Monday, 29 March 2021 00:00

"የከንፈር ወዳጅ” - የባይተዋርነት ዋሻ!

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ anileyt2@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

   (ክፍል ሁለት)
ጋሽ አሰፋ ጉያ፤ ሥነ-ፅሁፍንና ሥነ-ሥዕልን በፊደላትና በህብረ-ቀለማት አዋዶና ገምዶ በቤተ-ጥበባት የውበት እልፍኝ የሚመላለስ  ባለ ብርቱ ምናብ የጥበብ ሰው  ነው፡፡ “የከንፈር ወዳጅ” ከሥነ-ፅሁፍ አድባር (ዛር) የተፈለቀቀች  ድንቅ  የስነ-ግጥም መፅሐፍ ናት፡፡ በግጥሞቹ የተለያዩ ሰዋዊ ጉዳዮች ተሰናኝተዋል፡፡የግለሰብ ተብሰልስሎት፣ መነጠል የስሜት ጠገግ በስንኝ መዳፍ አፈፍ ተደርገዋል፡፡ እነሆ:-
ብቸኝነት
ራስ ማማጥ
ራስ መዋጥ
 (ህዳር 19 ቀን 1982 ዓ.ም ገፅ 38)
ብቸኝነት የግለሰብ ደሴት፤ የምናብ ህልቆ መሳፍርት ጉልላት፤ የነፃነት ምጥ ነው፡፡ ይህንን የግለሰብ ገጠመኝ በመንቶ ግጥም ቋጠረው፤ ጋሽ አሰፋ፡፡ ምርቱም፣ ገለባውም፤ ባድማውም፣ አውድማውም ያው - ራሱ ግለሰቡ ነውና በስፍሩ ይሰፈራል። አንዳንዴም የተፈጥሮ ረድኤት ተቋዳሽ ይሆናል፤ የመመረጡ ውጤት ነውና፡፡ በእርግጥ የህሊናን መዋለል፣ የልቦናን አለመርጋት በጊዜ ዥዋዥዌ ቀንብቦ በሰማይ ጥላ ስር ሲዳኝ የባይተዋርነት ስሜት ያጠላል፡፡ ይህን ያለ መርጋት ፤ ያለ መስከን ወይም የስሜት መዋለሉን ስንኞቹን ክፍት በማድረግ ገልጾታል፡፡ የተብሰልስሎቱን፤ የትዝብቱን ጥልቀት ህይወት የሰጠውም ይህ ኪናዊ ተግባሩ ነው፡፡ እፎይታ የሌለው መነጠል ስለሆነም ባዶነትን ያስተጋባል። በሌላኛው ግጥሙ  የባዶነት ተቃርኖን እጅግ ተራቀቀበትና ተቀኘ፡፡
አትመተር ... ጅምር _ የለህ
አትሰፈር ... መጠን _ የለህ
አትደረስ ... ድንበር _ የለህ
እዚህ ላይ “ሰማዩ!” ከጊዜ ጋር ያበረ ይመስል ቅርፅና መልኩን እየለዋወጠ አልጨበጥ ማለቱ ምናቡን እንዲቧጥጥ አስገደደው፤ ገጣሚውን፡፡ ይቀትራል። “ሰማዩ!” ተምሳሌታዊ ሚና የሚጫወተው ለ”ብቸኝነት” ጥላነት ነው፡፡ ቁዘማው፣ ቁጣና ንቀቱ ወይም ማሽሟጠጡ የመነጠሉ ውጤቶች ናቸው፡፡
የስሜቱ አለመጨበጥ፣ የህልሙ አለመቋጠር ያንገበግበዋል፡፡ አብዝቶ ይመሰጣል፤ ይቃትታል፡፡ እነሆ:-
...ሐሳብ...ብቻ ...ሐ...ሳ...ብ...
ብላሽ!...ብላሽ_ ሐሳብ
የለው ድምር የለው ብዜት
መሃን ሐሳብ ባዶ ውጤት፡፡
ሌላው መነሳት ያለበት ድንቅ ግጥም “ተናገር አንተ አፈር” ሲሆን በኢትዮጵያ የስነግጥም ታሪክ ታትመው ካነበብናቸው የተለየና አዲስ ጭብጥ (ምልከታ) ያስተዋወቀ  በመሆኑ ገጣሚውን ልዩ ቦታ ያሰጠዋል፡፡
“ተናገር አንተ አፈር” ዘይቤያዊ አገላለፅ ነው፤ እንቶኔ ዘይቤ፡፡ “አፈርን” በማወያየት፣ በመለመን እንዲሁም “በጥያቄ ድምፀት” ያናግረዋል-ተራኪው፡፡ ኸረ ያፋጥጠዋል ማለት ይቀላል፤ ”ምነው አፈር-ላፈር-ባፈር መፋጀቱ” በማለት፡፡ በርግጥ የግጥሙ ርዕስ እንቶኔ ቢሆንም፣ ስንኞቹ የተዋቀሩት በተምሳሌት ዘይቤ ነው፤ ሠውን ባፈር በመመሠል፡፡ እሡ አይወደኝ መከራው አይለቀኝ-እንዲሉ፡፡ ያም ሆኖ ተጨማሪ ዘይቤያዊ አገላለፅ የተሸከመ ነው፤ምፀት ዘይቤ፡፡ ስላቁ በፈጣሪው ላይ ይመሥላል፡፡ ሞቶ ተቀብሯልና (በልጁ) ክብሩን ለማግኘት በሞት መርከብ ላይ አዳሜ ለመሳፈር ይራኮትልሀል፡፡ ያው አፈር-ፈጣሪን፣ሀገርን (ቤትን)፣ የተሸከምነውን ስጋ፣ ከንቱነትን...ይወክላል፡፡ አፈር መዳኒትም (ፈውስ) ነው፡፡ ክብርና ሞገሱ ካንተው -- ምነው ጥድፊያው? የሚል ይመስላል፡፡
ስለሆነም “ካንተው÷ - ከሆነ ፍጥረቱ” ሲል የሠው (የፍጥረት ሁሉ) ምንጩ አንተ ከሆንክ ...እንዳለ እንረዳለን፡፡ “ያዳም ---የሰው ልጅ ግኝቱ” ሲል ደግሞ ያ የጥንቱ አዳም (የሰው መገኛ) መሠረቱ -አንተ ከሆንክ መነሻውም መድረሻውም “ምነው አንተ ለሰው፣ ሰውም ላንተ መፋጀቱ” እንዳለ እንገነዘባለን፣ ሽሙጥ (ምፀት) መሆኑ ነው፡፡
ግጥሙ ቀርነት የለውም፡፡ አይጎረብጥም፡፡ እንቡጥ አመልማሎ ነው --እያደር ይፈካል። አፈር ብለው አያፈሱህ÷እህል ብለው አያፍሱህ-- ሆነና ነገሩ የመረረ የባይተዋርነት ጥላ የሸፈነው ስሜት አዝሏል፡፡ ቀታሪ ነው፡፡ ስለሆነም “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ”ን ያስታውሰናል፡፡ እንዲያውም
የግጥሙን የመጨረሻ ስንኝ ደጋግመን ስናኝከው “ምነው ሞት ---ለሞት---በሞት መፋጀቱ” በሚል ተተክቶ ያቃጭልብናል። ሞትም ይሙት ---አይነት ነገር፡፡ ተቃርኖ ማስገሪያ _ ልበለው ይሆን!
ይበልጥ ያስረዳልኝ ዘንድ የሚከተለውን አሰኛኘት (አንጓ) ያጢኑት ፦
እነሆ ይታያል
እነሆ! ይሰማል
ላንዱ ጥበብ ሁለት - ሥያሜ ይሰጣል፡፡
“አይ ጊዜ? ይገርማል!......”
ጊዜ - በጊዜ ውስጥ በጊዜው ይሻራል፡፡
“አይ ቦታ? ይገርማል...”
ቦታ - በቦታ ውስጥ በቦታው ይሻራል፡፡
“አይ ጥበብ? ይገርማል....”
ጥበብ - በጥበብ ውስጥ በጥበብ ይሻራል።
“አይ ነገር? ይገርማል!....”
ነገር - በነገር ውስጥ  በነገር ይሻራል፡፡
ላንዱ ነገር-ሁለት ሥያሜ ይሉዋል
አይገርምም... ይገርማል፡፡
(ገፅ 30)
“ላንዱ ነገር-ሁለት”  በተቃርኖ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ቢሆንም በንቃት (ዕውቀት) ላይ  የጊዜን ዋጋ ያልቃል፡፡ያበረታል፡፡
   ሌላኛው መነሳት ያለበት ግጥም “ወፉ-ሰው” ነው፡፡ጥቂት ነጥቦች እናንሳ፡፡
“ድንገት ትዝ ሲለው
ወፍ ሆኖ ሲያስበው
በጭልፊት መጠለፍ...
በወንጭፍ መነደፍ...መኖሩ ሲታየው"
በነዚህ ስንኞች ተራኪው ዳር ቆሞ የሰውን ልጅ ግስጋሴ ጠቅላላ ግብ የሚቀምርባቸውን መንገዶች መዝኖ ምክንያታዊነቱን የገለጠባቸው ናቸው። የሰው ልጅ ውስንነቶችን ለመሻገር እና “ፍፁም ነፃነትን” ለመቀዳጀት ካለው ምኞት በመነሳት በወፍ ተመስሏል፡፡ የህዋውን የተንጣለለ ዓለም ያለምንም ገደብ ለመቅዘፍ እንደአንድ ምርጫ ቀርቦለታል፡፡ሆኖም ግን ውስንነቱ ሲገድበው ምኞቱ ይኮሰምናል። በርግጥ ያለውን ፀጋ ትርጉም አስፍቶ፣ አውጥቶ አውርዶ፤ ማዕዘናቱን ፈትሾ “ሰውነትን” ያፀድቃል-- ያልቃል፡፡ ሰው እንስሳ ነው፡፡ ከፍ ሲልም “መልዓክ” ነው። ሲልቅም ፈጣሪ ነውና ምርጫው ተገቢ ሆኖ እናገኘዋለን። በሌላ መልኩ ሰው መሆን ስለነበረብን ሰው ሆነናል፤ ቀድሞውንም የተሻለ ምርጫ ቢሆረን ሆኖ ሰው ባልሆን ነበር-- ያለ ይመስለኛል፡፡ ቀታሪ ነው፡፡ ሁሉም ነገር መሆን የቻለው መሆን ስላለበት ነው -- የሚለውን በአፅኖት ይጠቁማል። የሁሉም ምንጭ ሰው ሆኖ መገኘት ነውና --ያጀግናል፡፡ በመፅሐፍ ቅዱስ፤ “መመረጣችሁንና መጠራታችሁን ታፀኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ” መባሉን ማስታወሱ የግጥሙን መልከ ብዙነት ያፀናል፡፡ ለዚህም ይመስላል “ስነፅሁፍ አንድም ብዙም የሆነ ጥበብ ነው” የሚባለው፡፡ ከዚህም አንፃር ግጥም የልዕለ ተፈጥሮን ረድኤት መግለጫ ጥበብ ነው፡፡ቀታሪነቱ የላቀን ጉዳይ በላቀ ቋንቋ ወይም መንገድ የሚያቀርብ መሆኑ ላይ ነው፡፡
ግጥሙ በመጀመሪያዎቹ ሁለት አንጓዎች በፅኑ መሰረት ላይ ቆሞ የሰውን ልጅ የነፃነት እሴቶች ፅኑነት በማሰስ አስረጅ ስንኞችን በማስከተል በስሜት ይገሰግሳል፡፡ ሆኖም ጉዞው በምክንያት ተረትቶ ምኞት ይድበሰበሳል። ጥፋትን (ሞት እንበለው ይሆን) አምርሮ ይሸሻል። ነፃነትን በምናብ መዳፍ አፈፍ ለማድረግ መውተርተሩ ከንቱ ይሆናል፡፡
ግጥሙ ሰውን ወደ ሰውነት ለማላቅ የተሰናኘ ነው፤ አንዳንዴ በግልፅ በአብዛኛው በስውር። ከስውር ገፅታው አንዱ የወቅቱን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ በዘይቤ ሰፍቶ ካነፀረ በሗላ ይቆዝማል፡፡ ሀሰሳ ነፃነት በመሆኑ ቁጭትን አዝሏል፡፡ የሰውን ልጅ ውስንነቶች አጉልቷል፡፡ በሌላ ፅንፍም ሰውነትን አልቋል፤ አፅድቋል፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ካንቴ ሜር፤ “በግጥሞቼ እስቃለሁ -- በልቤ ግን ግፍን እያስታወስኩ አዝናለሁ” ማለታቸው፡፡ በመጨረሻም፦
በመቀነት ቀሚሷን ሸንሽና
በአልቦ በአሸንክታብ ተከሽና
“ሃባቢሌ...” እያለች...
ረገዳ እየረገደች... ታየች! በአውዳ ዓመት ተሸሞንሙና፡፡ ”የከንፈር ወዳጅ” ትውፊት ላይ የተመሰረተች ሆና ልጅነቱን ወደኋላ ተመልሶ በጠራ ምናብ ቁልጭ አድርጎ የከተበበት ድንቅ ግጥም ናት፡፡ በርካታ ጭብጦች ያዘለች ቢሆንም ለእኔ ግን በክፍል አንድ ላይ “የዘመኑ ጣር” ስር የሰፈሩ ጥልቅ ስሜቶችን አፈፍ ያደረገበት እና ድህነትን ፣የኑሮን ውጣውረድ እንዲሁም ያለመውን ጉዳይ ማሳካቱን ቀድሞ የመተረበት ትንቢታዊ ስራው ነው፤ ባይ ነኝ፡፡
በመጨረሻም  ገጣሚው በመፅሐፉ ስለተፈጥሮ፣ ስለባህሪ፣ ስለማህበራዊ ፍትህ፣ ስለውበት፣ ስለ ፍቅር  እና ስለኪነት አብዝቶ የተመሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ እስኪ ወደ መፅሐፉ እንዝለቅ...


Read 1391 times