሎ እንደጠሩ ተዘግቧል፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት የወርቅ ኳስ ማሸነፉ አይቀርም የተባለው አማዱ በ2021 መግቢያ ለማንችስተር ዩናይትድ በ37 ሚሊዮን ዶላር የፈረመ ነው፡፡ አሰልጣኙ የአጥቂ መስመራቸውን ለማጠናከር በፓርማ የሚገኘውን ጀርቪንሆ በቅድሚያ ጠርተው ነበር፡፡ ይሁንና የ33 ዓመቱን ጀርቪንሆ በጉዳት ሳቢያ  ለሁለቱ ጨዋታዎችም ሊደርስላቸው አልቻለም፡፡
ለ33ኛው የአፍሪካ ከተካሄዱት 5 ዙር የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በኋላ  ከሚሳተፉት 24 አገራት 13 ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። እነሱም አዘጋጇ ካሜሮን፤ ቱኒዚያ፤ ማሊ፤ ጊኒ፤ ቡርኪናፋሶ ዚምባቡዌ  ኢኳቶርያል ጊኒ፤ አልጄርያ፤ ጋና፤ ግብጽ፤ ኮሞሮስ እና ጋምቢያ ናቸው፡፡ ኮሞሮስ እና ጋምቢያ ወደ የአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡


Read 1038 times