Saturday, 20 March 2021 13:28

"ምህዳራዊ አስተሳሰብ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ"

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      (መቅድም)
የዚህን መጽሐፍ ርዕስ የሚመለከቱ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ተንታኞች በቀዳሚነት የደራሲውን ማንነት ለማወቅ እንደሚፈልጉ እገምታለሁ፡፡ የሙያ ማንነቴን በተመለከተ የዘመናችን በይነ-መረብ ያለብዙ ድካም በቂ መረጃ እንደሚሰጣቸው አምናለሁ። የፖለቲካ ‘የጀርባ ታሪኬን’ በሚመለከት ግን ብዙ እንዳይቸገሩ ስለ ራሴ በጥቂቱ ልግለጽ። የልጅነት ዘመኔ አስተሳሰብ የተቃኘው በአብዛኛው ባካባቢዬ ከምታዘባቸው
ማህበራዊ ጭቆናዎችና በተለያየ ወቅት ከአባቴ ከአቶ መብራቱ በላይ ጋር በማደርጋቸው ጭውውቶች ላይ የተመሰረቱ ነበሩ። ያም ሆኖ፣ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ከአጫፋሪነት የዘለለ ድርሻ አልነበረኝም። በ1966 ዓ.ም በወቅቱ ስሙ ናዝሬት፣ በአሁኑ ስሙ አዳማ በሚገኘው የአፄ ገላውዴዎስ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። ይህንን ተከትሎ የመጣው የእድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ በወቅቱ የነበረኝን የፖለቲካ አመለካከትም ሆነ አጠቃላይ የህይወት እይታ በመሰረታዊ መልኩ የቀየረ ሁነት
ነበረ። ከአስራ ሰባት እስክ ሃያ አንድ ዓመት እድሜዬ ድረስ፣ ከወጣትና የሰራተኛ ማህበር መሪነት እስከ ቀበሌ ሊቀ መንበርነትና የክፍለ ሃገር የፖለቲካ ሃላፊነት የደረሰ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ነበረኝ። በነዚሁ ዓመታት ውስጥ፣ በቀዳሚነት በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ተባባሪነት ሶስት ጊዜና በኋላም በማርክሳዊ ሌኒናዊ ሪቮሉዩሽናዊ ድርጅት (ማሌሪድ) አባልነት ሁለት ጊዜ፣ በአስራ አራት የተለያዩ እስር ቤቶች ቆይታ አድርጌአለሁ። በመጨረሻም፣ የአስር ዓመት እስራት ተፈርዶብኝ፣ በ1975 ህዳር ወር
‘በምህረት’ እስከተፈታሁበት ጊዜ ድረስ በወህኒ ቤት ታስሬአለሁ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበረኝ ንቁና ቀጥተኛ ተሳትፎ በዚሁ አብቅቷል ማለት ይቻላል።
ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ እኔም አንዳንድ የአሁኑ ዘመን ፖለቲከኞችና ተንታኞች ሊወቅሱት የሚዳዱት የዚያ ትውልድ አባል ነኝ። የዚያ ትውልድ እምነትና ጽናት ዋነኛው ምንጭ በወቅቱ የነበረውን ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ጭቆና እና አድልዎ ‘ለምን’ ብሎ መጠየቁና ሁኔታውን ለመቀየር ቆርጦ መነሳቱ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ በየትኛውም ወገን ለተከፈለው መስዋእትነት ታላቅ ክብር አለኝ። በዚያው መጠን ግን፣
የየራሳችንን ፖለቲካ መሪዎች የሚገባውን ያህል ‘ለምን’ ብለን አለመጠየቃችን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለን ይሰማኛል። ምንም እንኳን ሁሉም እስራቶቼ ይህንኑ ጥያቄ ከማንሳቴ ጋር የተያያዙ ቢሆንም፣ የዚያ ትውልድ አባል የሆንን ሁላችንም በበቂ ሁኔታ ባለመጠየቃችን ለተከተለው ቀውስ የየድርሻችንን ሃላፊነት ልንወስድ ይገባል። ከአስር ዓመታት የፖለቲካና የእስር ህይወት በኋላ፣ በ1966 ወዳቆምኩት ትምህርት በመመለስ የኬሚካል፣ ኢንዱስትሪና አካባቢ ምህንድስናን በማጥናት ላለፉት ሰላሳ ሁለት ዓመታት ለተለያዩ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ስሰራ ቆይቻለሁ። እንደመታደል ሆኖ፣ የሙያ ህይወቴም በዘመናችን ገኖ ያለው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት (globalization) በምድራችን የተፈጥሮ ሚዛን ላይ የሚያስከትለውን መዛባት ‘ለምን’ ብሎ በመመርመር፣ ሁሉንም አካታች የሆነ ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ማፈላለግ ላይ የሚያተኩር ሆኗል። በዚህ ሂደትም ውስጥ፣
ውስብስብ ችግሮችን ባግባቡ ለመረዳትና መፍትሔ ለመሻት ምህዳራዊ አስተሳሰብ (systems thinking) ያለውን አበይት አስተዋጽኦ ለመገንዘብና ለመረዳት ችያለሁ።
ዛሬ በሃገራችን ያለውን የፖለቲካ ምስቅልቅል ስንመለከት፣ በቀዳሚነት በማናቸውም ወገን ለሚወሰዱ የፖለቲካ አቋሞችና እርምጃዎች ‘ለምን’ የሚለውን ጥያቄ አንስቶ ከመመርመር ይልቅ አብዛኞቻችን አንድን የፖለቲካ አመለካከት በጅምላና በጭፍንነት መደገፍ ይታይብናል። ጥቂቶች የሚጠይቁ ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ውስብስብ የሆነውን የፖለቲካ መስተጋብር ወደ ጥቂት የአመክንዮ ሰበዞች የማቀናነስ አዝማሚያ
(simplification) ይታይባቸዋል። እንዲህ አይነቱ አዝማሚያዎች በተለይም ወጣቱን በስሜታዊነት በማነሳሳት አስፈላጊ ወዳልሆነ የእልቂት አዙሪት ሲመሩት ይታያሉ። ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ተሳትፎ ባይኖረኝም፣ ‘ለምን’ የሚለውን ጥያቄ ባገኘሁት የተናጠል አጋጣሚ ሁሉ እንደ ዜጋ ማንሳቴ አልቀረም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሃገራችን እየበረታ የመጣው የፖለቲካ ምስቅልቅል እያሳሰበኝ በመምጣቱ፣ በዋና ዋና ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ምሁራዊ ሃሳቦችን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንዳጋራ አድርጎኛል። እነኝህን ጽሁፎች የተከታታሉና በጽሁፎቹ ላይ ተመርኩዞ በጥቂት ሚዲያዎች የቀረቡትን ውይይቶች ያዳመጡ ኢትዮጵያውያን፣ ጽሁፎቹ በመጽሀፍ መልክ ተደራጅተውና ዳብረው ቢቀርቡ አመለካከቱ በይበልጥ ለህዝብ፣ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ተደራሽ እንዲሆን ያደርገዋል የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል።
ይህንን መሰረት በማድረግ የምህዳራዊ አስተሳሰብ ታሪካዊ አመጣጥና ዋና ዋና እሳቤዎቹን በማቅረብና ቀደም ሲል በጋዜጣ የወጡትን ጽሁፎች ይበልጥ በማብራራት በመጽሐፍ መልክ ተደራጅቶ ቀርቧል።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ሃሳቦች በወጣትነት ዘመኔ በነበረኝ የፖለቲካ እይታና በጎልማሳነት ከኖርኩበት የአካዳሚና ዓለም አቀፍ የስራ መስክ በተቀሰሙ የሙያ ልምዶች የተቃኙ በመሆናቸው የራሳቸው ውሱንነት እንደሚኖራቸው እገምታለሁ።
ይህ ውሱንነት እንዳለ ሆኖ፣ በተለይ ወቅቱ ለሚጠይቀው የብሔራዊ መግባባት ውይይት የራሱን ድርሻ ያበረክታል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ በተጨማሪም፣ ወጣቱን ትውልድ ዘመኑን ከሚመጥን የዕውቀት መስክ ጋር በመጠኑ በማስተዋወቅ የምክንያታዊ ጠያቂነት (critical thinking) ባህልን እንዲያዳብር ያግዛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
(ከላይ የቀረበው ጽሁፍ በፕሮፌሰር ደስታ መብራቱ ተዘጋጅቶ ከታተመው ;ምህዳራዊ አስተሳሰብ ለዘላቂ ሃገራዊ መፍትሔ; የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ የተወሰደ ሲሆን የመጽሐፉ የመጀመሪያ ህትመት 1500 ቅጂዎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ቤተመጻሕፍትና የሚዲያ ተቋማት በነጻ የሚሰራጭ መሆኑን ደራሲው አስታውቋል፡፡)

Read 2458 times