Tuesday, 23 March 2021 00:00

የመቀሌዋ የግቢያችን የጦርነቱ ቃል አቀባይ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (brooha3212@
Rate this item
(8 votes)

       ክፍል 7፡ ‹‹ባጫ ደበሌ ተማረከ!!››

https://youtu.be/XRbmhFKRdRw
           
              ህዳር 15 ቀን 2013 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ በምዕራባዊ ትግራይ ዞን «ማይካድራ» ከተማ የተፈፀመውን የጅምላ ጭፍጨፋ ማጣራቱንና የመጀመሪያ ዙር ሪፖርት ማጠናቀሩን ገለፀ። ኮሚሽኑ በሁለት ዙር ባደረገው ማጣራት፣ ህወሓት በዳንሻ መሸነፉን ተከትሎ በወሰደው የቂም በቀል ጥቃት፣ በአጠቃላይ 1200 የአማራ ተወላጆች በህወሓት ሚሊሽያና ሚሊሽያው ባደራጃቸው «ሳምሪ» በሚባል የትግራይ ወጣቶች ቡድን አማካኝነት ጭፍጨፋውን መፈፀሙንና ይሄም ቡድን ጩቤ፣ ካራ፣ ገጀራ፣ ፋስ፣ መጥረቢያ…  የመሳሰሉ መሳሪያዎችን መጠቀሙን ገለፀ፡፡
ህዳር 16 ቀን 2013 ማታ፣ መንግስት ለትግራይ ልዩ ኃይል አባላት በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ የሰጠው ሁለተኛው የ72 ሰዓታት የጊዜ ገደብ ማብቃቱን ገለፀ።
በዚሁ ዕለት፣ በሌላ ዜና፣ «ህወሓት ማይካድራ ላይ የፈፀመውን ዓይነት ጭፍጨፋ መቀሌ ላይም ለመፈፀም መዘጋጀቱን መረጃዎች ደርሰውኛል» ሲል መከላከያ ኃይል በኢቲቪ ተናገረ፡፡ ይሄም በመቀሌ የሚኖሩ የሌላ አካባቢ ተወላጆችን  ስጋት ላይ ጣላቸው።
መረጃው እኔንም እጅግ አስፈራኝ!! ይሄንን ነገር እኔም አስቀድሜ ሳስበው የነበረ ቢሆንም በየቀኑ በማደርገው ክትትል ግን ምንም ዓይነት ምልክትም ሆነ ፍንጭ ህዝቡ ላይም ሆነ ወጣቱ ላይ አላየሁም፡፡ የመቀሌ ህዝብም ሆነ ወጣት ‹‹ፀረ-መጤ›› የሆነ ሥነ ልቦና የለውም፤ ትንሽም እንኳ ቢሆን የለውም!! ይሄ ነገር አረጋጋኝ፡፡ ሆኖም ግን፣ ለማንኛውም ብዬ ሁኔታውን ለአከራያችን ልጅ ነገርኩት፡፡ እሱም፤ ‹‹እንደዚህ ዓይነት ነገር መቀሌ ላይ አይኖርም፤ የሚኖርም ከሆነ እነ ፋዘር ቤት እንድትደበቅ እናደርጋለን፤ አታስብ›› በማለት አረጋጋኝ፡፡
የማይካድራው ጭፍጨፋ በመንግስት ቴሌቪዥኖች ደጋግሞ መታየቱ ግን ህዝቡን ረብሾታል፤ «ትግሬ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል እንዳይኖርና ተዘዋውሮ እንዳይሰራ የሚያደርግ ነው፤ መንግስት በትግሬና በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ጥቁር መጋረጃ እየጋረደ ነው» የሚል ስጋት ውስጥ መግባት ጀመረ፤ ህዝቡ። በሌላ በኩል ግን፣ «ትግሬ እንደዚህ ዓይነት አረመኔያዊ ድርጊት አይፈፅምም» የሚሉ ተመፃዳቂዎችም አሉ።
ህወሓት ያመጣብን የዘር ፖለቲካ ካስከተለብን በርካታ ጦሶች መካከል አንዱ፣ ተመፃዳቂ ብሔርተኞች፣ የራሳቸውን ብሄር አባላት በሙሉ አንድ ዓይነት አድርገው፣ እንደ አንድ የሞራል ህላዌ (ብሔርን እንደ አንድ የሞራል ግለሰብ) ቆጥረው  የማቀንቀናቸው ነገር ነው፡፡ አማራ እንደዚህ ነው፤ ትግሬ እንደዚህ ነው፤ ኦሮሞ እንደዚህ ነው…እያሉ ለአንድ ብሔር አባላት በሙሉ አንድ የሞራል ኮድ ይሰጣሉ፡፡ በእያንዳንዱ ብሔር ውስጥ ብዙ ዓይነት ባህሪ፣ ብዙ ዓይነት የሞራል ደረጃ ያላቸው ግለሰቦች አሉ፤ እያንዳንዱ ብሔር በውስጡ ሩህሩህና ጨካኝ፣ ታማኝና ሌባ፣ ለሌሎች የሚያስብና ራስ ወዳድ፣ ለጋስና ንፉግ፣ ሰብዓዊነት የሚሰማቸውና አረመኔዎችን በውስጡ ይዟል፡፡ በመሆኑም፣ አንድ ብሔር በአንድ የሥነ ምግባር ደረጃ ሊገለፅ አይችልም፡፡
እነዚህ ተመፃዳቂ ብሔርተኞች፣ የአንድን ብሔር አባላት በሙሉ በአንድ የሞራል ደረጃ በመግለፅ፣ የእነሱ ብሔር እንከን የለሽ የሞራል ፍፁምና ላይ የደረሰ ህላዌ አድርገው ይስሉታል፡፡ ይሄም ማለት ኦሮሞ/ትግሬ/አማራ…አይዋሽም፣ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት አይፈፅምም፣ የሰው ላብ አይቀማም፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው ህዝብ ነው…እያሉ በጥቅሉ ይገልፁታል፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ጊዜ ጃዋር መሐመድ ስለ ቄሮ ሲናገር፤ ‹‹ቄሮ በሥነ ምግባር የተኮተኮተ ነው›› ብሎ ነበር። ጃዋር ይሄንን ያለው ቄሮን ልክ እንደ አንድ ግለሰብ በመውሰድ የሞራል ፍፁምና ላይ የደረሰ አንድ የሞራል ህላዌ አድርጎ ስላሰበው ነው፡፡ ብሔር የግለሰቦች ስብስብ ነው፤ ልክ ‹‹የጋራ አእምሮ፣ የጋራ ልብ፣ የጋራ ሳንባ…›› የሚባል ነገር እንደሌለው ሁሉ፣ ‹‹የጋራ ሞራሊቲ›› የሚባል ነገርም የለም፡፡ ሞራሊቲ የግል ነው፤ የሞራል ኮድን የሚሸከመው ወደ ሌላ ወደ ምንም የማይከፈለው የህብረተሰብ የመጨረሻው ክፋይ የሆነው ግለሰብ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም፣ አንድን ማህበረሰብ ወይም ብሔር በአንድ የሞራል ኮድ መግለፅ አይቻልም፡፡
ህዳር 17 ቀን 2013 ጠ/ሚ ዐቢይ በፌስቡክ ገፃቸው (ኢቲቪ እንደዘገበው)፤ በትግራይ ክልል ህግን የማስከበሩ ዘመቻ 3ኛው ምዕራፍ መጀመሩንና በህዝብ ላብ የተገነባችው መቀሌ ከተማም ከፍተኛ ጉዳት እንዳይደርስባት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ገለፁ። ይሄም ንግግራቸው ‹‹መቀሌ ላይ የአየር ድብደባ ለመፈፀም እንዳሰቡ ያሳያል›› በማለት ህዝቡ መረበሽ ጀመረ። ሆኖም ግን፣ ምንም ዓይነት የአየር ድብደባ አልነበረም፡፡ በሌላ በኩል፣ የትግራይ ልዩ ኃይል ጥይት መጨረሱ በመቀሌ ከተማ መወራት ጀመረ።
ቃል አቀባያችን ዛሬ ኩምትር ብላለች፤ አነጋገሯ ከሌላው ቀን ለዘብ ብሏል፤ ንግግሮቿ ከአጥቂነት ወደ ተከላካይነት፤ ከድል አድራጊነት ወደ ተስፋ መቁረጥ አዘንብሏል፣ ‹‹መከላከያ ሰራዊት ስንቅ ስላለቀበት ሰራዊቱ በርሃብ ተበታትኖ ወደ መቀሌ እየመጣ ነው፤ እንዳትወጡ በራችሁን ዘግታችሁ ቁጭ በሉ ተብሏል፡፡ ደግሞም መከላከያ መቀሌ ቢገባም ጌታቸው አሰፋን ማንም ስለማያውቀው ሊይዙት አይችሉም፤ መስሏቸው ነው እንጂ እሱ አሁን ያለው አዲስ አበባ ነው። የትግራይን ህዝብ የሚያድነው እሱ ነው።… ለነገሩ እኔ ምን አገባኝ፣ ያሸነፈ ይግዛ፤ ብቻ ሰላም ይሁን፡፡›› ቃል አቀባያችን ያ የድሮ ወኔዋ የለም፤ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ወሯታል፡፡
ቃል አቀባያችን በዚህ ሁኔታ እያለች መርማሪ ፖሊሱ ባሏ መጣ፤ ተከትላው ወደ ቤት ገባች፡፡ ትንሽ ቆይተው ቃል አቀባያችንና ባሏ መጨቃጨቅ ጀመሩ። ባሏ ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት ወስኖ ነው የመጣው፡፡ መከላከያ አዲግራትን ከያዘ በኋላ የመቀሌ ፖሊሶችና ሚሊሺያዎች እንዲዘምቱ ጥሪ ቀርቦላቸው ብዙዎቹ ሄደዋል፡፡ በከተማው የቀሩት ደህንነቶችና መርማሪ ፖሊሶች ብቻ ናቸው፡፡ እነሱም ግን አሁን ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ እናም ባለቤቷ ወደ ቤት የመጣው ሚስቱን ሊሰናበታት ነው፡፡ እሷ ግን ‹‹ነግሬሃለሁ እንዳትሄድ! የምትሄድም ከሆነ ፍታኝና ሂድ›› እያለች ተማፀነችው፡፡ እሱ ግን በሚስቱ ተማፅኖ መመለስ አይችልም፤ ምክንያቱም ደጅ ላይ ጓዶቹ በመኪና እየጠበቁት ነው፤ ወደ ቤት ያመጡትም ‹‹ሚስቴን ልሰናበት›› ብሎ ነው፡፡ እናም ለቅሶዋን እያየ ትቷት ሄደ፤ ሳይመለስ በዚያው አደረ፤ ማታ ስልክ ስትደውልለትም ስልኩ አይሰራም፤ በድጋሚ አነባች፤ በእንባ በርበሬ የመሰለ ዓይኗን ይዛ እናቷ ጋ ለማደር ሄደች፡፡
ህዳር 18 ቀን 2013 ጠዋት በመንግስትም ሆነ በትግራይ ቴሌቪዥን ምንም የተወራ ነገር ሳይኖር የመቀሌ መንገዶች ግን በጣም ጭር አሉብኝ። የሰፈራችን ሽማግሌዎች ያለ ወትሯቸው ጋቢያቸውን ለብሰው ከግቢያቸው ውጭ ተሰባስበው ማውራት ጀመሩ። ወጣት ወንዶች ለብቻ፣ ሴቶችም ለብቻ ከግቢ ውጭ ተሰባስበው ያወጋሉ። ህዝቡ ላይ የሚታየው ጭንቀት ያስፈራል፤ ሁሉም ተደብተዋል፤ ድባቡ በጣም ይከብዳል። መኪኖችም በየቤታቸው ተሰትረው አስፋልቱ ጭር ብሏል። ታክሲዎች የሚያልፉት በጣም አልፎ አልፎ ነው። ከቀኑ 07:30 አካባቢ ከርቀት አንድ የመድፍ ድምፅ ከመሰማቱ ውጭ መቀሌ ላይ ዛሬም ሆነ ሰሞኑን ምንም ዓይነት የተኩስ ድምፅ ባይሰማም ፍርሃት ግን በከተማው ነግሷል።
ደጃችን ላይ ጉሊት የምትቀመጠው ወ/ሮ ዛፉም፣ አስፈሪውን ድባብ በመመልከት፣ ሽንኩርቷን ይዛ ወደ ቤቷ ገባች፤ አከራያችን እማማ ፃድቃንም ህወሓት በማህበር አደራጅቶ የሰጣቸውን ወፍጮና ሻወር ቤት ዘግተው ወደ ቤት መጡ። ሊስትሮዎች እቃቸውን ሸክፈው ወደየቤታቸው ሄዱ። ሱቆች፣ ፋርማሲዎች፣ ሱፐርማርኬቶች ተዘጉ፤ ድባቡ እጅግ ያስፈራል። ማታ ላይ ኢቲቪ፣ መከላከያ መቀሌ ዙሪያውን መክበቡንና የህወሓትን ከፍተኛና የመንደር አለቆችን ለመያዝ እየተጋ መሆኑን ዘገበ። በልቤ ‹‹አሁን የተፈራው ሰዓት ደረሰ›› አልኩ፡፡
በዚህ አስፈሪ ድባብ ውስጥ ነበር ቃል አቀባያችን በነጋታው ጠዋት ወደ ተከራየችበት ቤት የመጣችው፡፡ ቤት ገብታ የባሏን ፎቶ ስታየው እንደገና ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡ የግቢው ሰው ሁሉ ተሰበሰበ፤ አፅናንቷትም ወደየ ጉዳዩ ሄደ፡፡ ለቅሶዋን እንደምንም አስታግሳ የባሏን ፎቶዎችና የፖሊስ ዩኒፎርሞች በማዳበሪያ ሰብስባ ወደ እናቷ ቤት ወሰደቻቸው።
ህዳር 19 ቀን 2013 ጠዋት የመቀሌው የከተማ ጦርነት ተጀመረ። ህወሓት ከመቀሌ ሆኖ ዛሬ ጠዋት ከ02:00 እስከ 03:00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሰባት መድፎችን ተኮሰ። በዚህ ጊዜ ውስጥ መከላከያ የመድፍ አፀፋ የሰጠው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው። እንዲያውም፣ አንደኛው መድፍ እኛ ካለንበት ሰፈር አልፎ ‹‹አዲሽምዱን›› የሚባለው አካባቢ ወድቆ ሰዎች እንደሞቱ ተወራ፡፡ የአምቡላንስና የእሳት አደጋ መኪናም በእኛ በኩል አልፎ ሲሄድ ሰማን፡፡ ከዚህ በኋላ ህወሓቶች ከመቀሌ ሆነው መተኮስ አቆሙ፣ መከላከያም ለጊዜው አፀፋ መስጠት አቆመ።
ትንሽ ቆይቶ ግን የመከላከያ የመድፍ ተኩስ የመቀሌን ሰማይ እያረሰው ማለፍ ጀመረ፡፡ ድምፁ እጅግ አስፈሪ ነው፡፡ ህዝቡም ፈርቶ በየዘመዱ ተሰባሰበ፣ አብዛኛዎቹ ሰዎች ግን ወደ  ቤተ ክርስትያንና የፎቆች ስርቻን (underground) እየፈለጉ መደበቅ ጀመሩ። ከእኛም ግቢ አንዳንዶቹ ልጆቻቸውን ይዘው underground ተደበቁ፤ ቃል አቀባያችን እናቷ ጋ እንደሄደች ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የትግራይ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞቹን ሁሉ አጥፎ የህወሓትን የትግል ዘፈኖች ብቻ እያስተላለፈ ነው፤ ዛሬ ሰበር ዜና የለውም። ትንሽ ቆይቶም ስርጭቱን ሙሉ በሙሉ አቆመ፡፡
ከቀኑ 06:00 አካባቢ ካፊያ ዝናብ መዝነብና ሰማዩም ነጎድጓድ ሲጀምር የመድፉም ድምፅ ጋብ አለ። የተፈራው የአየር ድብደባም አልነበረም፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ከኢንተርኔት በስተቀር መቀሌ ከተማ ላይ (ብቻ) ስልክ፣ መብራትና ውሃ አልተቋረጠም ነበር። ሌላው ነገር ግን (ትራንስፖርት፣ ሱቆች፣ ባንኮች፣....) ሁሉ ተዘግተዋል።
እኛ እንደዛ በፍርሃት ተኮማትረን ባለንበት ሰዓት ከቀኑ 08:20 ላይ በድንገት ከተማው በጥይት እሩምታ መናወጥ ጀመረ፤ ወዲያው የሰዎች ጩኸት ይሰማ ጀመር። ጩኸቱም በአይሱዙና በሲኖ ትራክ ላይ የተጫኑ ወጣቶች ናቸው፤ ጩኸት፣ ፉጨትና ተኩስ እያሰሙ በብዛት አለፉ። የት እንደሚሄዱ አላወኩም፤ ምናልባት ወደ ጦር ግንባር እየሄዱ ይሆናል ብዬ ገመትኩ። ልክ ከቀኑ 09:00 ላይ የግቢያችን በር ተንኳኳ። አከራያችን እማማ ፃድቃንም ቀስ ብለው ሲከፍቱ በእሳቸው ዕድሜ የሚገኙ ጎረቤታቸው እማማ ብርክቲ ነበሩ።
«ምነው ብርክቲ?» አሉ እማማ ፃድቃን፤  
«የምትሰሚው የወጣቶች ጩኸትና ጥይት እኮ የደስደስ ነው፤ በራያ ግንባር ባጫ ደበሌ ከ11 ታንኮች ጋር ተማረከ!! ኢሳያስም ሞተ፤ ልጁ ገደለው» አሉ እማማ ብርክቲ፤ በደስታ እይናቸውን እያበሩ።
እማማ ፃድቃን በደስታ ዘለሉ፤ እጃቸውን እያወናጨፉና በደስታ እየተፍነሸነሹ ግቢዋን ተመላለሱባት።  ደስታው የከተማዋን ህይወት ዳግም መለሰው። ሰው በደስታ ከየቤቱ እየወጣ ማውራት ጀመረ። ፀጥ ያለው መንገድ መኪና ይመላለስበት ጀመር፤ ሰው የራበው ሰፈራችን በአንድ ጊዜ ሰው ፈሰሰበት። ፍርሃት ተገፈፈ፣ ተስፋ ተመለሰ፣ ህይወት ለመለመ። underground ተደብቀው የነበሩ ሰዎች እየወጡ ወደየ ቤታቸው ሄዱ። ዜናው እውነትም ሆነ ውሸት ግድ የለኝም፤ ውሸትም እንኳ ቢሆን የመኖር ተስፋዬን አለምልሞታልና ዜናውን በደስታ ተቀበልኩት፤ ደግሞም አጣጣምኩት፤ የመኖር ተስፋ ማግኘት በጣም ደስ ይላል፡፡ ይሄ በሚሆንበት ሰዓት ግን ከመቀሌ ሲተኮስ የነበረው መድፍ ቆሞ ነበር።
(ይቀጥላል…)



Read 8153 times Last modified on Wednesday, 24 March 2021 07:52