Sunday, 21 March 2021 00:00

መሰረታችን ተናግቷል፤ መንፈሳችን ተበክሏል

Written by  ሮቤል ሙላት
Rate this item
(1 Vote)

 "--ስቃይ ተለማምደናል፤ ጭካኔ ከሱቅ እንደምንገዛው የሻይ ቅጠል ያክል የየቀን ግብራችን ሆኗል፡፡ በጋራ እየታመምን በጋራ እንክዳለን፡፡ በጋራ ለመታከም ፈርተን በየፊናችን መድሀኒታዊ ድብብቆሽ እንጫወታለን፡፡ ዝምታችንም አነጋገራችንም ቅስም ሰባሪ እየሆነ መጥቷል፡፡-"
          
           መሐረቤን…
(Suspicions)
አንድ የጌትነት እንየው ግጥም አለ፤ ’የሀበሻ ልጆች’ የሚል፡፡
“ምናል ብትረሱን ምነው ብትተውን
ጎበዝ ምነካችሁ ግሎባላይዜሽን ምናል ቢገባችሁ
ምናለበት እስኪ በኢትዮጵያ በሬ አሜሪካን ቢያርሱ
እስኪ ምናለበት ለገሀር ተኝቶ ለንደን ላይ ቢነሱ…”
ከአመታት በፊት ጸሀፌ ተውኔቱ በብሔራዊ ትያትር ቤት በስሜትና በጭብጨባ ታጅቦ ሲያነበው አበሳጭቶኝ ነበር፡፡ የምወደውን ኳስ በቃላታ መርፌ ወግቶ ሙሽሽ ሲያደርገው እረ ተው የሚለው አልነበረም፤ የምሳሳላትን አርቲስቱት በአሽሙር ስንኝ በጥፊ ሲያጮላት አሁንስ በዛ ብሎ የገለገለ አልነበረም፡፡ የ’ዶት ኮም’ ወጣት ስሜትን የሚረዳ  አንድስ እንኳ የ ’ያ ዘመን’ ሰው ይጥፋ ስል ከራሴ ጋር  ለብዙ ሰኮንዶች ተጨቃጭቄያለሁ፡፡ እንደውም ከበውቀቱ ስዩም “ኗሪ አልባ ጎጆዎች” የግጥም መድበል ተውሼ፤
“የአያቶቻችን ቤት፥ ይሁን ባዶ፣ ይሁን ኦና
በኛ ቁመት፣ በኛ መጠን አልተቀለሰምና” (ግጥሙን በቃሌ ስለያዝኩት ቃላት ልገድፍ እችላለሁ) ስል ተነጫንጫለሁ፡፡
አሁን ያ ኩንታል ሙሉ እልህና ቁጭት ጊዜ በሚሉት አገልግል ተቋጥሮ ከኑሮ ግርግዳ ላይ ተሰቅሏል፡፡ ከምር አሁን ምን አለበት ጎርጋዳ ጋደም ብዬ ካናዳ ብነቃ (ጎርጋዳ፤ ሀዋሳ ወስጥ ከሚገኙ ጭርንቁስ ሰፈሮች መካከል አንዱ ነው)፡፡ አንዳንድ ጊዜማ አረንጓዴ መነጸር ሰክቼ የቤትን መለምለም፣ የመንደሬን ማበብና  የከተማየን መበለጸግ ስመለከት ይአጅበኝና እንደገና ይአጅበኛል፡፡ ጎዳናው ደስታ ባጎሳቆላቸው የኔ ብጤዎች ተሞልቷል፤ አደባባዩ ከትላንት ጋር በተኳረፉ የዛሬ አበባዎች የነገ ቀቢጸ ተስፋዎች ተውቧል፤ አየሩ የሳቅ እንባ አዝሎ ይዞር ይመስል፣ በዘውግ የጠወለገ ገላን ያረሰርሳል፡፡ ሀይቁ አካባቢማ የሰማይ ቀጠሮ እንደ ሸማቾች ዘይትና ስኳር የራቀባቸው ሽማግሌዎች ከጉማሬ አጠገብ ይዋኛሉ፡፡ እዚህ ግጭት ቁርሱ፤ ድርቅ ምሱ፤ ማፈናቀል ሱሱ የሚሉት socially constructed የሆነ ወረርሽኝ እንደ አምስት ሳንቲም ድራሻቸው ጠፍቷል፡፡
ያያችሁ…
(Fear)
እ.ኤ.አ በ2009 የማህበረሰብ ሳይንስ መምህሩ Javier Auyero እና የስነ ሰብዕ ተመራማሪ የሆነችው Débora Alejandra Swistun አንድ ጥናት ወለድ መጽሐፍ ለአንባቢያን አድርሰው ነበር፡፡ “Flammable: Environmental Suffering in an Argentine Shantytown” ይሰኛል ድርሳኑ፡፡ በውቧ የላቲን አሜሪካ ሀገር ዋና ከተማ ቦነስ አይረስ መሀል ቱሪስት የሚተራመስበት “El Caminito” አለ፡፡ በዚህ አማላይ አደባባይ  ላይ የሚከወነው የታንጎ ዳንስ ተመልካችን እንደ ስልክ እንጨት ያስገትራል፤ እድሜ ጠገቦች የበረንዳ ላይ ካፌዎች ለእንግዶች ሆድና መንፈስ የእርካታ ምንጭ ናቸው፡፡ ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብቻ ሳይሆን እናቷን እንዳየች ጥጃ ቦርቃም ትመለሳለች፡፡ ታዲያ የማራዶና ዘመዶች ሙድ ሲይዙ ኢል ካሚንቶን “The Paris of South America” (የላቲን አሜሪካው ፓሪስ)  እያሉ ያቆላምጡታል፡፡
ከዚህ ማራኪ ስፍራ ብዙም ሳንርቅ የቦነስ አይረስ ሌላኛው መልክ ይገለጣል፡፡ የRiachuelo ወንዝን ስንሻገር ውጥንቅጧን Dock Sud እናገኛታለን፡፡ ድህነት ከእነ ግርማ ሞገሱ የሰፈረባቸው መንገዶች፤ ቆሻሻ ከእነ ግሳንግሱ የተጫናቸው የዘመሙ ህንጻዎች፤ ወንጀለኛ ከእነ ክላሽንኮፉ የወረራቸው መንደሮች፤ ግዴለሽነት ከእነ ትርፍና ኪሳራው መሄጃ ያሳጣቸው ሳቂታ ህጻናት እዛም እዚህም ይታያሉ፡፡ እነ አቪየሮና አሌክሳንድራ ለጥናታቸው ሁነኛ ቦታ የቪላ ኢንፍላማብልን ሰፍር (Villa Inflamable) መርጠዋል፡፡ ሼልን (Shell) የመሰሉ የነዳጅ ማጣሪያና የብረታ ብረት ማቅለጫዎች፣ የኬሚካል ማንጠሪያዎች፣ የቆሻሻ ማከመቻ ስፍራዎች ከ5ሺህ ነዋሪ ጋር በስስት ኑሮኗ ሽቀላቸውን ይገፋሉ፡፡
የአካባቢው ሰማይ በአያሌ ብናኝ ተወሯል፤ አየሩ በአሲዳማ ጠረን ተቀይሯል፤ የመንደሩ ወንዝ በመርዛማ ፈሳሽ ተበክሏል፤ የአስተዳደሩ ኪስና ጉንጭ ትንፋሽ በሚያሳጥር የጉቦ ጉርሻ ተጨናንቋል። አብዛኛው የፍላማብል ሰው ግን ጆሮ ዳቦ ልብስ ብሎ ተኝቷል፡፡ የጃፓን አለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ እ.ኤ.አ በ2002 አካባቢውን መርምሮ፣ ህጻናት ለተለያዩ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች እንደተጋለጡ፤ ወጣቶች የልብ መድከም እንደተከሰተባቸው፣ አዛውንቶች የሳንባ በሽታ እንዳጋጠማቸው በጥናቱ አረጋገጠ፡፡ አሁንም የአካባቢው ማህበረሰብ እውነቱን አላየንም፣ አልሰማንም ብለው ሸምጥጠው ካዱ ወይም የራሳቸውን ሌላ ’ሀይ ኮፒ’ ትርክት ፈጥረው ቁጭ አሉ፡፡
ይህ ሁለት ዓመት ተኩል የፈጀ ጥልቅና ዝርዝር የኢትኖግራፊ (የህብረተሰብን የቀን ተቀን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚሰነድና የሚተረጉም- The process of recording and interpreting another people’s way of life is called ethnography. Keesing and Strathern 1998፡፡ በነገራችን ላይ በመንዝ የአምሃራ ማህበረሰብ ላይ የሚያተኩረው የዶናልድ ሌቪን ሰምና ወርቅ ወይም “Wax and Gold” 1965፤ አይነተኛ የኢትኖግራፊክ ምርምር ውጤት ነው) መጽሐፉ መሰረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ይሞክራል። ምን ያህሉ የፍላማብል ሰው  ስለ ችግሩ መጠን፣ አይነትና ቆይታ መረጃ አለው? ስለ ክስተቱ መረጃ የሚያገኘው በየት፣ እንዴት እና በማን በኩል ነው? አደጋውን እንዴትና በምን ያህል ደረጃ ይረዱታል? የህዝቡ ግበረ መልስስ ምን ይዘትና ጥልቀት አለው? የዚህ አካባቢያዊ ሰለባ (environmental suffering) ስሪቱና ቅርጹ ምን ይመስላል?   
እዚህ ሀዋሳ ለምሳሌ እንደ ቀላል ’የፍቅር ሀይቅ’ ስነ ምህዳር እየተዛባ ነው የሚል ወሬ ሰምተን ኦ  ብለን አልፈናል፡፡ ደለል እየሞላ ሳሩን እያስፋፋው ነው፤  አጥማጅ እየበዛ ዓሳው እየተመናመነ ነው እየተባልን ከርመን እንዳልሰማን ጀርባችንን ሰጥተናል፡፡ ውኃው በኬሚካል እየተበከለ፤ አዕዋፋቱ በሰው ሰራሽ ጦስ እየተረበሹ እንደሆነ እየታዘብን ላሽ ብለን ለሽ ብለናል፡፡
የዚህ ጽሁፍ ጎማዎች በሚከተሉት የጥያቄ መሪዎች ይሽከረከራሉ፡፡ ራሳችንን እንዴት ነው የምንረዳው?  ለመሆኑ ከጎረቤታችን እውነታ መቼ ራቅን? ከቶ እንዴት ከአካባቢያችን ማህበራዊ ስሪት ተፋታን? እየሰጠን ያለው መልስስ ተገቢ ነው? የያዝነው መንገድ የት ያደርሰን ይሆን?
አላየንም…
(Disagreement)
በልጅነቴ ካልተጫወትኩት፤ ሲጫወቱ ሳይም ከሚያደክመኝ ጊዜ ማሳለፊያ አንዱ ’መሐረቤን ያያችሁ’ ነው፡፡ ፉክክሩ አነስተኛ፣ አዲስ ፈጠራ የለው፣ አሳታፊነቱ እዚህ ግባ አይባል፡፡ እየተሽከረከርክ ራሱ እንቅልፍ ሊወስድህ ይችላል፡፡ ቢሆንም የሀገሬ የህጻናት ጨዋታዎች የራሳቸው ፍልስፍናና ትዕምርታዊ (symbolic) ትርጉም እንዳላቸው አምናለሁ፡፡ እናም ክርክሬን ለማጎልበት ከመሐረቤን ያያችሁ አንድ ስንጥር ሀሳብ ልዋስ፡፡ እያዩ አለማየትን! የጨዋታው ጀማሪ መሐረቧን ጨብጦ ጓደኞቹን ይዞራል። መሐረቧን ሲደብቅ ከአንዱ በቀር ሁሉም ተጨዋቾች ይመለከቱታል፡፡ የጨዋታው ዙር እንዲከር ከተፈለገ የተሸሸገችው መሐረብ ቶሎ አለመገኘትና የደባቂው ጭራ አለመያዝ ወሳኝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የተቀመጡት የጨዋታው አካላት መሐረቧ እንድትገኝ ከመመኘት በቀር የመፍትሄ አካል አይደሉም፡፡ እያወቁ እንዳላወቁ፤ እያሉ እንደሌሉ፤ እየተመለከቱ እንዳልተመለከቱ ወደ ዳር ገሸሽ ይደረጋሉ። በዚህም ትኩረታቸው ከክቡ ባሻገር ባሉ ተዛማጅ እንቅስቃሴዎች ላይ ይሆናል። በአካል እየተጫወቱ በመንፈስ ግን ከመሐረቧ እና ከጓደኞቻቸው ይርቃሉ፡፡
በማህበረ ፖለቲካ ህይወታችን ውስጥ እይታችንን የሚሰርቁ፣ ስሜታችንን የሚቀርጹና መውጫ መውረጃችንን የሚሾፍሩ አካላት (Actors) አሉ፡፡ አቪየሮና አሌክሳንድራ የቪላ ኢንፍላማብል ማህበረሰብን ደንዳና ትርክት የፈጠሩት የተለያዩ አድራጊ-ሰሪዎች ቢሆኑም፣ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች፣ የህዝብ አስተዳዳሪዎችና የመገናኛ ብዙኃኑ ግን ዋነኞቹ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ ወፍራም ተቋማት ሀይል/ጉልበት አላቸው። የመቀመጫ ወንበራቸውን ለማደላደል አዳዲስ መረጃ ፈጥረው በተደጋጋሚ ያሰራጫሉ፤ በሂደት እውነት ሆኖ ተቀባይነቱ እንዲጨምር የሚታዩና የማይታዩ ማሳመኛ ስልቶችን ይተገብራሉ፡፡ ከድህረ-ዘመናዊነት ተጠቃሽ የፈረንሳይ ፈላስፎች መካከል አንዱ የሆነው ሚሸል ፉኮ (Michel Foucault) የስልጣን ምንጭ የሆኑ ተቋማትን የተቆጣጠሩ አካላት፣ እውቀትን የመፍጠር አቅም እንዳላቸው ይናገራል፡፡ ከጥርጣሬ ለመዳንም ተቀባይነት ባላቸው “ፊደላውያን” ሳይንሳዊ ማስረጃ በማሰጠትና በማስተንተን እውቀቱ ወደ ማህበረሰቡ እንዲወርድና እንዲለመድ ባለ በሌለ አቅማቸው ይጥራሉ። በጊዜ ሂደት ሀይል/ጉልበት ወለድ እውነት አድጋና ተመንድጋ የሁሉንም አፍ ታሟሻለች፡፡ ከዚህ በኋላ የሀዋሳ ሀይቅ እየተበከለ ነው ብለህ ብታወራ፣ ከቁብ ቆጥሮ የሚሰማህ አታገኝም፡፡ እረ ይሄ ነገር እንደ ሀሮምያ ሀይቅ ሊደርቅ ይችላል ብትል፣ ባክህ አታሟርት ተብለህ አፍህን ልትዘጋ ሁሉ ትችላለህ፡፡ ምክንያቱም ለጊዜው እውነት የተፈጠረችው፣ የጎለመሰችውና የተባዛችው በባለሀብቱ፣ በመንግስትና በሚዲያው ሶስትዮሻዊ ጥምረት ነው፡፡
መንግስት አቅጣጫ እስኪያስቀምጥ ወይም መገናኛ ብዙሀኑ አጀንዳ እስኪያደርጉት ድረስ አንተ ራሱ በትርክትህ ላይ ያለህ አቋም ይቀየራል፡፡ እውነትህ ተዛብቷል፤ እውቀትህ ተወስዷል፤ በነዚህ ላይ ተመስርቶ ፈርጥሞ የነበረው የመቃወምና የመደራደር አቅምህ እንደ ወንዝ ዳር አፈር ተሸርሽሯል፡፡  በጊዜ ሂደት የሀዋሳ ሀይቅማ ምንም ደለል አልገባበትም፤ ከሆቴሎች፣ ከፋብሪካዎችና ከሆስፒታሉም የሚወጣው መርዛማ ፍሳሽ እዚህ ግባ የሚባል ብክለት አያደርስበትም፤ የአሳ ምርቱም በሽ በሽ ነው እያልክ መከራከር ትጀምራለህ፡፡ “ውይ በሞትኩት ተሳስቼ ነበር ለካ” ብለህ ራሱ ልትጸጸት ትችለለህ፡፡ ምክንያቱም የተቀበልከው መረጃ/እውቀት/እውነት በባለ ሀይሎቹ በአግባቡ ተቀሽቦና ተላምጦ (designed and framed) እንድትውጠው ተደርጓላ፡፡
እባካችሁ…
(Endless waiting)
እንዲህ ባይሆን እመርጣለሁ፤ ግን የዘመኑ መንፈስ ይህን መስሏል፡፡ መሰረታችን ተናግቷል፣ መንፈሳችን ተበክሏል፣ ህልውናችን ተቃውሷል፣ የነገ ተስፋችን ሽል ኩርኩም በዝቶበታል፣ የመጪው ጊዜ ብሩህ ዓላማችን ቡጢ በርትቶበታል፡፡ እጓለ ገ/ዮሐንስ እንዳለው፤ በጥቁር ደመና ተከበናል። አቅመ ቢሶች ሆነናል ወይም ጉልበታችን  እንደ ፈረስ ፋንድያ በየቦታው ተንጠባጥቧል፤ የተረፈን የሽታው ትዝታ ብቻ ነው፡፡
ስቃይ ተለማምደናል፤ ጭካኔ ከሱቅ እንደምንገዛው የሻይ ቅጠል ያክል የየቀን ግብራችን ሆኗል፡፡ በጋራ እየታመምን በጋራ እንክዳለን፡፡ በጋራ ለመታከም ፈርተን በየፊናችን መድሀኒታዊ ድብብቆሽ እንጫወታለን፡፡ ዝምታችንም አነጋገራችንም ቅስም ሰባሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ የስነ አዕምሮ ባለሙያዎች cognitive schemata (organization of experience) የሚሉት ሀሳብ አለ። በእርግጥ እነሱ በሶስት ይከፍሉታል፡፡ perception፤ appreciation፤ እና action (Pierre Bourdieu 1986)፡፡ ግብረ-መልሳችን የሚወሰነው አዕምሯችን ውስጥ በተከማቸው የመረጃ ድግግሞሽ መሰረት ነው፡፡ የጥላቻ ፍትፍት እየጎረሰ ያደገ ወጣት በማህበራዊ ህይወቱ ውስጥ የሚንጸባረቀው ድርጊት ከቂም በቀል ሩብ ጉዳይ አይርቅም። ሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር) ዴቭድ ካሄንምን ጠቅሶ እንዳብራራው፤ ውሳኔ አሰጣጣችን በሁለት የተለያዩ ግን የሚመጋገቡ ስርዓቶች ይስተናገዳል፡፡ አንዱ ስርዓት የተመሰረተው በገጠመኝ ላይ ነው (2011)፡፡ ለምሳሌ በሀገራችን የሚከሰት ግጭት የዘውግ አንደሆነ  ተደጋግሞ ከተነገረን ካስተዋልን፤ ግላዊና ቡድናዊ ጥሎችን ሁሉ ካለፈው ገጠመኛችን ጋር ማያያዝ ይቀናናል፡፡ ተወራርዶ የተበላ ሁሉ በብሔሬ ነው ሊል ይችላል፡፡
ታዲያ እውነትን መካድ የመሰለ ምን ሰላም አለ? አጠገብን መርሳት የመሰለ ምን ጤና አለ? Physical and psychological suffering is compounded by suspicions (መሐረቤን), fear (ያያችሁ) disagreements (አላየንም), and endless waiting (እባካችሁ) (Auyero and Swistun 2009). ’ማምለጭ’ (የጋሽ ፈቃደ አዘዘ  አሪፍ ቃል ናት፡፡ ከቁሳዊ አካባቢ በመንፈስ መሸፈት፣ መመነን ወይም ማምለጥ ብሎ ይተረጉማታል) አዋጪ ምክር ሳይሆን ይቀራል፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ ሞልቶ ለሚፈስ ሀይቅ ምን አብከነከነኝ? ደርቆ ለሚተን ውኃ ምን አንገበገበኝ? ሰምቶ ለማይሰማኝ መራሄ ማህበረሰብ ምን ይሄን ሁሉ ጽሁፍ አዘከዘከኝ? “አልሰማሁም እባካችሁ” የምትል የመልስ ምት እንዴት ምቹ ናት በናታችሁ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 3890 times