Saturday, 13 March 2021 13:23

‘አለርጂክ’ ክፉ ነገር ነው!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

       "--እና አምስት መቶዋን ‘ላፍ’ ያደርግና አምስት ቀን፣ አምስት ሳምንት፣ አምስት ወር...ጭጭ! ምን አለፋችሁ... የአሥራ አምስት ዓመት ወዳጅነትን በአምስት መቶ ብር ይለውጠዋል፡፡ ምክንያቱም ዘንድሮ ብዙዎቻችን በተለይ ቅርብ ከሆኑ ሰዎቻችን የወሰድነውን የገንዘብም ሆነ የእቃ ብድር የመመለስ አለርጂክ አለብንና፡፡ ኮሚኩ ነገር እኮ...አለ አይደል...ስንመልስም ልክ ከኪሳችን አውጥተን የምንከፍለው የግል ገንዘባችን ይመስል እየከፋን ነው፡፡--"
    
                እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ስማ፣ ጊዜ የማይሰጥ በጣም አስቸኳይ ጉዳይ ነው ነው የገጠመኝ፡፡”
“ምን ሆንክ፣ ቤተሰብ ደህና አይደለም እንዴ!”
“ዘንድሮ ምን ደህንነት አለ ብለህ ነው! (ወዴት! ወዴት! ስለ ራስህ ቤተሰብ ነው እንጂ ስለ
ዘንድሮ አልተጠየቅህም! የምን በአክቲቪስቶች ሥራ መግባት ነው! ቂ...ቂ..ቂ..) ከቻልክ ትንሽ ገንዘብ ብታበድረኝ ብዬ ነው፡፡”
“የእኔ ጌታ፣ ይግረምሀና እኔ ራሴ አበድረኝ ልልህ ዳር፣ ዳር ስል ነው የቀደምከኝ፡፡”
“ይህን ያህል ብዙ ገንዘብ እኮ አይደለም። ከቤተሰብ ሰው ታሞብኝ ለመድኃኒት መግዣ አምስት መቶ ብር ብቻ ፈልጌ ነው።” ይቺ እንግዲህ አንዳንድ ጊዜ እውነት፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ ታክቲክ ነች፡፡ ዘንድሮ እንደሁ ያለ ‘ታክቲክ’ የሚሆን ነገር እየጠፋ ነው የምንቸገረው፡፡ ስለ ቤተሰብ ችግር ሲነገረን ነግ በእኔ ነውና መቼም ሰው እንደመሆናችን፣ ትንሽ ማዘናችን አይቀርም፡፡ እናም እኛ ብድር ልንጠይቅ ስንል ‘የተቀደምነው’ ሰዎች፣ እጃችንን ኪሳችን እንከትና በጣቶቻችን ፈልፍለን አምስት መቶዋን እንመዛለን፡፡
“እየው ኪሴ ያለው የመጨረሻ ገንዘብ ነው፡፡ (ኪሳችን ያለው ‘የመጨረሻው’ ገንዘብ ልክ የተጠየቀውን አምስት መቶ ብር መሆኑ የኩዋንተም ምናምን ምርምር ሳይጠይቅ አይቀርም፡፡)
“አታስብ፣ ነገ በጠዋቱ ነው የምመልስልህ።”
እና አምስት መቶዋን ‘ላፍ’ ያደርግና አምስት ቀን፣ አምስት ሳምንት፣ አምስት ወር...ጭጭ! ምን አለፋችሁ... የአሥራ አምስት ዓመት ወዳጅነትን በአምስት መቶ ብር ይለውጠዋል፡፡ ምክንያቱም ዘንድሮ ብዙዎቻችን በተለይ ቅርብ ከሆኑ ሰዎቻችን የወሰድነውን የገንዘብም ሆነ የእቃ ብድር የመመለስ አለርጂክ አለብንና፡፡ ኮሚኩ ነገር እኮ... አለ አይደል... ስንመልስም ልክ ከኪሳችን አውጥተን የምንከፍለው የግል ገንዘባችን ይመስል እየከፋን ነው። (እነ እንትና፣ በሉ ደግሞ “እንዲህ እኮ የሚያወራው ይሄኔ ከራሱ ኤክስፒሪየንስ ተነስቶ ነው፣” ምናምን እያላችሁ ለአቅመ ‘‘ኮንስፒሬሲ ቲዬሪ’ አብቁኝ አሉ!)
‘አለርጂክ’ ክፉ ነገር ነው፡፡
እናንተ የለበሳችሁት ልብስና እሱ የለበሰው ልብስ ቢወዳደር፣ የእናንተ ከሰንበት የሹሮ ሜዳና ኮልፌ ‘ቢግ ሴል’ የተገኘ፤ የእሱ ደግሞ በልዩ ትእዛዝ እንትን ከሚባል ሀገር የመጣለት ይመስላል። እንደውም... አለ አይደል... በሆዳችሁ “እንዲህ የሚያምር ጃኬት ከየት ሀገር ቢያስመጣው ነው?” ብላችሁ በሰው የግል ጉዳይ ጣልቃ ትገባላችሁ፡፡
እናማ...ፊት ለፊታችሁ እየቀረበ ሲመጣ እንግዳ ሳይሆን ያኔ ‘ቀዮ’ የሚባለው መጠሪያ እንደ ዛሬ የወል ስም ሳይሆን በፊት “ቀዮ” ትሉት የነበረው የሰፈር ልጅ ከአማሪካን ‘አምሮበት የመጣ’ ሊመስላችሁ ይችላል። (እኔ የምለው... አሜሪካ ያው መቼም ብዙ ነገሮች ያሉባት ሀገር ነች፡፡ እድሜ ለትረምፕ እንጂ፣ ብዙ ጉዷ የወጣው በእሳቸው ዘመን ነው፡፡ እናማ...ግራ የገባን ነገር አለ፡፡
 “መንዝሊ የምልክልህን ሀንድረድ ዶላር ከእንግዲህ ዋንስ ኤቭሪ ቱ መንዝስ ነው የምልክልህ፡፡ ላይፍ ኢዝ ታፍ!” የምትሉን ወገኖቻችን፤ ምነው የምትልኩልንና በማህበራዊ ሚዲያ የምትለጥፏቸው ፎቶዎች፤ ‘ታፍ’ የሚል ነገር አይታይባቸው! እናማ...በአማሪካን ኑሮ ‘ታፍ’ እየሆነ በሄደ ቁጥር የሰው መልክ እንዲህ ያበራል እንዴ! ብቻ የኑሮን ‘ታፍ’ መሆን የእኛን ታህል ብታውቋት ኖሮ፣ በበርገር ፈንታ ‘ሂሳችሁን’ ነበር የምትውጧት!)
እናላችሁ... ሰውየው ቀረብ ይልና በራስ አንቅስቃሴ ሰላም ይላችኋል፣ ግራ እንደገባችሁ ሰላም ትላላችሁ፡፡
“ወንድሜ ሀምሳ ብር ላስቸግርህ እችላለሁ!” ‘በትክክል ተመልሷል አስብሎ የሚያስጨበጭብ ምላሽ ቢኖር፣ “ልታስቸግረኝ አትችልም!” የሚለው ነበር። ግን ለእውነተኛ ስሜቶቻችን ሳይሆን ለእይታ የምንኖር በርከት ስላልን እንደዛ አንመልስም፡፡ ይልቁንም ወይ ኪሳችሁ ትገቡና፤
“ያለኝ ሀያ ብር ብቻ ነው...” ብላችሁ ትላላችሁ፡፡ እሱ ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው... “ኢትስ ኦልራይት፣” ብሎ ይቀበላችኋል። አለ አይደል... ‘የልመና ማርኬቲንግ’ ምናምን የሚል ነገር ያለ ነው የሚመስለው፡፡ ከፍ አደርጎ ጠይቆ ‘መደበኛዋን’ መቀበል፡፡ ልክ ዘጠኝ መቶ ብር የተባለውን ሱሪ ‘በድርድር’ አራት ከሀምሳ እንደምትወስዱት ማለት ነው፡፡
ወይ ደግሞ እንዳለች ሀምሳዋን መዛችሁ ትሰጣላችሁ፡፡ “ሲያሳዝን! አሁን ይህን የመሰለ ሰው ሲለምን እንዴት ነው እምቢ የምለው! ይሄኔ የቀኑበት ምቀኞች የሆነ ነገር አስጠምጥመውበት ይሆናል!” እናላችሁ... በእውነት ቸግሯቸው፣ የለበሱት ልብስ እላያቸው ላይ ተበጣጥሶ አልቆ፣ ከሰውነት ውጪ ሆነው እገዛ ከሚፈልጉት ይልቅ ለእንደነዚህ ያሉት ገና ከእነወዛቸው ላሉት ሰዎች ‘ልባችን የሚራራ’ ብዙ ነን። እሱዬው ግን በሆዱ... “ኦ! መቶ ነበር መጠየቅ የነበረብኝ!” ምናምን ማለቱ አይቀርም። ማርኬቲንግ ነዋ! ግን ደግሞ ዘንድሮ የሚያሳስቡን ነገሮች በርካታ ስለሆኑ እንጂ... አለ አይደል... እንዲህ አይነት ሰዎች፣ ማለት ተወልውለውና የ‘ቱ ታውዘንድ ፊፍቲ’ ብር ጫማቸውን በክሬምና በቀለም አስወለውለው ‘የሚለምኑ’ ሰዎች መብዛታቸው ሊያሳስብ ይገባል፡፡
“ሰው ምን ይለኛል?” አይነት ይሉኝታ ብዙ መደረግ ያለባቸውን ነገሮች ከማድረግ የሚያግደን ቢሆንም፣ አንዳንዴ ደግሞ ይሉኝታ ከእንዲህ አይነት በህብረተሰቡ ዘንድ ዝቅተኛ ስሜት ከሚያስከትሉብን ነገሮችም ይጠብቀናል፡፡ “እንትና የእንትን ቡቲክ ሙሉ ልብሱን ግጥም አድርጎ ሲለምን አላየው መሰለህ!” መባል እኮ የኒሻን ጉደይ አይደለም፡፡ ከመሀላቸው አንድም የቸገረው የለም ማለት የኢትዮጵያን ኑሮ አለማወቅ ነው፡፡ ብዙዎቹ ግን እናንተ ለምሳ የሹሮ ዋጋ ገና ከሀምሳ አምስት ብር ከፍ ያላለበትን እንትናዬ ሹሮ ቤትን ስታፈላልጉ፣ እነሱ አሪፍ ሬስቱራንት ስቴካቸውን ያማርጣሉ። (በአንድ ወቅት መሀል ከተማ አካባቢ አንድ በዚህ አይነት ‘ቢዝነስ’ የተሰማራ ሰው በየጥቂት ሰዓቱ በአካባቢው ባለ ቡና ቤት እየገባ ጎርደን ጂኑን ይገለብጥ ነበር፡፡ የሰጡት ሰዎች እኮ በድራፍታቸው ውስጥ ነው ‘የሚዋኙት!’  
ግን ምን ይደረግ፣ ዘንድሮ እንደሁ ከላይ እስከ ታች ለይሉኝታ አለርጂክ የሆንን ነው የሚመስለው፡፡
‘አለርጂክ’ ክፉ ነገር ነው፡፡
አለርጂክ የሆኑብን ነገሮች በዝተዋል። ስሙኝማ...እኔ የምለው፣ ሰዋችን ፈራንክ ሲያገኝ፣ የስልጣን የምትመስል ወንበር ምናምን ሲያገኝ ‘አለርጂክ‘ የሚሆኑበት ነገሮች ይበዛሉ እንዴ! ልክ ነዋ...
“እንዴት አይነት የተባረከ ሰው መሰላችሁ። የሰው ልጅ ሆኖ የተፈጠረው በስህተት ነው፡፡ መልእከ መሆን የነበረበት እኮ ነው!”
“እሷ እኮ ምን አለፋችሁ፣ ርህሩህ ለሰው አዛኝ፡፡ አንድ ዳቦ ብቻ ቢኖራት ግማሹን ቆርሳ ለቸገረው የምታካፍል ነች፣” ሲባልላቸው ይከርማል፡፡ እነሱም ቢሆኑ ትንሹንም፣ ትልቁንም ሰላም እንኳን ሲሉ ወገባቸው ሊቀነጠስ እስኪደርስ ጎንበስ ብለው ነው፡፡  
ከዛላችሁ... እሱዬው የሆነች የስልጣን የምትመስል ወንበር ያገኛል፡፡ ገና ቆዳ ወንበሩ የሽፋን ላስቲክ ሙሉ ለሙሉ ሳይነሳ ነገር ይጀምረዋል፡፡ እንደዛ እንደ መልአክ ሲያየውና ሲያከብረው የነበረው ህብረተሰብ ላይ ትከሻ ማሳየት ይጀምራል...የሌለውን ትከሻ! ደግሞላችሁ... ቀደም ሲል የእድሩም፣ የእቁቡም የምኑም ስብሰባ የማያመልጠው፣ በድግስም ሆነ በሀዘን ላይ የማይጠፋው ሰው በሁሉም ስፍራዎች የውሀ ሽታ ይሆናል። ቀደም ሲል ከወገቡም፣ ከአንገቱም ሰበር ብሎ ሰላምታ ይሰጣቸው ለነበሩ ሰዎች ሁሉ መጀመሪያ ወደ ራስ እንቅስቃሴ ብቻ ሰላምታ ያወርዳቸዋል፡፡ ከዛም ይቀጥልና በሆነ አጣና በሚያክል የካዝና ቁልፍ አይነት ይዘጋቸዋል፡፡ ሁሉም ነገር ድርግም ይላል፡፡ በዛ ቢበቃ ጥሩ...ጭራሽ ግልምጫ ይጀምራል እንጂ! ያላወቀው ነገር ዘንድሮ ስልጣን በድምጽ ፍጥነት እንደመጣች ሁሉ በብርሀን ፍጥነት መጥፋት እንደምትችል ነው፡፡
እኔ የምለው... ስልጣን ላይ ሲወጡ ትህትና ‘አለርጂክ’ የሚሆንባቸው ለምንድነው?”
እሷዬዋ ደግሞ ምን ታገኝ መሰላችሁ...መአት ፈራንክ! “እንዴት?” “በምን አይነት መንገድ?” ምናምን የሚሉትን ነገሮች ተዉአቸው፡፡ ግን ያቺ ሰው ከሰው የማትለየው፣ አንዲቱን ዳቦ ከቸገረው ጋር ስትካፈል የነበረችው ሴት...ምን አለፋችሁ... በአጠቃላለይ ሰው የሚባል ነገር ትጠየፋለች። ያላወቀችው ነገር ዘንድሮ ፈራንክ በድምጽ ፍጥነት እንደመጣች ሁሉ፣ በብርሀን ፍጥነት መጥፋት እንደምትችል ነው፡፡
እኔ የምለው... ፈራንክ ሲያገኙ ትህትና ‘አለርጂክ’ የሚሆንባቸው ለምንድነው?”
‘አለርጂክ’ ክፉ ነገር ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1367 times