Saturday, 13 March 2021 13:19

6ኛው አገራዊ ምርጫ 2013 “ከምርጫው ብንወጣም በሰላማዊ ትግል እንቀጥላለን”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 • ከሁሉም በፊት ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ይገባናል
   • በምርጫው ባለመሳተፋችን መቼም ቢሆን አይቆጨንም

           ከተመሰረተ ከ25 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ)፤ ከዘንድሮው አገራዊ ምርጫ ራሱን ማግለሉን ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል፡፡ ከምርጫው ለመውጣት ያስገደደውም የጽ/ቤቶቹ መዘጋትና የአመራር አባላቱ ለአስር መዳረግ መሆኑን ይገልፃል፡፡ መንግስት በቅድሚያ  ለብሔራዊ መግባባትና ምክክር ጊዜ ቢሰጥ ኖሮ፣ አሁን የሚታዩት ችግሮች ይቀረፉ እንደነበር የፓርቲው መሪ ያምናሉ፡፡  
ለመሆኑ ኦፌኮን ብዙዎች ታሪካዊ ከሚሉት የዘንድሮ አገራዊ ምርጫ ለመውጣት  በምክንያትነት ያቀረባቸው ጉዳዮች ምን ያህል ተጨባጭ ናቸው? ችግሮቹን ቀርፎ ወደ ምርጫው ለመግባት ያሳየው ጥረት ምን ያህል ነው? ወይስ ራሱን ለምርጫው በቅጡ ሳያዘጋጅ ቀርቶ ይሆን? ቀጣይ የፖለቲካ እንቅስቃሴውንስ እንዴት ሊቃኘው አስቧል? ለሁሉም ምላሽና ማብራሪያ የሚሰጡን አንጋፋው ፖለቲከኛና የፓርቲው ም/ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ናቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡

               ከምርጫው ለመውጣት የተገደዳችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?
እኛ ለምርጫው በቂ ዝግጅት አድርገን ነበር። ለ2012 ምርጫም በሚገባ ተዘጋጅተን ነበር። ነገር ግን በኮቪድ -19 ምክንያት ተራዘመ። በዚህ ጊዜ ውስጥ መንግስት ለብሔራዊ መግባባትና ምክክር ትኩረት ሰጥቶ ፖለቲካውን ለማስተካከል እንዲጠቀምበት አሳስበናል። ነገር ግን መንግስት  ይህን አላደረገም። የሆኖ ሆኖ እኛ በዘንድሮ ምርጫ  ለመሳተፍ አቅምም ዝግጅትም አያንሰንም ነበር። ነገር ግን ሀገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ምርጫን የሚጋብዝ  አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለብሔራዊ መግባባት እድል ቢሰጥ የተሻለ ሂደት መፍጠር ያስችል ነበር። ምርጫውም ከዚያ በኋላ ቢመጣ በተሻለ መግባባትና የፖለቲካ ምህዳር ማካሄድ ይቻል ነበር። ነገር ግን መንግስት ይሄን አልፈለገም። እኛ ይሄም ይሁን  ብለን ወደ ምርጫ ለመግባት ዝግጁ ነበርን። ነገር ግን የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ፣ የተፈጠረው ግን እኛን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ማሳደድ ሆነ። በኦሮሚያ የሚገኙ አባላቶችና አመራሮች በአብዛኛው ታስረውብናል፡፡ ወደ 10ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ናቸው በዚህ ሰበብ የታሰሩት። በሌላ በኩል፤ ኦሮሚያ ላይ ኮማንድ ፖስት ተዘርግቶ፣ አብዛኛው አካባቢ  በኮማንድ ፖስት ስር ነው ያለው። በሌላ በኩል፤ በትግራይ ደግሞ በርካታ ግፎች እየተፈጸሙ ነው።
እርሰዎ የሚሏቸው ነገሮች ከምርጫው ለመውጣት እንዴት ሰበብ ሊሆናችሁ ይችላል? ከዚህ በፊት በተደረጉት ምርጫዎች ከዚህ የባሱ ችግሮች አልነበሩም እንዴ? የአሁኑን አዲስ ያደረገውና ኦፌኮ ከምርጫው እንዲወጣ ያስገደደው ጉዳይ ምንድን ነው?
ድሮ ወያኔ አባላትን ያስር ነበር፤ ግን ፍ/ቤት ነጻ ናቸው ብሎ ከለቀቃቸው በኋላ አግቶ አያቆይም። ጽ/ቤቶቻችንም በዚህ መጠን ተዘግቶብን አያውቅም። አሁን ፍ/ቤት በዋስ ወይም በነጻ ይፈቱ ያላቸውን ግለሰቦች አግቶ ማቆየት የተለመደ ሆኗል። ይህ ሁኔታውን ልዩ ያደርገዋል። ህጉን አክብሬ አስከብራለሁ የሚለው መንግስት  ህግ የሚጥስ ሆኗል፡፡  ታዲያ ለማን ነው አቤት የሚባለው።
በፍ/ቤት ትእዛዝ እንዲፈቱ ተብለው ታስረው የቆዩ የኦፌኮ አባላት አሉ? ምን ያህል ናቸው?
ባይኖሩ እንዴት አሉ እልሃለሁ። ይህን ማንም ቢጠይቀን ማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን። እኛ ከመሬት ተነስተን አይደለም ይህን የምንለው። ማስረጃ ለጠየቀን አካል በዝርዝር ማቅረብ እንችላለን።
ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎችም “ጽ/ቤቶች ተዘጉብን፣አባላት ታሰሩብን” የሚሉ አቤቱታዎች ስታቀርቡ እንደ ነበር ይታወሳል። አሁን ያጋጠማችሁ ችግር ምን ያህል የከፋ ቢሆን ነው…?
እኛ አመራርና አባሎቻችን ሲታሰሩብን አሁንም ይሁን ብለን፣ ሌሎች አባሎችን ከየወረዳው መልምለን ለምርጫ ለማቅረብ ብናስብም፣ የጽ/ቤቶቻችን መዘጋት ግን እንቅፋት ሆነብን። ከዚህ በፊት ችግሩን አመልክተን እንደሚስተካከል ተነግሮን ነበር። እኛ እኮ መፍትሄ የሚሰጠን አካል ነው ያጣነው። ማንም ሊሰማን አልቻለም። አሁን እየደረሰብን ያለው እንግልት ከዚህ በፊት ከነበረው የከፋ ነው።
ችግራችሁን ለማን አመለከታችሁ? ምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ፤ ፓርቲዎች የፅ/ቤቶቻችን መዘጋት አስመልክቶ  ምን ያህል ጽ/ቤቶች እንደተዘጋባቸው ዝርዝር መረጃ ቢጠይቅም ሊያገኝ አለመቻሉን ነው ያስታወቀው እናንተ ምን ትላላችሁ?
ለምን እናንተ መጥታችሁ የተጻጻፍንባቸውን፣ ያመለከትናቸውን ሰነዶች አታዩም? እኛኮ እየገጠመን ያለው ማስረጃን የመካድ ችግር ነው። ሰው ታስሮብናል ስንል ያሰርነው የለም ይሉናል። ታዲያ ይሄ እንዴት ነው መፍትሄ የሚያገኘው? ለምሳሌ አዳማ ላይ የእኛን ተወካይ ከጽ/ቤት ወሰዱና አሰሩት፤ ትንሽ ቆይተው ለቀቁት። ሲለቀቅ ሄዶ ቢሮውን ከፈተ። ወዲያው “እዚህ ቦታ ከእንግዲህ ብትገኝ እንደፋሃለን” አሉት። አሁን ሰውየው ለነፍሱ ፈርቶ  አካባቢውን ለቆ ሄዷል። ለዚህ እንዴት ነው ማስረጃ ማቅረብ የሚቻለው? ሲጀመር ድርጊቱን ሲፈጽሙ ማስረጃ እንዳይይዝ አድርገው ነው። ነቀምቴም ተመሳሳይ ነገር ነው የገጠመን። ተወካያችንን  በዓመት ውስጥ ከአምስትና ስድስት ጊዜ በላይ እያሰሩ ሲፈቱት ቆይተዋል። ታዲያ ይሄ ምን ማለት ነው። እኛ´ኮ ግራ ነው የተጋባነው።
በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድሮ  ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ምርጫ ይካሄዳል በሚል እምነትና ተስፋ በምርጫው በንቃት እየተሳተፉ ነው። ከምርጫው በኋላም የሚመሰረተው መንግስት ከዚህ ቀደሙ በእጅጉ የተሻለ የሚሆንበት እድል እንዳለም ተስፋ አድርገዋል።  ኦፌኮ የዚህ ሂደት አካል አለመሆኑ በቀጣይ የፖለቲካ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አያሳድርበትም? ፓርቲው የሚያስቆጭ እድል እያመለጠው ይሆን?
እኛ ፈፅሞ  አይቆጨንም። ይህን አድርገን ቢሆን ኖሮ የምንለውና ለቁጭት የሚያበቃን ነገር የለም።  ሁሉም ነገር ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ነው ከምርጫው የወጣነው። በጉልበት አናምንም፤ በመነጋገር በመስማማት ችግሮችን በመፍታት ነው የምናምነው። ይሄን ለማድረግ ያልሞከርነው ነገር የለም። ነገር ግን ወደ ምርጫው ባዶ እጃችንን እንድንገባና አጫዋች እንድንሆን ነው የተፈለገው። ይሄን ደግሞ እኛ አንፈቅድም። በዚህ ውሳኔያችንም ምንም የሚቆጨን ነገር የለም፤ ለወደፊትም አይኖርም። የምንታገልለት የኦሮሞ ህዝብም ይሄን በሚገባ ይረዳናል።
ምናልባት ሃገሪቱ የተሳካ ምርጫ ከአካሄደች ቀጣዩ አምስት ዓመት ወሳኝ የሽግግር ጊዜ ይሆናል። ህገ-መንግስቱ የሚሻሻልበትና በርካታ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች የሚደረጉበት ጊዜ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ በምርጫው ላለመሳተፍ ስትወስኑ በዚህ ሂደት የመሳተፍ እድላችሁን እያጠበባችሁ መሆኑን አጢናችሁታል?
እኛን  ለመግፋት የተሞከረውም በዚህ ሂደት እንድንሳተፍ ስለማንፈለግ ነው። ኦፌኮም ኦነግም በዚህ ምርጫ እንዳይሳተፉ የተፈለገው ለዚህ ነው። እኛ ህብረ-ብሔራዊ ፌደራሊዝምን ነው የምንከተለው፡፡ ጠንካራ የምርጫ ተፎካካሪ እንደምንሆንባቸው አውቀውታል። ስለዚህ በስልት እኛን ከምርጫው ገለል ማድረግን ነው የመረጡት። ይሄ ዘለቄታዊ ሰላም ይፈጥራል ወይ? የሚለውን አብረን የምናየው ይሆናል። ሌሎችን በሸፍጥና በተንኮል በማግለል የሚደረጉ ነገሮች እስከ ምን ድረስ ይዘልቃሉ የሚለው ነው ጥያቄው  ይህን ደጋግመው ቢያስቡት መልካም ነው።
በቀጣይ የፖለቲካ ተሳትፏችሁ በምን መልኩ ይሆናል?
በደንብ ማሰብ የሚገባን ሃገራችን አሁን ምን ላይ ነው ያለችው የሚለውን ጉዳይ ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይሄን ሰከን ብሎ ማሰብ አለበት። ዓለም በሙሉ ምን ማድረግ እንደሚያዋጣን እየነገረን ነው። ግን አሁንም እንደ ድሮው በራሳችን ብቻ ነው እንጂ ሌላ አንሰማም ብለን ነው የቀጠልነው። ሱዳን በግልጽ ወርራናለች፣ ኤርትራ በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ገብታለች፣ በሃገር ውስጥ ያሉ የፀጥታ ችግሮች በግልጽ ይታወቃሉ። ንጹሀን ሰዎች በየቀኑ ይገደላሉ። የጅምላ ጭፍጨፋዎች ይፈፀማሉ፡፡ በስደት ላይ ያሉ እንኳ ከ400 በላይ ዜጎቻችን አልቀዋል። ሃገሪቱ በአጠቃላይ በውስብስብ ችግሮች ውስጥ ናት። እኛ ትግላችን ስልጣን ለመያዝ ብቻ አይደለም፤ ህዝባችን እረፍት እንዲያገኝም እንታገላለን። ተመልሰን ወደ አመፅና ብጥብጥ እንዳንገባ ምን ማድረግ ይገባል የሚለው ነው የኛ ጭንቀት። ህዝባችን  ላይ ያለው ችግር እንዴት መፍትሄ ያገኛል የሚለውን መነጋገር፣ መወያየት ይበጃል። ምርጫ በራሱ ያውም የሁሉንም ተሳትፎ ያላረጋገጠ መፍትሄ አያመጣም። እኛ በቀጣይ ከህዝባችን ጋር ሆነን በምንታወቅበት ሰላማዊ ትግል እንቀጥላለን። ከሰላማዊ የትግል መስመር አንወጣም።  
ከምርጫው መውጣታችሁን ከገለፃችሁ በኋላ ያነጋገራችሁ የመንግስት አካል የለም? ለምሳሌ ምርጫ ቦርድ?
ምርጫ ቦርድ ችግሩ ከአቅሙ በላይ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ። ከመንግስት በኩል ፈፅሞ ያነጋገረን የለም። መንግስት እኮ ከምርጫው እንድንወጣ ይፈልጋል። ታዲያ ምን ሁኑ ብሎ ነው የሚያነጋግረን።
ፓርቲያችሁ ከምርጫው በፊት የብሔራዊ መግባባትና እርቀ-ሰላም ውይይት ማድረግ ይገባል ብሏል….
አዎ፤ ቀጣዩ መንገድ በሀገሪቱ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ነው። በብሔራዊ መግባባት ችግሮችን በሙሉ መፍታትና ከዚያ በኋላ ወደ ምርጫ መግባቱ ነው ችግሮችን ሊያቀል የሚችለው።


Read 1428 times