Saturday, 27 March 2021 11:59

በሀገራችን ከ3 ሰዎች አንዱ በኮሮና ቫይረስ ተይዟል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

  • በአዲስ አበባ በአንድ ቀን ብቻ 514 ሰዎች ፅኑ ህሙማን ክፍል ገብተዋል
       • በቫይረሱ የስርጭት መጠን ሲዳማ ክልል ቀዳሚ መሆኑ ተረጋግጧል ከተመረመሩ ሰዎች 67 በመቶ ያህሉ በቫይረሱ ተይዘዋል
             
            የኮቪድ 19 ወረርሽኝ  በአገራችን  በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራጨ ሲሆን በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት አስታወቀ። በአሁኑ ወቅት በአገራችን ከ3 ሰዎች አንዱ በቫይረሱ መያዙንም  መረጃው ያመለክታል።
በአገሪቱ በተደረጉ የኮቪድ 19 ምርመራዎች ቫይረሱ በስፋት ከተገኘባቸው አካባቢዎች መካከል ሲዳማ ክልል ቀዳሚነቱን የያዘ ሲሆን  ከትናንት  በስቲያ ለ165 ሰዎች በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 112 ወይንም 67 በመቶ ያህሉ  በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ድሬዳዋ ቀጣይ ሲሆን ናሙና ከሰጡ 96 ግለሰቦች መካከል 42 ግለሰቦች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል። 43 በመቶ   በኦሮሚያ ምርመራ ካደረጉ 465 ሰዎች 199 የሚሆኑት ወይም 42 በመቶው  ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን በአዲስ አበባ  ናሙና ከሰጡ 5964 ሰዎች 1499 ወይም  25 በመቶው ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተገልጿል።
በአዲስ አበባ የሚደረጉ የኮቪድ 19 የላብራቶሪ ምርመራዎች በማህበረሰብ ቅኝትና ዳሰሳ እንዲሁም ወደ ውጪ አገር ለመሄድ የኮቪድ-19 ናሙና ምርመራ የሚያደርጉ ግለሰቦችን ያጠቃለለ እንደሆነም ኢንስቲቲዩቱ አመልክቷል።
ከማህበረሰብ ተቋም  የተገኘው መረጃ እንደሚመለክተው፤ በአዲስ አበባ ብቻ በአንድ ቀን ውስጥ 514 ሰዎች ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል የገቡ ሲሆን ወደ ህክምና ማዕከላት ከሚገቡ 100 ሰዎች መካከል  79 ያህሉ በተለያየ መጠን ኦክስጅን ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።
ቫይረሱ በከፍተኛ መጠን እየተሰራጨ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባዋል ያለው ኢንስቲቲዩቱ፤ ከሰዎች ጋር ያለንን ርቀት መጠበቅ፣ አፍና አፍንጫን መሸፈንና እጆችን በየጊዜው በሳሙናና ውሃ በመታጠብ ወይም በሳይኒታዘር  በማጽዳት በራስ፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በአገር ላይ ሊደርሰ የሚችለውን ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መከላከል ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብሏል።

Read 11524 times