Tuesday, 30 March 2021 00:00

በጭፍንነት ለነውጥ “ተቀባብሎ” የሚጠብቅ ነው የፖለቲካችን ቅኝት።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  • የአንዱ ፓርቲ “ጭፍን ደጋፊ”፣ ለሌኛው ፓርቲ “ጭፍን ተቃዋሚ” ነው።
    • በአንድ በኩል፣ የጭፍን ደጋፊዎች ግፊት አለ - “አናት ላይ የሚወጣ”።
    • በሌላ በኩልም፣ ከተቀናቃኞች “ጭፍን የተቃውሞ አፀፋ” አለ - በእልህ የሚያሰክር።
    • ማጋጋያ ግፊት እንጂ፣ ማረጋጊያ የደጋፊ ምክር፤ በአገራችን ብርቅ ነው።
    • “በለው፣ ያዘው፣ ድፋው፣ ናደው…” እያለ በጭፍን የሚጮህ ነው የሚበዛው።
    • እጅግ ከባድ የሆኑትን ሶስት አደጋዎች እንመለከታለን (በትግራይ የተከሰተውን አመፅና ጦርነት፣ የአማራ ክልል ሃላፊዎች የተገደሉበት ቀውስና አመፅ፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው አደገኛ ቀውስና አመፅ)።
    
            አእምሯቸውን የሚጠበቁ፣ እኔነታቸውን የሚያከብሩና ስልጣኔን የሚመኙ ሰዎች፣…. ተግሳፃቸው የሚበረታታው፣ በሚደገፉት ፓርቲ ላይ ነው። ከመነሻው፣ ጭፍን ደጋፊ አይደሉም። ተቀናቃኝ ፓርቲ ላይም ጭፍን ተቃዋሚ አይሆኑም።
አገራችን ለዚህ አልታደለችም። በርካታ ፓርቲዎችም፣ ለዚህ አልበቁም። እነሆም፣ በስክነት የሚያበረታታና በተግሳፅ የሚያረጋጋ ደጋፊ በማጣት፣ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣ በከንቱ እርስ በርስ ይቆራቆሳሉ። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር፣ ገዢው ፓርቲም ከእውነታ ጋር፣ በብላሽ እየተወዛገቡ የሚላተሙበት “አጋጣሚ”፣ የዘወትር “ትራጂክ” ውሎና አዳር ሆኗል።
በየእለቱ፣ ውዝግብ ይፈለፈላል፣ አተካራ ይካረራል። መጨረሻው እንደማያምር እያዩም፣ ምንም እንዳላዩ ይሆናሉ። እየተላተሙ ቁልቁል ወደ ጥፋት ይጣደፋሉ። ግን ምን ይገርማል? በትም አገር ቢሆን፤ “በጭፍን የሚገፋፋ” እንጂ፣ በጥበብ ወደ ህሊና የሚመልስ በቅንነት ስህተትን የሚገስፅ ደጋፊ ከሌለ፤ በትንሽ በትልቁ የሚናቆሩ ፓርቲዎች፣ እየደጋገሙ ወደ ለየለት ቀውስ ይገባሉ።
በድንገተኛ ምክንያት አይደለም ወደ ጥፋት የሚያመሩት። የውዝግብና የጥፋት መንገድ፣ መደበኛ መንገዳቸው ይሆናል። በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ተቃውሞ ግፊት ወደ ቀውስ እንደሚጓዙ፣ ከመነሻው ማወቅ ይቻላል።
በአገራችን የተፈጠሩትን ከባባድ ቀውሶች አስታውሱ።
በሶማሌ ክልል አስተዳደር እና የፌደራል መንግስት ውዝግብ፣ ገና ከመነሻው ነበር ማብቂያው እንደማያምር የሚያስታውቀው። ታዲያ፣ አተካራው እየጦዘ ወደ ቀውስ ሲያመራ፣ “ኧረ ይሄ ነገር በጎ አይደለም፤ ጨርሶም አያዋጣም” ብሎ፣ በቅንነት ምክር የሰጠ ደጋፊ ስንቱ ነው? ከተቀናቃኝ የሚመጣ ውግዘት ሳይሆን፣ ከደጋፊ የሚመጣ ተግሳፅ ማለቴ ነው።
ተቀናቃኞች፣ በእልህና በብሽሽቅ፣ አንዱ ፓርቲና ተቀናቃኙ ፓርቲ የሚወራወሩት ትችት፣ በጭፍን የሚያዘንቡት ስድብና ውንጀላ ሞልቷል። ከተቃራኒ አቅጣጫ ሳይሆን፣ ከራስ ፓርቲ አባላትና ከደጋፊዎች የሚቀርብ ተግሳፅ ነው በአገራችን የጠፋው። ችግርን የሚያባብስና የሚያወሳስብ የማጋጋያ ግፊት እንጂ፣ ችግርን የሚያቃልልና ለመፍትሔ የሚረዳ የደጋፊ ምክር፤ በአገራችን ብርቅ ነው።
“በለው፣ ያዘው፣ ድፋው፣ ናደው…” እያለ በጭፍን የሚጮህ ነው የሚበዛው። በዚህ መንገድም ነው፣ የሶማሌ ክልል አስተዳደርና የፌደራል መንግስት ውዝግብ፣ አይናችን እያየ፣ ወደ አስቀያሚ ቀውስና ወደ አሳዛኝ ጥፋት የተሻገረው። ይሄ ምኑ ያምራል?
በተለያዩ የደቡብ ክልል ዞኖች፣ “በእሽቅድምድም” የተፈጠሩ ቀውሶችም፤ ግብታዊ አደጋዎች፤ ወይም ድንገተኛ አጋጣሚዎች አልነበሩም። ቀስ በቀስ እየጦዙ የመጡ ቀውሶች ናቸው። ከተቀናቃኝ በኩል፣ በብሽሽቅና በእልህ ወደ ቁልቁለት የሚገፈታትሩ ውግዘቶችና ውንጀላዎች ለቁጥር ያስቸግራሉ። ተቀናቃኝን፣ በእልህ ስሜት ተብትበው፣ ወደ አጣብቂኝ ለማስገባት፣ ወይም ማኖ ለማስነካት የሚንጫጩ ጭፍን ሰዎች ሞልተዋል። ይህንንም፣ እንደ ፖለቲካ ጥበብ ይቆጥሩታል።
ከደጋፊዎች በኩልስ? የሚያጋግል ደጋፊ በሽ ነው። የሚያረጋጋ ደጋፊ ከየት ይምጣ? የሚል ነው ጥያቄው።
እሳትን የሚለኩስና የሚያርገበግብ ደጋፊ እንጂ፤ ለማብረድና ለማርገብ የሚረዳ መካር ደጋፊ የታለ? ቢኖርም፣ ብዙ አይደለም። በርከት ቢሉም እንኳ፣ ድምጻቸው አይሰማም። ከተሰማም፣ “ከሃዲ፣ ባንዳ፣ ሌባ፣”…. ተብለው፣ በስድብና በውንጀላ ጎርፍ ተጥለቅልቀው ተደፍቀው ይቀራሉ። ልባም፣ ቅን፣ አዋቂና መካር ደጋፊዎች ድምጻቸው ይጠፋል።
በጭፍን ወደ ፀብ የሚገፋፋና በሆይሆይታ ነገር የሚያቀጣጥል ደጋፊ ደግሞ፣ ቁልቁል ወደ ጥፋት ያንደረድራል እንጂ፣ ከህሊና ጋር የመገናኘትና የማሰብ ፋታ አይሰጥም። ለዚህም ነው፤ አላስፈላጊ ውዝግቦችና ትንቅንቆች፣ በጊዜ የማይረግቡት፤ በሰላም የማያበቁት።
በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ተቃውሞ፣ አናት የሚያዞር ፖለቲካ!
ያው፤ ይሄ የአገር ችግር ነው። የሁሉም ፓርቲዎች ፈተና ነው። በሁሉም ፓርቲ ውስጥ፣ በብዛትና በመጠን ቢለያዩም፣ ጭፍንነት የተጠናወታቸው ነውጥ ወዳድ አባላትና ደጋፊዎች ሁሌም አሉ። ጭፍንነት ባለሁለት ስለት ጠንቅ መሆኑ ደግሞ፣ ፈተናውን እጥፍ ያከብደዋል።
የአንዱ ፓርቲ “ጭፍን ደጋፊ”፣ ለሌኛው ፓርቲ “ጭፍን ተቃዋሚ” ነው። እገሌ ፓርቲ ላይ ክፉ ጥላቻ የተጠናወተው “ጭፍን ተቃዋሚ”፣ የሌላ ፓርቲ “ጭፍን ደጋፊ” ይሆናል።
“እርስ በእርስ እየተመጋገቡ መራባት” ይሉሃል - እንዲህ ነው።
በአንድ በኩል፣ የጭፍን ደጋፊዎች ግፊት አለ - “አናት ላይ የሚወጣና የሚያዞር”። በሌላ በኩልም፣ ከተቀናቃኞች የሚመጣ፣ “ጭፍን የተቃውሞ አፀፋ” እየተጨመረበት፣ የእልህ ስካር ይታከልበታል።
በየጎራው የፓርቲው፣ ጭፍን ደጋፊዎች እና ጭፍን ተቃዋሚዎች፣ በቅብብሎሽ ውዝግብን እያባባሱና ዙሩን እያከረሩ፣ ሰፈር መንደሩ ቀውጢ ይሆናል። አገር ምድሩ ይታወካል። በሌላ አነጋገር፤ መከራችን መብዛቱ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። አመፅና አዋጅ፣ የጅምላ ግድያና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የስርዓት አልበኝነት ውድመትና የእስር ዘመቻ፣ …እንዲህ ወደ ዘግናኝ ጥፋት፣ ደጋግመን የምንወርደው አለምክንያት አይደለም።
አላስፈላጊ አተካራ ወደ አስቀያሚ ውርደት ከመድረሱ በፊት፣ በጊዜ ስህተትን የመግታትና ከጥፋት መንገድ የመውጣት አቅም የምናጣውም አለምክንያት አይደለም።
በጭፍንነት ለነውጥ “ተቀባብሎ” የሚጠብቅ ነው - የፖለቲካችን ቅኝት።
የአገራችን የኋላቀርነት ፖለቲካ፣ ለጭፍን ድጋፍና ለጭፍን ተቃውሞ የሚያመች ነው። በቅንነት ወደ በጎ እያበረታታ፣ ከስህተት ደግሞ የሚገስፅ ደጋፊ፣ ፓርቲውን ለማዳከም እንደመጣ ሸርሻሪ ይቆጠራል።
ለእውነት በመታመን፣ ጥፋቶች እንዲታረሙ፣ በቅንነትና በጨዋነት፣ ተቀናቃኝን ያለ ጥላቻ መተቸትስ? ከስድብና ከክፋት የፀዳ ትችት፣ “የድክመትና የፍርሃት ምልክት” ተደርጎ ይታያል። በአጭሩ፣ ኋላቀሩ የአገራችን የፖለቲካ ቅኝት፣ ለእውነትና ለቅንነት አይመችም። እንዴት ብሎ!
“ነባርና መጤ”፣ ወይም “የዚህ ብሔረሰብና የዚያ ብሔር”፣ ወይም “የወዲያኛው ሃይማኖትና የወዲህኛው ሃይማኖት”፣ ወይም “ሃብታምና ድሃ፣ ነጋዴና ሸማች፣ ከተማና ገጠር” እያለ በጭፍን የሚያቧድን ነው - የአገራችን የፖለቲካ ኋላ ቀርነት። በጭፍን የሚያቧድን የፖለቲካ ኋላቀርነት ደግሞ፣ ሁሌም፣ የትም አገር፣ የጭፍን ተቃውሞና የጭፍን ድጋፍ መፈልፈያ ነው።
የጭፍንነት ስካር ክፋቱ፣ ከእውነታ ጋር ያጣላል፤ ይጋርዳል። ዘግናኝ መዘዝ እየተደራረበ ቢከመር እንኳ፣ እውነታውን የማየትና ስህተትን የማረም አቅምን ያሳጣል - ጭፍንነት። ከስህተትና ከጥፋት የመማር አቅማቸውን በመጣልም፣ ጭፍን ደጋፊዎች እየደጋገሙ እየመላለሱ ውድቀትን ይጋብዛሉ። እንዴት?
አንደኛ፣ የሚደግፉትን መንግስት ወይም የሚደግፉትን ፓርቲ፣ በጭፍን ሆይሆይታ ወደ ጥፋት ይገፋፉታል።
ሁለተኛ፣ የሚቃወሙትን ፓርቲ ወይም የሚቃወሙትን መንግስትስ? እንዲሻሻል ሳይሆን እንዲብስበት ያዋክቡታል።
በጭፍን ድጋፍና በጭፍን ጥላቻ፣ ወደ አጣብቂኝ እንዲገባ ወይም ማኖ እንዲነካ ይተነኳኩሱታል። እንደምታዩትም፣ ጭፍን ድጋፍና ጭፍን ተቃውሞ፣ እርስ በርስ ተያይዘው ተባብረው ወደ ጥፋት የሚሽቀዳደሙበት አዙሪት ሆኗል - የአገራችን የፖለቲካ ዑደት።
ከስህተት የሚገስፅና ወደ ተቃና መንገድ የሚያበረታታ ድጋፍ ማለት፣ ከጭፍንነት የሚቀሰቅስ ደወል እንደ ማለት ነው። “ከቅዠት የሚያባንን፣ ወደ ህሊናም ሚመልስ ድጋፍ” እንደ ማለት ነው። የውድቀት ቁልቁለትን ለመግታትም ያግዛል - እንደ ፍሬን።
“የሚገስፅ ደጋፍ” ሲመናመንና ድምፁ ሲሳሳ፣ ያለልጓም ወደ ውድቀት መንደርደር ይበረክታል። ቀድሞ መባነን የለም። በቃ፤ ነገሩ ሁሉ ሲፈነዳ፤ እርስ በርስ እየተላተመ እየተፈጠፈጠ ሲፈረካከስ ነው፣ የምንባንነው። ለዚያውም በደንብ ከነቃን ነው። ሌላ ዙር ቅዠት ለመፍጠርና ለመነከር ጊዜ አይፈጅብንማ። ወደ ቅዠት የምንሰምጥበት ፍጥነት፣ ከመባነናችን ይፈጥናል።
እንደዚያ ባይሆንማ፣ ለመባነንና ለመንቃት፣ ከአንድ ከሁለት ጥፋት ብቻ፣ በቂ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። ግን ምን ያደርጋል? ተጋርዶብናል፤ ተጨፍነናል። የፖለቲካ ኋላቀርነት፣ መውጫ መግቢያው የማይታወቅ፣ ድንግዝግዝ ዋሻ ሆኖብናል። እውነታና ተለዋዋጭ ጥላ ተቀላቅሎብናል። ከቅዠት አለም ጋር ተጣብቀናል።
ከሳምንት ሳምንት፣ ሌላ ዙር ቀውስና ዘግናኝ ጥቃት…. በሦስት ዓመት ውስጥ፣ መቶ ምናምነኛ ዓመፅና ዘመቻ፣ ጥቃትና እልቂት፣… ለሚባንን ሰው፣ ይሄ ሁሉ ባላስፈለገ ነበር። ስህተትንና ጥፋትን በጊዜ ለመከላከል አለመቻል ብቻ ሳይሆን፣ አዝማሚያው አፍጥጦ ሲመጣም፣ መጨረሻው እንደማያምር በግልፅ ሲታየንም እንኳ፣ ወደ ህሊና የመመለስና አደብ የመግዛት አቅም ርቆናል። ርቀነዋል።
እጅግ ከባድ የሆኑትን ሶስት አደጋዎች ተመለከቱ። አስቡት። ድንገተኛ አደጋዎች አይደሉም ታዲያ፣ ለምን አስቀድመን መከላከል አልቻልንም? ወይም ወደ ክፉ ውድቀት ከመውረዳቸው በፊት በጊዜ ማርገብና መግታት አቃተን?
በትግራይ የተከሰተውን አመፅና ጦርነት፣ አሁን የሚታየው ምስቅልቅልና መከራ የቱን ያህል አደገኛ፣ እጅጉን ዘግናኝ፣ ምንኛ አሳዛኝ እንደሆነ፤ ለገለጻ ያስቸግራል። አይነቱና ቁጥሩ መብዛቱ ብቻ ሳይሆን፣ ጨርሶ መፈጠር ያልነበረበት ጥፋትና መከራ መሆኑ ያሳዝናል።
ድንገተኛና ዱብዳ አደጋ ነው? አይደለም። ገና ከዓመት ከሁለት ዓመት በፊት፣ አዝማሚያውን መገንዘብ ይቻል ነበር። እለት ተእለት፣ የቀውስ ጥሪና ቅስቀሳ ሲጦዝ፣ ተንተክትኮ ሲፍለቀለቅ፣ ይህንም በይፋ ስናይ ስንት ወራት ተቆጠሩ? በዚያ ጊዜ ውስጥ፣ ነገሩን ለማርገብ ለማብረድ የሞከረ ሰው ስንቱ ነው? እጅግ የሚበዛው፣ በማራገብና በማጋጋል የተጠመደ አልነበረም?
ከዚያ በፊት፣ የአማራ ክልል አስተዳደር ሃላፊዎች የተገደሉበት ቀውስና አመፅም፤ ድንገተኛ አደጋ እንዳልሆነ አስታውሱ። አዎ፤ አደገኛ ነው፤ ድንገተኛ ግን አይደለም። ለበርካታ ወራት ሲንተከተክ የቆየ ቀውስ ነው። ሰፊ የጥላቻ ቅስቀሳ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ፣ እየሰፋ እየከፋ ነው፤ በመጨረሻ የገነፈለው፤ የፈነዳው።
በ2012 የመጨረሻ ወራት፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው፣ በጣም አደገኛ ቀውስና አመፅ፣ ግድያና እስር፣ በድንገተኛ ክስተት ሳቢያ ብቻ የተፈጠረ አደጋ አይደለም። ነባር ነቀርሳ ነው። የአመታት መጥፎ የፖለቲካ ቅስቀሳና ውዝግብ፣ በየጊዜውና በየቦታው ለጥፋት ሲዳርገን ከርሟል። ይሄው ለአመታት እየተሳከረና እየጦዘ የመጣ መጥፎ ፖለቲካ ነው፣ በድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ ሰበብ፣ ወደ ከፋ አመፅ አደጋ የመሸጋገር አጋጣሚ ያገኘው።
ታዲያ፣ ድንገተኛ ካልሆነ፣ አስቀድሞ መከላከል፣ በተግሳፅና በምክክር አማካኝነትም ነገሩን በጊዜ ማስከን አይቻልም ነበር? ተቀናቃኞች በሚሰነዝሩት ትችትና ተቃውሞ፣ በሚያዘንቡት ወቀሳና ውንጀላ አማካኝነት ማለቴ ነው። የአዋቂ ደጋፊዎች ተግሳፅና ምክር ከሌለ፤ ከተቀናቃኝ በኩል ብቻ የሚሰነዘር ወቀሳና ተቃውሞ፣ ብዙም ውጤት እንደ ሌለው አይተናላ።
ለዚህም ነው፤ ገዢው ፓርቲም ሆነ መንግስት፣ አጋርም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ፤ …ሁሉም ተቀናቃኝ ፓርቲዎችና መንግስት፤ ናላቸው በጭፍን ድጋፍ እንዳይዞር ጭፍን ተቃውሞም በእልህ እንዳያሰክራቸው መጠንቀቅ የሚገባቸው በቅንነት እያበረታቱ ስህተትን የሚገስጹ አባላትና ደጋፊዎች ያስፈልጓቸዋል። አለበለዚያም፣ በጭፍን ድጋፍ እየተገፋፉ፣ በጭፍን ተቃውሞም እልህ ውስጥ እየተዘፈቁ፣ አብሮ ተባብሮ የመውረድ አዙሪታችን አያበቃም።Read 7081 times