Saturday, 20 March 2021 11:29

ተመድ የትግራይ የሰብአዊ መብት ጥሰትን በጋራ ለመመርመር መስማማቱን ገለፀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


              በትግራይ በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የጦር ወንጀል ሳይፈጸም አይቀርም የሚል ጥርጣሬ እንዳለው የገለፀው የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን፤ ጉዳዩን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋር በጋራ እንዲመረምር ከኢትዮጵያ መንግስት የቀረበለትን ግብዣ መቀበሉን አስታወቀ፡:
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊ ሚሼል ባቼት፤ ተቋማቸው በትግራይ ተፈጽመዋል እየተባሉ የሚነገሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሚያሳስበው ጠቁመዋል። ጉዳዩ አለማቀፍ ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ እንዲመረምር ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ የጠየቀው ተቋሙ፤ ይህ የማይቻል መሆኑን በመረዳቱ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር የጋራ የምርመራ ቡድን አቋቁሞ ጥልቅ ምርመራ ለማድረግ ማቀዱን አመልክቷል።
በአሁኑ ወቅትም ኢሰመኮ እና የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ቡድን ማቋቋም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየተነጋገሩ መሆኑን የተቋሙ ቃል አቀባይ ጆናታ ውለር ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስዎች ባወጣቸው የምርመራ ሪፖርቶች፤ በተለይ በአክሱም መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ገልጸው የነበረ ሲሆን ይህን ድርጊትም በዋናነት የኤርትራ ወታደሮች እንደፈጸሙት መጥቀሳቸው ይታወቃል።

Read 1013 times