Tuesday, 30 March 2021 00:00

የመቀሌዋ የግቢያችን የጦርነቱ ቃል አቀባይ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (brooha3212@gmail.com)
Rate this item
(9 votes)

           ክፍል 8፡ «ቤቢዬ ልንሞት ነው፤ በደንብ ልቀፍህ»
             
           በክፍል-7 ፅሁፌ ‹‹የባጫ ደበሌ መማረክ በመቀሌ ከተማ እንደተወራና ወሬውም የከተማዋን ህይወት እንዳለመለመው›› ነግሬያችሁ ነበረ ያቆምኩት፡፡
መቀሌ በእንደዚህ ዓይነት የደስታ ስካር ላይ እያለች ትንሽ ቆይቶ ከየትኛው ወገን እንደሆነ ያላወቅነው መድፍ መተኮስ ተጀመረ፤ «አይዟችሁ የደስደስ ነው» በማለት እማማ ፃድቃን አፅናኑን። የተኩሱን መጠንከር ስንሰማ ግን ነገሩ የደስደስ ሳይሆን የጦርነት መሆኑ ገባን፡፡ መድፉ ጭራሽ በላያችን ላይ እያለፈ ሲወድቅ ይሰማን ጀመር። በከተማዋ ፍርሃት ዳግም ነገሰ፡፡ ‹‹አሁን እንኳ አንተርፍም!!›› ብዬ ለራሴ ደመደምኩ፡፡ ለብሄራዊ በዓላት ጊዜ የሚተኮሰውን መድፍ ካልሆነ በስተቀር በህይወቴ እንደዚህ ዓይነት የመድፍ ድምፅ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ድምፁ እጅግ አስፈራኝ፤ ውስጤ ታወከ፤ ምግብ ርቦኝ እንኳ መብላት ተሳነኝ፤ ተኝቼ እንቅልፍ አይወስደኝም፤ በውስጤ ያለው ፍርሃት ሰውነቴን እንኳ ተሸክሜ መቀመጥ አቃተኝ። እናም ልጄን እቅፍ አድርጌው ተኛሁና «ቤቢዬ ልንሞት ነው፤ በደንብ ልቀፍህ» አልኩት። ልጄ ገና የ2 ዓመት ከ4 ወር ልጅ ስለሆነ «ሞት» ምን እንደሆነ አያውቅም። ብቻ የመድፍ ድምፅ ሲሰማ ጉያዬ ውስጥ ይገባል። ስንተኛው መድፍ እላያችን ላይ እንደሚወድቅ ነው ያላወቅሁት እንጂ እንደምንሞት ግን ደምድሜያለሁ። ከሞቴ ጋር ለህትመት ያዘጋጀኋቸው መፃህፍትም ለትውልዱ ሳይደርሱ መና እንደሚቀሩ ሳስብ ሀዘኔ በረታ፡፡
‹‹ለመሆኑ እንዴት በእንደዚህ ዓይነት አስፈሪ ሁኔታና ቦታ ላይ ልገኝ ቻልኩ?›› በማለት ነገሮችን ወደ ኋላ ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡ ከከተማ ሸሽቼ አለመውጣቴን እንደ ትልቅ ስህተት ቆጠርኩት። አንድ ቀን ወደ አዲሳባ እመለሳለሁ እያልኩ ለመወሰን ሳመነታ፣ ይሄው ጦርነት መሃል ተገኘሁ። ዛሬ ሳንሞት ካደርን ነገ በጠዋት ወደ ገጠር ለመሸሽ ከቤቢ እናት ጋር እያወራሁ ሳለ፣ ዋልታ ቴሌቪዥን በማታው የአንድ ሰዓቱ ዜና ላይ፤ «ሰበር ዜና - መከላከያ ሰራዊታችን መቀሌ መግባቱን ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ ገለፁ» ሲል ሰማሁ፡፡ ጆሮዬን ማመን አቃተኝ፤ ሰበሩ ዜና ተደገመ። ወደ ትግራይ ቴሌቪዥን ስቀይረው፤ «በዳንሻ በኩል ሠራዊታችን የጠላትን ኃይል እየደመሰሰው ይገኛል» ይላል። «እናንተ አሁንም አታምኑም» ብዬ እየቀያየርኩ ሰበር ዜናዬን ማጣጣም ጀመርኩ።
የመከላከያ ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ፣ ከምሽቱ 01፡00 ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ «መቀሌን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረናል፤ የጦርነቱ 3ኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ በድል ተጠናቋል፤ ጦርነቱም ቆሟል። ከዚህ በኋላ የሚቀረው የለቀማ ስራ ብቻ ነው፤ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ፤ መላው የትግራይ ህዝብም እንኳን ነፃ ወጣችሁ» አሉ። ፍርሃቴ ከውስጤ ለቆኝ ሲሄድ ተሰማኝ፤ ከሞት ተነሳሁ። ከ30 ደቂቃ በፊት በመድፍ ድምፅ ሲታረስ የነበረው የመቀሌ ሰማይ፣ በአንድ ጊዜ ፀጥ አለ። ህዝቡ የግቢውንና የመኖሪያ ቤቱን በር ቆልፎ፣ በፍርሃት ቤቱ ውስጥ እንደተቀመጠ ነው።
ሌሊት 06:00 በመቀሌ ሰማይ ላይ የትንሽ አውሮፕላን ድምፅ ተሰማ። «እውነትም ተቆጣጥረውታል» አልኩኝ። በነጋታው ጠዋት (ህዳር 20 ቀን 2013) በ11:00 ጎረቤታችን የሆኑት ተሾመና ገሬ (ሚስቱንና ልጁን ይዞ) በተለያየ አቅጣጫ ከተማውን ለቀው፣ ወደ ገጠር መሄዳቸውን ሰማን። ወደ ስራ ባልደረቦቼ ስደውል ደግሞ ተስፍሽና ጓደኞቹ ሌሊት በእግራቸው ወደ ተንቤን (ኣብይ ኣዲ) መሄዳቸውን ሰማሁ። ወደ ገጠር የሄዱበት ምክንያት ደግሞ ‹‹መከላከያ መቀሌ ከገባ ህዝቡን ይገድላል›› የሚለውን የህወሓት ፕሮፓጋንዳ ስላመኑ ነበር፤ የተማረውም ሆነ ያልተማረው ሰው ሁሉ ይሄንን የህወሓት ፕሮፓጋንዳ አምኖ ተቀብሏል፤ በዚህም የተነሳ የመከላከያ ሰራዊት ወደ መቀሌ መግባት ህዝቡ ውስጥ ትልቅ ፍርሃት ፈጠረ። ለአብዛኛዎቹ የህወሓት አባላት ብቻ ሳይሆን ለደጋፊዎቹ ጭምር ‹‹ህወሓት የእውቀት፣ የእውነትና የመረጃ ምንጫቸው ነው፤ ዶ/ር ደብረፅዮን ደግሞ ከመድሃኒያለም ቀጥለው የሚያዩት ሰው ነው››፡፡ በዚህም የተነሳ ህወሓት የሚለውን ነገር ያለምንም ጥርጣሬና ማጣራት እውነት ነው ብለው ይወስዱታል። ይሄም ነገር አንዳንድ የህወሓት አባላት ድርጅታቸውን ወደ ማምለክ ደረጃ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል፤ ‹‹ህወሓት በዓለም ታሪክ ውስጥ ከታዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ በጣም ምርጥ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ነው›› እያሉ የሚመፃደቁ ሰዎችም አጋጥመውኛል፡፡
ብዙ ጊዜ የመሐል ሀገር ሰው ‹‹የትግራይ ህዝብ በህወሓት ታፍኗል፤ ተበድሏል፤ ተጨቁኗል›› ሲሉ እሰማለሁ፡፡ እውነት ነው፤ በትግራይ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አየር ውስጥ ነፃነትና አማራጭ የሚባሉ ነገሮች የሉም፤ ሁሉም ነገር በህወሓት ቁጥጥር ውስጥ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን፣ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ "በህወሓት ታፍኛለሁ፣ ተበድያለሁ፣ አማራጭ አጥቻለሁ፣ ነፃነቴንም ተገፍፌያለሁ" በማለት አያማርርም፡፡ ከዚያ ይልቅ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ህወሓትን እንደ "እውነተኛ፣ ሀቀኛ፣ ሰብዓዊነት የሚሰማው፣ የማያዳላ፣ ትግራይን በመርሳት ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕድገት መስዋዕትነት የከፈለ፣ ሁልጊዜ አሸናፊ፣ መቼም ቢሆን ምትክ የማይገኝለትና ዘላለማዊ መሪ ድርጅታቸው" አድርጎ ነው የሚያየው። በአጭሩ፣ ‹‹የፖለቲካ ቅዱስነት››ን ይሰጡታል። በዚህም የተነሳ አብዛኛው ህዝብ ከድርጅቱ ጋር ያለው የሥነ ልቦና ትስስር በጣም ጠንካራ ነው፡፡
እንግዲህ በልባቸው ውስጥ ይሄንን ያህል የፍፁምነት ቦታ የያዘው ድርጅት ነው፣ ህዳር 19 ቀን 2013 በይፋ መሸነፉ የታወጀው፡፡ እናም ‹‹በቅዱሱ›› ህወሓት መሸነፍ እነዚህ ደጋፊዎቹ እንዴት በስሜትና በስነ ልቦና እንደሚሰበሩ አስቡት፡፡ ከህዳር 20 ቀን 2013 ጀምሮ በመቀሌ የሆነው ይሄ ነው፤ ሀዘን፣ ቁጭት፣ ብስጭት፣ ስብራት!! ብዙዎቹም ‹‹ህወሓት ተሸነፈ›› የሚለውን ነገር እስከ አሁን ድረስ አምኖ ለመቀበል ተቸግረዋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ‹‹ህወሓት ተመልሶ ይመጣል›› የሚለውን የዳግም ትንሳኤ ተስፋ መጠበቅን መርጠዋል፡፡
በተቃራኒው ህዳር 20 ቀን 2013 በህወሓት መሸነፍ አብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደስታ በደስታ ሆኑ። የመንግስት ባለሥልጣናትና የሁሉም ክልል መሪዎች፣ የእንኳን ደስ አለን/አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ። በአማራ ክልል ብዙ ከተሞች ላይ የደስታ ሰልፎች ተደረጉ። የአማራ ማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸው የአላማጣና የወልቃይት ነዋሪዎች ደስታ ግን ከሁሉም የላቀ ሆኖ ታይቷል፡፡
ጦርነቱ አለቀ ብለን የሰላም አየር መተንፈስ ስንጀምር፣ ህዳር 22 ቀን 2013 ሌላ የጦርነት አደጋ እያንዣበበብን እንደሆነ አወቅን፡፡ ይኸውም ከህዳር 22 – 24 ቀን 2013 በመቀሌ ዙሪያ ለተከታታይ ሦስት ቀናት፣ ቀኑን ሙሉ የመድፍ ተኩስ መሰማቱ ነው። ተኩሱ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በየ15 ሰከንዱ ይደረግ ነበር። በጨረቃ ብርሃን እየታገዙ፣ እስከ ሌሊቱ 08:00 ድረስ መድፍና ከባድ መሳሪያዎች ሲተኮሱ ያደረበት ቀንም ነበረ። ይሄ የማያቋርጥ የተኩስ ድምፅ ለአብዛኛው የመቀሌ ህዝብ አስፈሪ ቢሆንም፣ ለቃል አቀባያችን ግን መልካም ዜና ሆነላት፡፡  
ቃል አቀባያችን የመከላከያ መቀሌ መግባት ትንግርት ሆኖባታል፤ ‹‹መከላከያ መቀሌ የገባው ተዋግቶ ሳይሆን በሄሊኮፕተር ነው፡፡ ህወሓት ደግሞ ይሄንን ያደረገችው (መከላከያ መቀሌ እንዲገባ መንገዱን ክፍት ያደረገችለት) ወደ መቀሌ የሚያስገቡትን ሁሉንም ድልድዮች በመስበር መቀሌ ያለውን መከላከያ ከኋላ በመቁረጥ ልትፈጀው ስላሰበች ነው፤ ይሄ አሁን የምትሰሙት የመድፍ ድምፅም ህወሓት መከላከያን እየጠራረገች ወደ መቀሌ ስትመጣ ነው፡፡›› አለችን፡፡ ቃል አቀባያችን ከፍርሃት ውስጥ ዜናን መስራት ትችላለች፡፡ ገና ምንነታቸው ያልታወቁ ኩነቶችን፣ ለእሷ የድል ዜና አስረጂ አድርጋ ማቅረብ ትችልበታለች፡፡
ምንም እንኳ ቃል አቀባያችን ራሷ በምትፈጥረው የድል ዜና፣ ራሷን ብታፅናናም፣ ሰሞኑን እየሰማን ባለነው የመድፍ ድምፅ ግን አብዛኛው የመቀሌ ህዝብ ከባድ ፍርሃት ላይ ወድቋል፤ ፍርሃቱንም ከግቢ ውጭ ተሰባስቦ በመቀመጥ አሳይቷል።
ከፀጥታ ስጋት ጋር በተገናኘ የመቀሌ ህዝብ አንድ ልማድ አለው፡፡ ይሄውም የፀጥታ ስጋት ከርቀት እየመጣ እንደሆነ ሲሰማ፣ ሰው ሁሉ ከግቢ በመውጣት ተሰባስቦ በየዕድሜውና በየፆታው እየተከፋፈለ ይቀመጣል፤ (ወጣት ወንዶች ለብቻ፣ አዛውንቶቹ ጋቢያቸውን ለብሰው ለብቻ፣ ሴቶች (ወጣቶችና እናቶች በአንድ ላይ) ተቀምጠው ያወራሉ። ስጋቱ ቅርብ ሲሆን ደግሞ ሁሉም ሰው በሩን ቆልፎ በየቤቱ ይቀመጣል።
ህዳር 21 ቀን 2013 ጠ/ሚ ዐቢይ፣ ከህወሓት ጋር ስለተደረገው ጦርነት ለፓርላማው ገለፃ አደረጉ። በንግግራቸውም ጦርነቱ ላይ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ለቅኝት መጠቀማቸውን፣ በዚህ ቴክኖሎጂ በመታገዝም የህወሓት አመራሮች በሀገረ ሰላምና በአብይ አዲ መካከል መደበቃቸውንና ትናንት ምሽት ሲንቀሳቀሱ በእነዚህ ከተሞች የነበረውን ትርምስ እንዳዩት፣ ነገር ግን  ለሰላማዊ ሰዎች ተብሎ ተኩስ እንዳልተከፈተ ተናገሩ። ሆኖም ግን፣ ይሄ ሁኔታ እንደማይቀጥልና ህዝብ ከማለቁ በፊት እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ ጠየቁ።
ህዳር 21 ቀን 2013 በመላው መቀሌ ከተማ መብራት ጠፋ፡፡ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታትም ያለ መብራት በጨለማ ውስጥ አሳለፍን፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረበት ቀን ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ጀምሮ በመላው ትግራይ የኢንተርኔትና የባንክ አገልግሎት እንደተቋረጠ ነው፡፡ አሁን ደግሞ መብራት ተጨመረበት፡፡
ህዳር 23 ቀን 2013 በመቀሌ ዙሪያ ሲደረግ በነበረው ከባድ ጦርነት የተነሳ መከላከያ ከመቀሌ ከተማ እንዲወጣ ተደረገ። በነጋታውም የህወሓት ሚሊሺያዎች ከየተደበቁበት እየወጡ መቀሌን በጥይት እሩምታ ያናውጧት ጀመር። አይደር ሆስፒታል አካባቢ አንድ ጊዜ ‹‹መከላከያ ሌላ ጊዜ ደግሞ የሻቢያ ወታደሮች አይደር ሆስፒታልን ሊዘርፉ ነው›› የሚል ወሬ ስለተናፈሰ፣ የአካባቢው ወጣቶች መንገዱን በድንጋይ ዘጉት፣ ጎማም አቃጠሉ፡፡ የወጣቶቹ ቀጣይ እርምጃ ምን ይሆን ብዬ ለራሴ ፈራሁ፡፡ ጎረቤቶቼ ግን ‹‹አይ፣ ወጣቶቹ ሆስፒታሉን ከመጠበቅ የዘለለ ነገር አያደርጉም›› ብለው አረጋጉኝ፡፡
‹‹መከላከያ ሰራዊት አይደር ሆስፒታልን ሊዘርፉ ነው›› የሚለው ወሬ ላይ ግን ትንሽ ተብሰለሰልኩ፡፡ ይሄንን ወሬ እውነት ነው ብዬ ባስብ እንኳ ለሚከተሉት ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ ማግኘት አልቻልኩም፤
መከላከያ ሰራዊት ሆስፒታሉን የሚዘርፈው በማን ትዕዛዝ ነው? በመከላከያ ሚኒስቴር? ወይስ ሰራዊቱ በራሱ ፈቃድ? መከላከያ ሚኒስቴር ይሄንን ትዕዛዝ የሚሰጠው፣ በስሩ ለሚያስተዳድራቸው ሆስፒታሎች የቁሳቁስ እጥረት አጋጥሞት ይሆን? ይሄ የማይመስል ነገር ሆነብኝ፡፡ በሌላ በኩል፤ ሰራዊቱ በራሱ ፈቃድ ወደ ዘረፋ ገብቶ ይሆን? ብዬ አስብኩ፡፡ ሆኖም ግን፣ ሰራዊቱ ሆስፒታሉን ዘርፎ የሰረቀውን ዕቃ የት ያስቀምጠዋል? መቀሌ ላይ ቤትና ቤተሰብ የለውም፤ ወደ ገበያ ወስዶ እንዳይሸጠው ደግሞ ገና መቀሌ መግባቱ ነው፤ ከተማዋን ገና በቅጡ እንኳ አያውቃትም፡፡ በስተመጨረሻም፣ ‹‹መከላከያ ሰራዊት አይደር ሆስፒታልን ሊዘርፉ ነው›› የሚለውን ወሬ ውድቅ አደረኩት፡፡ ቆይቶም የተረጋገጠው ነገር፣ በአይደር ሆስፒታል ምንም የተሰረቀ ዕቃ አለመኖሩን ነው።
(ይቀጥላል….)


Read 7354 times