Saturday, 20 March 2021 11:32

“አብን” እና “ባልደራስ” በምርጫው ተባብረው ይወዳደራሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

   ለአዲስ አበባ ራስ ገዝነት እታገላለሁ የሚለው ባልደራስ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ በመጪው አገራዊ ምርጫ በትብብር ለመስራት መስማማታቸው ታውቋል፡፡
ለቀጣዩ ምርጫ በአዲስ አበባ ለፓርላማና ለከተማ ም/ቤት 160 እጩዎች ያቀረበው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲና በዋናነት የአማራን ህዝብ መሠረት አድርጎ የሚወዳደረው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፈጸሙት የትብብር ስምምነት፤ በምርጫው እርስ በእርስ ለመደጋገፍና አንዱ ከአንደኛው ሃሳብ በተቃረነ መልኩ ላለመጓዝ ነው ተብሏል።
አዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎቿ መሆኗን ሁለቱም ፓርቲዎች አምነው በጋራ የሚታገሉበት ጉዳይ ሲሆን በአማራ ህዝብ ላይ የሚቀርቡ የጥላቻ ትርክቶችና ይህን ተከትሎ የሚፈጸሙ ግፎች ፓርቲዎቹ በትብብር የሚቆሙባቸውና እኩል የሚታገሉባቸው ጉዳዮች እንደሚሆኑ አስታውቀዋል አመራሮቹ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ።
የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎቿ መሆኗን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት የጋራ ትግል መነሻ ዲሞክራሲን ፣ ነጻነትንና እኩልነትን በማስፈን ላይ የተመሰረተ መሆኑን፣ ከተማዋ የአንድ ንጥል ብሔር አለመሆኗን በይፋ በመግለጽ የማታገያ አጀንዳ እንደሚያደርጉት ያስታወቁት ፓርቲዎቹ፤ በአዲስ አበባ ህዘብ ህልውና ላይ ተጋርጧል ያሉትን አደጋም  በጋራ እንደሚታገሉት አስረድተዋል።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲናና የነዋሪዎቿ መሆኗን፤እንዲሁም ለማንም  የልዩ ጥቅም መስጠትም እንደሌለባት የጠቀሱት አብንና ባልደራስ፤ ከህገ-መንግስቱ ድንጋጌ ጀምሮ በፖለቲካ ጥያቄአችን ጭምር ከምርጫው በኋላም በጋራ ትብብር  እንታገላለን ብለዋል።
“የአማራ ህዝብና የአዲስ አበባ ህዝብ የህልውና አደጋ ተጋርጦባቸዋል” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ትብብራቸው በዋናነት ይህን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
አብን በአዲስ አበባ ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ እውቅና ሰጥቶ ባልደራስ ከሚያደርገው ትግል ጎን ሲቆም፤ ባልደራስም በተመሳሳይ ለአማራ ህዝብ ህልውና የሚደረግን ትግል ይደግፋል፤ ለሚደረገው ትግልም ክብርና እውቅና ይሰጣል ተብሏል።


Read 11438 times