Print this page
Tuesday, 30 March 2021 00:00

በሕዝብ ላይ እያሤሩ፣ በብሔር ማንነት የመደበቅ ስልት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ለ27 ዓመታት ያህል ገዢ ኃይል ሆኖ አገሪቷን በተለያየ  መንገድ ጠፍኖ ይዞ የነበረው ህውሐት/ኢህአዴግ፣ እስከ ቅርብ ወራት ድረስ፣ “የትግራይ ክልልን በሕግና በስልጣን የምወክል ፓርቲ ነኝ፤” ይል ነበር። አሁን በተግባር እንደታየውም ፍጻሜያቸው አላማረም። የትግራይ ሕዝብ በሙሉ በምቾት በተድላ፣ በፍሥሐ ፣ የሚኖር አድርጎ የሚቆጥር የህብረተሰብ ክፍል ቀላል አይደለም። ጀነራል ሳሞራ የኑስን የመሳሰሉ የህወሓት ታጋዮች፤ ለፖለቲካ ትርፋቸው ሲሉ፣ “ህወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብ ነው፤ የትግራይ ሕዝብም ሕወሓት ነው። ሁለቱም የማይነጣጠሉ ናቸው፤” በሚል፣ህወሓትንና የትግራይ ሕዝብን በአንድ ላይ  በመግመድ፣ በዐደባባይ ደጋግመው ሲገልጹ ተስማምተዋል። ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉአላዊነት (ዓረና) እና የትግራይ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ትዴፓ)፣ እንዲሁም ሌሎች በክልሉና ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ ተወላጆች፣ ህውሓት እና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ መሆናቸውን ደጋግመው ለማስረዳት ይጥራሉ። ሁለቱን ነጥሎ ማየት እንደሚገባ ያስረዳል። የህወሓት ነባር አመራሮችም፣ ህውሓት እና መላው የትግራይ ሕዝብ በሙሉ አንድ አለመሆናቸወን፣ አዘውትረው በግልጽ ባይናገሩም፣ በልባቸው እውነቱ እንደማይጠፋቸው መገመት ይቻላል።
ህውሓታውያን (ሁሉም ላይሆኑ ይችላሉ)፣ እንደ አይን ብሌን የሚሳሱለትና በንቃት የሚጠብቁትን ስልጣናቸውን አስጠብቀው ለማስቀጠል፣ የብሔር ቅራኔንና ከፋፋይ ፖለቲካን እንደ ዋነና መሳሪያ አድርገው ላለፉት 29 ዓመታት ተጠቅመውበታል። ለዚህ የፖለቲካ ጨዋታም ፣ በትግራይ  ሕዝብ ስም መነገድ ሁነኛ ስልታቸው ነው። በትግራይ ሕዝብ ስም ካልተጠለሉ በስተቀር ፣ ድብቅና ግልጽ ዓላማቸውን ማስፈጸም እንደማይችሉ ያውቁታል።
ይህን መሰሪ ሐሳባቸውን ጠንቅቀው የተረዱ የትግራይ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ የተባሉትን ሁሉ እንደ ፈጣሪ ቃል አምነው የተቀበሉና የቀድሞ አገዛዝን የሚደግፉ መኖራቸው አይዘነጋም። በብዙ አገራዊ ችግሮች ዝምታን ከመረጡቱ መካከል፣ ሁሉም ባይባሉም የዚህ ማሳያዎች መኖራቸው አይጠረጠርም።
በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ውጥንቅጡ በወጣው ብሔርተኝነት ሳቢያ፣ ችግሩ ስር ሰድዶ መራራ ፍሬው እየታጨደ በመሆኑ ፣ የጎሳው መተላለቅ ጨርሶ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት ፣ በሐቅ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት በርጋታ ማሰብን ይጠይቃል።
ልዩነት በአንድነት
ማንነት ተኮር ግጭትና ጥቃት በልዩ ልዩ ጊዜያት እየተቀሰቀሰና እየተስፋፋ፣ የዜጎቻችንን ሕይወት እየቀጠፈ ነው፤ ቤት ንብረታቸውን እያወደመ ከመኖሪያ ቀዬያቸው እያፈናቀለ ፣ ለተለያየ አካላዊ ጉዳትና ስነ-ልቡናዊ ቀውስ እየዳረጋቸውም ይገኛል። ለችግሩ ሁነኛ እልባት መሻት ግዴታችን ነው። የጉልበቱን መንገድ ትተን፣ በሐሳቦቻችን ፍጭት ብርሃን የጋራ የሆነ ቤታችንን እንገንባ፤ በሀሳብ ባንስማማም እንኳን፣ ልዩነታችን በአንድነታችን ማዕቀፍ ውስጥ እንዲከበር እንግባባ። ከአንድ ማህጸን የወጡ መንትዮች ሳይቀሩ የአስተሳሰብ ልዩነት አላቸው። እንዲህ ከሆነ ዘንድ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ባሉባት አገራችን የተለያየ የአስተሳሰብና እምነት መኖሩ የማይቀር ሀቅ ነው። እነኚህ ልዩነቶች ሕብር እስካላቸው ድረስ ፣ በየፊናቸው ለአገር ግንባታ የሚኖራቸው ጠቀሜታ የላቀ ይሆናል። ለዚህም ሐሳብን በሐሳ ነጥሎ ማስረዳት ፣ መወያየት፣ መከራከርና መሟገት ፣ ሁሉንም አመለካከት ለማስተናገድ የሚያስችል ምህዳር መፍጠር አስፈላጊ ነው። የተለየ አመለካከት ለአደባባይ ሲቀርብ “ለምን ተነሳ፣ ለምን ቀረበ?” ብሎ በእልክ መንቀጥቀጥ መሳደብና በሃይል እርምጃዎች ማፈን፣ ትክክለኛና ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚያመጣ አይደለም።
ሁለቱ መንገዶች
የብሔር   ወገንተኝነት፣ ሁለት የተለያዩ የተግባር ምላሾችን አነቃቅቷል። አንደኛው በዚያው የብሄርተኝነት አሳቤና አደረጃጀት፣ ሌላውም ብሔርተኛ ተደራጅቶ እንዲታገል ማነሳሳቱ ሲሆን ፣ ሁለተኛው ደግሞ፣ ሰፋ ባለ ህብረ ብሔራዊ አገራዊ አደረጃጀት ቅርጽ ተደራጅቶ መታገል ነው።
የመጀመሪያው አማራጭ መንገድ፣ ለአገር ሰላምና ለሕዝብ አንድነት ትርጉም ያለው ለውጥ አላመጣም። በተጨባጭ ሲታይ፣ አንዱን የብሔር ፖለቲከኛ ስብስብን (ብሔሩን ሕዝብ በሙሉ የማይወክል) በሌላ መተካት ሆኗል። ይህ ደግሞ አገርንና ሕዝብን በተመሳሳይ የጨቋኝ አዙሪት ውስጥ በማቆየት መበደል ይሆናል። “ተጨቁኗል” ብሎ የታገለለት ብሔር ልዩ ጥቅምና የበላይነት እንዳገኘ በማስመሰል ፤ ጨቁኖኛል ያለውንና ሌሎች ጭቁን የሆኑ ብሔሮችን በአንድነት ጨፍልቆ ወደ መጨቆን ያመራል። ብሔሬ ያለውን ከፍ ለማድረግ መንቀሳቀሱ ተገማች ነው። ሌላውን ሳይበድ እና ሳይጋፋ የራሱን ከፍ ለማድረግ አይችልም። ለፖለቲካ ትክክለኝነት ሲል፣ በቃል ባይገልጸውም በገቢር ግን ይከውነዋል። ሌላኛውም የህብረ ብሔራዊና አንድት አማራጭ የተሞከረበት መንገድ ፣ ከውድቀት አልታደግንም። ሶስተኛ አማራጭ መፈለግ ሳያሻን አይቀርም።
ብዝሃን ቋንቋና ማንነት ባለበት አገር፣ ዜጎች እኩልነት በተግባር መረጋገጥ ካልቻሉ፣ ኢ-እኩልነት መስፈኑ በገሃድ የሚታይ እውነታ ይሆናል። አንዲት ሉአላዊት አገር መጠንከር፣ ማደግና መበልጸግ የምትችለው፣ በዜጎቿ መካከል በተግባር የተረጋገጠ እኩልነት ሲኖር ነው። በትላንቷና በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በወረቀት ላይ በደማቅ ቀለማት ተጽፎ የሚነበበው የዜጎች እኩልነት ጉዳይ፣ አማካይ ሜዳ ተፈልጎለት የተግባር እውነታና ልምምድ ሆኖ መታየት ይኖርበታል።
(ከጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና “የአገዛዞች ቀይ መስመር” የተቀነበበ)

Read 1348 times
Administrator

Latest from Administrator