Print this page
Saturday, 20 March 2021 11:17

ተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በሚያጋጥሙባቸው አካባቢዎች መንግስት የፀጥታ ሃይሉን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

          በተደጋጋሚ መጠነ ሰፊ የሠብአዊ መብት ጥሰቶች ባጋጠመባቸው አካባቢዎች መንግስት የፀጥታ ሃይሉን ከወትሮ በተለየ እንዲያጠናክር ያሳሰበው ኢሠመጉ፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መባባስ የሃገሪቱን ህልውና እንዳይፈታተን እሰጋለሁ ብሏል፡፡
በተለይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋና በደቡብ ክልል በአማሮ ልዩ ወረዳ የተፈፀመው የጅምላ ግድያ ሃገሪቱ በአለም አቀፍ የሠብአዊ መብት ስምምነት ሲመዘን ማቆሚያ የሌለው የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ መሆኑን ያመላክታል ብሏል ኢሰመጉ፡፡
ኢሰመጉ ባሰባሰበው መረጃ መሰረት፤ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ አቤደንጎሮ ወረዳ የካቲት 27/ቀን/2013 በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩ ምዕመናንና ካህናትን ጨምሮ 29 የሚደርሱ ንጹሀን መገደላቸውንና የ22ቱ እስክሬን ተገኝቶ በሶስተኛው ቀን መቀበሩን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በተመሳሳይ የካቲት 29/ቀን/2013 በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በእርቀ ሰላም ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት ስድስት ሰዎች ተገድለው፣ ስድስቱ ደግሞ በፅኑ መቁሰላቸውን አስታውቋል፡፡
ጥቃቱንም ኦነግ ሸኔ ስለመፈፀሙ የመንግስት መግለጫን የጠቀሰው ኢሠመጉ፤  ጥቃቶች በእጅጉ መደጋገማቸውን በማመልከት በዜጎች የአካል ደህንነትና ነፃነት መብቶች ላይ ማቆሚያ የሌለው ጥሰቶች እየተፈጸመ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
መንግስት የሠብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመባቸው ባሉት አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱትን የፀጥታ ሃይሎች አቅም እንዲሁም ዝግጁነት እንዲያጠናክር፣ደረሱ የተባሉትንም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በማጣራት ተገቢውን ህጋዊ መፍትሄ እንዲያበጅ በህገ ወጥ መንገድ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ባሉበት አካባቢ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የዜጎችን ደህንነት አስተማማኝ እንዲያደርግ ኢሰመጉ ጠይቋል፡፡
ገለልተኛ የሠብአዊ መብት ተቋማት በአካባቢዎቹ ተንቀሳቅሰው በአስቸኳይ ማጣራት ያደርጉ ዘንድ መንግስት ሁኔታዎቹን እንዲያመቻችም ኢሠመጉ በመግለጫው አሳስቧል፡፡

Read 704 times