Saturday, 20 March 2021 11:22

በትግራይ ለ4.2 ሚሊዮን ዜጎች እርዳታ ማቅረብ ተችሏል - መንግስት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   “አሁንም ግጭት ባሉባቸው ሥፍራዎች እርዳታ እየቀረበ አይደለም”

            መንግስት በትግራይ ለ4.2 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ እርዳታ ተደራሽ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን አለማቀፍ ተቋማት በበኩላቸው፤ አሁንም እርዳታው በበቂ መጠን እየተዳረሰ አይደለም ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት መንግስትና አለማቀፍ የረድኤት ድርጅቶች በትብብር ያቀረቡት የእለት ደራሽ እርዳታ 4.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች መድረሱን ነው መንግስት ያስታወቀው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ያልደረሰባቸው ቦታዎች መኖራቸውን የጠቆመ ሲሆን በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች የቀጠሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ እርዳታ አቅርቦቱን አስቸጋሪ አድርጎታል ብሏል።
መንግስት  በበኩሉ፤ ለእርዳታ አቅርቦት አመቺ በሆኑ አካባቢዎች አስካሁን መንግስት 70 በመቶ እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች 30 በመቶ የሚሆነውን እርዳታ ማቅረባቸውን  አመልክቷል። ይሁን እንጂ እርዳታው አሁንም በቂ ነው ብሎ መንግስት እንደማያምን ጠቁሞ፤ ነገር ግን አስፈላጊውን እርዳታ ለማቅረብም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግሯል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ በበኩሉ፤ እስካሁን ከሚያስፈልገው  የእርዳታ መጠን 59 በመቶ ያህል ተሟልቶ መገኘቱን በሪፖርቱ አስታውቋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ጠንካራ የተኩስ ልውውጦች በመኖራቸውና የፀጥታው ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ነዋሪዎች ያሉበትን ሁኔታ እንኳን ለማወቅ እንዳልተቻለ ያስታወቀው ቢሮው፤ መንግስትና የሚመለከታቸው ሁሉ  ለንፁሃን ደህንነትና በሕይወት መቆየት ቅድሚያ በመስጠት በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቋል።


Read 335 times