Saturday, 20 March 2021 13:20

በቶኪዮ 2020 የኢትዮጵያ ማራቶን ቡድን ምርጫ ዘግይቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)


           ጃፓን በምታካሂደው 32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ  ከፍተኛ ትኩረት ከሳቡ የኦሎምፒክ ውድድሮች  ዋንኛው  ማራቶን ቢሆንም የኢትዮጵያ የማራቶን ቡድን ምርጫ እንደዘገየ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በ32ኛው ኦሎምፒያድ የምታደርገውን ተሳትፎ አስመልክቶ ‹‹ከቶኪዮ እስከ ቶኪዮ›› በሚል ስያሜ ብሄራዊ አሎምፒክ ኮሚቴው ዘመቻ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን በማራቶን ቡድኑ አጠቃላይ ምርጫ ዝግጅት እና አሰራር ላይ ከአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ጋር ተግባብቶ እየሰራ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ታሪክ በማራቶን የተመዘገቡት ውጤቶች ትኩረት መሰጠት በሁለቱ ተቋማት መካከል መግባባት ያስፈልግ ነበር፡፡
ባለፉት 4 ኦሎምፒያዶች የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ማራቶን ቡድን አመራረጥ ብዙ ውዝግብ ውስጥ ሲከት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ዘንድሮም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለቶኪዮ 2020 የማራቶን ቡድን የመጨረሻ ዝርዝር እንዲገባ ያወጣው ማሳሰቢያ በሁለቱ የስፖርት ተቋማት ያለውን ውዝግብ እንዲያገረሽ አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በሰጠው መግለጫ ደግሞ  ለቶኪዮ 2020 የኢትዮጵያን  ማራቶን ቡድንን ለመምረጥ ልዩ የማጣርያ ውድድር መዘጋጀቱ ነው የታወቀው። ምርጥ ቡድን ለመምረጥ ያግዛል የተባለው የውድድር ሃሳብ ከፌደሬሽኑ፤ ከአሰልጣኞቹ፤ ከአትሌቶቹ ማናጀሮች ወይ ከስፖርት ትጥቅ ኩባንያዎች ከማን እንደፈለቀ ግልፅ አይደለም። በታሪክ የመጀመርያው የኦሎምፒክ ማጣርያ በማራቶን ተብሎ ግን በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ታሪክ  ሊጠቀስ ይችላል፡፡  
በመላው ዓለም የሚካሄዱ ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች መሰረዛቸው አትሌቶችን በወቅታዊ ውጤት ለመምረጥ የሚለውን መስፈርት አወሳስቦታል፡፡ የማራቶን ቡድኑ ዝግጅት በየትኛው ከተማ ይካሄድ በሚለው ጉዳይም መግባባት አልተስተዋለም፡፡ አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ሐዋሳ ላይ 18 ምርጥ የማራቶን ሯጮች እንዲዘጋጁ ሲገልፅ የኦሎምፒክ ቡድኑ ሀገረሰላም ላይ ቢሰራ ብለው ሃሳብ ያቀረቡም ነበሩ፡፡ በቶኪዮ 2020 ዝግጅት ላይ የአትሌቶቹ ብዛት፤ የልምምድ መስርያ ከተማ እና የሚያስፈልገው የአየር ንብረት ሌሎችም መሰረታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ግልፅ ነገር አልቀረበም፡፡ ይሁንና ለኦሎምፒኩ የሚደረገው ዝግጅት፤ የተሳታፊ አትሌቶች ዝርዝር ገለፃ እና ውጤታማነት፤ የአዘጋጅ አገር  አየር ንብረት፤ የተፎካካሪ አገራት የዝግጅት ሁኔታ እና አቅም በዝርዝር የተጠና መሆን ይኖርበታል፡፡ በቀሪ የኦሎምፒክ ዝግጅት የኢትዮጵያን ተሳትፎ ከሌሎች አንፃር መገምገም ግድ ይላል፡፡ የሌሎች አገራትን የቡድን አመራረጥ እና ወቅታዊ ስብስብ አነፃፅሮ ማየትም ተገቢ ነበር፡፡
ታላቁ የስፖርት መድረክ በኮቪድ 19 ሳቢያ በአንድ ዓመት መሸጋሸጉ ደግሞ ከሁሉም ኦሎምፒያኖች በተለይ የማራቶን ሯጮችን ጎድቷቸዋል፡፡ አንዳንድ ኦሎምፒያኖች ለኦሎምፒክ ማራቶን እስከ 2 ዓመት የሚዘጋጁ ሲሆን ይህንን የልምምድ መርሃ ግብር ያለውድድር ማራዘም ከፍተኛ የጉልበት ኪሳራ ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች በዓለም የተለያዩ አገራት አለመካሄዳቸውም የሁሉንም ማራቶኒስቶች ኢኮኖሚ አናግቶታል፡፡ በወቅታዊ ብቃታቸው እንዳይቆዩም አድርጓቸዋል፡፡ በጃፓን የኦሎምፒክ አዘጋጅ  ብሄራዊ ኮሚቴም ማራቶንን ከጅምሩ ካሰበባቸው የኦሎምፒክ ውድድሮች  አንዱ ነው፡፡ የኦሎምፒክ ማራቶን የሚካሄድበትን ከተማ የመወሰኑ ሂደት አነጋጋሪ ነበር፡፡  የቶኪዮ  እጅግ ሞቃታማ አየር ንብረት እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል በመባሉ አዲስ የመወዳደርያ ከተማ ለማግኘት ብዙ ምክክሮች ተደርገዋል፡፡ በኦሎምፒክ አዘጋጇ ቶኪዮ ከተማ ላይ የኦሎምፒክ ማራቶን ውድድሮች እንዲካሄድ ብዙዎች ፈልገዋል። በርካታ የስፖርት ባለሙያዎች ግን ውድድሩ ወደ ሌላ ስፍራ እንዲዛወር ጥረት አድርገዋል። በመጨረሻም የኦሎምፒክ ማራቶንና ሌሎች በጎዳና ላይ የሚካሄዱ ውድድሮች ከቶኪዮ በስተ ሰሜን  800 ኪሜ ርቃ በምትገኘው ሳፕፐሮ  ላይ እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለቶኪዮ 2020 ኬንያ በማራቶን የመረጠቻቸውን ኦሎምፒያኖች ካሳወቀች ወር አልፏታል፡፡ በፖል ቴርጋት የሚመራው የኬንያ ብሄራዊ ኦሎምፒክ ኮሚቴው ለማራቶኑ ቡድኑ ዝግጅት የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት ከአትሌቲክስ ኬንያ ጋር በግልጽ አሰራር እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በየጊዜው ከሚሰጠው የሞራል ማበረታቻ ባሻገር የገንዘብ ድጋፍም እያደረገ ነው፡፡ በማራቶን የሚወዳደሩትን የኬንያ ኦሎምፒያኖቹ ዝግጅት ቀለል ባለ መንገድ እንዲካሄድ ጥረት እያደረገ የሚገኘው ብሄራዊ ኮሚቴው፤ የአገሪቱ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የሚያቀርባቸውን ሃሳቦች በመስማት ከአሎምፒያኖቹ፤  ከአሰልጣኞቻቸውና ከማናጀሮቻቸው እየተመካከረም ነው፡፡
የኬንያ ኦሎምፒክ ማራቶን ቡድን የሚመራው የዓለምን ሪከርድ በያዙት ምርጥ አትሌቶች ሲሆን ከእነሱ ጋር በዓለማችን ትልልቅ የማራቶን ውድድሮችን ያሸነፉ፤ ፈጣን ሰዓት ያላቸውና በወቅታዊ ብቃታቸው ውጤታማ ይሆናሉ የተባሉ  በወንዶች 3 በሴቶች 3 የዓለም ምርጥ ማራቶኒስቶች ተይዘዋል፡፡ በወንዶች የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ እና የዓለም ሪከርድ ባለቤት ኤሊውድ ኪፕቾጌ እንዲሁም በሴቶች የዓለም ሻምፒዮኗ እና የዓለም ሪከርድ ባለቤት ብሪግድ ኮሴጊ መያዛቸው ኬንያ በሁለቱም ፆታዎች የሚኖራትን እድል እንዳሰፋው ነው የሚገለፀው፡፡   
የዓለም ማራቶን ሪከርድ የያዘው ኤሊውድ ኪፕቾጌ በቶኪዮ 2020 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ክብሩን በማስጠበቅ ከኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ ጋር ታሪክ ለመጋራት ያነጣጥራል። ኪፕቾጌ ቶኪዮ ላይ አራተኛውን የኦሎምፒክ ተሳትፎ የሚያደርግ ሲሆን በ2004 በ2008 እና በ2016 ላይ በተካሄዱ ሶስት ኦሎምፒያዶች በመሳተፍ 1 የወርቅ ሜዳልያ በማራቶንና በ5ሺ ሜትር የብርና የነሐስ ሜዳልያዎችን አግኝቷል፡፡ በወንዶች ሌሎቹ የኬንያ የማራቶን ኦለምፒያኖች በ2019 የቦስተን እና የቺካጎ ማራቶኖችን ያሸነፈው ላውረንስ ቼሮኖ በማራቶን 11ኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው አሞስ ኪፕሮቶ እና በተጠባባቂነት የተያዘው ቪንሰንት ኪፕቹምባ ናቸው፡፡
በሴቶች የዓለም ማራቶን ሪከርድን ላስመዘገበችው ኬንያዊት ብሪግድ ኮሴጌ ቶኪዮ 2020 በታሪክ የመጀመርያዋን ኦሎምፒክ ተሳትፎ ያገኘችበት ነው፡፡ በ2019 እኤአ ላይ ለ17 ዓመታት ሳይሰበር የቆየውን የራድክሊፍ የዓለም ሪከርድ ያሻሻለችው ብርጊድ የቡድን አጋሮች የሆኑት የዓለም ግማሽ ማራቶን ሪከርድን በፕራግ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ላይ ያስመዘገበችው ፔሬስ ጄፕቼሪር፤ በ2000፣ በ2008፣ በ2012 እና በ2016 እኤአ ላይ በረጅም ርቀት የአምስት ሺ ውድድሮች በመሳተፍ ከፍተኛ ልምድ ያላት ቪቪያን ቼሮይት እንዲሁም በሴቶች ማራቶን 4ኛው ፈጣን ሰዓት ያላት ሩዝ ቼፕቴጊ ናቸው፡፡
በቶኪዮ 2020 ኬንያ 100 ኦሎምፒያኖችን የማሳተፍ እቅድ ያላት ሲሆን ከ80 በላይ ስፖርተኞቿ አስፈላጊውን ሚኒማ በሟሟላት እየተጠባበቁ ናቸው፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት ኬንያ ኦሎምፒኩን የተሳተፈችው በ86 ኦሎምፒያኖች ነበር፡፡

Read 1101 times