Print this page
Saturday, 20 March 2021 11:45

የህውሃት መሪዎች እጅ እንዲሰጡ፣ ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ 1 ሳምንት ተሰጠ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   ከህወኃት ቡድን ጋር ተባብረው ነፍጥ ላነሱ አካላትና በወንጀል ለሚፈለጉ የህወኃት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች መንግስት ለመጨረሻ ጊዜ በሰላም እጅቸውን እንዲሰጡና ወደ ሰላማዊ ኑሮአቸው እንዲመለሱ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የሰላም ጥሪ አቀረበ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ትናንትን ከሠአት “ከህገወጡ የህወኃት ቡድን ጋር ለተባበሩ አካላት ከመንግስት የተሰጠ የመጨረሻ ማሳሰቢያ” በሚል ባሰራጨው መግለጫው፤ በህወኃት ቡድን ተደናግረው ነፍጥ ያነሱ አካላት በአንድ ሳምንት  ውስጥ በሠላም ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ፣ በወንጀል የሚፈለጉ አመራሮች ደግሞ በተሰጠው የጊዜ ገደብ እጃቸውን እንዲሰጡ አሳስቧል።
 የፌደራል ሃይል በህወኃት ህገ ወጥ ቡድን ላይ የሃገሪቱ ህግ የሚያዘውን ህጋዊ እርምጃ ወስዷል ያለው መግለጫው፤ በዚህ እርምጃ ከሃገር አልፎ ለቀጠናው ስጋት ሆኖ የቆየው የህወኃት ህገ ወጦች ቡድን ከፍተኛ ወታደራዊ አቅምና ዝግጁነት ተደምስሷል፡፡ የዚህ ቡድን ቁልፍ አመራር የሆኑት ግለሰቦች ከፊሎቹ በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ የቀረቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ አቅማቸውና ሃይላቸው እጅጉን ተዳክሞ ከህግ ለመሸሽ የሚባዝኑ የፍትህ ተሳዳጅ ሆነዋል ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በህወኃት ጉትጎታና ውዥንብር የክልሉ ወጣቶች ከመንግስት ጋር በተቃራኒ መሳሪያ ታጥቀው ህወኃት ጎን መሰለፋቸውን ያስገነዘበው መግለጫው፤ ወጣቶቹ የተከናወነውን የህግ ማስከበር ሂደት አላማ፣ ተረድተው በአስቸኳይ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ አሳስቧል፡፡
ከጦርነትና ተያያዥ በሆኑ የወንጀል ተግባራት ጉልህ ተሳትፎ አላቸው ተብለው ከተጠረጠሩና በዚሁ መነሻ የፍ/ቤት መያዣ ከወጣባቸው የህወኃት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች  በስተቀር ሌሎች ዜጎች ያለ ስጋት ወደ ቀደመው ሠላማዊ  ኑሮአቸው እንዲመለሱ ሲል ጥሪ ያቀረበው መንግስት፤  ወደ ነበሩበት ኑሮአቸው እንዲመለሱ የአንድ ሳምንት ጊዜ ሰጥቷል፡፡
በዚሁ ጥሪ በወንጀል ተግባራት ጉልህ ተሳትፎ የሌላቸውና የፍርድ መያዣ ከወጣባቸው የወንጀል ተጠርጣሪዎች በስተቀር የክልሉ ተወላጅ ዜጎች የትኛውም የህግ ተጠያቂነት ሣይኖርባቸው፣ ከአጥፊ ተግባራቸው ተቆጥበው ወደ ስራቸውና ሰላማዊ ኑሮአቸው ሊመለሱ ይችላሉ ብሏል-መግለጫው፤ ይህን የመጨረሻ ጥሪ ተጠቅመው ራሳቸውን ለፍትህ በማያቀርቡ የሕወኃት ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ ህግ ለማስከበር ሲባል፣ አስፈላጊው ሁሉ የሚፈፀም ይሆናል ብሏል- በመግለጫው።

Read 11510 times