Saturday, 20 March 2021 11:33

የምርጫ ክርክር ለማዘጋጀት 3 ሚዲያዎችን ጨምሮ 11 ድርጅቶች ተመርጠዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ሶስት የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ 11 ድርጅቶች የዘንድሮ ምርጫ የክርክር መድረኮችን እንዲያዘጋጁ መመረጣቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮ ምርጫ የክርክር  መድረኮችን በብቃት የሚችሉ ተቋማት እንዲያመለክቱ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት፤ 5 የሚዲያ ተቋማትን ጨምሮ 23 ድርጅቶች ማመልከቻ ያስገቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በብቃት ክርክሩን ማካሄድ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸው 11 ድርጅቶች መመረጣቸውን ነው ቦርዱ ያስታወቀው፡፡
እነዚህን በቦርዱ የተመረጡ የክርክር መድረክ አዘጋጆችን በተመለከተም የቦርዱ አመራሮች ከትናንት በስቲያ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ያሳወቁ ሲሆን፤ ፓርቲዎቹ በሌሎች ተቋማትም  ክርክራቸውን ማካሄድ ይችላሉ ተብሏል፡፡
ከሚዲያዎች የምርጫ ክርክር መድረክ እንዲያዘጋጁ እውቅና የተሰጣቸው፡- አሃዱ ቴሌቪዥን፣ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔት-ወርክ  ሲሆኑ ከተቋማት ደግሞ ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሸን፣ የኢትዮጵያ መሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማህበር፣ የኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲሴቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅት ህብረት፣ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋችና ሴታዊት ሙቭመንት መሆናቸው ታውቋል።
ክርክሩ የሚካሄድባቸው ቋንቋዎች አማርኛን ጨምሮ አፋን ኦሮሞ ሶማሊኛና አፋርኛ ይገኙበታል፡፡ ሴታዊት ሙቭመንት 2 ክርክሮች ለማዘጋጀት ያቀደ ሲሆን ተቀርፆ በቴሌቪዥን የሚቀርብ ይሆናል። በክርክሩ 10 የተመረጡ ፓርቲዎች የሚሳተፉ ሲሆን ርዕሰ ጉዳዩም የሥርአተ ጾታ ፖሊሲ እንደሚሆን ታውቋል። ለክርክር የሚሆኑ ጥያቄዎችም ማህበራዊና መደበኛ ሚዲያዎች አማካይነት እንደሚሰበሰቡ ሴታዊት ሙቭመንት ካስገባው የመወዳደሪያ መስፈርት መዘርዘር መረዳት ተችሏል፡፡
ከ30 እስከ 50 የሚደርሱ ተሳታፊዎች የሚገኙበት ክርክር ለማዘጋጀት ያቀደው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በበኩሉ፤ ተወዳዳሪዎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን የሚከላከሉበት ስልታዊ እቅድን ጨምሮ በሴቶችና አካል ጉዳተኞች መብት ዙሪያ  አከራከራለሁ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መሬት አስተዳደር ባለሙያዎች ማሕበር ደግሞ በመሬት  አስተዳደር ፖሊሲ ላይ ከ15 እስከ 20 የዘርፉ ባለሙያዎች በሚሳተፉበት ሁኔታ 1 የክርክር መድረክ አዘጋጃለሁ፤ ክርክሩም ተቀድቶ በቴሌቪዥን ይተላለፋል ብሏል፡፡
በኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ የክርክር መድረክ ለማዘጋጀት ያቀደው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሶሽን፤  5 ያህል የክርክር መድረኮችን እንደሚያዘጋጅ ጠቁሞ፤ ክርክሮቹ ተቀድተው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያዎች እንደሚቀርቡ አስታውቋል።
በ1997 ምርጫ ክርክሮች በማዘጋጀት የሚታወቀው ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ በበኩሉ፤ በተመረጡ ዋና ዋና ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ 3 የክርክር መድረኮችን በደብረ ብርሀን፣ አርባ ምንጭና ጅግጅጋ ከተሞች በአማርኛና በሶማሊኛ አዘጋጃለሁ ብሏል፡፡
አሃዱ ቴሌቪዥን 12 የክርክር መድረኮችን ለማዘጋጀት ማቀዱን ከእነዚህም 4ቱ በቀጥታ 8ቱ ተቀድተው የሚቀርቡ ይሆናል ብሏል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ በበኩሉ፤ 13 ክርክሮችን ለማዘጋጀት ያቀደ ሲሆን 4 በሃገር አቀፍ ደረጃ፣3 በኦሮሚያ፣2 በአማራ፣ 2 በሶማሊያ፣ 2 በአፋር እንዲሁም 2 በሃዋሳ እንደሚያዘጋጅ ያመለከተ ሲሆን ከሁለቱ በስተቀር ቀሪዎቹ በቀጥታ ስርጭት የሚቀርቡ ይሆናሉ ተብሏል።
የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን)፤ 55 የክርክር መድረኮችን አዘጋጃለሁ ብሏል። 25 በአፋን ኦሮሞ፣ 10 በሱማሊኛ 10 በአፋርኛና 10 በአማርኛ ቋንቋ ይሆናሉ። በአንድየ ክርክር መድረክ ከ3 እስከ 4 ፓርቲዎች ይሳተፋሉ፣ ሁሉም ክርክሮች በኤዲቶሪያል ፖሊሲ መሰረት ኤዲት ተደርገው በሬዲዮና ቴሌቪዥን ይቀርባሉ ብሏል፡፡

Read 11930 times