Monday, 29 March 2021 00:00

የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ለቀው ሊወጡ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 • ጠ/ሚኒስትሩ በአስመራ ቆይታቸው በትግራይ ያሉት የኤርትራ ወታደሮች ድንበር ለቀው ስለሚወጡበት ጉዳይ ስምምነት ተደርሷል ብለዋል።
• ኤርትራ በክፉ ቀን የደረሰችልን ባለውለታችን መሆኗን መካድ የለብንም
• ኤርትራ መንግስት ለሚያቀርበው የደህንነት “ስጋት ጉዳይ ዋስትና መስጠት አንችልም፡፡
• የኤርትራ ወታደሮች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አካባቢውን ለቀው ሊወጡ ይገባል፡፡
• የኤርትራ ወታደሮች በህወኃት ላይ ባላቸው ቂምና ቁርሾ በንፁሀን ላይ ወንጀሉል ሊፈፅሙ ይችላሉ
       
         የኤርትራ መንግስት በትግራይ ክልል በተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ውስጥ ተሳትፎ ያደረገው የራሱን የድንበር አካባቢ ክፍተት ለመሙላትና ራሱን ከጥቃት ለመከላከል እንደሆነ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ገለፁ፡፡ ለሰራዊቱ ድንበር ለቆ ስለሚወጣበት ጉዳይ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር መወያየታቸውንና ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ በሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲና የንግድ ግንኙነት ዙሪያ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር በስፋት መነጋገራቸውንና ግንኙነታቸው ተጠናክሮ ስለሚቀጥልበት ጉዳይ መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እደገለፁት የኤርትራ መንግስት በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ለኢትዮጵያ  መንግስትና ህዝብ የዋሉት ውለታ ታሪክ የማይረሳው ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በገዛ ወገኑ ክህደት ተፈፅሞበት በነበረበት ወቅት ከሞት ሸሽቶ ድንበር አልፎ የገባውን ሠራዊታችንን ተቀብለውና ተንከባክበው ሕይወቱን  ማትረፋቸው የኢትዮጵያ የምንግዜም ባለውለታ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ በችግር ወቅት እንኳን ሰው የራስ ጥላም ይከዳል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ የኤርትራ መንግስት ህዝብ ግን በዛ ከባድ ጊዜ ከጎናችን በመሆን አጋርነታቸውን ያሳዩንና ታሪክ የማይረሳቸው ባለውለታዎቻችን ናቸው ብለዋል ህግ የማስከበሩ ዘመቻ ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ሰራዊቱ በንፁሀን ኢትዮጵያውያን ላይ አደረሰ የተባለውን ጥፋት በፅኑ የምንቃወም ከመሆናችንም በላይ በአጥፊዎቹ ላይ ህጋዊ እርምጃ ስለሚወሰድበት ጉዳይ ላይ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጋር እንደሚወያዩ ተናግረዋል፡፡
የኤርትራ ሰራዊት በድንበር አካባቢ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላትና ጥቃት እንዳይፈፀምበት ለመካላከል  አሁንም  በድንበር  አካባቢዎች ሰፍሮ እንደሚገኝ ያመለከቱት ጠ/ሚኒስትሩ ለደህንነታችን ዋስትና ከሰጣችሁን አካባቢውን አሁኑኑ ለቀን  መሄድ እንችላለን ብለውናል ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እኛ ለደህንነታቸው ዋስትና መስጠት አንችልም ብለዋል፡፡
ይህንኑ የጠ/ሚኒስትሩን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የሰጡትን ማብራሪያ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡን የፖለቲካ ምሁሩ  አቶ ሰለሞን ፍርድ አወቅ እንደተናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ የኤርትራ ሰራዊት ህግ በማስከበር በዘመቻው እንዳልተሳተፉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የቆዩ ቢሆኑም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት  ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎችም ዓለም ዓቀፍ ተቋማት በርካታ ንፁሃን መገደላቸውንና የኤርትራ ሰራዊት በጦርነቱ መሳተፉን መግለፃቸውን ተከትሎ መንግስት ጉዳዩን አምኗል፡፡ ምንም እንኳን መንግስት በኤርትራ ወታደሮች ተፈፀመ ስለተባለው ወንጀል በግልፅ ባያምንም የኤርትራ ሰራዊት ፈፀመ የተባለውን ወንጀል ከመፈጸም ወደ ኋላ ሊል ይችላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የኤርትራ ህዝብና ሰራዊቱ ከትግራይ ህዝብና መንግስት ጋር ለዓመታት የዘለቀ ቂምና ቁርሾ ይዞ የኖረ ህዝብ ነው፡፡ ሰራዊቱ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ንጹሃኑን የቂም በቀል መውጫ በማድረግ የተባሉትን ወንጀሎች በንጹሃኑ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ መፈጸሙን ለማመን ከባድ አይሆንም። ይህ ሁኔታ ግን በኤርትራ መንግስት በኩል ተቀባይነት ያለው ጉዳይ ነው ማለት አይደለም፡፡ መንግሰት ጉዳዩን ሊቃወም ቢችልም ድርጊቱን ከመፈጸም አያድነውም ስለዚህም አሁን ያለው ብቸኛ አማራጭ የከፋ ጉዳትና ችግር ከመከሰቱ በፊት ድንበር ተሻግሮ የገባው የኤርትራ ሰራዊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ መደረግ አለበት። የሰሞኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአስመራ ጉብኝትም ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመፈለግ ነው የሚል እምነት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት አቶ አብርሃም ካሰሁን በበኩላቸው የኤርትራ መንግስት ወደ ጦርነቱ እንዲገባ ከህወኃት አመራሮች በተለያዩ መንገዶች ተደጋጋሚ ግብዣ ቢደረግለትም በበዛ ትዕግስቱ ወደ ጦርነት ሳይቀላቀል መቆየቱን ጠቁመው ሁኔታው እየከፋ ሲሄድ ግን አገሪቱ ህልውናዋን ለማስጠበቅ እና የዜጎቿን የደህንነት ስጋት ለማስቀረት ተገደው ወደ ጦርነቱ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዘመቻው ሲጠናቀቅ ሠራዊቱ ወደ ነበረበት መመለስ ሲገባው አሁንም በዚያው በመቆየት በንጹሀን የትግራይ ህዝብ ላይ የዘረፋና የአስገድዶ መደፈር ወንጀል እየፈፀመ መሆኑን ይናገራል፡፡
ይህ ሁኔታ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ተደርጎ አጥፊዎቹ ለህግ እንዲቀርቡና ሠራዊቱም የያዘውን የኢትዮጵያ መሬት ለቆ እንዲወጣ ሊደረግ ይገባል ብለዋል። ምሁራኑ እንደሚናገሩት የኤርትራና የትግራይ ህዝብ ለዓመታት አብሮ የኖረ እርስ በእርሱ በታሪክ በባህልና በቋንቋ የተሳሰረና ፈጽሞ ሊለያይ የማይችል ህዝብ ሆኖ ሳለ በዚህ ዓይነት መንገድ በህዝቡ ውስጥ ቂምና ቁርሾ እንዲፈጠርና ስር እየሰደደ እንዲሄድ ማድረጉ ለሁለቱም አገራት እጅግ አደገኛ ነገር ነው ብለዋል፡፡
ትግራይ ውስጥ በኤርትራ ሰራዊት ተፈፀመ ከተባሉ ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ አሜሪካንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አገራትና አለም አቀፍ ተቋማት ሠራዊቱ ከክልሉ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡  Read 498 times