Print this page
Monday, 15 March 2021 07:54

ቤተኛ ባይተዋርነት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ጆርጅ ዚመል የተባለ የሥነ-ማኅበረሰብ ጥናት ሊቅ “ቤተኛው ባይተዋር” (ዘ ስትሬንጀር) የተሰኘ ጽሑፍ አለው። ይህ በብዙ መስኮች ላይ ተጽዕኖውን ያሳደረ ጽሑፍ ቤተኛ ባይተዋርነት ያለውን ልዩ ባህርይ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ዚመል እንደሚለው፤ “ቤተኛ ባይተዋር” ማለት፤ ቤተኛነትንም ባይተዋርነትንም በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ሕይወት ማለት ነው። ቤተኛ ባይተዋር ከእንግዳ ይለያል፤ እንግዳ ዛሬ መጥቶ ነገ የሚሄድ ሲሆን ቤተኛ ባይተዋር ግን ዛሬ መጥቶ ነገም የሚቆይ ነው። የውጭ ሰው አይደለም፤ መጥቶ የሚሄድም አይደለም። በአንድ በኩል የውስጥ ሰው ነው፤ በሌላ በኩል የውጭ ሰው ነው። መንታ ሥሪት አለው። ቤተኛ ባይተዋር፤ በአንድ ቡድን ውስጥ የቡድኑ አባል ሆነው ነገር ግን የተለየ የተግባር ወይም የአስተሳሰብ ልምድ ያላቸው ሰዎች ጠባይ ነው።
የቤተኛ ባይተዋርነት ንድፈ ሐሳብ ፈጣሪው ጆርጅ ዚመል፣ በዚሁ የቤተኛ ባይተዋርነት ተፈጥሮ ውስጥ ያለፈ ይመስላል። ዚመል በጀርመን የሚኖር አይሁዳዊ ሊቅ ነበር። በአንድ በኩል ጀርመናዊ ነውና ከጀርመን ጋር የነበረው ትስስር ቤተኝነት አለ። በሌላ በኩል ደግሞ አይሁዳዊ በመሆኑ ምክንያት የናኘ ምሁር ቢሆንም እስከ ሕይወቱ መገባደጃ ድረስ በመደበኛ ዩኒቨርሲቲ መምህር ለመሆን አልተፈቀደለትም።
ተማሪዎች እየከፈሉት ነው ያስተምር የነበረው። ይህ ሁኔታ ለዚመል የቤተኛ ባይተዋርነትን ጠባይ እንዲያዳብር አድርጎታል። ብዙ አዳዲስ ሐሳቦችን በመፍጠር ረገድም አስተዋፅዖ አድርጎለታል። ካርል ማርክስ፣ ሲግመንድ ፍሮይድ፣ አልበርት አነስታይን እና ሌሎች መሰል  አይሁድ-ጀርመናውያን ሊቃውንት፤ ይህ የቤተኛ ባይተዋርነት ጠባይ ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ ለማየት ዕድል የሰጣቸው ይመስለኛል።
ቤተኛ ባይተዋርነት የውስጥም የውጭም እይታ እንዲኖረን ዕድል ይሰጣል። ስለ አንድ ተቋም ከውስጥ የሚያዩት የተቋሙ ባልደረቦችና ከውጭ ሆነው ተቋሙን የሚመለከቱ ሰዎች ተመሳሳይ እይታ አይኖራቸውም። የተቋሙ ባልደረቦች የተቋሙን ስኬት አጋንነው መመልከታቸው አይቀርም። በተቋሙ ውስጥ ሆነው እየለፉ ነውና የተቋሙን ብርታት እንጅ  ስሕተቱን ለመመልከት ይከብዳቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭ ሆነው ተቋሙን የሚመለከቱ ሰዎች የተቋሙን የውስጥ ጥረትና ያለበትን ተግዳሮት አይመለከቱም። የተቋሙን ጥረትና ስኬት  ዘንግተው ጉድፍ ፍለጋ ላይ ብቻ ያተኩራሉ። እውነቱ ያለው በእነዚህ በሁለቱ መካከል ነው።
ቤተኛ ባይተዋርነት የውስጥንም የውጭም እይታዎች በማካተት ሚዛናዊ እይታ ይፈጥራል። ቤተኛ ባይተዋሮች በሌሉበት ከባቢ ውስጥ ለውጥ እንደ ከዋክብት የራቀ ጉዳይ ይሆናል። ይህ መንታ ሁኔታ ነው ቤተኛ ባይተዋሮችን የለውጥ ለኳሾች የሚደርጋቸው።
ኢህአዴግን ከውጭ የሚመለከቱ ሰዎች ኢህአዴግ ውስጥ በተግባር የተሰራውን ስራ፣ የተደከመውን ድካም፣ የተደረገውን ጥረትና የመጣውን ስኬት ሁሉ ገደል ከትተው፣ የኢህአዴግን ስህተቶችና ድክመቶች ብቻ ያወራሉ።
እነዚህ ሰዎች ስህተትን ለመጠቆም፣ ጎዶሎን ለመሙላትና አቅጣጫ ለማሳየት የውጭ ተመልካችነታቸው ያግዛቸዋል። በአንጻሩ የመሪነት ቦታ ላይ ሆነው መሬት ላይ ያለውን እውነታና የውስጡን ውጣ ውረድ ስለማያስተያዩት ከተጨባጭ እውነታ መራቃቸው አይቀርም። እዚህ ጋ እውነት ሁሉ ተጨባጭ እውነት አለመሆኑን ልብ ይሏል።
በሌላ በኩል፤ ኢህአዴግን ከውስጥ የሚመለከቱት ሰዎች ሃያ አራት ሰዓት ስለ ኢህአዴግ ስኬትና ድል ማውራት አይሰለቻቸውም። የኢህአዴግ ድክመቶች ግን ፈጽመው አይሸቷቸውም። ችግሮቹን ከመላመዳቸው ብዛት የችግሮቹን መጥፎ ሽታ እንደ መልካም መዓዛ ለማጣጣም መሞከራቸው አይቀርም።
ኢህአዴግ የውስጥና የውጭ እይታዎችን አጣምሮ ይዞ ድርጅቱን መለወጥ የሚፈልግ ሰው ያሻው ነበር። ኢህአዴግ፤ ተቃዋሚ ኢህአዴግ ያስፈልገው ነበር። ተቃዋሚ ኢህአዴግ፣ የውጭንና የውስጥን እይታ አካትቶ ኢህአዴግን የሚለውጥ የኢህአዴግ ሰው ማለት ነው። ኢህአዴግ ከውጭ በሚነሳ የአልፎ-ሂያጅ ትችት ብቻ ሊለወጥ አይችልም።  ከውስጥ በሚደረግ የመታበይ ስሜትና የድል ትርክት ብቻም ሊከርም አይችልም።
ቤተኛ ባይተዋርነት ባሳለፍነው ልምድ ወይም የአስተሳሰብ ጎራ ብቻ የሚመጣ አይደለም። ሰዎች ቤተኛ ባይተዋርነትን በራሳቸው ጥረት ሊያመጡት ይችላሉ። ጆሴፍ ሉፍት እና ሃሪ ኢንግሃም የተባሉ የስነ-ልቦና ምሁራን፤ “የጆሃሪ መስኮት” የተሰኘ ዝነኛ የጠባይ መግባቢያ ዘዴ ፈጥረዋል። ዘዴውን “ጆሃሪ” የሚል ስያሜ የሰጡት የስማቸውን የመጀመሪያ ፊደላት ጆሴፍ እና ሃሪ በማጋጠም ነበር። በጆሃሪ መስኮት ንድፈ ሃሳብ መሰረት ሰብዕናችን በአራት መስኮቶች ሊታይ ይችላል። “ለሁላችን የሚታይ፣ ለእኛ የተሰወረ፣ ለሌሎች የተሰወረ፣ ለሁላችን የተሰወረ” ይሰኛሉ፤ አራቱ መስኮቶች።
ለሁሉ የሚታየው ጠባይ - ግልጽና ለመግባባት ምቹ የሆነው ባህሪያችን ነው። ይህን ጠባያችንን እኛም ራሳችን እናውቀዋለን፤ ሌሎች ሰዎችም ይህንን ጠባያችንን ያውቁልናል።
ከባለቤቱ የተሰወረው ጠባይ - ሰዎች የሚያውቁት እንጂ እኛ የምናውቀው አይደለም። “ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው” እንደሚባለው። ሰዎች ስለ እኛ የሚያውቁት፣ እኛ ራሳችን ግን በፍጹም የማናውቀው ጠባይ አለን።
ከሌሎች የተሰወረው ጠባይ - እኛ ራሳችን እናውቀዋለን እንጂ ሌላ ሰው አያውቅልንም። እኛ እያወቅነው ሰው ግን በሌላ መልኩ ከተረዳን ይሄ ጠባያችን ለሌሎች ሰዎች የተሰወረ ነው ማለት ነው።
ለሁሉ የተሰወረው ጠባይ - ይህ እኛም ሆንን ሌሎች ሰዎች በግልጽ የማናውቀው፣ በጨለማ ያለ ሰውር ጠባያችን ነው። ለምሳሌ ያህል እኛም ሆንን ሌሎች ሰዎች የማናውቀው ድብቅ አቅምና ችሎታ ሊኖረን ይችላል። በአጠቃላይ ይህ የማንነታችን መስኮት ማንም ምንም ሊመለከትበት የማይችል ጸሊም መስኮት ነው።
የሰው ልጆች እርስ በርስ ለመተባበርና አንዱ በአንዱ ላይ እምነት ለማሳደር ይችል ዘንድ ለሁላችን የሚታየው የሰብዕናችን መስኮት ሊሰፋ ይገባል። ይሄ መስኮት እየሰፋ ሲመጣ ነው መደመር እውን የሚሆነው። ይህ መስኮት እንዲሰፋ ራስን በግልጽነት ተጋላጭ ማድረግና የሌሎችን ግብረ-መልስ  በጸጋ መቀበል ያስፈልጋል።
ለሌሎች የተሰወረውን ማንነታችንን ሌሎች እንዲረዱልን ለማድረግ ራሳችንን ተጋላጭ ማድረግ ያስፈልጋል። ሰዎች የማያውቁልን ብዙ መልካም ሀሳብና ቅን ምኞት ሊኖረን ይችላል። ሆኖም ይህንን መልካም ሃሳባችንን ለሌሎች ለማስረዳትና ራሳችንን ለሌሎች ግልጽ ለማድረግ ካልቻልን፣ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሊረዱን ይችላሉ። በረጅም ጊዜ ሂደት ሃሳቤን ለአጋሮቼ በግልጽ ባላስረዳ ኖሮ የገዛ ወዳጆቼ እንኳን እንቅስቃሴዬን በሌላ ሊተረጉሙብኝና የመደመርን ጉዞ ሊያጨናግፉት ይችሉ ነበር። ራሳችንን ለሌሎች ካልገለጽን ብዙ መልካም ነገር ብናስብና ብንሰራ እንኳን ሌሎች ሰዎች ይሄንን አይረዱንም። አልተረዱንም ብለን ከማዘንና  ሰዎችን ከመክሰሳችን በፊት ራሳችንን በትክክል ስለ መግለጻችን ማሰብ ይኖርብናል።
በሌላ በኩል ደግሞ ለእኛ የተሰወረውን ጠባያችንን ለማወቅና ለማስተካከል ከሌሎች ሰዎች ግብረ መልስ መቀበል ያስፈልጋል። ለራሳችን የማይታወቀን ብዙ ጉድለት ሊኖርብን ይችላል። ጉድለታችንን የምንሞላው ሰዎች ስለ እኛ የሚሉትን በመስማትና ስህተታችንን በግልጽ እንዲነግሩን በማድረግ ነው።
ራስን ተጋላጭ ማድረግና ግብረ መልስ መቀበል የመደመር ዋልታና ማገሩ ነው። ሰዎች ባይረዱንም በትዕግስት ስለ ራሳችን ማስረዳት፣ ማሳወቅና በተግባር ማሳየት ያስፈልገናል። በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ስለ ራሳችን ያልተረዳነው ድክመትም ሆነ ጥንካሬ ካለ ሰዎች እንዲያስረዱን እድል መስጠት አለብን። ይህ ሲሆን ለሁላችን የሚታየው መስኮት እየሰፋ ይመጣል። አንዱ ስለ አንዱ ስለሚያውቅ ለመግባባት፣ ለመተማመን፣ በጋራ ለመስራት አንቸገርም። ለመደመር አንቸገርም።
ይህ የጆሃሪ መስኮት የቤተኛ ባይተዋርነትን የአስተውሎት ጥቅም ያላብሰናል። የውስጥና የውጭ እይታ እንዲኖረን ያደርጋል። የውስጥ እይታን ለሌሎች በማካፈልና የውጭ እይታን ከሌሎች በመቀበል መደመር እንችላለን። በመናገርና በማዳመጥ መደመር እንችላለን። ሌሎች ቀና ሃሳባችንን እስካልተረዱን ድረስ ቀና ማሰባችን ብቻ ትርጉም የለውም። ስለዚህ ሁሌም ሌሎች ሃሳባችንን እንዲረዱና ማንነታችንን እንዲያውቁ ከመናገር መቆጠብ የለብንም። ሌሎች የሚነግሩንን እስካልሰማንና ራሳችንን እስካልፈተሽን ድረስ መናገርም ብቻውን እንደ ሽንቁር እንስራ ፍጻሜው ባዶነትና ለማንም የማይጠቅም ሆኖ መጣል ብቻ ነው።
ሁሌም ራሳችን የምናውቀውን ነገር ሰው ደግሞ እንዲነግረን ብቻ የምንፈልግ ከሆነ ቤተኛ ባይተዋርነታችን አይዳብርም። የራስን ጩኸት መልሶ እንደማዳመጥ ነው። ራሳችንን ማወቅ ይሳነናል። ኢህአዴግ ለውጥ ማምጣት የሚችለው ከሁለት በኩል በሚመጣ ሰይፍ ነው። ያሉበትን ስህተቶች ከሌሎች አስተያየት እየተቀበለ በማረምና የሰራቸውን በጎ ስራዎችና ሀገር በማስተዳደር ሂደት ውስጥ መሬት ላይ ያለውን ተግዳሮት ደግሞ በግልጽ ለሌሎች በማስረዳት ነው።
እኛ ያደረግነው ይኸንኑ ነው። ከጥርጣሬና ከመጠላለፍ ፖለቲካ ነጻ የምንወጣው በሌሎች መንደር ምን ይባላል? ብለን ካዳመጥናቸውና ሌሎች ስለ እኛ የማያውቁትን ከነገርናቸው ብቻ ነው። ሁሉም በየጎራው የራሱን ብቻ የሙጥኝ ብሎ ካጉረመረመና ራሱን ብቻ ከሰማ ለውጥ አይኖርም። ሁለቱም ነገሮች ያስፈልጋሉ፤ ራስን ማወቅና ራስን ማሳወቅ። ይህ ሲሆን ነው ሁላችንም ነፍስ ለነፍስ መደማመጥ የምንችለው። በአራቱ የጆሀሪ መስኮቶች መካከል እየተመላለሱ የራስንና የሌሎችን ምልከታ ተጠቅሞ ራስን መፈተሽና ለማሳደግ መሞከር በእመርታ ለመደመር ወሳኝ እርምጃ ነው። ሀሳብን መናገርና የሌሎችን ሃሳብ (ግብረ መልስ) ማዳመጥ ቀስ በቀስ ተመሳሳይ አቋምና ራዕይ ያላቸው ሰዎች እየተሰባሰቡ እንዲሄዱ ያደርጋል። ይኸም የብቸኝነትን ጉድለት በመሙላት አቅም ለመፍጠር ያስችላል። ኢንሳ ውስጥ በነበርኩባቸው ዓመታት ያደረግኩት አንዱ ስኬታማ ስራ ሰዎችን ማብቃትና የተሻለ ነገር እንዲያልሙ ማነሳሳት እንደሆነ ቀደም ብዬ ገልጫለሁ። ይህ ጥረቴም በአጭር ጊዜ ፍሬ ማፍራት ጀምሮ ነበር። እንደውም በአንድ ወቅት ኢንሣ ላይ እየተፈጠረ የነበረውን አቅም ይበልጥ በሁሉም ደረጃዎች ተደራሽ ለማድረግ አስበን ነበር። ለዚህም ከሃያ በላይ የሚሆኑ በኢንሳ ጥሩ አቅም የፈጠሩ መካከለኛ አመራሮችን ወደ ሌሎች የመንግስት ተቋማት እንዲዘዋወሩ ማድረጋችን አብነት መሆን ይችላል።
(ባለፈው ቅዳሜ ተመርቆ ለንባብ ከበቃው የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “የመደመር መንገድ” የተቀነጨበ)


Read 2558 times
Administrator

Latest from Administrator