Monday, 15 March 2021 07:45

ፋኢቅ ቦልካይ ቤንች አሟቂው ቢሊዬነር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

እግር ኳስን በዓለም ዙርያ በ200 አገራት ከ250 ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንደሚጫወቱ ዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፊፋ ያመለክታል፡፡ ብሩኔያዊው ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋች ፋኢቅ ጄፈሪ ቦልካይ አንዱ ነው፡፡ ኳስን በፕሮፌሽናል ደረጃ ሲጫወት ከ12 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን  በእንግሊዝና በፖርቱጋል ሊጎች በሚወዳደሩ ክለቦች ወጣት ቡድኖች ተይዞ ልምምዱን እየሰራ ቆይቷል። በየክለቦቹ ዋና ቡድኖች ውስጥ ግን መሰለፍ አልቻለም፡፡ ከብሩኔይ ንጉሳውያን ቤተሰብ አንዱ መሆኑና እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር  ውርስ ሃብት እንዳለው መገመቱ ግን የመላው አለም ሚዲያን ትኩረት ስቦለታል፡፡ የዓለማችን ሃብታም እግር ኳስ ተጨዋች እየተባለ ከሚያሞቀው ቤንች ላይ ራሱንና አገሩን  ብሩኔይ ማስጠራቱን ቀጥሏል፡፡
ፋኢቅ ጄፈሪ ቦልካይ ትልውዱ በሎስ አንጀለስ ከተማ አሜሪካ ውስጥ ቢሆንም ወጣትነቱን ያሳለፈው በእንግሊዝ ነው፡፡  የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው በ2009 እኤአ ላይ ኤኤፍሲ ኒውበሪ በተባለ ክለብ ውስጥ በመጫወት ሲሆን፤ በሳውዝሃምፕተን ፉትቦል አካዳሚ ለአራት ዓመታት በፕሮፌሽናል ደረጃ ስልጠና መውሰድ ችሏል፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ወጣት ቡድን ለ1 ዓመት የሚሰራበትን እድል ቢያገኝም፤  ወደ ዋናው ቡድን ለመግባት ይቅርና በወጣት ቡድኑም ከልምምድ ውጭ የመሰለፍ እድል አልነበረውም፡፡ ስለዚህም  ወደ ሌላ ክለብ ለመዛወር አሰበና  ወደ ምዕራብ ለንደን አቅንቶ ለአርሰናል ተቀናቃኝ ቼልሲ ለሁለት ዓመት  ለመጫወት ፊርማውን አኑሮ ወጣት ቡድኑን ተቀላቀለ፡፡ በቼልሲ ወጣት ቡድን ውስጥ የተወሰኑ ጨዋታዎችን በዝቅተኛ ሊግ ከማድረጉም በላይ ሩበን ሎፍተስና ታሚ አብርሃም ጋር የመጫወት እድል ተፈጥሮለታል፡፡  ወደ  ቼልሲ ዋና ቡድን የሚያድግበት ሁኔታ እየጠበበ በመምጣቱ ወደ ሌላው የእንግሊዝ ክለብ ሌችስተር ሲቲ ለመዛወር ወስኗል፡፡ በሌችስተር ሲቲ ክለብ ለአምስት የውድድር ዘመናት ቆይታ ለማድረግ ነበር የተስማማው፡፡ በዋናው ቡድን ምንም አይነት የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ቢቆይም በክለቡ ደጋፊዎች ግን የሚደነቅ ዝነኛ ተጨዋቻቸው ነበር፡፡ በነዳጅ ሃብት የበለፀገችው  የብሩኔይ ደሴትና ከሚያስተዳድራት ንጉሳውያን ቤተሰብ ጋር ስሙ እየተሳሰረ  በሌችስተር ቆይታው በእንግሊዝ ሚዲያዎች ብዙ ተወርቶለታል፡፡
የሌችስተር ደጋፊዎች የዓለማችን ሃብታም ተጨዋች እኛ ጋር ነው በሚል ኩራታቸውን ገልፀዋል።  ንጉሳዊ ቤተሰቡን ዝነኛ ያደረጉ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘገባዎች ሲያዘናጉት አለማየታቸው ያስገርማቸዋል፡፡ በቤተሰቡ ሃብት ሳይመካ በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሙያው ላይ የመስራት ትጋቱንም በማድነቅ ያበረታቱት ነበር፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በቅርብ የሚያውቁት  ሃብታም ቤተሰብ እያለህ ኳስን መጫወት ምን ያደርግልሃል ሲሉ ደጋግመው ይጠይቁታል፡፡ ‹‹ በእኛ ቤተሰብ  ወንድሞቼና እህቶቼ ያለምንም ስራ ተንደላቅቀው የሚኖሩ ናቸው፡፡ እኔ የራሴን ሙያ እፈልጋለሁ፡፡ ምርጫዬ ደግሞ እግር ኳስ ነው›› ነበር መልሱ፡፡
ባንድ ወቅት ከፎርፎርቱ መፅሄት ጋር ባደረገው  ቃለምልልስ ላይ ደግሞ ‹‹ ከህፃንነቴ ጀምሮ ኳስን እጫወት ነበር፡፡ ሜዳ ላይ ኳስን በእግሬ ማንከባለል በጣም ያስደስተኛል፡፡ ወላጆቼ ሁሌም ድጋፋቸውን ይሰጡኛል፤ እግር ኳስ ተጨዋች ለመሆን ያለኝን ህልም እንዳሳካ ሲረዱኝ ቆይተዋል፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ በስነልቦናና በአካል ብቃት የሚያስፈልገኝን ስልጠና ሰጥተውኛል፡፡ ስለዚህም ቤተሰቦቼ ተምሳሌት ሆነውኛል፡፡›› በማለት ፋኢቅ ለስፖርቱ ያለውን ፍቅር ገልጿል፡፡
በአማካይ መስመር ላይ የሚጫወተው ፋኢቅ በአውሮፓ እግር ኳስ በተመሳሳይ የጨዋታ ቦታ ያለው ሰፊ ገበያ ውጥረት ውስጥ አልከተተውም፡፡ ከ16 ወራት በፊት የእንግሊዙን ክለብ ሌችስተር ሲቲ ለመልቀቅ ሲወስን በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ህይወቱ አዲስ ምዕራፍ እንደከፈተ ሁሉ ጉጉት አድሮበታል። በ22 ዓመቱ ላይ መገኘቱን፤ በእንግሊዝ ምርጥ ክለቦች ጥሩ ስልጠና መውሰዱን በመረዳት በፍጥነት ያስፈረመው ክለብ ደግሞ የፖርቱጋሉ ማርቲሞ ነበር።
‹‹የእግር ኳስ ሙያን ለመቀጠል ይህ ምርጥ ስፍራ ነው›› ሲል ለማርቲሞ በፈረመበት ወቅት የተናገረ ሲሆን የክለቡ ሃላፊዎችም  በዋናው ቡድን የሚሰለፍበትን እድል ሰፊ መሆኑን በመግለፅ 14 ቁጥር ማሊያ ሰጥተውታል፡፡ በፖርቱጋል ሊግ  በ14ኛ ደረጃ ወራጅ ቀጠና ላይ በሚገኘው ማርቲሞ  ያለፈውን 1 ዓመት በታታሪነት እየሰራ ቢሆንም በዋናው ቡድን የመሰለፉን እድል አላገኘም፡፡ በሚጫወትበት አማካይ ስፍራ ከ4 እና 5 በላይ ተጨዋቾችን የክለቡ አሰልጣኝ እያፈራረቁ ናቸው፡፡  ከሁለት ወር በፊት በማርቲሞ ሀ-23 ቡድን ተሰልፎ መጫወቱ አበረታቶታል፡፡ ከሳምንት በፊት ደግሞ በዋናው ቡድን በፖርቱጋል ሊግ ከስፖርቲንግ ጋር በነበረው  ጨዋታ ላይ ቤንች ላይ ተቀምጦም ማሳለፉ ተስፋውን አጠናክሮለታል፡፡
ፋኢቅ ጄፍሪ በክለብ ደረጃ በእንግሊዝ እና ፖርቱጋል ያገኛቸው ተመክሮዎች በወጣትነቱ ለብሩኔይ ብሄራዊ ቡድን እንዲጫወት አስችሎታል። በ22 ዓመቱ የብሄራዊ ቡድኑ አምበል ለመሆን የበቃ ሲሆን ባለፉት 5 ዓመታት በአገሩ ማሊያ 6 ጨዋታዎችን አድርጎ 1 ጎል ለማስቆጠር ችሏል፡፡ ከብሄራዊ ቡድን ባሻገር ለብሩኔይ እግር ኳስ በርካታ ፈርቀዳጅ ታሪኮችን የፈፀመም ነው፡፡ በእንግሊዝና ፖርቱጋል ክለቦች ለመጫወት የበቃ የመጀመርያው የብሩኔይ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ከመሆኑም በላይ በአሁን ወቅት ከኤሽያ ውድ ተጨዋቾች አንዱ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡  በጀርመኑ ድረገፅ ትራንስፈርማርከት ምልክታ መሰረት  ፋኢቅ ጄፍሪ ቦልካይ በተጨዋቾች ዝውውር ገበያው  200ሺ ዩሮ የዋጋ ተመን የተሰጠው ሲሆን ይህም የብሄራዊ ቡድኑ ውዱ ተከፋይ ያደርገዋል፡፡ ብዙዎቹ የብሩኔይ ተጨዋቾች ከ50ሺ ዩሮ በላይ  የዋጋ ተመን የላቸውም፡፡
ፋኢቅ በፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጨዋችነትን ሙያው በማድረጉ ደስተኛ ነው፡፡
በእንግሊዝና ፖርቱጋል ክለቦች ሲዘዋወር በዋና ቡድኖች ተሰልፎ የሚጫወትበትን እድል አለማግኘቱ ተስፋ አላስቆረጠውም፡፡ በማርቲሞ ክለብ ዘንድሮ መሰለፍ ከቻለ እና በከፍተኛ ሊግ ደረጃ ለመጫወት ከበቃ ለመታየት የሚችልበት እድሜ ላይ ይገኛል፡፡  ከእግር ኳስ ሜዳ ውጭ ስሙ በዓለም ዙርያ መግነኑ ግን አልቀረም፡፡ የዓለማችን ሃብታም ኳስ ተጨዋች እየተባለ በየጊዜው በተለያዩ ሚዲያዎች ሽፋን ማግኘቱን ቀጥሏል፡፡
በኤስያ የምትገኘው ብሩኔይ በነዳጅ ሃብቷ የበለፀገች አገር ናት፡፡ ፋኢቅ የብሩኔይ ንጉሳውያን ቤተሰብም አባል ሲሆን አባቱ  ጄፍሪ ቦልካይ የብሩኔይ ገዢ የሆኑት ሱልጣን ታናሽ ወንድም ናቸው፡፡  የብሩኔይ ሱልጣን ለፋኢቅ አጎቱ ሲሆኑ ያላቸው የሃብት መጠን ደግሞ ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡
የፋኢቅ አባት ጄፍሪ ቦልካይ ከ28 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት ያስመዘገቡ ሲሆን ሙሉ ስማቸው ርዝማኔው በጣም ያስገርማል፡፡ ‹‹ፔንጊራን ዲጋንዶግ ሻይቡል ማል ፔንጊራን ሙዳ ጄፍሪ ቦልካይ ኢብኒ አልማህሩም ሱልጣን ሃጂ ኦማር አሊ ሳይፉዲንሳዱል ካሃሪዋደዳይን›› ተብለው ይጠራሉ፡፡ በብሩኔይ ስረወመንግስት የልዑልነት ማዕረግ ያላቸው እኝህ ሰው ለመዝናናት በሚያደርጓቸው አስደናቂ ተግባራት የዓለም ሚዲያዎችን በተለያዩ ጊዜያት አነጋግረዋል፡፡ የብሩኔይ ሱልጣን 50ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ ማይክል ጃክሰን ላቀረበው ኮንሰርት 17 ሚሊዮን ዶላር ከፍለዋል፡፡ በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ዊትኒ ሃውሰተን በግላቸው ኮንሰርት እንድታቀርብላቸው ጠይቀው ባዶ ቼክ ፈርመው ዋጋሽን ሙይው ብለዋታል፡፡ ዊትኒም 7 ሚሊዮን ዶላር ቼኩ ላይ መፃፏን ዘገባዎች አውስተዋል፡፡
የብሩኔይ ልዑል የሆኑት አባቱ በቅንጡ አኗኗራቸው የዓለም ሚዲያ የሚያውቃቸው ሲሆን፤ በታዋቂው የአሜሪካ መፅሄት ቫኒቲፌር “notorious playboy”  በሚል ርእስ ሙሉ ዘገባ ተሰርቶባቸዋል። ብሩኔይ በኢንዶኔዠያ አቅራቢያ የምትገኝ ዙርያዋን በማሌዠያ እና በደቡብ ቻይና ባህር የተከበበች ደሴት ናት፡፡ አብዛኛው ህዝቧ የእስልምና ሓይማኖት ተከታይ ሲሆን፤ ነዳጅ እጅግ ርካሽ በመሆኑ ከ10 ሰው 7 ያህሉ መኪና አላቸው፡፡ የብሩኔይ ሱልጣን ከ5ሺ በላይ መኪና ያላቸው ሲሆን 20 ላበርጊኒ፤  160 ፖርሽ ፤ 130 ሮልስ ሮይስ፤ 360  ፌራሪ፤ 170 ጃግዋር፤ 180 ቢኤም ደብሊው፤ 360 ቤንትሌይ፤ 530 መርሴዲስ ቤንዝ መኪናዎች ከስብስቦቹ ይገኙበታል፡፡ በአለም ውስጥ ትልቁ የመኖሪያ ቤተመንግስት የሱልጣኑ ነው፡፡ የአገሪቱ መንግስት መቀመጫ ሆኖ ያገለግላል። ቤተ መንግስቱ 1,788 ክፍሎች፣ 257 የመታጠቢያ ቤቶች፣ መስጊድ፣ ለ 110 መኪናዎች የሚሆን ጋራዥ፣ 5 የመዋኛ ገንዳዎች ፣ ግዙፍ የግብዣ አዳራሽ እና ሌሎችም አሉት፡፡
 በፋኢቅ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ህይወት ላይ የቤተሰቡ ቱጃርነት ተፅእኖ ፈጥሮበታል ማለት ይቻላል፡፡ የስፖርት ሚዲያዎች ስለእሱ ከፃፉ የዓለማችን ሃብታሙ እግር ኳስ ተጨዋች የሚለውን ይጠቅሳሉ፡፡ የሃብት መጠኑንም እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ይገምታሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እጅግ ሀብታም የእግር ኳስ ተጫዋች እንደሆነና ያለው ሃብት  የሮናልዶ ፣ ሜሲ ፣ ኔይማር ፣ ምባፔ እና ፖግባ አጠቃላይ ሃብት ተደምሮም እንደሚበልጥ አውስተዋል፡፡ በወኪልነት አብረውት ከሰሩት አንዱ ይህን ሁኔታ በአደባባይ ተቃውሞታል፡፡
‹‹ፋኢቅ የዓለማችን ሃብታም ኳስ ተጨዋች አይደለም፡፡ እንደዚያ ብሎ ማሰብ ተገቢ አይደለም፡፡ በየሚዲያው እንደዚያም መዘገቡም አልጠቀመውም። እሱ በእግር ኳስ ሙያ ላይ መስራት የሚፈልግ ወጣት ነው›› ብሎ ተናግሯል፡፡  በአውሮፓ እግር ኳስ ለቢሊየነሩ ፋኢቅ ቦልኪያ አሁንም ጊዜው አልረፈደም፡፡ የሱ ፍላጎት ከቤተሰባቸው ዛፍ ይልቅ ሁሉም አይኖች በእግሩ ቢያተኩሩ ነው። ችሎታውን ለማዳበር ጊዜ እንዳለው በሙያውም ራሱን ለማስጠራትም እንደሚችል ያምናል፡፡


Read 936 times