Print this page
Saturday, 20 March 2021 11:19

በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናትን ለከፋ ችግር ዳርጓል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ከአንድ አመት በኋላ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት፣ ወላጅና አሳዳጊዎቻቸው
በወረርሽኙ ምክንያት ከስራ ገበታቸው በመፈናቀላቸው ወይም የስራ ሰዓት በመቀነሳቸው ምክንያት ለከፋ ድህነት ተጋላጭ እንደሆኑ  ሴቭ ዘ ችልድረን ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ወረርሽኙ በቤተሰብ ላይ በሚያሳድረው ከባድ ተጽእኖ የተነሳም፣ ሕፃናት ወደ ጉልበት ስራ እንዲገቡ እየተገደዱ መሆኑን ተቋሙ ጠቁሟል፡፡   
የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ በመጋቢት 2012 ባዘጋጀው የኮቪድ 19 ተጽእኖ የአጭር ጊዜ የፖሊሲ ምክረ ሃሳብ፣ እስከ 2.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ስራዎች እ.ኤ.አ እስከ 2020 አጋማሽ ሊዘጉና በዚህም አገሪቱ 296 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሊታጣ እንደምችል መገመቱን ሴቭ ዘ ችልድረን  ጠቅሷል፡፡
በወረርሽኙ ሳቢያ የወላጆች ከስራ መፈናቀልና የልጆቻቸውን መሰረታዊ ፍላጐት ማሟላት አለመቻል የሕፃናት አድን
ድርጅትን በእጅጉ እንደሚያሳስበው በመግለጫው  አስታውቋል፡፡ ሕፃናት የወላጆቻቸው የገቢ ሁኔታ ሲዋዥቅ ለምግብ እጥረት፣ ለህመምና  ለአደገኛ የጉልበት ብዝበዛ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ውስጥ ይወድቃሉ ያለው ተቋሙ፤ ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስና በትምህርታቸው የመግፋት እድላቸውም ይመናመናል ብሏል፡፡
ኑሮአቸው በወረርሽኙ ምክንያት ከተዛባባቸውና  ለድህነት ከተዳረጉ ሕፃናት መካከል አንዷ የሆነችው የስምንት አመቷ ራሄል* (ስሟ ለደህንነቷ ሲባል የተቀየረ) የተናገረችውን ለአብነት ይጠቅሳል፤
ሕይወት ከኮሮና በፊት ጥሩ ነበር። ሁለቱም ወላጆቼ ጥሩ ገቢ የነበራቸው ሲሆን ኑሮአችንም ምቹ ነበር፡፡ አባቴ የተለያዩ መጫወቻዎች ወዳሉበት መዝናኛ ቦታ ሲወስደኝ እኔም እሽክርክሪት፣ ሸርተቴና ሌሎች ጨዋታዎች እጫወታለሁ። አይስክሬምና ፍራፍሬዎችም ይገዙልኝ ነበር። ከወረርሽኙ በሁዋላ ግን አባቴ ገቢው ቀነሰ ፤እናቴም ስራዋን በማጣቷ ቤት መዋል ጀመረች፡፡ በፊት ወተት እንቁላልና ስጋ እንመገብ ነበር፤ አሁን ግን የምንበላው ሽሮ ብቻ ነው፡፡´
የዓለማቀፍ ሌበር ድርጅትን የቅርብ ጊዜ ጥናት ጠቅሶ ሴቭ ዘ ቺልድረን እንዳመለከተው፤ በአለም አቀፍ ደረጃ 255 ሚሊዮን ስራዎች በወረርሽኙ ሳቢያ  የተዘጉ ሲሆን  በአፍሪካ ደግሞ 38 ሚሊዮን ሰዎች እ.ኤ.አ በ2020 ስራቸውን በኮቪድ ምክንያት አጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያም በዚሁ ዓመት መጨረሻ ላይ  3.7 ሚሊዮን የስራ እድሎች ሊዘጉ እንደሚችሉ ጥናቱ አመልክቷል።



Read 1012 times
Administrator

Latest from Administrator