Saturday, 27 March 2021 12:08

6ኛው አገራዊ ምርጫ 2013 አረና በትግራይ ቀውስ ዙሪያ ምን ይላል?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   • ኢሰመኮ ወገንተኛ ስለሆነ አናምነውም
      • በህወኃት ሰበብ የሕዝባችን ጥቅም እንዲነካ አንፈልግም
      • አረና በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ተሳታፊ አይደለም

           የህወኃት ቀንደኛ ተፎካካሪ የነበረው አረና ከፍተኛ አመራር የማይካድራን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ምርመራ አድርጎ ሪፖርት ያወጣውን ኢሰመኮ፤አናምነውም ብለዋል ምክንያታቸውን ያስረዳሉ በትግራይ ያለውን ሁኔታ ይናገራሉ፡፡ በጊዜያዊ አስተዳደር ወስጥ የተሾሙትን የአረና ሊቀመንበር በተመለከተም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በትግራይ ግጭቱ እንዲቆምና መረጋጋት እንዲፈጥር  መፍትሔው አንድ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ምን መፍትሔ ምን ይሆን? በሚሉና ተያያዥ  የአረናን ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡

             በአሁኑ ወቅት ትግራይ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
እኛም ራሳችን ከተለያዩ አካላት የምናገኛቸው መረጃዎች ናቸው በእጃችን ያሉት፡፡ ከመጀመሪያም  ዘር ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ናቸው ሲፈፀሙ የነበረው። በተለያዩ ቦታዎች እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ተፈፅመዋል። በመቀሌ፣ ተንቤን፣ ምዕራብ ትግራይ ጥቃቱን ሸሽተው የተጠለሉ ሰዎች ስላሉ መረጃውን ከእነሱም ማግኘት ይቻላል። የማይካድራ ጉዳይም የሚነገርበት መንገድ የተሳሳተ መሆኑን ነው የተረዳነው፡፡ አማራ ብቻ እንደተገደለ ተደርጎ ነው የሚቀርበው፤ ነገር ግን እኔ በግሌ የማውቃቸው ሁለት ትግራዋይ ስለመገደላቸው ተጨባጭ መረጃ አለኝ፡፡ ይሄ የተሳሳተ መረጃ  መሰራጨቱ ራሱ ሌላ  መጥፎ  ዘረኝነት ነው የፈጠረው። የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት፤ የተሳሳተ መሆኑን ተገንዝበዋል፡፡ በወቅቱ አማራ አልተገደለም አላልንም፤ ነገር ግን ሁሉም የጥቃቱ ሠለባ ነበር፡፡ ይሄን ጉዳይ በቀጣይ ገለልተኛ አካል ማጣራት አለበት፡፡
የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ኮሚሽን ምርመራውን ያካሄደው በገለልተኛነት መሆኑን  አስታውቋል፡፡ እርስዎ በገለልተኛ አካል ይመርመር ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? የማን የምርመራ ውጤት ነው የሚታመነው?
እኛ እሱን አናምነውም፡፡ ኮሚሽኑ ዘረኛ መሆኑ  ነው የገባን፡፡ ሪፖርቱን ሲያወጣ በአንድ ወገን ብቻ የደረሠ ጥፋትን ማዕከል አድርጎ፣ አጋኖ ነው ያቀረበው፡፡ መጋነኑ ብቻ ሳይሆን እውነታን የደበቀ  ነው እያልን ነው ያለነው፡፡ የተሳሳተ ሪፖርት በማቅረብ በጦርነት ሂደት ሌላ ወንጀልና ጥላቻ እንዲፈፀም አድርጓል፡፡ ስለዚህ ይሄ ድርጅት ጉዳዩን ቢያጣራ ተቀባይነት  የለውም። ገለልተኛ ይሆናል ብለን አናምንም፡፡  የትግራይ ጉዳይ በሱ በኩል መጣራት የለበትም፡፡ እኔ በግሌ የማውቃቸው የሞቱበትን ጉዳይ የከዳ ተቋም፤ እንዴት ብዬ ነው ገለልተኛ ነው ብዬ ማመን የምችለው? አሁንም እኮ ተወልደው ካደጉበት ቦታ ውጡ ሲባሉ፣ ማንም ድምጽ የሆናቸው፤ ተው ብሎ የተከላከለ የለም። ይሄ ተቋምም ዝምታን ነው የመረጠው። በአጠቃላይ ችግሩ በእጅጉ የሚያስከፋ ነው፡፡ ይሄ ሃገራችን የማይጠቅም አካሄድና አስተሳሰብን መቃወም ይገባል፡፡ ለሀገሪቱ ቀጣይ ሁኔታም አይጠቅምም፡፡
በመጀመሪያ ከህወሃት ጋር ቅራኔ በነበራችሁ ጊዜና አሁን ያላችሁ አቋም በተለይ በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ላይ የተለያየ ነው፡፡ ለምን ይሆን?
መጀመሪያም ቢሆንም እኛ የህወኃትን በደል እንጂ ሌላ ነገር አይደለም ተቃውሟችን። ህወኃትን ተቃወምን ማለት በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት እንደግፋለን ማለት አይደለም። የህወኃት በደልን እየተቃወምን፣ ሌላ በደልን እንደግፋለን ማለት አይደለም። በመጀመሪያም ቢሆን እኛ የተካረረ ቅራኔ ለኢትዮጵያዊነት ጠቃሚ አለመሆኑን ስናስገነዝብ ነው የቆየነው፡፡ ህወኃትን ስንቃወም በመርህ ነው፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፤ የትግራይ ፖለቲከኞች ህወኃትን ነበር ሲደግፉ የነበሩት የአማራ ፖለቲከኞች ብአዴንን ወይንም ኦዴፓን ነው ሲደግፉ የነበረው፡፡ ሌላውም እንደዚያው። ከራሱ ድርጅት ጎን ነው ሲቆም የነበረው፡፡ ስለዚህ በትግራይ የተለየ ነገር አይደለም የተሰራው፡፡ የአማራ ፖለቲከኞች በማንኛውም መንገድ የህዝባቸው  ጥቅም እንዳይነካ እንደሚፈልጉት ሁሉ፣ እኛም በህወኃት ሰበብ የህዝባችን ጥቅም እንዲነካ አንፈልግም፡፡ ስለዚህ የኛ ትክክል፣ የእናንተ ስህተት የሚል የዘረኛ አካሄድ ፈፅሞ አንፈልግም፡፡ የአማራ ክልል ልዩ ሃይል፣ ያን ሁሉ ጥፋት እያደረሠ ሲኮነን አናይም፡፡
እርስዎ የሚሏቸው ጥፋቶች ምንድን ናቸው? ማስረጃ ሊያቀርቡባቸው ይችላሉ?
ይሔ ማስረጃ የሚለው ነገር ሁሌም አንድ ሃገር ለመገንባት አስቸጋሪ ከሚያደርጉት ሁኔታዎች አንዱ ነው፡፡ ሃውዜን እኮ የተደበደበው በጀት ነው፡፡ ደርግ ነው በጀት የደበደበው፤ ነገር ግን አሁን ሌላ መልክ ይዞ ነው የሚነገረው፡፡ ህወኃት ነው የፈፀመው ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ ድርጊቱን ማውገዝ ሣይሆን ማን አደረገው ብለው ነው ሲከራከሩ የኖሩት፡፡ ታዲያ እነዚሁ ሃይሎች እኛ በትግራይ ያለን ሰዎች የምንናገረውን ሩቅ ሆነው አልተፈፀመም ብለው ቢከራከሩን ለምን ይደንቀናል? ስለዚሁ እኛ ስንናገር እነሱ ማስረጃ ካሉ፣ ምን አይነት ማስረጃ እንደሚፈልጉ ራሱ አይገባኝም። ይሔ መካካድ ለሃገራችን አሳፋሪ  ነው፡፡ እውነት በመደበቅና ከእውነት በመሸሽ የትም አይደርስም አያግባባንም፡፡ እስከ ዛሬ እኛ ዝም ስንል የነበረው፤ መዳከም የነበረበት ሃይል ስላለ  እንጂ የህዝቡ በደል ሣያንገበግበን ቀርቶ አይደለም፡፡ እኛ ማስረጃ ለሚሉን አይደለም ይሔንን የምናቀርበው፤ ምክንያታዊነትን  አምነው ለሚረዱን ነው፡፡
አሁን በትግራይ እየተካሄደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ የእናንተ አቋም ምንድን ነው?
ሲጀመር አሁን እየተካሄደ ያለው የምን ህግ ማስከበር ነው? ምን አይነት ኦፕሬሽን ነው? በስሙ ስንጠራው፡፡ ጦርነት ነው እየተካሄደ ያለው፡፡ በሌላ  ስም መጥራት ይከብዳል፡፡ ጦርነቱ እስከ ዛሬ በትግራይ ከነበሩ ጦርነቶች የከበደ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሰብአዊ ቀውስ ያስከተለ ነው። በጣም ብዙ ሰው የጎዳ፣ የብዙዎችን በር ያንኳኳ ጦርነት ነው፡፡ መንግስትም ይሄን በሚገባ ያውቃል፡፡ የተረጂዎችን ቁጥርም  ሰምተናል፡፡  በአጠቃላይ ጦርነቱ ትግራይን ያወደመ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ሁኔታውን አስመልክቶ የሚቀርቡ  ነገሮች ግነት የበዛባቸው ናቸው ብለዋል….
እሳቸው ሊሉ ይችላሉ፡፡ ብዙ ነገር ብለው አሜን ብለን ተቀብለናል፡፡ ነገር ግን እውነታው ሌላ ነበር፡፡ የኤርትራ ወታደር ሲገባ አልገባም ሲባል ቆይቶ አሁን አምነዋል። አንድም ሠው በጦርነቱ አልሞተም ብለውን አምነን ነበር፤ አሁን ደግሞ ሠው መሞቱን ነግረውናል፤ ይሄንንም አምነናቸዋል፡፡ ነገሩ ሁሉ እንዲህ ነው እየሆነ ያለው፡፡ ስለዚህ ሁሉም እያደር የሚጠራ ይሆናል፡፡
የፓርቲያችሁ አመራሮች የሚሳተፉበትን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥራዎች እንዴት ይገመገማሉ?
በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የሚሳተፉ አመራሮች እየተሳተፉ ያሉት እንደ አረና አይደለም፤ በግላቸው ነው፡፡ አረና በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር ውስጥ ተሣታፊ አይደለም፡፡  ህወኃትን ህዝብ ሳይመርጠው ስልጣን ይዟል ብለን ስንቃወም ኖረን፣ እኛም ህዝብ ሳይመርጠን ስልጣን  መያዝ አንችልም፡፡ እኛ ውጊያውን በሁሉም  አቅጣጫ አልደገፍነውም፡፡ አሁንም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ስለሚሰራው ስራም የተሟላ አረዳድ የለንም፡፡
ትግራይን ለማረጋጋት መፍትሔው ምንድን ነው ትላላችሁ?
ከሠላም ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም። ዋናው ሠላም ማውረድ ነው፡፡ ሁሌም የሠላም መንገድ ነው የሚያስፈልገው፤ ምክንያቱም በጦርነት እኮ የሃገር ድንበር ሉአላዊነት ተጥሷል፡፡ ክብር ተዋርዷል፡፡ ህግ  ማስከበር ተብሎ ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ህዝቡ ተጎሳቁላል ተጎድቷል፡፡ ይሔ እንዴት መስተካከል እንዳለበት ለኛ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም ከሰላማዊ መንገድ ውጪ የሚሆን ነገር አይታየንም፡፡
በጊዜያዊ አስተዳደር እየተሳተፉ ያሉ ሠዎች ሳይቀሩ ቅሬታ እየገባቸው እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ይሄ ሄዶ ሄዶ የሚፈጥረው ነገር ጥሩ አይመስለኝም። ጦርነቱ አላለቀም፤  አሁንም አለ፡፡ ህወኃት  የደፈጣ ውግያ እንደገባ እናውቃለን። ይሄ ሆኖ አሁንም ጦርነት እንዳያበቃ ለፕሮፓጋንዳ ይነገራል፣ መሬት ላይ ግን ህዝቡ ላይ ያለው ሠቆቃ በቃላት ሊገለፅ የማይችል ነው፡፡ ጦርነቱ አልቋል፣አየር ላይ የተበታተነ ሃይል ነው የሚባለው ነገር ትክክለኛውን ምስል አያሳየንም፡፡ መሬት ላይ ያለውን እውነት መካድ፤ ወደ ሠላማዊ መንገድ አያደርስም፡፡
እርስዎ የሚሉት ሠላማዊ መንገድ ምንድን ነው? መንግስት ምን ማድረግ አለበት  ነው የሚሉት?
መነጋገር ነዋ! ህዝብ እየተጎዳ፣በረሃብ እየተጎሳቆለ፣ እየተዘረፈ እንዴት ይቀጥላል? ህዝብ እኮ ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅሏል፡፡
በእርስዎ አመለካከት በአሁኑ ወቅት ማን ከማን ጋር ነው የሚነጋገረው?  
የችግሩ መነሻና የችግሩ ባለቤት  የሆኑ ሁሉ መነጋገር አለባቸው፡፡

Read 3575 times