Monday, 15 March 2021 08:09

የመደመር መንገድ;

Written by 
Rate this item
(4 votes)


          አንድ የንስር ጫጩት እናቱ መብረር ስታለማምደው ቆይታ በመጨረሻ #አሁን ያለ እኔ ድጋፍ መብረር ስለምትችል ከእንግዲህ ብቻህን ከጎጆ ወጥተህ ክንፍህን ማንቀሳቀስ ትችላለህ; አለችው።
ጨቅላው ንሥርም በደስታ ከጎጆ ሲወጣ በአቅራቢያው አንድ አሳማ ሲሮጥ ያያል። በደስታ ውስጥ ሆኖ እንዲህ ሲል ለእናቱ ነገራት፤ "እዪውማ! ያንን ጮማ የሆነ አሳማ" አለና ሄዶ ለቀም ሊያደርገው ተጣደፈ።
"ተው ተው የእኔ ልጅ! እሱ ይቅርብህ!" በማለት ተቃወመች፤ የንሥሩ እናት። "አንተ አሁን አሳማ ለማደን አልደረስክም፤ ገና ነህ። ባይሆን አነስ አነስ ያሉትን አይጦች በማደን ብትጀምር ጥሩ ነው፤ ጉልበትህ መጠንከር አለበት"  አለችው።
ንሥሩ በእናቱ ክልከላ ቅር ቢለውም ምክሯን ግን ከመስማት አላመነታም። ከዚያ እየዞረ አይጦችን እያደነ ይበላ ጀመር። መጀመሪያ ላይ አይጦቹን ለመያዝ በጣም ተቸግሮ ነበር። እየቆየ ግን አያያዙን ስለለመደው በቀላሉ ለቀም ያደርጋቸው ጀመር። እያደገ ሲመጣ አይጥ ማደኑ በጣም ቀላል ሆነበት፤ ሥጋቸውም አላጠግብ አለው። በዚህ መሐል ግዙፉን አሳማ ሲሮጥ ተመለከተው።
"አሃ! አሁን ተገኘህ፣ መጣሁልህ ጠብቀኝ"  ብሎ ወደ አሳማው ሊወረወር ሲል እናቱ በድጋሚ አስቆመችው።
"አሁን ጥንቸል ምናምን ማደን ጀምር። አሳማውን ለጊዜው ተወው" አለችው።
ንሥሩ ሳያመነታ አሳማውን ትቶ ጥንቸል ማደን ጀመረ። ሆኖም ጥንቸሎቹ እንደ አይጥ ለማደን ቀላል አልሆኑለትም። ሲሮጡ አይጣል ነው። ደርሶ ለቀም ሊያደርጋቸው ሲል እጥፍ ብለው አቅጣጫ ይቀይሩበታል። መጀመሪያ አካባቢ ቀኑን ሙሉ ታግሎ አንድ ጥንቸል መያዝ ይከብደው ነበር። እየቆየ ሲሄድ በቀን ሁለትም ሦስትም መያዝ ለመደ። በዚህ መሐል የተለመደው አሳማ ትውስ ሲለው ከእንግዲህ እሱን ማደን አለብኝ ብሎ ተነሳ። ችግሩ አሁንም እናትየው አልፈቀደችለትም።
"በጥንቸሎቹ ቅልጥፍና ብትማርም ክብደት ያለው ነገር መሸከም ደግሞ በግና ፍየሎችን በማደን መለማመድ አለብህ" ስትል ነገረችው።
ንሥሩም እንደተባለው አደረገ። ብዙ በጎችንና ፍየሎችን እያደነ ሲበላ ከረመ።
አንድ ቀን እንደተለመደው በግ ሊያድን ሲወጣ ያንን አሳማ አየው። ዞር ብሎ እናቱን ሲመለከት በዐይኗ "አሁን ጊዜው ነው" የሚል ምልክት ሰጠችው። ክንፉን እያማታ ሽቅብ ወጣና አነጣጥሮ ቁልቁል ተወረወረ። ተወርውሮም አልሳተውም፤ አፈፍ አደረገው። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዐቅሙን ሲያከማች መቆየቱ አሳማውን ያለ ችግር እንዲጨብጥ አደረገው።
ደራሲ: ዐቢይ አህመድ አሊ (ዶ/ር)
(kገፅ 19 እና 20 የተቀነጨበ)

Read 4260 times