Saturday, 27 March 2021 11:56

ም/ቤቱ ከህግና ስነ ምግባር ውጪ እየሆነ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(4 votes)

   • “ጥላቻና ግጭትን የሚያባብሱና የፌደሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ጉዳዮች በአባላቱ ተነስተዋል”
   • በም/ቤቱ የሚነሱ ጉዳዮች ከህግ፣ከፖለቲካ ከሞራልና ከሃይማኖት አኳያ የሚገመገም ኮሚቴ አለ
   • ምክር ቤቱ ህዝቡንና መንግስትን በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል
               
             የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አሰራር በሴራ ፖለቲካ መጣሱ ተገለፀ፡፡ ምክር ቤቱ ሰሞኑን ለተፈጠረው የህግና ስነ-ምግባር ጥሰት በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅና በአጥፊዎቹ ላይም እርምጃ  ሊወስድ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ አንድ የምክር ቤት አባል ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ምክር ቤቱ የአባላት ስነ ግባር ደንብን ተከትሎ የሚሰራ ሲሆን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችስ ስብሰባ ከመካሄዱ ከ3-5 ቀን ባለው ጊዜ በፅሁፍ ገቢ መደረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ የአፈ ጉባኤው ፅ/ቤትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በየአጀንዳው ለይቶና አደራጅቶ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ይልካል፡፡ የጥያቄዎቹ ይዘት ከፖለቲካ ከህግና ከሞራል አኴያ ያለባቸውን ችግር የሚገመግምው አስተባባሪ ኮሚቴ ተብሎ የተቋቋመ ቡድን ነው።
ቡድኑ በአሁኑ ወቅት የሚመራው የኦሮሞ ብልጽግና ወኪል በሆኑት አቶ ጫላ ለሚ ነው፡፡
እንደ ምንጫችን ገለፃ፤ የዚህ ቡድን ዋነኛ ዓላማ የምክር ቤቱን አባላት ከመንግስት ፍላጎትና አቋም ውጪ እንዳይሆኑ ማድረግ ሆኖ የቆየ ሲሆን አሰራሩ ቀጥሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በፓርላማ የተደረገውም ይኼ ነው፡፡ በም/ቤቱ አባላት ድንገተኛ ወቅታዊ ጉዳዮችን ማንሳት ጥያቄ ማቅረብ ወይም መወያየት የሚያስፈልግበት ሁኔታ ከተፈጠረም፤ ጉዳዩን ለዚህ ኮሚቴ አስቀድመው ማሳወቅና አጀንዳ ማስያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ከፖለቲካው ጉዳይ በተጨማሪ ህዝቡን ከህዝብ የሚያጋጩ ጉዳዮች በአባላቱ እንዳይነሱ ለማድረግ ነው የሚሉት የም/ቤቱ አባል፤ ሰሞኑን ግን ይህን ጉዳይ በግልጽ የሚጥስና የም/ቤቱ አሰራር በሴራ ፖለቲካ የተተበተበ መሆኑን የሚያሳይ ሁኔታ ተፈፅሟል ብለዋል፡፡ ድርጊቱ ሲፈፀም የም/ቤቱ ጉባኤም ሆነ ገምጋሚ ኮሚቴው ድርጊቱን ለማስቆም ምንም ጥረት አላደረገም ተብሏል፡፡
ይህ ሁኔታ ከህግና ስርዓት ውጪ የተካሄደ በመሆኑ ም/ቤቱ ህዝብንና መንግስት በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ይላሉ የምክር ቤቱ አባላት፡፡ የህዝብ ም/ቤት አባላት ለህሊናቸው ለመረጣቸው ህዝብና ለህገ መንግስቱ ታማኝ መሆን ይገባቸዋል ያሉት ምንጫችን፤ ሰሞኑን በአማራ ክልል የከሚሴ ልዩ ዞን የምርጫ ወረዳዎች የፓርላማ ተመራጭ የሆኑት ሁለት የም/ቤት አባላት፣ ከም/ቤቱ አባላት ስነ ምግባርና ደንብ ጋር የሚቃረኑ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭና ሃይማኖታዊ መካረሮችን የሚያባብስ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ በም/ቤት አባላት ደረጃ የማይጠበቅ ተግባር ከመሆኑም በላይ አጥፊዎች በህግ የሚያስቀጣ  ሲሆን የም/ቤቱን አመራርም ሊያስጠይቅ የሚችል ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የም/ቤት አባላት በምክር ቤቱ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ካወጣው መግለጫ ጋር የሚመሳስል አንደሆነ የገለፁት ምንጫችን ከተፈፀሙ ሰዓታት ብቻ ያስቆጠሩ ጉዳዮችን  በተሳሳተና በተዛባ መልኩ በመቅረባቸውና በዚህ ወቅትም የም/ቤቱ የአመራር አካላ፤ት ምንም አይነት የማስቆም እርምጃ ባለመውሰዳቸው ተጠያቂዎች ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡ ይህም የም/ቤቱን አሰራርና ደንብ ማንም እየተነሳ መጣስ እንደማይችል ሊያሳይና ሊያስተምር የሚችል እርምጃ  ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ ስማቸው የተነሱ ግለሰቦችም ሆኑ የአማራ ልዩ ኃይልን ም/ቤቱ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል ብለዋል፡፡

Read 11459 times