Saturday, 13 March 2021 13:38

አዲስ አበባ በጤናማ ከተሞች ሽርክና ድጋፍ የጀመረችውን የመንገድ ደህንነት ሥራ አጠናክራ ቀጥላለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   በአዲስ አበባ በየዓመቱ በአማካይ 450 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ይሞታሉ

                  አዲስ አበባ የዓለም ዓቀፍ ከተሞች መረብ አባል እንደመሆኗ የከተማዋ ኮሪደር ደኅንነት ማሻሻያ እና ሁለተኛ ዙር የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት መጠናቀቁን የትራፊክ ማጅመንት ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር ኢንጂነር ጃሬኛ ሂርጳ አስታወቁ፡፡ የጤናማ ከተሞች ሽርክና እውቅና ያለው ዓለም ዓቀፍ የከተሞች መረብ ሲሆን እንደ ካንሰር፣ስኳር፣የመንገድ ትራፊክ አደጋና የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በዓለም ዙሪያ ከ300 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወት ለመታደግ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከዚህ ዓለም አቀፍ ኢኒሽዬቲቭ ጋር የመንገድ ደህንነት ማሻሻያ ሥራዎች ላይ በጋራ እንደምትሰራ ተገልጿል፡፡ በከተማዋ በየዓመቱ ከ450 በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ይሞታሉ ተብሏል
“የማህበረሰብ ጤናን ለማሻሻል ጠንካራ አመራር ይጠይቃል” ያሉት ኢንጂነር ጂሬኛ፤የጤናማ ከተሞች ሽርክና ዓለም ዓቀፍ መረብ የመጀመሪያ ዙር አዲስ አበባ የተጀመረው በ2010 ዓ.ም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ዋና ዳሬክተሩ አክለውም፤ ነዋሪዎቻቸው የተሟላ ህይወትና ረጅም እድሜ እንዲኖራቸው አበክረው ከሚሰሩ ከእነዚህ ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው የከተሞች ቡድን አባላት ጋር በጋራ የመስራት እድል በማግኘታችን ደስተኛ ነን በለዋል፡፡
ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር የሚከሰት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል፣ የጤናማ ከተሞች ሽርክና 50 ሺ የአሜሪካ ዶላር የሚታደስ እርዳታ (renewal grant) ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳር ግዢ የሚውል ድጋፍ አበርክቷል፡፡ በዚሁ ጋር በተያያዘ፣ ኢንጂነር ጂሬኛ እንዳስታወሱት ባለፈው ዓመት በዚሁ ድርጅት የመጀመሪያ ዙር የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት፤90,819.12 ዶላር እርዳታ የተገዙና በፒያሳ ዙሪያ የተተከሉ ዲጂታል ቋሚ የፍጥነት መጠን ቋሚዎችን በመግዛትና በመትከል በአካባቢው ያለውን ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ለመቀነስና የህግ ማስከበሩን ስራ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ተችሏል ተብሏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ በአማካይ ከ450 ሰዎች በላይ በትራፊክ ግጭት ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ ለመንገድ ትራፊክ አደጋ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ውስጥ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር የአደጋ መንስኤ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በፍጥነት ማሽከርከር ለአደጋ የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ ሲሆን የሚያደርሰው ጉዳትም እንዲሁ የከፋ ያደርገዋል፡፡ ይኸውም በአጠቃላይ ከሚደርሰው የትራፊክ ግጭት ውስጥ 1/3ኛ የሚሆነው ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር እንደሚሸፍን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንቴ ኤጀንሲ ከጤናማ ከተሞች ሽርክና ጋር በመተባበር በከተማዋ የተመረጡ የተለያዩ ኮሪደሮች የመንገድ ደህንነት ለማረጋገጥ ሁለተኛውን ዙር የመንገድ አካፋይ ደኅንነት ማሻሻያና የፍጥነት አስተዳደር ፕሮጀክት በስፋት አከናውነዋል ያለው መግለጫው፤ ኤጀንሲው በመጀመሪያ 4.5 ኪ.ሜ የሚሸፍኑትን ከጎሮ-ጃክሮስ መብራት ኃይል በሀያአራት ኮሪደሮች ለይቷል ብሏል፡፡ የኮሪደሮቹ ሁለቱም አቅጣጫዎች 30 ሜትር ስፋት ያላቸው ሁለት ሌነሮች የያዙ ሲሆኑ በተጨማሪም የእግረኛ መንገድና የመንገድ አካፋይ ዲዛይን የተደረገውና የተገነባው ዋና መጋቢ መንገዶች ( principal arterial street ) ጥቅም ላይ ለማዋል በወጣው መመዘኛ መስፈርት መሰረት ነው ተብሏል፡፡
የተመረጡ ኮሪደሮች ከመሀል ከተማ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ፣ ከመኖሪያ አካባቢ ወደ ስራ ቦታ ደርሶ መልስ የሚያጓጉዝ መስመር በመሆኑ ስትራቴጂካሊ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ ከምንም በላይ ኮሪደሮቹ የተመረጡ የመንገድ ደህንነት እና የትራፊክ እንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ያለው የትራፊክ አደጋ መረጃ እንሚያሳየው እነዚህ የመንገድ አካፋዮች ከ31 ሰዎች በላይ በትራፊክ ግጭት ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡


Read 3430 times