Wednesday, 17 March 2021 00:00

የመቀሌዋ የግቢያችን የጦርነቱ ቃል አቀባይ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(3 votes)

ክፍል 6፡- ‹‹በጦርነቱ ብልፅግና አሸንፎ ትግራይን የሚገዛ ከሆነ እኔ ራሴን አጠፋለሁ!!››
                               
              በክፍል - 5 ትረካዬ ጦርነቱ ወደ መቀሌ እየተቃረበ መሄዱንና እኔም ከመቀሌ ለመውጣት ከጓደኞቼ ጋር መመካከር መጀመሬን ነግሬያችሁ ነበር ያቆምኩት፡፡ ዛሬም ከዚያው ካቆምኩበት እቀጥላለሁ፡፡
 ‹‹የዐቢይና የአማራ ፖለቲካ አንድ መሆኑ በጣም አስገርሞኛል›› አለኝ ሌላኛው ጓደኛዬ ደግሞ፡፡
‹‹እንዴት?›› አልኩት እኔም፡፡
እሱም፤ ‹‹የዐቢይ ፖለቲካና የአማራ ፖለቲካ መቼም ቢሆን ተስማምተው አያውቁም ነበር፤ በዚህ ጦርነት ግን በጣም እስኪገርመኝ ድረስ ፍፁም አንድ ዓይነት ሆነዋል›› አለኝ፡፡
‹‹ጦርነቱ የኢትዮጵያና የትግራይ ብቻ እንዳይመስልህ፤ የምስራቅ አፍሪካና የአረቦችም ሆኗል›› አለኝ ሦስተኛው ጓደኛዬ ተስፉ ደግሞ፡፡
እኔም፤ ‹‹እነዚህ ሀገሮች እነማን ናቸው? እንዴትስ ነው የተሳተፉት?; አልኩት፡፡
እሱም፤ ‹‹ሻዕቢያ በርካታ ክፍለ ጦሮችን በሁመራና በዛላንበሳ በኩል አስገብቷል። እንዲያውም ባለፈው መቀሌ አካባቢ ደብድባ የሄደችው ሚግ የሻቢያ ናት፤ ኢትዮጵያ ሚግ-23 የላትም›› አለኝ በስሜት።
‹‹እሺ ሌሎቹስ ሀገራት እነማን ናቸው?›› ጥያቄዬን አስከተልኩ፡፡
‹‹ዐቢይ ከሶማሊያ 1000 ወታደር ተቀብሏል፤ ሱዳንን 4000 ሰራዊት ቢጠይቃትም እንቢ ብለዋለች። ኤምሬት ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ሰጥታዋለች፤ ድሮኖቹ ከአሰብ ሲነሱ የሚያሳይ ምስል ከሳተላይት ተገኝቷል›› አለኝ፡፡
እኔም፤ ‹‹ኤምሬት ይሄንን የምታደርገው ምን ጥቅም ለማግኘት ነው?›› አልኩት፡፡
እሱም፤ ‹‹ሻዕቢያን ለመደገፍ ነው፤ ሻዕቢያ ልክ በሁመራ በኩል መግባት ሲጀምር እኛ የአስመራ ኤርፖርትን በሮኬት ዶግ አመድ አደረግንለት፤ ከሰናፌ አምስት ሺ ወታደር ሊያስገባ እየተዘጋጀ እያለ እንዲሁ በሮኬት ደመሰስናቸው፡፡ ይሄ ነገር ኤምሬትን አስቆጥቷታል፡፡ ኤምሬት ሻዕቢያ እንዲነካባት የማትፈልገው ደግሞ ኢሳያስ አሰብን ስለሸጠላት ነው፡፡ የሻዕቢያ ጣልቃ ገብነት ይሄ ብቻ እንዳይመስልህ፤ አሁን የህዳሴን ግድብ በተመለከተ ከግብፅ ጋር እየተደራደሩ ያሉት ሻዕቢያዎች ናቸው፤ ከሦስት ቀናት በፊት የኢሳያስ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር ካይሮ ሄደው በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከግብፅ ባለ ሥልጣናት ጋር ተደራድረው ሲመለሱ ታይተዋል"
ተስፉ የሚያወራው በንዴት ነው። ተስፉ ዕድሜው ገና 25 አካባቢ ቢሆን ነው፤ ለህወሓት ያለው ከልክ ያለፈ ቀናኢነት በጣም ስሜታዊ አድርጎታል፡፡ እንዲያውም ጦርነቱ የተጀመረ  አካባቢ ‹‹እዘምታለሁ›› እያለ ሲፎክር ነበር፡፡
ተስፉ በጣም ታናሼ ስለሆነ ‹‹እንደዚህማ ስሜታዊ አትሁን፤ በዚህ ንዴትህ ላይ መከላከያ መቀሌ ቢገባ በስነ ልቦና ትጎዳለህ›› አልኩት፡፡
እሱም፤ ‹‹ኧ! የመከላከያ ሰራዊት እኮ በራያ ግንባር በግራካሱ ተራራ እንደ ቅጠል ነው የረገፈው፡፡ መንግስት ስለደበቀው ነው ያልተወራው፡፡ እነ CNN ‹‹በቦታው ሄደን እንዘግብ›› ስላሉ ነው ከሀገር የተባረሩት። ጦርነት የገጠሙት እኮ የሁለት ሀገር መከላከያዎች ናቸው፡፡ ዐቢይ አሸንፎ መቀሌ ቢገባ እንኳ ጦርነቱ ወደ ሽምቅ ውጊያ ይቀየራል እንጂ ዐቢይማ ተረጋግቶ ትግራይን አይገዛም›› አለኝ፡፡
እኔ ለማረጋጋት ብዬ የተናገርኩት ነገር ጭራሽ እንዲገነፍል አደረገው፡፡
ለማንኛውም ወደመጣሁበት ጉዳይ ልግባ በማለት መጀመሪያ ላይ ወዳናገርኩት ጓደኛዬ ዞር አልኩና፤ ‹‹‹‹ህወሓት መቀሌ ተቀምጦ መድፍ የሚተኩስ ከሆነ እኛም እንተኩሳለን›› የሚለው የመከላከያ መግለጫ በጣም አሳስቦኛል፤ ቤቴን ለቅቄ ወደ ገጠር ልሄድ አስቤያለሁ፤ እናንተም እንዲሁ ካሰባችሁ አብረን እንሂድ፤ ነገውኑ ብንወጣ ደስ ይለኛል›› አልኩት፡፡
እሱ ግን ተረጋግቶ ‹‹ዋና ከተማ ውስጥ እንኳ ጦርነት አይኖርም፤ ጦርነቱን እዚያው ገጠር ጨርሰውት ነው የሚመጡት። ደግሞስ ከተማ ውስጥ ጦርነት ወይም የአየር ድብደባ ቢኖር እንኳ የቱ አካባቢ እንደሚመታ ማወቅ አይቻልም፤ የሸሸህበት አካባቢ የጦርነት አውድማ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ፣ አርፎ ቤት ውስጥ መቀመጥ ይሻላል›› አለኝ፡፡
‹‹የእኔም ተስፋ ዋና ከተማ የአሸናፊው የድል ቦታ እንጂ የጦርነት ስፍራ አይሆንም የሚል ነው፤ ግን ደግሞ ባይሆንስ እያልኩ እጨነቃለሁ›› አልኩትና አመስግኜው ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡ ወደ ግቢ ስገባ ቃል አቀባያችን የግቢያችንን ሴቶች ሰብስባ የዕለቱን መግለጫ ስትሰጥ አገኘኋት፤
‹‹ዐቢይ ዓለማቀፍ ጫና በዝቶበታል፡፡ ሱዳን ትግራይን በማገዝ ወደ ጦርነቱ ልትገባ ነው። ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ባደረገው ውትወታ አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ልትጥል ነው። በነገራችን ላይ፣ የትግራይ ልዩ ኃይል ድንበሩን ክፍት ያደረገው መከላከያ ኃይል በመቀሌ ዙሪያ ከተሰባሰበ በኋላ በአንድ ላይ በሚሳየል ሊደመስሳቸው ስላሰበ ነው። ሁሉም ትግራዋይ ህወሓትን ደግፎ በዚህ ጦርነት መሰለፍ አለበት፡፡ ትግሬ ሆኖ የህወሓት ደጋፊ ያልሆነ በብር የተገዛ ነው። አንድ ነገር ልንገራችሁ አይደል… በዚህ ጦርነት ብልፅግና አሸንፎ ትግራይን የሚገዛ ከሆነ እኔ ራሴን አጠፋለሁ፡፡ ለነገሩ ራሴን ባላጠፋ እንኳ እነሱ ይገድሉናል፡፡ ባጫ ደበሌ እኮ ከ14 ዓመት በላይ የሆነ ትግራዋይ ሁሉ መገደል አለበት›› ብሏል›› አለች፡፡
‹‹የባጫ ደበሌን ንግግር ሙሉውን ተከታትዬዋለሁ፤ መቼ ነው ደግሞ እንደዚህ ያለው!?›› በማለት ሳብሰለስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ባጫ ደበሌ መከላከያን ሰንጋ በሰንጋ ባደረገበት ንግግሩ ላይ ‹‹እነዚህን የሰይጣን ቁራጮች በህይወት እንዲኖሩ ልንፈቅድላቸው አይገባም›› የምትል ንግግር አለችው፤ ስለ ህወሓት የተናገራት ናት። ይሄንን ንግግሩን ነው ቃል አቀባያችን ‹‹ባጫ ደበሌ እንዲህ ብሏል›› በማለት የጠመዘዘችው፡፡ ያው ነገር መበለት የህወሓት ልዩ ችሎታው እንደሆነ ቀደም ብዬ ነግሬያችኋለሁ፡፡ ለማንኛውም፣ ቃል አቀባያችን ተስፋ ማድረግና ተስፋ መቁረጥ እየተፈራረቁባት ተቸግራለች፡፡ ስሜቷ በየሰዓቱ ይለዋወጣል፤ እንደምትሰማው ነገር አንድ ጊዜ ትፈካለች፤ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ኩምትር ትላለች፡፡
ህዳር 14 ቀን 2013 ኢቲቪ ሽሬ ላይ ያደረገውን ቃለ-መጠይቅ  አስተላለፈ። አብዛኛው የመቀሌ ህዝብ ግን አሁንም ሽሬና አክሱም በመከላከያ መያዛቸውን አያምንም።
ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ በየቀኑ መግለጫ ሲሰጡ የነበሩት ዶ/ር ደብረፅዮን፣ ከቴሌቪዥን መስኮት ከጠፉ በአምስተኛ ቀናቸው ዛሬ ህዳር 14 ቀን 2013 በትግራይ ቴሌቪዥን ብቅ አሉ፡፡ ዶ/ር ደብረፅዮን ከመቅረባቸው በፊት ለተወሰኑ ሰዓታት የትግራይ ቴሌቪዥንና ድምፂ ወያኔ ስርጭታቸው ተቋረጠ። እኔም በልቤ ‹‹ስርጭታቸው የተቋረጠው የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ስቱዲያቸውን ዶ/ር ደብረፅዮን ወዳሉበት ሥፍራ እስኪያዘዋውሩ ድረስ ነው፤ ይሄም ፕሬዚደንቱ ከመቀሌ ወጥተው መደበቃቸውን ያሳያል›› ብዬ ደመደምኩ። ለማንኛውም፣ ዶ/ር ደብረፅዮን በዚህ መግለጫቸው የሚከተሉትን ሐሳቦች አነሱ፣
ሰራዊታቸው የኢፌዲሪን መከላከያ ኃይል አዲስ በሆነ የማጥቃት ስልት በ3 ግንባር ከኋላው እንደወጋውና ድል እንዳደረገው፣
በዕዳጋ ሓሙስ የመጣው ሰራዊት የሻዕቢያ እንደሆነና እንደተደመሰሰ፣
በጦርነቱ ሶማሊያ በወታደር፣ ኤምሬት ደግሞ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ኢትዮጵያን እየረዱ እንደሆነ፣
እንዲሁም፣ ጦርነቱ የትግራይን ብሔርና ማንነት ለማጥፋት የተቃጣ «ህዝባዊ ጦርነት»  ስለሆነ ሁሉም ትግራዋይ በትግራይ ምድር የሚገኘውን ብረት ሁሉ ወደ ጠላት መወርወር እንዳለበት ገለፁ።
ዶ/ር ደብረ ፅዮን ይሄንን መግለጫ በሰጡ በነጋታው የትግራይ ቴሌቪዥን ሌላ የድል ሰበር ዜና ይዞ መጣ፤ ሰበር ዜናውም ‹‹የትግራይ ሰራዊት በራያ ግምባር 21ኛውን «የዐቢይ» መከላከያ ክፍለ ጦር ሙሉ በሙሉ ደምስሶ አላማጣን ተቆጣጠረ›› የሚል ነው።
የመከላከያ ኃይል 21ኛው ክፍለ ጦር በጀግንነቱ የታወቀ ስለሆነ፣ ይሄንን ዜና ዶ/ር ደብረፅዮንና አቶ ጌታቸው ረዳም አስተጋቡት፡፡ ዜናውም የመቀሌን ህዝብ አስፈነደቀ፡፡ በኢቲቪ ማታውኑ የቀረበው የ21ኛው ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ ግን ‹‹ይሄው አለን እየመጣን ነው›› በማለት አሾፈባቸው፡፡
ሆኖም ግን፣ ይሄ የህዝቡ ደስታ በነጋታው (ህዳር 16/2013) ይሸሻቸው ጀመር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መከላከያ ውቅሮ የመግባቱ ወሬ በመቀሌ ከተማ በስፋት መወራቱ ነው። ውቅሮ በአዲግራት መስመር የምትገኝ ከተማ ስትሆን፣ ለመቀሌ በመኪና የ45 ደቂቃ መንገድ ናት፡፡ ህዝቡ ይሄንን ወሬ የሰማው ከሚዲያዎች ሳይሆን ውቅሮ ከሚኖሩ ዘመዶቹ በስልክ ደውሎ ነው፡፡
ከጥቅምት 27 ቀን 2013 ጀምሮ የስልክ አገልግሎት በትግራይ ክልል ብቻ እንዲሰራ ቢደረግም፣ እሱም ግን መከላከያ የያዛቸው የትግራይ አካባቢዎች ስልክ እንዳይሰራ ተደርጓል፡፡ አሁን ስልክ የሚሰራው በመቀሌና በአካባቢዋ (ውቅሮን ጨምሮ) ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ መከላከያ ውቅሮ መግባቱን ተከትሎ ውቅሮ ከስልክ ኔትወርክ ውጭ ከመደረጓ በፊት ነው የመቀሌ ህዝብ አስደንጋጩን ዜና ውቅሮ ከሚኖሩ ዘመዶቹ የሰማው፡፡
ይሄም ወሬ የመቀሌን ከተማ ይበልጥ ሽባ አደረጋት፡፡ መንገዶች በአንድ ጊዜ ጭር አሉ፤ ትራንስፖርት ማግኘት ከባድ ሆነ፤ ታክሲዎችና ባጃጆች አልፎ አልፎ ቢታዩም፣ የአገልግሎት ታሪፋቸውን በአንድ ጊዜ ከ100% እስከ 300% አሳደጉት። ህዳር 12 ቀን 2013 አዲግራት በመከላከያ ከተያዘች በኋላ መቀሌ ያለ ፖሊስ ነው ውላ የምታድረው፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን መቀሌ ላይ ከፍርሃት በስተቀር ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር አልነበረም፡፡
ህዳር 16 ቀን 2013 የትግራይ ቴሌቪዥን ያሰራጨው ሰበር ዜና ግን ህዝቡን ከዚህ ፍርሃት አስወጥቶ ደስታ በደስታ አደረገው። ሰበር ዜናውም በራያ ግንባር በሰንቃጣ አካባቢ አራት ‹‹የዐቢይ›› ክፍለ ጦሮችን፣ አራት ታንኮችናና ጥይት የጫነ መኪና ደምስሰናል የሚል ነው፡፡
(ይቀጥላል…).


Read 6780 times