Saturday, 20 March 2021 12:32

“የመደመር መንገድ”ን እንዳነበብኩት

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

    መጽሐፉን-ገለጥ እያደረኩ ሳየው ዜማ ያላቸው፣ ግጥማዊ ንዑስ ርዕሶች፣ በዓይኔ ፊት ሲደንሱ ነፍሴ ማለለች። በየመግቢያው እንደኔ ግጥም ለሚወድድ ሰው፣ ስሜት ኮርኳሪና  ሀገራዊ ስንኞችም ወረቀቱ ላይ ተቃቅፈው ክራር ይመታሉ። … “የመደመር መንገድ” እንደ ቀድሞው “መደመር” እሾህ የተጠቀጠቀባት ጽጌረዳ ሆና እንደማትወጋኝ፣ ግን በውበትና በጥሩ መዓዛ ነፍሴን ልታረካ፣ መንፈሴን ልታድስ ትችላለች ብዬ ጓጓሁ።
እናም ጥርጣሬዬ እንደ ጉም እየበነነ፣ ውስጤ እየተፍነከነከ፣ በጉጉት ልቤን እያላመጥኩ፣ እንደ ጎርፍ ሊያንከባልለኝ ሲል ልጓም እያበጀሁ (ግጥምና ጠላት እያልኩ) ማንበቤን ቀጠልኩ። ስክን ብሎ ይፈስሳል፣ አንዳንዴም በስሜት ከድንጋይ እንደሚላጋ ጅረት እየዘለለ  ይጋልባል። እጅግ በተለየ የቋንቋ አጠቃቀምና የገለጻው ብቃት በእጅጉ አስደመመኝ። በዚህ ላቅ ያለ አቀም ያላቸውን እጅግ ጥቂት ደራስያን አስታወሰኝ። ፀሐፊው ረዥም ልብወለድ (ኖቬል) የሚጽፉበት ጉልበት እንዳላቸው ብዙ ቦታ ልብ አልኩኝ።… ጥሎብኝ ውበት እወዳለሁ፣ ለእውነት እሰግዳለሁ!
በተለይ “በሻሻ ኦልማፍ ገሊን ብለሽ” የሚለው ንዑስ ርዕስ መሰጠኝ። እንዳች ኪናዊ ስልት በውስጤ ለኩሶ ሁለተንናዬን እንደ ሻማ ሲያቀልጠው ማመን እያቃተኝ ነበር። የዚህ ዓይነት ስሜት የተሰማኝ፣ገና ልጅ እያለሁ በዐሉ ግርማ በ”ሀዲስ” ላይ ስለ ሱፔ በጻፈው ትረካ ላይ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ የተስፋዬ ገብረአብን “የደራሲው ማስታወሻ”ን ባነበብኩበት ጊዜ ነበር።
እዚያው ገጽ ላይ “ጂማን አትበይ እንዳይቀድምሽ ቀኑ፣
በሻሻና አጋሮ ሄድሽ ወይ ለመሆኑ!” የሚለው መንቶ ግጥም አለ።
ግጥም ስሜት ያጭራል፤ የዘይቤ ልዕቀት ደግሞ ለነፍስ ክንፍ ይቀጥልለታል። ሰማዩን ያቀርባል፣ ውበትን ይፈተፍታል!...
እናም በዚሁ ገጽ 182 ላይ በዓይኔ በብረቱ ያየኋትን በሻሻን እንዲህ አነበብኳት፡-“ከከበቧት የጎማ ዛፎች መካከል በዝምታ የተጋመችው የገጠር ከተማ በሻሻ፣ በዘመን ሐዲድ ላይ ለዘመናት አያሌ ታሪኮችን አስተናግዳለች። በበጎውም በክፉውም የምታስታውሳቸው እልፍ የታሪክ ኩነቶችን አንዴም በሳቅ፣ ደግሞም በእሮሮና በልቅሶ አስተናግዳ ሁሉን እንዳመጣጣቸው አሳልፋቸዋለች። የብዙ እሴት ማዕበሏ፣ የብሔርና እምነት ውብ ጥበብ መሸመኛዋ ትንሿ በሻሻ፤ የብዙሃንነት ቅይጥ ውብ መልኳ ከፊቷ ይነበባል። ከዚህች ዝም ካለች ሙዳይ ውስጥ ሕይወት በዝግታ ትፈሳለች። አረንጓዴ ለብሳ፣ አረንጓዴ ሆና ዓመትን ከዓመት የምትገጥመው በሻሻ፣ የሳምንቱን ቀናት በአርምሞ ውስጥ ብዙ ተመስጦ፣ በርጋታዋ ውስጥ ብዙ አስተውሎት እየደመረች መሽቶ ይነጋል።
እዚህ ጋ ውበቱ ጣፋጭ፣ ተምሳሌቱ ድንቅ ነው። በተለይ ስለ ገበያ ቀን ቀጥሎ የተጻፈው ማሳያ ብዙ ከመተንተን፣ በቴሌቪዥን ጆሮ ከመውቀጥና ነፍስ ከማባተት፣ “መደመር” ምን እንደሚመስል የግጥም ምሰላ /Imagery/ በመሰለ ጥበብ በቀላሉ ያስረዳል።
የመጽሐፉ አተራረክም እንደ ጥንታዊ ስነ-ጽሑፍ ከውልደት አለመጀመሩና ከለውጡ ጥንስስ ጀምሮ ወደ ኋላ በምልሰት ወደ ከዋኙ ሕይወት መሄዱ እንዲጥም እንዳይሰለች አድርጎታል። በየመሀሉ የአርትዖት ችግሮች የፈጠሩት የአንቀጽ አገባብ፣ የዐረፍተ ነገሮች አደረጃጀትና የአያያዦች ችግር ቢኖርዎ፣ መልዕክቱን በውበት ማስተላለፍ እንዲችል ተደርጎ የተጻፈ በመሆኑ ምቾት አይነሳም። በተጨማሪም በዚህ ሁሉ የሀገር ነውጥ ውስጥ እንዴት፣ በየትኛው ጊዜ ጻፉት? የሚለው ጥያቄ፤ አድናቆት ፈጥሮብኛል።
መጽሐፉ ሲጀምር “ቤተኛው ባይተዋር” ብሎ ኢሕአዴግ ድንኳን ውስጥ ስላደጉት የአንድ ቤተሰብ ልጆች ልዩነት በምሳሌ ያቀረቡበት መንገድ በእጅጉ ተመችቶኛል። በግሌ ታሪኩን ባነብበውም ከቤተሰብ ጉዳይ አልፌ አስቤው ስለማላውቅ የዚህኛው ግጥምጥሞሽ አስደስቶኛል።
“ሰሚ ፍለጋ” የሚለው በፓርቲ ውስጥ የቆረቆራቸውን ሀሳብ ለማካፈል ጆሮ የተራቡበትን ዘመን የሚያስታውስ ሲሆን፣ ቀጣዩ ንዑስ ርዕስም ከዚሁ ጋር ተያያዞ ባልንጀራ ፍለጋ፣ ሕልምን የማጋራት ናፍቆት፣ ተስፋ ፍለጋ የምትንከራተት ነፍስ ያሳያል። ለውጡ እንዴት እንደተፀነሰ፣ እየረገፈ የመጣው የኢሕአዴግ ውበት ቅጠሉ እየወደቀ፣ አበባው ቀለም እያጣ፣ ወደ ፍሬ መሻገር ሲያቅተው፣ ግንዱ ሳያወድቅ፣ ስሩ ሳይነቀል፣ የሚድንበትን መንገድ በማሰስ ያሳተፉትን መንገድ ያሳያል።
ሰውየው፣… ብዙ ፈተናዎችን፣ ሲዘለሉ የማይችሉ አጥሮችን ፣ ግራ አጋቢ ውሳኔዎችን፣ አልፈዋል። “ሚዛን መጠበቅ” በሚለው ንዑስ ርዕስ፤ ሕውሃት ጣሪው ላይ በተፈናጠጠችበት ዘመን የተሰጠን ትዕዛዝ በእምቢታና በጥንቃቄ ፍትህን ለማቀፍ እጅ መዘርጋት በእጅጉ ቁርጠኝነት የሚጠይቅና የሚያስፈራራ የሞት  ጥርስ ላይ ዥዋዥዌ የመጫወት ያህል የሚዘገንን ነው። “መሞት የለበትም” ያሉትን፣ ለሞት በማያበቃው ጥፋት፣ ይገደል!” የተባለውን የኦነግ አባል ለመታደግ የወሰዱት እርምጃ የሚያስደምም ነው።
ከሙሉ መጽሐፉ ውስጥ በእጅጉ ቀልቤን ከነዙት ምዕራፎች ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነት አስፈላጊነት የሚገልጠው “ኑ እንዋቀስ!” የሚለው ንዑስ ርዕስ ውስጥ የሚነዝር ስሜት ይፈጥራል።… አንድ ከመሆን ይልቅ ለምን መለያየት እንመርጣለን? የሚለውን ጥያቄ ይዞ የሚፈስሰው ሀሳብ ውስጥ “ባልና ሚስት ትዳራቸው እንዴት እንደሚሰምርና ብልፅግና የተሞላ ህይወት ስለመኖር እንጂ ስለ መፋታት ማታ ማታ እይመክሩም” የሚለው ሀሳብ አሁን ወዳለንበት የተከፋፈለ ልብ ያመጣና ይወቅሰናል።… ክፍሉ ብዙ ግሩም የሚባሉ ማሳያዎችም አሉት። የተለያዩና ታላላቅ የሚባሉ ሀገራትን አመሠራረት እያነሳ በእጅጉ ከእኛ በባሰ ሁኔታ ተመስርተው፣ ግን ደግሞ ዛሬ ወደኋላ እያዩ እንደማይናከሱ በማንፀር አሳማኝ መፍትሔ ይጠቁማል።
በተለይ የቀደሙ አባቶቻችን ላይ ቅር የምንሰኝባቸው ነገሮች ቢኖሩ እንኳ በሀገረ መንግስት ግንባታው የተሻለ መንገድ መሄዳቸወን እንድናደንቅ የሚደርገንን ነገር በአፅንዖት አስቀምጧል። እስቲ ይህቺን ዐረፍተ ነገር እንዋስ፡-
አባቶ ከየትም ይምጡ ከየት የተከተሉትን መንገድ ላንስማማበት እንችላለን እንጂ የራሳቸውን “ብሔር” የሀገራቸው ስም ባለማድረጋቸው ግን የሚያስመሰግናቸው ነው- ይላሉ። ሌሎቹ ግን ለምሳሌ ቢሊቪያ በስምዖን ቦሊቫር፣ አሜሪካ በአሜሪጎ ቬስቱስ መጠራታቸውን በመጥቀስና ሌሎችንም ጉድለት በማስታወስ እኛ ግን “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስያሜ ከማንም ብሔር ስያሜ ጋር ባለማያያዛችን የቴሻልን የታሪክ መንገደኞች እንደሆንን ልንቆጥር እንደሚገባሉ ያሳስባሉ።
ምዕራፍ ሁለት “የፖለቲካ ትግል” ይልና ከስሩ፡-
ፋኖ ተሰማራ
እንደ ሆቺ ሚኒ፣ እንደ ቼጉቬራ።
በማለት በተማሪዎች ንቅናቄ መዝሙር አጅበው ወደ ዋና ሀሳቡ ይወስዱናል። በእዚህ ክፍል እስራኤልና ቻይና ማሳያቸው ናቸው። የእስራኤሉ ሃሳብ፣ ከቅዱስ መጽሐፍ ሀሳብ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ የቻይናው ጉዳይ ወደ እነ ማኦ ዜዱንግ አብዮት ዘመን ይወስደንና የቀዩን ጦር እልህ አሥጨራሽ ፍልሚያ ያመላክተናል። እናም ለውጥና ነውጥ ይዘዋቸው የሚመጡትን አበሳ ፍለጋ፣ ሽንቁር ማሳደድ ግድ እንደሚል ይጠቁማሉ።
የኛ ምርጫ ግን ሰላማዊ ትግል ነው ባይ ናቸው። ይህ ሀሳብ መጽሐፉ ውስጥ በተደጋጋሚ ይነሳል። ማርቲን ሉተር፣ ኪንግ፣ ማህተማ ጋንዲ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ሮዛ ፓርክስ ወዘተ ይጠቀሳሉ። ወደ እኛ ሀገር ስንመጣ ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ  ማሳያ ሆነው ተቀምጠዋል።
ለምሳሌ ስለፕሮፌሰር መስፍን ገጽ 72 ላይ እንዲህ አስፍረዋል፡- ዛሬም እንደ ትናንቱ  የመሳሪያ ትግልን ይጠየፋሉ። ዛሬም እንደ ትናንቱ ከወጣቶች  ቢበልጥ እንጂ በማያንስ መልኩ በየጋዜጣው ይሞግታሉ፤ የተሳሳተውጥ ነቅስው ይተቻሉ። መንግስትን ለማስተካከል መሳሪያ ሳይሆን ብዕር አንስተው በሃሳብ ይፋለሙታል። ህዝቡንም ሳያፈሩና ጥፋትህን አርም ብለው ይሞግቱታል። ፊት አይተው ሳያዳሉ ግፋና እየተቃወሙ ፣ ስህተት ውስጥ ያሉትን እያስተማሩና እየገሰጹ ፣ በስድብና በማንጓጠጥ ሳይበገሩ ዘልቀዋል።
ይህ ገፅ  የአርትት ችግር ገጥሞት የሚያበሳጭ መሆኑን ግን ሳልገልፅ ማለፍ አልፈልግም። ከፍተኛ ብልሽት የገጠመውና በቀጥታ የተደጋገሙ ሃሳቦች ያሉበት ነው።
ስለ ሰላማዊ ትግል ባነሱበት ክፍል ውስጥ የወጣቶችን የትግል ሚና ለማንሳት ወደ ኋላ ታሪካችን ዘግነው መትተው እስካለንበት  ዘመን ዘልቀዋል። በኢሕአፓ በመኢሶን፣ በሕወሐት ወዘተ የነበሩትን ወጣቶች ይጠቅሳሉ። የሁሉም ዓላማ አንድ ባይሆንም ጭቆናና “እምቢ ባይነት” ነው ይላሉ።  ከነዚህም መካከል ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ አቤ ጉበኛን የመሰሉ ደራሲያንን የትግል ድርሻ ያወሳሉ።
ወደ አሁኖቹ  ሲመጡ የዘመናችንን ትግል በዚህ መልክ አይተውታል። እንግዲህ ወጣትነት ነጻነት ይመጥነናል፤ ይገባናልም፤ ብለው እሳት በታጠቀ ሰራዊት ፊት የተጋፈጡት እልፍ ቄሮና ፋኖዎችን ይመስላል። ወጣትነት ሚሊዮኖች ለእሬቻ በታደሙበት አደባባይ ከተቀባበለ ከላሽ፣ ካፈጠጠ ወታደር፣ ዓይኑ እሳት ከሚተፋ ባለ ስልጣን፣ ከተወደረ የሚዲያ ካሜራ ፊት “ዳውን ዳውን ወያኔ!” ለማለት የጀገነውንና ትግሉን ያቀጣጠለወን ገመዳ ዋሪኦን ይመስላል… ይላሉ።
ስለ ወጣቶቹ ባነሱት ክፍል ግን የወጣቶች እንቅስቃሴ ብለው የፈረጁት የተማሪዎችን ትግል ብቻ መሆኑ፣ ነገሩን ያለማስተዋል ወይም ባንድ ወገን ያለው ላይ ብቻ ማተኮር የፈጠረው ችግር የሚመስል ነገር አለ። ወታደራዊው መንግስት የወጣቶቹን ትግል ነጥቆ ስልጣን ላይ ፊጥ አለ ቢሉም፣ የረጉ አባላትም በራሳቸው ርዕዮት ለትግል የቆሙ ወጣቶች መሆናቸው የተዘነጋ ይመስላል (ገጽ 56)
ብዙ ስፍራዎች ላይ የሚታየው የትረካ አንጻር ችግር፣ እዚህ ክፍል ውስጥም አለ። የወጣትነት ትግል ይዘው ብዙ ካወጉን በኋላ ወደ ስራ አጥነቱ ገብተው ችግሮችን ይተነትናሉ። ከዚያ በኋላ ስልቶችን አስቀምጠው ወደ መፍትሔ ሀሳብ ይገባሉ። ይሄ ለክፍሉ ጉዳይ ከሰጡት ርዕስ ውጭ ይወጣል። ርዕስ መከፋፈልና የአንቀጽ አደረጃጀት ላይ ችግር ከሚታይባቸው ክፍሎች አንዱ ብለን ልንጠቅሰው የምንችለው መስለኛል።
ምዕራፍ - ሦስት፤ የለወጠ “ጥንስስ” በሚል ርዕስ ብቅ ካለ በኋላ፣ የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴን መንቶ አጃቢ ያደርጋል።
ለጌሾ ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ
ለመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ።
ይህ ምዕራፍና ክፍል ዓስር ዓመታት ወደ ኋላ እና “እግሮች ሁሉ ወደ ትክክለኛው የትግል ሜዳ ያመራሉ” በሚሉ ርዕስች “የለውጡ ጥንስሶች” እንዴት እንደተጀመሩ፣ ከውትድርና ለቅቀው ወደ ፓርቲና ክልል የገቡበትን ሁኔታ ያወሳል፡፡
እዚህ ቦታ በትግሉ ወቅት አብረው አሳልፈው የለውጡን ችቦ አብረዋቸው ይዘው ወደ አደባባይ የወጡት አቶ ለማ መገርሳን፣ አባዱላ ገመዳን፣ወርቅነህ ገበየውን ያስታውሳሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል የተጀመረው ጥንስስ  ወደ አማራ ክልል መዛመቱንና የትግሉ ተሳታፊዎች እነማን እንደነበሩ ማወቁ በህዝቡ ላይ የነበረውን ብዥታ ስለሚቀይረው ለታሪክ ተማራማሪዎች ሆነ ለእኛ የፖለቲካው ባይተዋሮች ጠቀሜታ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡
ይቀጥላል

Read 1653 times